ሁለቱ ራሶች

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በወታደርነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነት፣ በዲፕሎማትነት… በአጠቃላይ ለሀገራቸው ሕይወታቸውን የገበሩ ብዙ ጀግኖች አሉ። እነዚህንም ጀግኖች የጀግንነት ታሪክ የፈጸሙበትን፣ የተወለዱበትን ወይም በተፈጥሮ ሞትም ሆነ በጀግንነት ሲዋጉ መስዋዕት የሆኑበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ታሪካቸውን እናስታውሳለን። ባለፈው ሳምንት የዓፄ ዮሐንስ 4ኛን ገድል እና መስዋዕትነት ማስታወሳችን ይታወሳል።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ወታደር፣ ግዛት አስተዳዳሪ እና ዲፕሎማት የሆኑትን ራስ መኮንን እና በጀግንነታቸው በሁሉም ልብ ዘንድ የሚታወሱት ዓፄ ቴዎድሮስ የሚፈሯቸውን ራስ ዳርጌን እናስታውሳለን።

ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ።

ከአምስት ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም በ60 ዓመታት ወርቃማ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ከ60 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሕይወት የሰጡት አንጋፋዋ የፅንስና የማህፀን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን አረፉ። በዚህ ውለታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ሲታወሱ ይኖራሉ። የዶክተር ካትሪን ሐምሌንን ዝርዝር ታሪክ ከዚህ በፊት በሳምንቱን በታሪክ እና በሌሎች ዓምዶቻችን ጭምር በዝርዝር አይተናል።

ከ79 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 11 ቀን 1938 ዓ.ም ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት በመቃወም፣ የተማሪዎችን ንቅናቄ በመፍጠርና አብዮት በማስጀመር፣ የብሔር ፖለቲካን በማቀንቀን የሚታወቀው ዋለልኝ መኮንን ተወለደ። ዋለልኝ፤ የብሔር ፖለቲካን በሚደግፉ ወገኖች የብሔሮችን መብት አስከብሯል በሚል የሚደነቅ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን በብሔር በመከፋፈል ለሀገራዊ ቀውስ ምክንያት ሆኗል በሚል ከፍተኛ ወቀሳና ውግዘት ይደርስበታል። በምሑራን እና በአንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ ‹‹ዋለልኝን አልተረዱትም›› የሚል ክርክር አለ። ያም ሆነ ይህ ዋለልኝ መኮንን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም የብሔር ፖለቲካን በማቀንቀን በደጋፊዎቹም በወቃሾቹም ሲታወስ ይኖራል።

ከ51 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 12 ቀን 1964 ዓ.ም በአትሌትነት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማቀንቀን እና በብዙ የማኅበራዊና ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች የምትታወቀው ደራርቱ ቱሉ ተወለደች።

Marcus, Menelik II, የመርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ዕለታዊ የታሪክ ድርጊት እና የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ መጽሕፍትን እንዲሁም የተለያዩ ድረ ገጾችን ዋቢ አድርገን በዝርዝር ወደምናየው የሁለቱ ራሶች ታሪክ ስንሄድ በመጀመሪያ የራስ መኮንንን እናገኛለን።

የሸዋ ንጉሥ የነበሩት የንጉሥ ሳሕለሥላሴ የልጅ ልጅ ናቸው። የንጉሥ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአክስት ልጅ ናቸው። እኚህ ሰው የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ናቸው።

የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑት ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ያረፉት ከ119 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ነበር።

ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱት ግንቦት 1 ቀን 1844 ዓ.ም በሸዋ ግዛተ ዓፄ፣ ጎላ ወረዳ፣ ደረፎ ማርያም በሚባል ሥፍራ ነው። ገና በወጣትነታቸው ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሄደው ከአጎታቸው ልጅ ከንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ጋር ተዋውቀው ቤተሰባዊ ዝምድናቸውን አጸኑ፡፡

በፀባያቸው ታጋሽና አስተዋይ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ልዑል ራስ መኮንን ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ጠንካራ ወዳጆች በመሆን እንደ አባትና ልጅ ይተያዩ ጀመር። የሐረርጌን ግዛት በሚገባ በማስተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ ሀገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ ሆኑ። ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ተነስተው በዘመኑ ከንጉሥ በመቀጠል ከፍተኛ ለሆነው የ‹‹ራስ›› ማዕረግም በቁ፡፡

ልዑል ራስ መኮንን የዓፄ ምኒልክ ተወካይ በመሆን ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ ሀገራት ተጉዘዋል። ወደ ኢጣሊያ በሄዱ ጊዜም የኢጣሊያ ጋዜጦች የውጫሌ ውልን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ስር እንዳለች አድርገው የሚጽፉትን ጽሑፍ በመመልከታቸው ራስ መኮንን ተቃውሟቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የውሉን መበላሸት ለዓፄ ምኒልክም አሳውቀዋል።

የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ የመጨረሻ መፍትሔው ጦርነት ሲሆንም ልዑል ራስ መኮንን ሠራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ ዓድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ታሪክ የማይዘነጋው ታላቅ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል። ልዑል ራስ መኮንን ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነትና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ እንደሚያደርጓቸውም ይወራ ነበር።

ነገር ግን ምኒልክ ያሰቡት ሳይሆን ቀረና ልዑል ራስ መኮንን መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሞታቸው በንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት (አዲስ አበባ) በተሰማ ጊዜም ከፍተኛ ኀዘን ሆነ። ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክም አምርረው አለቀሱ። በወቅቱም ይህንን የተመለከቱ ሰዎች እንዲህ ብለው ገጠሙ

‹‹ዋ! አጤ ምኒልክ እግዚአብሔር ያጥናዎ፣

በየበሩ ቋሚ ከልካይ ሞተብዎ፡፡

ሲታሰር አየነው ብረቱ ሲመታ፣

ምን ዋስ አገኘና ሐረርጌ ተፈታ፡፡

ጃንሆይ ምኒልክ ጠጉራቸው ሳሳና በራ ገለጣቸው፣

እንግዲህ ንጉሡ ምን ራስ አላቸው፡፡››

ከአልቃሾቹ መካከል አንደኛው ደግሞ የልዑል ራስ መኮንንን ደግነት ለማስታወስ እንዲህ ብሎ ሙሾ አወረደ።

«ስልከኛው ሲያረዳ ነገር የተሳሳተው፣

መኮንን አይደለም ድሀ ነው የሞተው፡፡»

ተብሎላቸዋል። ‹‹እንግዲህ ንጉሡ ምን ራስ አላቸው!›› የሚለው ሰምና ወርቅ ያለው መሆኑ ነው። ራስ መኮንን ከውጫሌ ውል ጀምሮ እስከ ዓድዋ ጦርነት ድረስ የነበራቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ እና የጦር ጀግንነት ለዓፄ ምኒልክ ትልቅ ቦታ ነበረው። ስለዚህ ዓፄ ምኒልክ የራስነት ማዕረግ ያለው አንድ ትልቅ ሰው አጡ ማለት ነው። የሰውነታችን ዋናው ክፍል ያለው ራስ (ጭንቅላት) ላይ ነውና ዓፄ ምኒልክ ራሳቸውን (ጭንቅላታቸውን) ያጡ ያህል ይቆጠራል እንደማለትም ነው።

ዲፕሎማቱ፣ የግዛት አስተዳዳሪውና ወታደሩ ራስ መኮንንም እነሆ በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ።

በአጼ ቴዎድሮስ የተፈሩት ራስ ዳርጌ

የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ አጎት የሆኑትና በጀግንነታቸው ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስን ጭምር ያስጨነቁትና ያስደነቁት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ ያረፉት ከ125 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም ነበር፡፡

ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ የሸዋው ንጉሥ የንጉሥ ሣሕለሥላሴ ወሰን ሰገድ ልጅ ናቸው። ራስ ዳርጌ የደጃዝማች አስፋው፣ የደጃዝማች ደስታ፣ የፊታውራሪ ሸዋረገድ፣ የወይዘሮ ትሰሜ፣ የወይዘሮ አስካለ፣ የወይዘሮ ፀሐይወርቅ እና የልጅ ጉግሳ አባት ናቸው። ወይዘሮ ትሰሜ ዳርጌ የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ እናት ናቸው።

ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ የንጉሥ ኃይለመለኮት ሣሕለሥላሴ (የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ አባት ማለት ነው) ወንድም ናቸው። በ1822 ዓ.ም ሸዋ ውስጥ የተወለዱት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ፣ የልጅነት ጊዜያቸውን በአንኮበርና በአንጎለላ አሳልፈው ወደ ጎንደር ተጉዘው በነበሩበት ወቅት በሰላይነት ተጠርጥረው ታስረው ነበር።

ይሁን እንጂ ራስ ዳርጌ ንፁሕነታቸው ታውቆ ነፃ ከወጡ በኋላ በመልካም ጠባያቸውና በጦር ሜዳ ጀግንነታቸው በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ተወዳጅነትን አተረፉ። በዚህም ምክንያት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ራስ ዳርጌን ‹‹ዳሩ››፣ ‹‹ዳርዬ›› እያሉ ይጠሯቸው ነበር።

የርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ ጀግንነት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስን ጭምር ያስጨነቀ ነበር። በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ጊዜ ሸዋን ይገዙ የነበሩት መርዕድ አዝማች ኃይሌ ንጉሠ ነገሥቱን በመክዳት ተጠርጥረው ታስረው ነበር።

ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስም አቤቶ ዳርጌን የሸዋ ገዢ አድርገው እንደሾሙ ተናገሩ፤ ነገር ግን ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የራስ ዳርጌን የጦር ሰፈር ሲመለከቱት በጣም የደመቀና የተደራጀ ስለነበር በጣም ተጨነቁ። ንጉሠ ነገሥቱም አቤቶ ዳርጌን አስጠርተው ‹‹ዳሩዬ ፈራሁህ! በጥንድ ጦር የሚስተውን ኃይሌን ሽሬ በነጠላ ጦር ደርበህ ሁለት ሰው የምትገለውን አንተን በሸዋ ላይ አልሾምም›› ብለው በግልጽ ነገሯቸው። ራስ ዳርጌም የመከፋትና የቅሬታ ምልክት ሳያሳዩና ሳይከፉ ‹‹እሺ›› ብለው ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስን በትሕትና እጅ ነሱ።

ልጅ ምኒልክ (በኋላ ንጉሥ ምኒልክ፣ ከዚያም ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ) ከመቅደላ አምልጠው ሸዋ በገቡና በአባታቸው ዙፋን በተቀመጡ ጊዜም፣ ራስ ዳርጌ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ወደ ሸዋ ተመልሰው ከምኒልክ ጋር ተገናኙ። ምኒልክም ሸዋ ገብተው በአባቶቻቸው አልጋ ተተክተው የሸዋ ንጉሥ ሆነው ነበርና ራስ ዳርጌ እንደመጡ ‹‹እርስዎ ቀጥታ የንጉሥ ሣሕለሥላሴ ልጅ ስለሆኑ ንጉሥነቴን ልተውልዎ›› ብለው ጠየቋቸው።

ራስ ዳርጌም ‹‹አይሆንም! አባታችን ሣሕለሥላሴ አልጋቸውን አውርሰው የሞቱት በቀጥታ ለአንተ አባት ለንጉሥ ኃይለመለኮት ነው፤ አሁንም የነጋሢነት መስመሩ በዚያው ባንተ በኩል ነው መቀጠል ያለበት›› ብለው ንግሥናውን እንደማይፈልጉ ተናገሩ። ከዚያ በኋላም ራስ ዳርጌና ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ እንደአባትና ልጅ ሆነው ከ30 ዓመታት በላይ ዓመታት ኖሩ፡፡

ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ የተለያዩ አካባቢዎችን በማቅናትና በማስተዳደር ሥራ ውስጥ የላቀ ድርሻ ነበራቸው። ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል አርሲ እና ሰላሌና አካባቢው ይጠቀሳሉ። ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ዮሐንስ 4ኛ እና ንጉሥ ምኒልክ በተቀያየሙ ጊዜም አስታራቂ ሽማግሌ ሆነው ያገለገሉት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ ነበሩ። ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ዮሐንስ 4ኛ እና ንጉሥ ምኒልክ ደብዳቤ የሚፃፃፉት በርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ በኩል ነበር። ደጃዝማች መሸሻ ሰይፉ በሸፈቱ ጊዜም ተቆጭው፣ አስማሚውና መካሪው ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ ነበሩ።

በዓድዋ ጦርነት ወቅትም ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ለጦርነቱ ወደ ዓድዋ በተጓዙበት ወቅት የንጉሠ ነገሥቱን ቦታ ተክተው ዙፋን የጠበቁትና ሀገር ያስተዳደሩት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ ነበሩ።

በመልካም ፀባያቸው፣ በታማኝነታቸው፣ በበጎ አሳቢነታቸውና በጦር ጀግንነታቸው የሚታወቁት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሣሕለሥላሴ መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸውም በደብረሊባኖስ ገዳም ተፈጽሟል፡፡

ከላይ ያየናቸው ሁለቱ ራሶች (ራስ መኮንን እና ራስ ዳርጌ) ሁለቱም የዚህ ሳምንት ተዘካሪ ናቸው። እንደመገጣጠም ሆኖ ሁለቱም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ቤተሰቦች ናቸው። ሁለቱም በአንድ ወር ውስጥ ለዚያውም በአንድ ሳምንት ውስጥ ነው ያረፉት። እነሆ ይህንንም ታሪክ ያስታውሰዋል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You