
አቶ እንዳለው ፈቃዱ ይባላሉ፤ የመምቤ ዱቄት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ናቸው። ፋብሪካው የሚገኘው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ነው። ፋብሪካው ከዛሬ አስር ዓመታት በፊት በአነስተኛ ማሽን በሶስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ ሥራ መግባቱን ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ ግን የማሽኖችን ቁጥር በማሳደጋቸው በ24 ሰዓት ውስጥም አንድ ሺህ ኩንታል ያመርታል ይላሉ። ካፒታላቸውም 160 ሚሊዮን ብር መድረሱን ያመለክታሉ።
ፋብሪካው በቀን አንድ ሺህ ኩንታል ሲያመርት የሚያጋጥመው የገበያ ችግር እንደሌለው የሚናገሩት አቶ እንዳለው፣ ማሽኑ የሚያመርተው 24 ሰዓት ሲሆን ለአፍታ እንኳ ቢሆን አይቆም ይላሉ።
የገበያ ሰንሰለቱ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ ያለው ምርት በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ገበያው ተጨማሪ ማሽን እንዲጨምሩ እያስገደዳቸው መሆኑን ያስረዳሉ። የገበያ መዳረሻቸውም ያሉበትን ክልል ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳና በሌሎችም እንደሆነ ያመለክታሉ። በአሁኑ ጊዜ በፋብሪካው ውስጥ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው በጊዜያዊነትና በቋሚነት 80 ሠራተኞች ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በፋብሪካው ቢንያስ በወር እስከ 28 ሺህ ኩንታል ዱቄት ተፈጭቶ ለገበያ ይቀርባል። የዚህን ያህል በርካታ ምርት ለገበያ ሲቀርብ በስንዴ አቅርቦት በኩል አንዳች ክፍተት የለም። ስንዴ የሚያገኙት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ሲሆን፣ ለምሳሌ ከአርሲ፣ አሳሳ፣ መቂ፣ ባሌ፣ ከአማራ ክልልና ከሌሎችም አካባቢ ነው። ያለምንም ውጣ ውረድ ስንዴው የሚመጣላቸው ፋብሪካቸው ድረስ ነው። የገበያም የአቅርቦትም ችግር ባለመኖሩ ፋብሪካውን ለማስፋፋት መሬት ጠይቀው አዎንታዊ ምላሽ እየተሰጣቸው ይገኛል።
በዱቄት ፋብሪካው ከዋናው የዱቄት ምርት በተጨማሪ የሚገኘው ተረፈ ምርት የየራሱ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የሚጣል ምንም ነገር የለም። ለአብነት አንደኛው ተረፈ ምርት ፉርሻካ ሲሆን፣ ለከብቶች መኖነት የሚያገለግል ነው። ከዚህ ሌላ ከስንዴው ተበጥሮ የሚወጣው ብጣሪ አፈር፤ ለከብቶች ማደለቢያነት እንዲሁም ለበግና ዶሮ መኖነት የሚፈለግ ነው። መኖው ከአካባቢው አልፎ በአብዛኛው የሚጫነውም ወደ አዳማ ሲሆን፣ የገበያ ችግርም እንዳላጋጠማቸው ያስረዳሉ።
ከተማ አስተዳደሩ ሁልጊዜ ከጎናችን ነው ያሉት አቶ እንዳለው፣ በቀጣይም ፋብሪካውን ለማካሮኒ ምርት ለማስፋፋት በጠየቁት መሠረት አምስት ሺህ ካሬ መሬት በከተማ አስተዳደሩ እንደተዘጋጀላቸው ገልጸዋል። በተመሳሳይ አሁን የሚያመርቱትን ዱቄት ለማስፋት ባቀዱት መሠረት ተጨማሪ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
እስካሁንም ማሽኖችን የሚገዙት ከልማት ባንክ በሚያገኙት ብድር ሲሆን፣ አሁንም ሊያመጡት ያሰቡትን ማሽን የሚያስመጡት ከልማት ባንክ በሚያገኙት ብድር እንደሆነም ነው ያስረዱት።
ይሁንና ማሽኑ እንዲመጣላቸው ካዘዙ ሁለት ዓመት ማስቆጠሩን ጠቅሰው፤ የዘገየባቸው ልማት ባንክ ቶሎ ባለመፍቀድ እንደሆነም ይናገራሉ። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በንግድ ባንክም አካባቢ የተመቻቸ ሁኔታ ከመኖሩም በላይ የዶላርም ችግር ባለመኖሩ ይፋጠናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ይገልጻሉ። የማሽኑ ዋጋ ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነው ሲሉም ይጠቁማሉ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ ከሚገኙት 24 የዱቄት ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ ከድጃና ቤተሰቧ የዱቄት ፋብሪካ ነው። የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ ወገን አዳነ እንደሚናገሩት፤ ፋብሪካው ከተቋቋመ 19 ዓመት ሞልቶታል። በጀመረበት ወቅት መነሻ ካፒታሉ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ነበር። በአሁኑ ጊዜ ካፒታሉ ወደ 100 ሚሊዮን ብር አካባቢ ደርሷል። በሶስት ማሽን በመጠቀም እየሠራ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ አራተኛው ማሽን ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል።
ወደ 70 ለሚጠጉ ሰዎች የሥራ እድል የፈጠረው ይህ ፋብሪካ፣ የስንዴ ምርት የሚያገኘው አብዛኛው ከአሳሳ፣ ባሌ አካባቢ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 70 በመቶ ያህል የስንዴ ግብዓት የሚያገኘው ከዞናቸው አሊያም ከክልላቸው ውጭ ካሉ ክልሎች እንደሆነ አቶ ወገን ይናገራሉ። ቀሪውን 30 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት የሚያገኙት ደግሞ በቅርብ ካሉ ወረዳዎች ነው ይላሉ።
የምርታቸው መዳረሻ ጅማ፣ አጋሮ፣ መቱ፣ አዲስ አበባ ሲሆን፣ እስከ 30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ከተሞች እንደሆነ ይናገራሉ። አብዛኛውን የሚልኩት ግን ወደ ኦሮሚያ ክልል መሆኑን በመጥቀስ፤ የገበያ ችግር ባለመኖሩም አዲስ ማሽን መጨመር ግድ ብሏቸው ወደ ሥራ እያስገቡ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ማሽኑ በቀን 920 ኩንታል አካባቢ ማምረት የሚያስችል አቅም ቢኖረውም፤ ከመብራት፣ ከውሃና ከማሽኑ ያገለገለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚስተዋል ችግር በመኖሩ የቁጥሩን 80 በመቶ አካባቢ እየሠራ ነው ይላሉ።
እርሳቸው እንደተናገሩት፤ ተረፈ ምርቱ ፉርሽካ ነው። ለከብት መኖነት አገልግሎት ላይ ይውላል። የጥሬ እቃ አቅርቦት ዋጋው ወጥ ካለመሆኑ የተነሳ ችግር ነው፤ የቦታ እና የመጋዘን እጥረትም አለ። እንዲያም ሆኖ በአሁኑ ጊዜ ከዱቄት ፋብሪካነት ወደ ፉድ ኮምፕሌክስነት ለማደግ እቅድ ይዘዋል።
የወራቤ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አክመል አብደላ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩን የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የአስር ዓመት እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ ይናገራሉ። የዱቄት ፋብሪካን ጨምሮ ሌሎችም የዚያ አካል ናቸው ይላሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ በወራቤ ከተማ ወደ 24 የዱቄት ፋብሪካዎች አሉ። ወደ 400 ሔክታር መሬት የሚጠጋ አንድ ራሱን የቻለ የኢንዱስትሪ መንደር አለ። በዚያም ውስጥ በተመሳሳይ የዱቄት ፋብሪካዎች የጀመሩበትና ልዩ ልዩ ፋብሪካዎች እየተገነቡ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ግንባታቸውን አጠናቅቀው ማሽነሪዎችን አስገብተው መብራት የሚጠብቁ አሉ፤ አሁን የቀረው ሥራ በከተማ አስተዳደሩ፣ በዞኑና በክልሉ ትብብር የመብራት ምሰሶ ተተክሎ ያንን ወደ መስመር የማስገባት ነው።
በከተማው የዱቄት ፋብሪካ መብዛቱ ፍላጎት በመኖሩ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በተጨማሪም ባለሀብቱ ኢንቨስት ለማድረግ በሚመጣበትና ኢንቨስት በሚያደርግበት ጊዜ በከተማ አስተዳደሩም ሆነ በክልሉ በኩል የሚሰጠው አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ በመሆኑ ነው ይላሉ።
አቶ አክመል እንደሚሉት፤ ከመብራት ጋር ተያይዞ የነበረው ችግር ሰፊ ነው። በአሁኑ ወቅት ችግሩ ተቀርፏል ማለት ይቻላል። ቀደም ሲል የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ (ሰብስቴሽን) አልነበረም፤ አሁን ግን ሰብስቴሽኑ የሚጠብቀው ምረቃ ብቻ ነው። የሙከራ አገልግሎት እየሰጠ ነው። ከዚህ ጋር ተተያይዞ ትልቅ ለውጥ መኖሩን ይገልጻሉ።
ከዚህ ቀደም የነበረው ሒደት ፋብሪካዎቹ ምርት ካስገቡ በኋላ መብራት የሚጠፋበት ሁኔታ ነው። ይህ ተቀርፏል ማለት ይቻላል። ከውሃ ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የምንጭ ውሃ አለ። በአሁኑ ጊዜ ግን በርካታ የጉድጓድ (የከርሰ ምድር) ውሃ ተቆፍሯል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የሚቀረው የኢንስታሌሽን ሥራ ብቻ ነው ያሉት።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም