የዓሳ ሀብታችንና የአመጋገብ ባህላችን መሳ ለመሳ መሄድ ለምን ተሳናቸው?

ዜና ትንታኔ

በኢትዮጵያ 880 ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር የሚሆን ለዓሳ ግብርና ተስማሚ የሆነ መሬትና የውሃ ሀብት አለ። ከምርት አንጻርም ለአብነት ያህል በ2015 በጀት ዓመት 101 ነጥብ 36 ሺህ ቶን የዓሳ ምርት ማምረት ተችሏል። ይህንን ምርት በ2018 ዓ.ም መጨረሻ ወደ 215 ሺህ ቶን ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ለአብነት ያህል የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሀይቅ በዓመት 9 ሺህ 450 ቶን በላይ ዓሳ የማምረት አቅም እንዳለው በእዚህ ዙሪያ የወጡ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በአሁኑ ወቅት ከግድቡ በቀን ከ14 ሺህ 500 ኪሎ ግራም የዓሳ ምርት የሚገኝበት አቅም መፈጠሩንም የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

በሀገራችን የአንድ ሰው የዓሳ ፍጆታ 1 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም ስለመሆኑ የሚኒስቴሩ መረጃ ይናገራል። ይህ ማለት ከህዳሴ ግድብ ብቻ የሚገኘው የዓሳ ምርት 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን መመገብ ይችላል ማለት ነው።ዓሳን መመገብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ቢኖረውም በሀገር ደረጃ ግን ባህል ሆኖ አይታይም። ጥቅሙን የመረዳቱ ሁኔታም እምብዛም ነው።ለመሆኑ ዓሳን መመገብ ለምን ባህል ማድረግ አልተቻለም?፤ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ምን ይደረግ? እና መሰል ጥያቄዎች ዙሪያ ምሁራኑ የሚሉት አላቸው።

ጋሻው ተስፋዬ (ዶ/ር) በብሔራዊ ዓሳና የውሃ ውስጥ ምርምር ማዕከል ዳይሬከተር ናቸው። ኢትዮጵያ ከጨዋማም ሆነ ከኬሚካል የጸዱ ሃይቆች፣ ወንዞችና ኩሬዎች የሚገኙባት መሆኗ ዓሳን በስፋት ለማምረት ያስችላታል። ነገር ግን የምርት መጠኑ ካለን ሀብት ጋር የሚነጻጸር አይደለም። ለአብነት በቅርብ በተጠና ጥናት እንደተመላከተው ማምረት ይቻላል ተብሎ የሚታሰበው  ዓመታዊ የዓሳ ምርት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ቶን ይደርሳል። ይህም በዓሳ ግብርናና በተፈጥሮ ያሉ የውሃ አካላትን በመጠቀም በማስገር ጭምር መከናወን የሚችለው ነው። ነገር ግን እስከ አሁን የተደረሰው ከ130ሺህ ቶን አይበልጥም። ከዚህ አኳያም ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር ይናገራሉ።

ምርቱ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑና ዓሳን ለመመገብ የምንሰጠው ቦታ ዝቅተኛ መሆን እንደ ሀገር ጭምር ዓሳን በብዛት ከማይመገቡት ውስጥ ያስመድበናል የሚሉት ጋሻው (ዶ/ር)፤ ይህንን ያመጣው ልክ እንደ ሕዝብ ስብጥሩ ባህሉም የተለያየ መሆኑ ነው። በተጨማሪም አሰፋፈራችን ከፍተኛ ቦታዎች አካባቢ ካሉት ሀገራት ውስጥ ስለከተተን ሌሎች የሥጋ አማራጮችን ለምሳሌ ዶሮን ጨምሮ ፍየልና በግ እንዲሁም የቀንድ ከብቶችን በስፋት ስለምናገኝ ከዓሳ ይልቅ እነርሱን መመገብ ባህላችን አድርገን የቀጠልን መሆኑ ነው ይላሉ።

አቅርቦቱና ፍላጎቱ እንደ አካባቢው ሁኔታ የተመጣጠነ አለመሆን፣ ሰዎች የዓሳን ጥቅም በሚገባቸው ልክ አለማወቅና ለምርቱ ትኩረት አለመስጠት፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ደካማ መሆንና ዓሳ አስጋሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ምርት እንዲያመርቱ የሚያደርጋቸው ምቹ ሁኔታ አለማግኘታቸው በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች እንደሆኑ አንስተው፤ እንደ አበባና ፍራፍሬ ተገቢው የትራንስፖርት አማራጭ እንደሌውም ያብራራሉ።

እንደ ጋሻው (ዶ/ር) ገለጻ፤ ከፍተኛ የዓሳ ምርት የሚመረትባቸው እንደ ጋምቤላ፣ ኦሞ ወንዝ አካባቢ ያሉ እና ኢትዮጵያንና ኬንያን የሚያዋስነው የቱርካና ሀይቅን ጨምሮ ምርታቸው የሰፋ ቢሆንም ከገበያው ጋር በሚገባ ባለመተሳሰሩ ምርታቸውን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጡ ይገደዳሉ። የቱርካና ሀይቅ ብዛት ያለው ክፍል ኬንያ ውስጥ ቢሆንም ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት ግን ኢትዮጵያን የሚሸፍነው ክፍል ነው።

በአካባቢው ዳሰነች የሚባሉት ማህበረሰቦች በስፋት ቢኖሩም የገበያ እድላቸው የሰፋ ስላልሆነ ብዙ ቢያመርቱም ምርታቸው የሚሄደው በሕገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ነው። ከሕገወጥነቱ ባሻገር ግብይቱ እንደ ድሮው የገበያ ሁኔታ በመለዋወጥ የሚከናወን ነው። አልባሳት ዘይትና የበቆሎ ዱቄት ሰጥተዋቸው እነርሱ በምትኩ ዓሳ የሚሰጡበት ሁኔታ ነው ያለው።

ከተሞች አካባቢ ዓሳን የመመገብ ባህል ያልዳበረው የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ እንደሆነ አንስተው፤ በዘመናዊ መልኩ ሰው-ሠራሽ ዓሳ ማምረቻ ማዘጋጀት አለመቻሉም ሌላው እንደተግዳሮት የሚነሳ ጉዳይ እንደሆነ ያብራራሉ።

የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቢራራ መለሰ እንደሚሉት ደግሞ፤ ዓሳ ከእንስሳት ተዋዕጽኦ ውስጥ የሚመደብ ገንቢ ምግብ ነው። በጣም ጠቃሚ የሚባሉ ቫታሚንና ማዕድናትን የያዘ በመሆኑ ሰውነትን ይጠግናል። ዓሳ በጥቃቅን ንጥረ ምግቦች የበለጸገም ነው። ኦሜጋ 3 የሚባል ፋቲ አሲድን የሚይዝ በመሆኑ ጠቀሜታው በተለይ ለሕጻናት ከፍተኛ ነው። የአዕምሮ እድገታቸውን ያፋጥነዋል።

ዓሳ ከሌሎች የሥጋ ምግቦች ተመራጭ የሚሆንበት በርካታ ምክንያቶች አሉት የሚሉት ባለሙያው፤ ዋናው ብዙ ቅባት የሌለው መሆኑና በርካታ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ስለሆነ የተመጣጠነ ምግብ ሰውነት ላይ እንዲኖር ማድረጉ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ደም ማነስን ለመከላከል የአይረን፤ እንቅርትና መሰል በሽታዎችን ለመከላከል፤ የአይኦዲን ፤ የምግብ መፈጨትና ሌሎች ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ ንጥረ ምግቦችን የያዘ እንደሆነ ቢታወቅም፤ እንደ ሀገር ያለው ዓሳን የመመገብ ባህል ግን ወጥነት የጎደለው መሆኑን ይናገራሉ።

ዓሳን መመገብ ሀይቆች ባሉባቸውና ዓሳ በብዛት በሚመረትባቸው ቦታዎች ላይ ባህሉ ይታያል። በከተሞች አካባቢም እንዲሁ በተለይ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ሃሳቦች እንዳሉ ሆነው በጾም ወቅቶች በስፋት የመመገብ ባህሉ ይስተዋላል።ይህ ግን በቁጥር ሲታይ እጅግ ያነሰ ነው። ምክንያቶቹ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ናቸው።አንዱ ያለው ዓሳን እንደ ሀገር የዶሮን ያህል እንኳን የመመገብ ባህሉ አለመዳበሩ ነው።ይህ ደግሞ የምግቡን ጥቅም አለመረዳት ነው።ሌላው የአቅርቦቱ ጉዳይ በተለያየ መልኩ ሊታይ አለመቻሉ እንደሆነ ያመላክታሉ።

እንደ ቻይና እና ጃፓንን የመሳሰሉ ሀገራት ዓሳ ያለውን ጥቅም በሚገባ ስለሚረዱና በብዛትና በቀላሉ የማምረት እድሉ ስላላቸው እንደ መደበኛ ምግብ የሚመገቡ ናቸው። ይህ ልምድ ደግሞ እኛ ሀገርም መምጣት የሚችልበት ብዙ እድል አለ።ነገር ግን ከምግቡ ጥራትና አቅርቦት ጋር፤ በስፋት ከማምረቱ ጋርና በፋብሪካ ደረጃ ጭምር ማምረት አለመቻላችን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሚፈለገው ልክ መመገብ ባህል እንዳይሆን አድርጎታል ይላሉ።

እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ከሚያረጋግጡ ነገሮች መካከል አንዱ የእንስሳት ዘርፉ ልማት ነው።በዚህም ዓሳን ማምረትና በስፋት መጠቀሙ ከጤናው ባሻገር እንደ ሀገር ያለንበትን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ችግርን ይፈታል።ለዚህም ከመደበኛው የውሃ አካላት ውጪ በሰው ሠራሽ መንገድ ዓሳዎችን በብዛት በማምረትና ከቦታው ላይ አውጥቶ በንጽህና መጠቀም በእጅጉ ጠቃሚ እንደሆነ አመላክተዋል።

ምርቱ በብዛት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ በፋብሪካ ደረጃ ማምረት ቢቻልና እንደልብ ተፈላጊ የሆነባቸው አካባቢዎች ላይ ማቅረብ ቢቻል፤ በሌላ መልኩ ዘመኑን የዋጁ የዓሳ ማምረት ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች ላይ ቢሠሩ፤ ጥሩ የገበያ ሰንሰለት ቢፈጠር መሻሻሎች ይኖራሉም ነው ያሉት።

ሌላው ዓሳን መመገብን ባህል ለማድረግ የባህል ሽግግር መደረግ ይኖርበታል። ይህም ከአመጋገብ እስከ አሠራር ድረስ በስፋት ተመጋቢና አቅራቢ ካለበት አካባቢ ምንም ወደ ሌለበት መስፋፋት ይኖርበታል። ለዚህም የንግዱ ዘርፍ፤ የጤና እና የግብርናው እንዲሁም የውሃ አካላት ክትትል የሚያደርጉና የሎጂስቲክ አቅርቦት ላይ የሚሠሩ የመንግሥት አካላት ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

ጋሻው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዓሳን ባህል አድርጎ ለመመገብ መደረግ ያለበት የገበያ ትስስሩን ለማሳለጥ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት፤ የዓሳ መመገብን ጥቅም ለማህበረሰቡ ማስገንዘብ፤ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ንጽህናው የተጠበቀ ምርትን ወደ ገበያ ማቅረብ፤ በስፋት የሚመረትባቸው ቦታዎች ላይ እና ዓሳ ባህላዊ ምግብ በሆነባቸው ስፍራዎች የጥራት ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።

የግብርና ሥራዎችን ማስፋት፤ የተባባሪ ተቋማትን ትስስር ማጠናከር፤ ለእንስሳትና ዓሳ ልማት ተብለው ከዓለም ድርጅቶች የተገኙ ብድሮችን ካለፉት ጊዜያት በተሻለ መልኩ ማምጣትና መሰል ተግባራትን ማከናወን ዓሳን መመገብ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ያደርገዋል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ አሁን እየተሠሩ ባሉ ተግባራት በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን ያነሳሉ።በተለይም በሌማት ቱሩፋት በኩል እየተሠሩ ያሉ ተግባራት የዓሳ ልማቱን በእጅጉ እያፋጠነው እንደሆነ ይናገራሉ።

ከአስር ዓመት በፊት የነበረው ዓሳን የማምረት ሥራ ከ20ና 30ሺህ ቶን አይበልጥም ነበር። አሁን ላይ ግን ይህ ቁጥር በተሠሩ በርካታ ተግባራት 130ሺህ ቶን ደርሷል።

በቀጣይ ተግባራቱ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ከሆኑ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ከማረጋገጥ አልፋ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙ ዜጎቿን ታበራክታለች።በሽታን መከላከል የሚችሉ ዜጎችንም ትፈጥራለች። ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ሕጻናት እንዲፈጠሩም እድል ታገኛለች። ከራሷ አልፋ ለሌሎች ምርቶቿን በማቅረብ የገቢ ምንጭ ታገኛለች።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You