
አዲስ አበባ፡- የመንግሥትን የበጀት አጠቃቀም ሥርዓት ውጤታማ የሚያደርግ አሠራር ተግባራዊ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የትሬዠሪና የመንግሥት ሂሳብ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ነጠሩ ወንድወሰን እንደገለፁት፤ መንግሥት በጀቱን በቅርብ ለመከታተል የሚያስችለው በአንድ አካውንት ብቻ ገቢ እና ወጪ መደረግ የሚቻልበት መተግበሪያ ሥራ ጀምሯል፤ መተግበሪያው ገንዘብ ያለ ሥራ እንዳይቀመጥ ከማድረግ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፤ መንግሥት በጀቱን በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዲሁም ምን ያህል ብድር በምን ያህል ጊዜ መበደር እንዳለበት እና የተለያዩ ወጪዎችን ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል፡፡
የዲጂታል የክፍያ ሥርዓቱ የተጀመረው ከአስራ አምስት ዓመት በፊት መሆኑን የገለፁት ኃላፊዋ፤የትሬዠሪ ነጠላ አካውንት ሥርዓት በበርካታ የባንክ ሂሳቦች ተበታትነው የሚገኙ የመንግሥት ገንዘቦችን አሰባስቦ ሁሉንም የመንግሥት ገንዘቦች ወደ አንድ ቋት የሚያመጣ በመሆኑ በተበታተነ የባንክ ሂሳብ አያያዝ ምክንያት የሚመጣ የመንግሥት ሂሳብ አያያዝ ችግርን በማቃለል ዘመናዊ የመንግሥት ጥሬ ገንዘብ አስተዳደር እንዲኖር አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የክፍያ ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ የሚፈፀም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፤ የመሠረተ ልማት ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በየጊዜው የሚገጥመው የቴክኖሎጂ ውስንነቶችን በመቅረፍ ውጤታማ ሥራ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት ፋይናንስ ሪፎርም ክፍል ኃላፊ አቶ ዳዊት ሽመልስ በበኩላቸው፤ ሪፎርሞች ሲሠሩ በዋናነት ዝግጅቶችን በማረጋገጥ እና የሕግ ማዕቀፎችን መዘርጋት እንዲሁም ሥርዓቱን ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም በማረጋገጥ በአተገባበር ላይ ለሚገጥሙ ችግሮች ቴክኒክ በመደገፍ መፍትሄ እያስቀመጥን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር ) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የመንግሥትን ገንዘብ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ ሥርዓት ማስተዳደር ሀገራዊ ግዴታችን ነው፡፡
ጠንካራና በአግባቡ የተደራጀ የፋይናንስ ሥርዓት ከታክስ እና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች፣ ከርዳታ፣ ከብድርና ከሌሎች ምንጮች የተሰበሰበ እያንዳንዱ የመንግሥት ገንዘብ ለሀገራዊ ልማት በአግባቡ በሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
ዘመናዊ የመንግሥት ጥሬ ገንዘብ አስተዳደር መኖር ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ መንግሥት ለአጭር ጊዜ ብድሮች የሚያወጣቸውን ወጪዎች በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።
አሠራሩ በተለያዩ መንገዶች መንግሥት የሚያገኛቸውን ገንዘቦች ወደ አንድ ቋት ለመሰብሰብ የሚያስችል እና ለታለመለት አገልግሎት እንዲውል የሚያስችል ‘የትሬዥሪ ነጠላ አካውንት አሠራር’ መሆኑ ተገልጿል።
ይህም መንግሥት ያለውን የገንዘብ መጠን ማወቅ እንደሚያስችለው የተገለጸ ሲሆን፤ ገንዘብን የመያዝ እና የማስተዳደር ሂደትን በአንድ ማዕከል እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።
ሄርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም