
በሰመራ ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባ ዘመናዊ የዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ
አዲስ አበባ፡– የአፋር ክልል ያለው እምቅ ሀብት እና ፀጋ ኢትዮጵያ ለመበልጸግ የያዘችውን ውጥን ለማሳካት የሚያስችል ሰፊ አቅም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፋር ክልል ጉብኝታቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ ስንዴ እርሻ ልማት፣ በእንስሳት መኖ፣ ኢንዱስትሪ እና በኮሪደር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እጅጉን ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።
በአፋር ክልል በሰመራ ከተማና አካባቢው ግብርና፣ የኢንዱስትሪና የከተማ ኮሪደር ልማት ሥራዎችን መመልከታቸውን ገልጸው በክልሉ ገጠሩን ከከተማው የሚያስተሳስር የልማት እሳቤዎችን በማሰናሰል የሚታሰበውን ብልጽግና የሚያስጨብጥ ጅማሮ እንዳለ ለመመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በመስኖ እርሻ በ500 ሄክታር ገደማ የታረሰው አዲሱ የሳር ዝርያ አማካኝነት እየቀረበ ያለው የእንስሳት መኖ በድርቅ ምክንያት የቁም እንስሳቶች እንዳይጎዱ አስተዋጽኦ የሚያደርግ አዲስ ኢኒሼቲቭ መሆኑን አመልክተው፤ በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁ በቦረና እንስሳት በቂ መኖ እንዲያገኙ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ማስፋት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በአፋር ክልል ባለው ሙቀት ከዚህ ቀደም ስንዴ ማምረት የማይታሰብ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ጊዜ በበጋ መስኖ ከአንድ ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ስንዴ እየተመረተ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በክልሉ መኖና ስንዴ ማልማት አዲስ ታሪክ ነው ብለዋል፡፡
በቀዳማዊ እመቤት ፅህፈት ቤት ተገንብቶ በሰመራ ከተማ የተመረቀው የዳቦ ፋብሪካ በቀን 300 ሺህ ዳቦ እና 450 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸው፤ ይህም የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ የሚያሟላ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል በአፋር ክልል ያለው የኮሪደር ልማት መልካም ጅማሮ እንደሚገኝ ጠቅሰው ፤ የሰመራ ኮሪደር ልማት ከሌሎች አካባቢዎች ለየት የሚያደርገው ብዙ የሚፈርስ ቤትና የደቀቁ ሰፈሮች የሉበትም፡፡ ይልቁንስ የመንገድ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት መገንባት ፣ የመብራት ሥርዓት መዘርጋት፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራ እና የከተማን ደረጃ የመጠበቅ ሥራ በዋናነት በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። የኮሪደር ልማት ሥራው እስከ ቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ባለው ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።
በአፋር ክልል ያለው የእርሻ እና ኢንዱስትሪ ሥራው አመርቂ የሚባል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይሁንና ክልሉ ካለው ሀብት እና ፀጋ አንጻር ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል። የክልሉን ሀብት በሚገባ መጠቀም ከተቻለ ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ብልፅግና የሚጠቅም ትልቅ አቅም እንዳለው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በሀገሪቷ ያሉትን ሀብቶች ዓይንን ገልጦ በመመልከት እና በትጋት በመሥራት መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አፋር ክልል በመገኘት የክልሉን የግብርና እና የኢንዱስትሪ አቅሞች የሚያሳዩ ቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡ ፋብሪካው በተገጠሙለት ዘመናዊ ማሽኖች በመጠቀም 420 ኩንታል ስንዴ በቀን መፍጨት እና 300 ሺህ ዳቦዎችንም በ24 ሰዓታት ማምረት እንደሚችል ተገልጿል።
ጉብኝታቸው ከስድስት ወራት በፊት ምርት የጀመረውንና 15 ቶን በሰዓት የሚያመርተውን የአዮዳይ ዝድ ጨው ማምረቻ ምልከታን ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም በአፋር ክልል የተሳካ የበጋ ስንዴ ምርት እየተካሄደበት ያለውን ልማት ሥራ እና የአይሮላፍ መኖ ባንክ ልማት ማዕከልንም መጎብኘታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም