ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች እንዴት ይሳቡ?

ኮንፈረንስ ቱሪዝም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። ሀገሪቱ እንዲህ እንዳሁኑም ባይሆን ፊትም በዘርፉ የጎላ ባይባልም ስትሠራ ቆይታለች፤ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች በስፋት ሲካሄዱ የቆዩበት ሁኔታም ይህንኑ ያመላክታል።

ይህ የቱሪዝም ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ እየታየ መጥቷል። ሀገሪቱ ለዚህ የቱሪዝም ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማካሄድ የሚያስችሉ የጉባዔ አዳራሾች፣ የሁነቶቹ ተሳታፊዎች የሚያርፉባቸውና የሚገለገሉባቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች በበቂ ሁኔታ አፍርታለች።

በአንግዶች አቀባበልና ደህንነት መጠበቅ በኩል ያለው የመንግሥት ቁርጠኝነትም ሌላው ለዚህ ለቱሪዝም ዘርፍ የሚያስፈልግ ትልቅ አቅም ነው። መንግሥት ይህን ሥራ የሚሠራ ኮንቬንሽን ቢሮ በቱሪዝም ሚኒስቴር ስር አቋቁሞ ወደ ሥራ ካስገባ ዓመታት ተቆጥረዋል። ሌሎች ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚያስፈልጉ ምቹ ሁኔታዎች እንደ ሀገር ስለመኖራቸው የዘርፉ ባለሙያዎችም ያረጋግጣሉ።

ሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የምታስተናግዳቸው ኮንፈረንሶች በብዛትም በአይነትም እየጨመረ የመጣበት ሁኔታም ይህንኑ ምቹ ሁኔታ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን እንዳስታወቁትም ሀገሪቱ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ወራት ብቻ ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን አስተናግዳለች።

ሀገሪቱ በቅርቡም ይህን እየጨመረ የመጣውን ዓለም አቀፍ ሁነት የማስተናገድ እቅም በሚገባ ማሳደግ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኮንቬንሽን ማእከል ግንባታ ወደ ሥራ አስገብታለች። ማእከሉም ገና በተመረቀ ማግስት አስር ዓለም አቀፍ ሁነቶችን እንዲያስተናግድ መጠየቁንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ደግሞ በዘርፉ ያላትን አቅም ከማጠናከር ጎን ለጎን ሁነቶቹን ለመሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት መንቀሳቀስ እንዳለባት ይታመናል። ሁነቶቹን የማምጣት ሥራ ሀገሪቱ ያላትን አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅን ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠትን የግድ ይላሉ፡፡

እነዚህን ሁነቶች በማስተናገድ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ አሜሪካ፣ ጀርመንና የመሳሰሉት ሀገሮች በእጅጉ ይታወቃሉ፤ ከአፍሪካም ደቡብ አፍሪካ፣ ርዋንዳና ኬንያ እንደሚታወቁ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘትን የግድ እንደሚል እየተጠቆመ ነው።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የኮንቬንሽን ቢሮ የማይስ ዴስክ ሃላፊ አቶ ብዙአለም ጌቱ የማይስ /የኮንፈረንስ ቱሪዝም/ ቢዝነስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ማርኬቶች እንዳሉት ይጠቁማሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከእነዚህ ማርኬቶች አንዱ የጀርመኑ አይኤምኤክስ /imex/ ፍራንከፈርት ነው፤ በእዚህ ሁሉም የዓለም ኮንቬንሽን ቢሮዎች /የኬንያ፣ የኢትዮጵያ፣ የርዋዳ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የለንደን፣ ወዘተ ኮንቪንሽን ቢሮች/ ሁነቶችን ለመሳብ ይገኙበታል።

ከእነዚህ መድረኮች መካከል የስፔን ባርሴሎናው መድረክ እንዱ ነው። በአፍሪካም ሚቲንግስ አፍሪካ አለ። ለአሜሪካ ገበያ ደግሞ አይኤምኤክስ ላስቬጋስ ወይም ደግሞ አይሜክስ ቬጋዝ እንዳለ ጠቁመዋል።

እነዚህ አራቱ በኢሲያ ገበያ /ቻይናም ህንድም ገልፍ ላይ/ም አሉ። አራቱም ታዋቂ ናቸው፤ ከአራቱ ደግሞ አይኤምኤክስ ፍራንክፈርት ሁሉም ኮርፖሬት ካምፓኒዎች፣ ሁሉም ሁነት ያላቸው ማህበራት ወይም ድርጅቶች ይገኙበታል። ኢትዮጵያም በእነዚህ ላይ ትሳተፋለች። ሆቴሎችና ቱር ኦፕሬተሮችም ይሳተፋሉ፡፡

የዲጂታል አማራጭ ሌላው ሁነት መሳቢያው መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል። የኮንፈረስን ቱሪዝም ቢዝነስ ባለድርሻዎች በአብዛኛው የሚገኙት ሊንከዲንና ትዊተር ላይ መሆኑን አመልክተው፣ ፌስ ቡክ እንዲሁም ዩቲዩብ ላይም ጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ብዙአለም እንዳብራሩት፤ ከዚያ ውጪ ጨረታ /ቢድ/ ሌላው ሁነት የማግኛው መንገድ ነው። ሁነት ሲመጣ በመጫረት እንዲመጣ ይደረጋል። ‹‹እኛ ጋ ሁነታችሁን ብታከናውኑ እኛ ጋ ይሄ ነገር ይገኛል፤ እኛ ይህን እንደግፋለን›› እየተባለ ሁነት ሊሳብ እንደሚችል አብራርተው፣ ውድድሩ የገንዘብ ብቻ አይደለም፤ የጥራትም ጉዳይ አለ ብለዋል።

የአፍሪካ መዳረሻነቷን ለመመለስ ለምትተጋ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር አንዳንዴ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው፤ በገንዘብ መደገፍ ያለብን ነገር ይኖራል ሲሉም አስታውቀዋል። ከዚያ ውጪ ግን ከጥራት አኳያ መንግሥት የሚሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ተቋም ሁነት ለማካሄድ ችግር አይኖርበትም ሲሉም ጠቅሰው፣ ሁነቶች የመንግሥትን ትኩረት በእጅጉ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ እንዲህ አይነት ከመንግሥት የሚገኝ ትኩረት በአብዛኛዎቹ ሀገሮች አይታየም፤ አልፎ አልፎ ርዋንዳ ላይ ይታያል፤ ርዋንዳ አንዱ ስትራቴጂዋ አርጋ የምትሰራበትም ይሄው ነው። በኢትዮጵያ ሚኒስትሮች በተለያዩ ሁነቶች ላይ ተገኝተው ያበረታታሉ፤ እነዚህ ሥራዎች ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ትልቅ መሣሪያዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የዓለም የሥራ ድርጅት ሁነትን አስተናግዳ እንደነበር አስታውሰዋል። ድርጅቱ ይህን ሁነት በጥሩ መልኩ በማስተናገዳችን በ2025 የሚያካሂደውን ሁነትም ኢትዮጵያ ውስጥ ለማድረግ አስቧል ሲሉም ጠቁመዋል። የመንግሥት ድጋፍ፣ ከኤርፖርት ተቀብሎ ሁነት የሚስተናገድበት ሁኔታ ማድረሱ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቅሰው፣ ይሄ እንደ ፕሮሞሽን የሚወሰድ ስትራቴጂ ነው ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ዓለም አቀፍ መድረኮችን ለማምጣት፣ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር መተሳሰር በጣም ያስፈልጋል። ይሄ የዘርፉን የዘመኑ ታዋቂ ተመራማሪዎች፣ እውቀትና ፈጠራን ለማምጣት ይጠቅማል።

የሁነት ኢንዱስትሪ እንደ ቱሪዝም ዘርፍ ብቻ አይደለም የሚታየው። እንደ ፖለቲካ መሣሪያም ይታያል። ለሀገር ገጽታና ዲፕሎማሲ ግንባታ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። የአንድ ሀገር መሪ አዲስ አበባ ሲመጣ ሀገሩም ጭምር ናት የምትዘገበው። ሁነቱ ከቱሪዝምም በላይ ስለሆነ የሁሉንም ዘርፍ ትብብር በጣም ይፈልጋል። የሙያ ማህበራትና ዩኒቨርሲቲዎች ቁልፍ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። በተለይ የዘርፉ ምሁራንን፣ ሊህቃንን ከማስተሳሰር አንጻር የሁነት ቢዝነስ በጣም አዋጭ ነው።

የሙያ ማህበራት ከዓለም አቀፍ የሙያ ማህበራት ጋር ትስስር ቢያደርጉ የዓለም አቀፍ ሙያ ማህበራትን ሁነቶች በቀላሉ በተርም ወይም በተራ ወደ ሀገራችን መሳብ ያስችለናል ሲሉም ጠቁመው፣ ‹‹ብዙ ሙያ ማህበራት አሉን፤ ትስስር ላይ ግን ውስንነት አለብን። በዚህ ላይ የንግድ ማህበራትን ጨምሮ ከሙያ ማህበራት ጋር በመተባበር መሥራት ይኖርብናል›› ሲሉም አስገንዝበዋል።

ዘርፎችም እንዲሁ ተጽእኖ የሚፈጥሩ /ኢምፓክት ያላቸው/ ሁነቶችን መሳብ እንዳለባቸውም አመልክተዋል፤ በቱሪዝም ዘርፍ በተለይ በሚኒስትሯ የተሰጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ሁሉም በሚባል ደረጃ ዘርፎች እያመጡ ናቸው ሲሉ አብነት ጠቅሰው አብራርተዋል።

‹‹ይህ ሊበረታታ ይገባል፤ አንዴ ብቻ ብልጭ ብሎ እንዳይጠፋ በቀጣይ የኢምፓክት ግምገማ እየተሠራ ቁልፍ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማምጣት ያስፈልጋል›› ሲሉም አስገንዝበዋል።

በዚህ በኩል ሆቴሎች የሚሰጡት አገልግሎት ቁልፍ መሆኑንም ሃላፊው አስገንዝበዋል። የሁነቶች ተሳታፊዎች ቆይታቸውን ከሚያሳልፉባቸው ቦታዎች መሀል ሆቴሎች እንደሚጠቀሱ ተናግረው፣ እዚህ ላይ በትኩረት በመሥራት ሁነቶችን መሳብ ይገባል›› ብለዋል። በአገልግሎት በማላቅ እንዲሁም መረጃ በመስጠት ላይም መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ልዩ የታክሲ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ የመሥራት አስፈላጊነትንም አመልክተዋል። ባለፈው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ቱሪዝም ሚኒስቴር ወደ ሁለት ሺህ ለሚሆኑ የዚህ አገልግሎት ሰጪዎች ስልጠና መስጠቱን ጠቅሰው፣ በሀገሪቱ የሚከናወኑ ሁኔቶችን መረጃ በማወቅና በማሰራጨት ላይ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ብዙአለም እንዳስታወቁት፤ መንግሥትም ሃላፊነት አለበት። ኢትዮጵያ እስከ በ2020 የኮንቬንሽን ቢሮ መስርታ አታውቅም፤፡ የኮንቬንሽን ቢዝነስን አንደ ቢዝነስ አስባው አታውቅም፤ ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ከፍተኛ ሁነት ከሚያስተናግዱ ሀገሮች አንዷ ናት። ለምሳሌ በአመት ከ100 በላይ የሙያ ማሀበራት ሁነቶችን ታስተናግዳለች።

የደቡብ አፍሪካ ኮንቬንሽን ቢሮ ከሃያ አመት በፊት ነው የተቋቋመው። እነሱ ከሀገር አልፈው በከተሞችም ደረጃ ኮንቬንሽን ቢሮ መመስረት ችለዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ እኛም አዲስ አበባም ራሷን ለኮንፈረንስ ቢዝነስ እንድትሸጥ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል፤ ይህም ይሳካል ብዩ እስባለሁ›› ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶስት ዓመት በፊት በ2020 የኮንቬንሽን ቢሮ በመክፈት ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰው፣ በዚህም ጨረታ ማድረግና ማስተዋወቅ ላይ ይሠራል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የኮንቬንስ ቢዝነስ ሥራ በሁነት ላይ ይመሰረታል፤ ከዚያም አልፎ ቱሪዝሙን በሀገር በቀል ኢኮኖሚው የትኩረት አቅጣጫ አንዲሆን አድርጎ እየሠራ ነው። ይህ መጠናከር ይኖርበታል። መቀናጀት ሌላው የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው።

እንደ ማህበረሰብም ወደ ኢኮኖሚው የሚመጣውን ነገር ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ራስን ማዘጋጀት ይገባል። ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ምን ይፈልጋሉ፤ ምን አይነት የእደ ጥበብ ውጤት ላይ ራሴን ላሰማራ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።

አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሆነው አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅትም ምርምሮችን ይሠራሉ፤ በትርፍ ጌዜያቸውም በከፍተኛ ትምህርት ያስተምራሉ።

በሀገሪቱ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች ስለመሟላቸው አያለውም (ዶ/ር) ይገልጻሉ። ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀውን አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማእከልን እንዲሁም የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን ለእዚህ በአብነት ጠቅሰዋል።

ቀደም ሲል ጀምሮ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አፍሪካ ህብረት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያሏቸው ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ አዳራሾችም ሌሎች ለሁነቱ ከሚያስፈልጉ ማእከላት መካከል ተጠቃሾቹ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሀገሪቱ ቀደም ሲል ብዙ ሺዎችን ይዘው የሚመጡ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ በቂ ሥፍራ የላትም የሚል ቅሬታ ይቀርብባት እንደነበር አያሌው (ዶ/ር) አስታውሰው፣ አሁን ግን ይሄ ተፈትቶ ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በበቂ መልኩ ማስተናገድ የምትችልበት ሁኔታ ላይ ደርሳለች ብለዋል።

በቀጣይ በርካታ መሥራት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ አንዱና ዋናው ትልቁ ነገር የተሠሩትን መሠረተ ልማቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ማስተዋወቅ ነው። የስብሰባ አዘጋጆችንና ተሳታፊዎችን ለመሳብ እነዚህን መሠረተ ልማቶች ለማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን መጠቀም ይገባል። እንደ በቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አጃንስፍራንፕሬስ፣ ዥንዋ ያሉትን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የግድ መጠቀም ይገባል። ማህበራዊ ሚዲያውንም መጠቀም ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው ሀገራችን ይህን በሚገባ ለማስተዋወቅ አቅም የላትም ያሉት አያሌው (ዶ/ር) ፣ ሰፋ ያለ በጀት መድቦ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ዘመቻ ለማካሄድ በቂ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ‹‹እኛ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለብን። ስለዚህ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የግድ ይሆናል›› ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም ስንነጋገርበት የኖርነው ሀገሪቱ ይህን አይነቱን ገጽታዋን የሚያስተዋውቅላት ቢሮ በውጭ ሀገሮች እንደሌላትም ተናግረው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰንደቅ ዓላማዋን ይዞ በመንቀሳቀስ በአብዛኘውን የሀገሪቱን ገጽታ እያስተዋወቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የማስተዋወቅ ሥራችንም ቢሆን ከአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ ትንሽ ደከም ያለ ነው ሲሉ አመልክተው፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ድርጅቶች እንዲያግዙን በማድረግ የማስተዋወቁን ሥራ በስፋት መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የዚህ ሃላፊነት የቱሪዝም ሚኒስቴር ነው። እሱም ብቻውን አይደለም፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እጅ ለእጅ ተያይዞ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፤ በፕሮሞሽን ሥራ ላይ ከፍተኛ ሀብት መድቦ መሥራት ያስፈልጋል።

አሁን እያወራን ያለነው አዲስ አበባ ከተማ ስላለው ኮንፈረንስ ነው ያሉት አያሌው(ዶ/ር) ፣ የውጭ ዜጎች ለኮንፈረንስ መጥተው እንዲሁ ተመልሰው እንዲሄዱ ማድረግም እንደማይገባም አስገንዝበዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ተሳታፊዎቹ ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው ወደ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያሉትን ሀይቆች እንዲሁም ወደ ሰሜን ሄደው ታሪካዊ ሥፍራዎችን በተጨማሪም ወደ ደቡብ ሄደው የብሄር ብሄረሰቦችን ሕይወት እንዲጎበኙ ማድረግ ላይ መስራት ይገባል፡፡

ተሳታፊዎቹ ሀብታሞች ናቸው፤ ብዙ ገንዝብ ሊያወጡ ይችላሉ፤ በቂ ጊዜ ግን ላይኖራቸው ይችላል፤ እዚህ ላይ አስጎብኚ ድርጅቶችን በሚገባ አንቅቶና አደራጅቶ የሚጎበኙ ሥፍራዎችን እንዲያዘጋጁ በማድረግ ተሳታፊዎች ጉብኝት አርገው የሚመለሱበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።

‹‹አሁን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የሰላም ጉዳይ ነው›› ያሉት አያሌው(ዶ/ር)፣ ወደ ሰሜንም፣ ደቡብም ለመንቀሳቀስ የግድ ሰላም መኖር አለበት ፤ የሰላም ጉዳይ እየታሰበበት አይደለም ለማለት ሳይሆን የበለጠ ዋና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ለማለት ነው›› ሲሉም አስገንዝበዋል።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You