
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የሚሰበሰበው ደም ከዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት እጅግ ያነሰ መሆኑን ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡ ደም ማግኘት ያለባቸው ህመምተኞች ደም ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው እንደሚያልፍ እና አንዳንዶች አላስፈላጊ የሆስፒታል ቆይታ እንደሚኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው የደም ልገሳ አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚያስቀምጠው ከአንድ ሀገር አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ አንድ በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ደም ለጋሽ መሆን አለበት፡፡ ወይም የሕዝቡን አንድ በመቶ ደም ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚሰበሰበው ደም ከአጠቃላይ ሕዝቡ ዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ አይሞላም፡፡
‹‹የሕዝቡን አንድ በመቶ ደም ያስፈልጋል፡፡›› ሲባል አነስተኛው መስፈርት መሆኑን አስታውሰው፤ ሌሎች ተጨማሪ ፍላጎቶች እና አገልግሎቶች ሲኖሩ እንደ ደም ካንሰር ዓይነት ሕክምናዎች ሲያስፈልጉ፤ ፍላጎቱ ከሶስት እስከ አራት በመቶ ይደርሳል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ በመቶ ማለት ከአንድ እስከ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ ሰው መለገስ እንዳለበት አስታውሰው፤ በኢትዮጵያ እየተሰበሰበ ያለው የደም መጠን በየጊዜው እየጨመረ ቢመጣም የሚፈለገውን ግማሽ ያህሉን እንደማይሞላ አስረድተዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት በአጠቃላይ የተሰበሰበው ሁለት መቶ አርባ ሺህ ዩኒት ብቻ መሆኑን አውስተው፤ በዚህ ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት የተሰበሰበው 243 ሺህ ዩኒት ነው፤ መጠኑ እየጨመረ ነው፡፡ በዚሁ መቀጠል ቢቻል በዚህ ዓመት ከ450 ሺህ እስከ 500 ሺህ ዩኒት መሰብሰብ ቢቻልም የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት ላይ ለመድረስ አዳጋች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደሀገር ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ወደ ፍቃደኛ ደም ለጋሽ መዞር ከተቻለ በኋላ፤ የፈቃደኛ ደም ለጋሽ መጠን እየጨመረ ቢሆንም፤ ከዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከፍላጎት አንፃር ክፍተቱ እጅግ የሰፋ መሆኑን መካድ አይቻልም ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር አሸናፊ ገለፃ፤ ከደም ውስጥ የፕላትሌት እና ነጭ የደም ሴል ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ፍላጎት እና አቅርቦቱን ለማመጣጠን በየቦታው የደም ባንክ ያስፈልጋል፡፡ ክብደታቸው ከ50 ኪሎ በላይ የሚመዝኑ ብዙ የደም ለጋሾች ያስፈልጋሉ። በተጨማሪ የሰው ኃይል እና ቴክኖሎጂ ላይም በሰፊው መሠራት አለበት፡፡
ሁሉም ክልሎች የደም ባንኮች አሏቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገር ደረጃ 54 የደም ባንኮች አሉ ያሉት ዶክተር አሸናፊ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ በጣም ትልቅ እና የተወሳሰበ በመሆኑ በሚመች መልኩ እንደልብ የደም ባንክ አለ ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም