
– አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር
አዲስ አበባ፡- በሪፎርም ሥራው ከ28 ሺህ በላይ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በሰነድም በአድራሻም አልተገኙም ሲሉ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ አስታወቁ።
በሪፎርሙ መረጃ የማጥራት ሥራ ተሠርቶ 36 ሺህ 292 መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት እና 19 ዩኒየኖች መሰረዛቸውን ጠቁመዋል።
አቶ ሺሰማ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ላለፉት አንድ ዓመት ተኩል በህብረት ሥራ ማህበራት ላይ በተሠራው የሪፎርም ሥራ 28 ሺህ 212 መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በሰነድም ሆነ በአድራሻም አልተገኙም፡፡ ከዚህ በፊት ይህን ያህል ቁጥር እየተባለ ሲነገር የቆየው በስም ደረጃ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሺሰማ ገለጻ፤ ማህበራቱን በሰነድም በአድራሻ ማግኘት ስላልተቻለ ጥሪ ተደርጎላቸው እንዲቀርቡ ቢጠየቁም አልተገኙም፡፡ ማህበራቱ ጥሪ ሲደረግላቸው ያለመገኘታቸው ምክንያት የሚገመተው በሆነ ወቅት ለሥራ እድል ፈጠራ ለማገዝ ተብሎ እንዲደራጁ የተደረጉ እንደነበር ነው፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ አልፎ አልፎም የሀሰት ሪፖርቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በዋናነት ለተዘዋዋሪ ፈንድ ተብሎ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በነበረ ሂደት የተደራጁ እንደሆኑ ገልጸው፤ ሪፎርሙ መረጃን በማጥራት ማህበራት እንድንቀንስ እድል ሰጥቶናል ነው ያሉት፡፡
በሪፎርሙ መረጃ የማጥራት ሥራ ተሠርቶ 36 ሺህ 292 መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት እና 19 ዩኒየኖች መሰረዛቸውን የገለጹት አቶ ሺሰማ፤ ምክንያቱም ሕጋዊ ሥርዓት ተከትለው የህብረት ሥራ ማህበራት በራሳቸው ፈርሰው የምስክር ወረቀት መልሰው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማህበር ሲፈርስ ጥንቃቄ ይፈልጋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ተበድሮ፣ አበድሮ፤ ዱቤ ገዝቶ፣ የሰበሰበው የሕዝብ ገንዘብ በተወሰኑ ሰዎች አካውንት ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ የተጠቀሱ ህብረት ሥራ ማህበራት ሥርዓቱን ተከትለው የፈረሱ የምስክር ወረቀታቸውን መልሰው በአግባቡ እንዲፈርሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡
አንዱ የሪፎርሙ መነሻ የቁጥራቸውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ሚናቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ሺሰማ፤ በአሁኑ ወቅት የቀሩት 89 ሺህ 164 የህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሪፎርሙ በተጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በውህደት የተፈጠሩ ዓላማ ይዘው ያሉ በርካታ የህብረት ሥራ ማህበራት እንዳሉም አመልክተዋል፡፡
በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ ጋር ያደረግነው ቆይታ በተጠየቅ ዓምዳችን ገጽ 6 እና 7 ያገኙታል፡፡
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም