
ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 በፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉዓላዊነትን፣ የግዛት አንድነትን እና ብሄራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ዕልባት አግኝቷል፡፡ ይህም ስምምነት ከትግራይ አልፎም ለመላ ኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋትን አስፍኗል፡፡
የፕሪቶርያው ስምምነት በተፈረመ በኩልም “በዘላቂነት የጦር መሣሪያ ድምጽ እንዳይሰማ ለማድረግ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ግጭት እንዲቆም ተስማምተናል” ሲሉ የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት መስማማታቸው የሚታወስ ነው ።
በወቅቱም ሕወሓት እና መንግሥት በአንድ ድምጽ ግጭቱ ከፍተኛ ሠብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎችን አስከትሏል ካሉ በኋላ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ከግምት በማስገባት የግጭቱን ምዕራፍ ከኋላችን ትተን “በሰላም እና በመቻቻል ለመኖር” ተስማምተናል ማለታቸው የሚታወስ ነው። ይህንኑ መነሻ በማድረግም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም በማድረግ የትግራይ ሕዝብ ከጦርነት ስጋት ተላቆ ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ እንዲመለስ ጥረት ተደርጓል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል። የትግራይ ሕዝብም ፊቱን ወደ ልማት ማዞር ችሏል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል፤ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰፍረዋል፡፡ አርሶ አደሩም ፊቱን ወደ ግብርና ሥራ መልሷል፡፡ በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ከጦርነቱ በፊት ወ ደነበረው ሕይወቱ መመለስ ጀምሯል፡፡
ሆኖም በትግራይ ውስጥ የሚገኙ በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አካላት ይህንን አንጻራዊ ሰላም ለመረበሽና ዳግም በክልሉ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እና የፕሪቶርያው ስምምነት እንዳይተገበር እንቅፋት ሲሆኑ ታይተዋል፡፡
እነዚህ ቡድኖች ሠብዓዊነት እና ፖለቲካን በመቀላቀል የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዳይመለሱ ተግዳሮት ሲፈጥሩ ተስተውለዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በጦርነቱ የተሳተፉ ወጣቶች በመልሶ ማቋቋም ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የሚደረገውንም ጥረት ሲያስተጓጉሉ ታይተዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣም እንቅፋት በመሆን ክልሉ ዳግም ወደ ግጭት እና ጦርነት እንዲገባቡ ሲገፋፉ ተስተውለዋል፡፡
ከሁሉ በከፋ መልኩ ክልሉ ያለውን በጀት ለልማት እንዳያውለው ከ200ሺ በላይ ሠራዊት በማከማች እና በመቀለብ በወር እስከ 8 ቢሊዮን ብር በመገፍገፍ ትግራይ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንድትቆይ የተደረገበት መንገድ ከተስዋሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ስለዚህም አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቆዩ ችግችሮችን በማረም በትግራይ ሰላም እና ልማት እንዲረጋገጥ አበክሮ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ላለፉት 100 ዓመታት ባልተገቡ ጦርነቶች ውስጥ እንዲያሳልፍ ተፈርዶበት ቆይቷል፡፡ በረባ ባልረባው በሚነሱ ጦርነቶች የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖር እና ኑሮውንም እንዳያሻሽል ችግር ገጥሞት ቆይቷል፡፡ ስለዚህም ይህ ታሪክ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ማግኘት አለበት፡፡ የትግራይ ሕዝብ በሰላም የመኖር መብቱ ሊረጋገጥለት ይገባል፡፡ ይህን ደግሞ የአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር የመጀመርያ ተግባሩ መሆን አለበት፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም በፖለቲከ ሽፋን ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ የተደረጉ ዜጎችን መመለስ እና ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ማድረግ በአዲሱ የትግራይ አስተዳደር ሊተገበሩ ከሚገቡ ሥራዎች ቀዳሚው ነው፡፡ የተፈናቃዮችን ጉዳይ ከወሰን ማካለል ጋር በማምታት የሚደረጉ ፖለቲካዊ ሴራዎች ከሠብዓዊ ጉዳዮች ተለይተው መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ አዲሱ አስተዳደር ለሠብዓዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ተፈናቃዮች የመመለሱን ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በሌላም በኩል በጦርነት ውስጥ የቆዩ ወጣቶችን በመደገፍ ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የማድረጉም ተግባር ከአዲሱ አስተዳደር የሚጠበቅ ነው፡፡ በአሠራር ውስንነቶች እና በፖለቲካ ሸፍጦች ምክንያት በመርሃ ግብሩ መሠረት መፈጸም ያልተቻለውን በጦርነት ውስጥ የነበሩትን ወጣቶች የመመለሱ ተግባር ከአጋዥ አካላት ጋር በመሆን ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው መመለስ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋነኛ ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ ከፌዴራል መንግሥት የሚመደብለትን በጀት ለታጣቂዎች ማከፋፈሉን በመተው ለክልሉ ልማት የሚውልበትን ስልት መንደፍ ይጠበቅበታል፡፡
በአጠቃላይ አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለው የአንድ ዓመት የሥልጣን ዘመን ውስጥ ቀደም ሲል የተፈጠሩ ችግሮችን በማረም እና ወቅቱን የዋጀ አሠራር በመተግበር በትግራይ ዘላቂ ሰላም እና ልማት እንደሚጠበቅበት ተገንዝቦ ከወዲሁ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም