
– ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ደም እና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር
በቂ ደም ባለማግኘታቸው በሚሊየን የሚቆጠሩ እናቶች እና ሕፃናት በየዓመቱ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል:: ከተመዘገበው ሞት ውስጥ 72 በመቶ የሚሆነው በወሊድ ጊዜ በሚያጋጥም በቂ ደም ካለማግኘት ችግር ጋር የተያያዘ ነው:: ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ እናቶች እና ሕፃናቶች ተጠቃሾች ናቸው:: በኢትዮጵያ የሚዘጋጀው ደም የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መሥፈርት እጅግ የራቀ መሆኑን የሚናገሩት በኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር (ዶ/ር) አሸናፊ ታዘበው ናቸው:: የመጋቢት ወር የደም ልግስና ወር መባሉን ተከትሎ ከዕለቱ የወቅታዊ እንግዳችን ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው ጋር ቆይታ አድርገን በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል::
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ደም ባንክ የተመሠረተው መቼ ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው?
ዶ/ር አሸናፊ ፡– የኢትዮጵያ ደም ባንክ የተመሠረተው በ1964 ዓ.ም ነው:: እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በቀይ መስቀል ስር ሆኖ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር:: በቀይ መስቀል ውስጥ ሆኖ ለሕሙማን የሚያስፈልገውን ደም ሠብስቦ፣ መርምሮ እና ጥራቱን ጠብቆ ለማድረስ በሚል ዓላማ የተመሠረተ ነው:: ነገር ግን የተቋቋመበት ዓላማ እየሰፋ ለሕብረተሰባችን የደም እና የዓይን ብሌን አቅርቦት ሰብስቦ ጥራቱን ጠብቆ ለተጠቃሚ አካላት ማድረስ ጀመረ:: እናም ሥራው ለተጠቃሚው በትክክል አገልግሎቱ መሰጠቱን እስከማረጋገጥ የሚደርስ ሥራ ማከናወን ቀጠለ:: ከ2004 ዓ.ም በፊት አገልግሎት ሲሰጥ ብዙ ደም የሚሰበስበው በቤተሰብ ምትክ ነበር::
አዲስ ዘመን፡- የቤተሰብ ምትክ ምን ማለት ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡- የቤተሰብ ምትክ ማለት አንድ ቤተሰብ ቤተሰቡ ሲታመምበት የቤተሰብ አባል የግድ ደም እንዲያቀርብ ማድረግ ነው:: በዚያ ጊዜ አብዛኞቹ ደም ባንኮች በቀይ መስቀል ውስጥ ነበሩ:: እስከ 2004 ዓ.ም የነበሩት የደም ባንኮች በብቃትም፣ በጥራትም ሆነ በመጠን የተደራሽነት ውስንነት ነበረባቸው:: በሌላ በኩል ደም የማድረስ ኃላፊነት የመንግሥት ነው:: በዚህ ላይ መተማመን ስለመጣ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ የደም ባንክን በጤና ሚኒስቴር አንድ ዳይሬክቶሬት ሆኖ እንዲሠራ ወሰነ::
ከዳይሬክተርነት በኋላ በ2007 ዓ.ም ሚያዚያ ላይ በተጠሪ ተቋምነት ተቋቋመ:: ስለዚህ አጠቃላይ የኢትዮጵያ የደም ባንክ ጉዞ ይሔንን ይመስላል:: በመጨረሻም የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ 2015 ዓ.ም የካቲት ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ተብሎ እንደገና ተቋቋመ:: ተቋሙ ከደም ባንክ በተጨማሪ የዓይን ባንክ አገልግሎትን ይዞ በመምጣቱ፤ በዚህ ስያሜ በአሁኑ ሰዓት የደም እና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት በመባል ይታወቃል::
አዲስ ዘመን፡- በዋናነት ምን ምን አገልግሎቶችን ይሰጣል?
ዶ/ር አሸናፊ፡- አገልግሎቱ እየሰፋ ነው:: ልዩነቱ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት ከቤተሰብ ምትክ በመውጣት፤ በበጎ ፈቃድ የሚሰጥ ደም እየተሰበሰበ ነው:: ተቋሙ የተሰበሰበውን ደም እየመረመረ፤ ጥራቱን እያረጋገጠ፤ ለሆስፒታሎች ያደርሳል:: ሆስፒታሎችም በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ይከታተላል:: በተመሳሳይ የዓይን ብሌን ጠባሳ ላጋጠማቸውም ከመሞታቸው በፊት ቃል በገቡ ሰዎች አማካኝነት የዓይን ብሌንን በመሰብሰብ፤ የተለገሰውን ዓይን በመመርመር እና ጥራቱን በማረጋገጥ በሆስፒታች አማካኝነት ለተጠቃሚዎች ያደርሳል::
የተለገሰው የዓይን ብሌን በትክክል መድረሱን እና ለሚገባው አካል ቀዶ ጥገና መሠራቱን ያረጋግጣል:: ዓይን የተለገሱት ሰዎች የዓይን ብርሃናቸው መመለሱን እና ያገኙትን ውጤት ይከታተላል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከዓይን ባንክ ጋር ተያይዞ የእንግዴ ልጅ ሕብረ ሕዋስ የ(Amniotic membrane tissue) አገልግሎት ጀምረናል:: ካለፈው ዓመት ሰኔ ጀምሮ ይህንን እየሠራን ነው::
አዲስ ዘመን፡- የእንግዴ ልጅ ሕብረ ሕዋስ ማለት ምንድን ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡- የእንግዴ ልጅ ክርታስ የዓይን ጠባሳ ላለባቸው ይውላል:: ልጆች ሲወለዱ የሚጣለው ክርታስ በሕክምና ዘዴ ተዘጋጅቶ ተመርምሮ እና ጥራቱ ተጠብቆ በእዚሕ ዓይነት ሕክምና ሊድኑ ለሚችሉ በሽታዎች እየዋለ ይገኛል:: ይሄ ከሰኔ 16 ዓ.ም 2016 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ላይ የዋለ ነው::
ሌላው ከደም እና ከዓይን በተጨማሪ ስርሕዋር ሕክምና (Stem cell therapy) ላይም እየሠራን እንገኛለን:: ይህ አብዛኛው በደም ካንሰር ላይ የሚሰጠውን ሕክምና ማሻሻል ነው:: ለደም ካንሰር ውጪ አገር በመሄድ ንቅለ ተከላ ይሠራል:: ያንን ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረግን እንገኛለን:: በጀት ተመድቦለት፤ የሰው ኃይል ኖሮት፤ አገልግሎቱ የሚሰጠው በሆስፒታሎች ነው:: እንደማንኛውም ንቅለ ተከላ ስርወ ሕዋሱን (Stem cell) የምንሰራው በመመርመር፤ ጥራቱን በማረጋገጥ እና ለበሽተኛው እንዲደርስ በማድረግ ነው:: መጨረሻ ላይ የደረሰውን ደግሞ እንደማንኛውም የደም እና የዓይን ክትትል የሕብረ ሕዋሱንም ውጤቱን ለማወቅ እንሠራለን:: በዚህ ላይ መሠረት ለመጣል ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር እየሠራን ነው:: አንዴ መሠረት ከጣልን በኋላ ደግሞ ወደ ሌሎች እንደርሳለን::
በመጨረሻ እየሠራን ያለነው የደም ክፍልፋዮችን ማምረት ላይ ነው:: ደም ሲባል ብዙ ንጥረ ነገሮች አሉ:: ነጭ የደም ሴል፤ ቀይ የደም ሴል፣ ፕላትሌት የሚባሉ ለደም መርጋት የሚያገለግሉ እና የውሃ ክፍሉ ፕላዝማ የሚባል ነገር አለ:: ስለዚህ ደም ሲሰጥ እንደዓለም አቀፍ ምክረ ሃሳብ፣ ያደጉት አገራት እንደሚገልፁት ሙሉ ደም እንዳለ በጭራሽ አይሰጥም:: የሚሰጠው ሂደቱ ተጠብቆ ተለይቶ ነው:: እኛ ግን ሙሉ በሙሉ በእዚህ አቅም ላይ ስላልደረሰን ወደ 30 እና 40 በመቶውን ብቻ ለይተን እንሰጣለን::
አዲስ ዘመን፡- ማለትም ነጭ የደም ሴል፤ ቀይ የደም ሴል፣ ፕላትሌት የሚባሉ ለደም መርጋት የሚያገለግለውን እና የውሃ ክፍሉ ፕላዝማው ሳይለይ እየተሰጠ ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡– በእርግጥ እየለየን ለመስጠት እየሞከርን ነው:: ነገር ግን ይህን ያህል አላደግንም:: እንዲህ እየለየን እንስጥ ካልን በጣም ዘመናዊ መሳሪያዎችን እና የሰው ኃይል ይፈልጋል:: ሆኖም እርሱን በመስራት ላይ እንገኛለን:: ከዛ ውስጥ በዋናነት እየሰራን ያለነው ሁለቱ ፕላትሌት የሚባሉ ለደም መርጋት የሚያገለግለውን በተለይ ለካንሰር ሕክምና የሚያገለግለውን እና የውሃ ክፍሉን ፕላዝማውን እየለየን ነው:: እዛ ላይ ብዙ ተጠቃሚ የለም:: ፕላዝማን የሚፈልጉት በጣም ጥቂት ተጠቃሚዎች ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- ውሃማ ሲሉ ግልፅ ቢያደርጉት?
ዶ/ር አሸናፊ፡- ውሃማ ክፍል ስንል ውሃ አይደለም:: የውሃማ መሳይ ፈሳሹ በረቀቀ ቴክኖሎጂ ወደ መድሃኒትነት መቀየር ይቻላል:: እኛ ይህንን እየለየን እንዲሰበሰብ እያደረግን ነው:: እርሱን ወደ መድሃኒትነት ለመቀየር ጥረት እያደረግን ነው:: ወደ መድሃትነት ሲቀየር ፋብሪካ ያስፈልገዋል:: ለእዚህ የሚሆን ፋብሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም:: አንድ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኝ ተመሳሳይ ፋብሪካ ጋር በቅርበት እየሠራን እንገኛለን::
ከፕላዝማ የሚገኘው መድሃኒት በጣም ውድ ነው:: ለሾተላይ የሚውለው አንታይ ዲ የሚባለው መድሃኒት አለ:: ለሂሞፊሊያ የሚፈለግ አልቦ ሚ መድሃኒትም በተመሳሳይ ከዚሁ የሚገኝ ነው:: ተላላፊ ለሆኑም ይሁን ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ለሂፕታይተስ የሚያገለግሉ በጣም ውድ መድሃኒቶች ከፕላዝማ ይወጣሉ::
እነዚህ መድሃኒቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የመግባት ዕድላቸው አነስተኛ ነው:: የሚገዙት በጣም በውድ ነው:: ስለዚህ አሁን እነርሱን እየሠራን እንገኛለን:: ስናጠቃልለው ከአዲሱ አዋጅ ጋር ተያይዞ አራቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን እንገኛለን:: አሁን ደግሞ የአካል ንቅለ ተከላ የሚመለከተው ተቋም ይሄ ስለሆነ በቅርቡ በመፅደቁ ወደ እዛም እንገባለን::
አዲስ ዘመን፡- የትኞቹ የአካል ንቅለ ተከላዎች?
ዶ/ር አሸናፊ፡- ከደም እና ከአይን ንቅለ ተከላ ባሻገር የደም እና ሕብረ ሕዋስ ባንኩ የኩላሊት እና የጉበት ንቅለ ተከላዎች ላይም ይሰራል:: እርሱ ሕብረ ሕዋስ ስለሆነ አዋጃችን ሕብረ ሕዋስ ላይ ስለደረሰ ነው:: አሁን አካል ስንል ደግሞ ከሕብረ ሕዋስ ከፍ ይላል:: ስለዚህ እርሱ አዋጃችን ላይ ስላልነበረ፤ እነርሱ ላይ አልሠራንም:: አሁን ደግሞ የአካል የሚለው ላይ ለመድረስ አዋጅ ላይ ለመመርኮዝ ሥራዎችን ጀማምረናል::
አዲስ ዘመን፡- ወደ እዚህ ሥራ ለመግባት የተቸገራችሁት ለምንድን ነው? በአዋጁ ምክንያት ብቻ ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡- መቸገር ሳይሆን ረዥም የዝግጅት ሂደትን ይፈልጋል:: መጀመሪያ የመቋቋሚያ አዋጃችን መቀየር አለበት:: እስከ አሁን ድረስ የመቋቋሚያ አዋጃችን እስከ ሕብረ ሕዋስ ድረስ ብቻ ነበር:: አሁን ያንን የምንጠቀልልበት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠን ስልጣን አለ:: ነገር ግን ገና የፀደቀው ጥር ላይ ነው:: በዚሁ መሠረት በእኛ በኩል ያለውን ጨርሰናል:: ለሚኒስትሪው አቅርበን ሚኒስትሪው ደግሞ ለካቢኔ ያቀርባል ማለት ነው:: እርሱ ደረጃ ላይ ነን::
ሁለተኛ ዝግጅት የሚያስፈልገው የተቋሙ መዋቅር ላይ ነው:: ተቋሙ ያለው የሰው ሃብት መዋቅር ከሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ጋር አያይዘን ሪፎርም እየሠራን ስለሆነ እንደጤና ሚኒስቴር ከተመረጡ ተቋማት ውስጥ ስለሆንን ከዛ ጋር አያይዘን መዋቅር እየሰራን ነው:: ይህንን ብሔራዊ የንቅለ ተከላ መሸከም የሚችል ሥርዓት ለመገንባት እየሠራን ነው:: በቀጣይ የሰው ኃይልን ማሰልጠን እና ማብቃት ያስፈልጋል:: ላብራቶሪዎች ላይ የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ:: ሥራው የላብራቶሪ አገልግሎት የሚፈልግ በመሆኑ ያንን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል::
አዲስ ዘመን፡- የተቋቋማችሁበትን ዓላማ አሳክተናል ብላችሁ ታምናላችሁ?
ዶ/ር አሸናፊ፡– ይህንን በማድረግ ዙሪያ ከመጨረሻው ዓላማ ውጪ ሌሎቹ ላይ ጥሩ ነን ብዬ አስባለሁ:: የመጨረሻው ዓላማ ስንል የጤና ተቋማት ጋር በመሄድ በትክክል በአግባቡ እንደተጠቀሙት እና ደምም ይሁን ሌላ የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው የሚለውን ማረጋገጥ ማለቴ ነው:: ያንን የጎንዮሽ ጉዳት ከመከታተል አንፃር ውስንነት አለ:: ውስንነቱም የመጣው የተቋቋምንበት አዋጅ የሚያስቀምጥልን እስከ ማሰራጨት ድረስ በመሆኑ ነው:: ነገር ግን ከስርጭት በኋላ ሆስፒታሎች ጋር ሲሄድ ቢያንስ የደም ባንኮችን መቆጣጠር ያለበት አካል በግልፅ አልተቀመጠም::
አዲሱ አዋጅ ላይ ለማስተካከል እየሞከርን ነው:: ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ እርሱ ክፍተት ስለነበረበት በትክክል አልተቆጣጠርንም:: ሌላው ሆስፒታሎች ላይ ልክ እንደሌላው ስርዓት ሁሉ ይሄንን የደም እና የደም አቅርቦት የሚያስተዳድረው ሆስፒታል ትራንስፊውሽን የሚባሉ ኮሚቴዎች ነበሩ:: እነርሱ እየሠሩ አይደሉም:: እየሰሩ ቢሆንም የዓቅም ውስንነት እና የክትትል ውስንነት ችግር አለባቸው:: እኛም ጋር በዛ ፊልድ ላይ በደንብ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አለብን::
መሠረታዊ እውቀት ሊኖር ይችላል:: ነገር ግን በደንብ ስፔሻላይዝድ ያደረገ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፤ እነዚህን ነገሮች ለማስተዳደር ክፍተት ፈጥሮብናል:: በደም እና የደም ሕክምና ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል ምንም የለም ማለት ይቻላል:: ማንም ሰው በደም ብቻ ላይ ሰልጥኖ የሚሠራ የለም:: ስለዚህ አንድ ዋነኛው ችግር ነው:: እኔም በሙያዬ ሐኪም ብሆንም በትራንስፊውሽን ወይም በደም ሕክምና አልሰለጠንኩም:: እኔ ተሿሚ ስለሆንኩ መሰልጠን ላይጠበቅብኝ ይችላል:: ነገር ግን ታች ያሉ ቴክኒካል ባለሞያዎች እንዲሰለጥኑ ይፈለጋል:: ነገር ግን ይህ አልሆነም::
አዲስ ዘመን፡- የማይሰለጥኑት ለምንድን ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡– አንደኛው እና ዋነኛው ምክንያት ትምህርቱ እዚህ አገር አለመኖሩ ነው:: ትራንስፊውሽን ሜዲስን ይባላል:: ትራንስፊውሽን ሜዲስን እዚህ አገር የለም:: ስለዚህ ዋናው ችግር እርሱ ነው:: ሌላው ፍላጎት ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ የሕክምና ዘርፍ ገበያ መር ነው:: ከፍላጎት ይልቅ ከተማ ውስጥ ያለው ገበያ ይታወቃል:: ስለዚህ የተወሰነ የፍላጎት ጉዳይ አለ:: ነገር ግን ከዚህ በፊት የነበሩ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፤ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር ሆነን ካሪኩለም ለማዘጋጀት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ነበሩ:: አሁን እዚህ ላይ አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው::
አዲስ ዘመን፡- ውጪ ልኮ ማስተማር አይቻልም?
ዶ/ር አሸናፊ፡- እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት የውጪ አገር የትምህርት ዕድል ቀላል አልነበረም:: አሁን ግን መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ በጀት መድቦልን ውጪ ለማሰልጠን እየሞከርን ነው:: በተለይ በስርወ ሕክምና ላይ በጀት ተፈቅዶልናል:: ምክንያቱም እዚህ አገር ላይ በዚህ ዘርፍ ምንም ዓይነት ስልጠና ስለሌለ ነው:: ነገር ግን በዚህ አገልግሎት ላይ የደምም ሆነ የዓይን እንዲሁም የሌሎች አካላት ንቅለ ተከላ ሁሉም የውጪ ስልጠናዎችን ይፈልጋሉ:: ሁሉም ነገሮች እዚህ አገር የሉም:: ስለዚህ መንግሥት የተወሰነ ዕድል ሰጥቶናል:: ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ዓይነት በጀት መድቦልናል:: ዘንድሮ የታሰበው የበጀት ዕቅድ ላይ ተይዟል:: ስለዚህ ወደ ውጪ እየላክን ለማሰልጠን እና አቅማችንን ለማሳደግ እንሞክራለን::
አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን እንዲማሩ የላካችኋቸው አሉ?
ዶ/ር አሸናፊ፡- አሁን በቀጣይ ወር የሚሔዱ አሉ::
አዲስ ዘመን፡- እየሰበሰባችሁ ያለው የደም መጠን ሕዝብ ከሚፈልገው አንፃር ምን ያህል የተመጣጠነ ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡– ሕብረተሰቡ ምን ያህል ያስፈልገዋል የሚለው ለማወቅ ትንሽ አዳጋች ነው:: ከሆስፒታሎች መረጃዎችን እንወስዳለን:: የእርካታ መጠንን ለመገምገም እንሞክራለን:: ነገር ግን አጠቃላይ የዓለም ጤና ድርጅት የሚመክረው ወይም የሚያስቀምጠው ወሰን አለ:: እርሱ የሚያስቀምጠው ከአንድ አገር ሕዝብ ውስጥ አንድ በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ደም ለጋሽ መሆን አለበት:: ወይም የሕዝቡን አንድ በመቶ ደም ያስፈልጋል:: ያ ማለት አነስተኛው መስፈርት ነው:: ነገር ግን ሌሎች ተጨማሪ ፍላጎቶች እና አገልግሎቶች ሲኖሩ እንደ ደም ካንሰር ዓይነት ሕክምናዎች ሲያስፈልጉ፤ ፍላጎቱ ከሶስት እስከ አራት በመቶ ይደርሳሉ:: የእኛ አንድ በመቶ ማለት አንድ ሚሊየን እስከ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን አካባቢ ሰው መለገስ አለበት ማለት ነው::
እንደ አገር ካለፉት አስር ዓመታት ጀምሮ ወደ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ከዞርን አንስቶ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች መጠን እየጨመረ ነው:: የዛሬ አምስት ዓመት በአጠቃላይ የተሰበሰበው ሁለት መቶ አርባ ሺህ ዩኒት ነበር:: አሁን ባለፉት ሰባት ወራት የሰበሰብነው 243 ሺህ ዩኒት ነው፤ መጠኑ እየጨመረ ነው:: ነገር ግን ከዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት አንፃር አሁንም በጣም ሩቅ ነን:: በዚሁ ብንቀጥል በዚህ ዓመት 450ሺህ አካባቢ ልንደርስ እንችላለን:: በጣም ብንሠራ እንኳ የምንደርሰው 500 ሺህ ዩኒት ብቻ ነው:: ይህ ማለት ዜሮ ነጥብ አምስት አካባቢ ነን:: የደም ክምችታችን ከዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት ግማሽም አልደረስንም::
ከፍላጎት አንፃር ሲታሰብ ደግሞ ክፍተቱ ይብሳል:: በጣም ብዙ በሽተኞች ደም ማግኘት እያለባቸው፤ ደም ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው ያልፋል:: ወይም አላስፈላጊ የሆስፒታል ቆይታ ይኖራቸዋል:: ስለዚህ ይሄ የማይካድ ሃቅ ነው:: ክፍተቱ በጣም ሰፊ ነው:: ይህን ክፍተት ከማጥበብ አንፃር ተቋሙ ብዙ እየሠራ ነው:: ነገር ግን ለውጡ እና ፍላጎቱ አሁንም ገና አልተሟላም:: በተለይ ፕላትሌት እና ነጭ የደም ሴል ላይ ያለው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው:: በተቃራኒው ፍላጎት እና አቅርቦቱ እጅግ የተራራቀ ነው:: በተጨማሪ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ይፈልጋል:: በተለይ ክብደታቸው ገፋ ያሉ ከ50 ኪሎ በላይ የሚመዝኑ ብዙ የደም ለጋሾች ያስፈልጉናል::
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ አቅርቦቱን ማሻሻል የሚቻለው እንዴት ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡– ግንዛቤ መፍጠር አንዱ ነው:: በተለይ በከተሞች አካባቢ የግንዛቤ ችግር አለ ብለን አናስብም:: ነገር ግን በክልል ገጠሮች አካባቢ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሠራት አለበት:: ከማዕከል የራቀ ማኅበረሰብ የግንዛቤ ችግር እንዳለበት አስተውለናል:: እዛ ላይ በቀጣይ እንሠራለን:: ሁለተኛው ተደራሽነት ላይ መሥራት ነው:: በየቦታው የደም ባንክ ያስፈልጋል:: በአሁኑ ሰዓት በአገር ደረጃ 54 የደም ባንኮች አሉ:: ሁሉም ክልሎች የደም ባንክ አሏቸው:: ነገር ግን የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ በጣም ትልቅ እና የተወሳሰበ ነው:: የደም ባንክ በሚመች መልኩ እንደ ልብ አለ ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም::
ለአገሪቱ የሚመጥን የደም ባንክ እንዲኖር ብዙ ይጠይቃል:: ሌላው የደም ባንኮቹ ቢኖሩም የሰው ኃይል ይፈልጋል:: ይሄ በጣም ከማሕበረሰብ ጋር የሚሠራ ሥራ እንደመሆኑ መጠን ብዙ መመላለስ፣ ብዙ ማስተማር እና ብዙ ማነቃቃት ያስፈልጋል:: በጣም የተነቃቃ በደንብ የሰለጠነ አገልግሎት ሰጪ ያስፈልገናል:: ከእርሱ አንፃር ሲታይ ውስን ነው::
ሶስተኛ ፋይናንስ ነው:: ብዙ ነገሮች ላይ ወጪው የሚወጣው ከማዕከል ነው:: በተለይ የደም መሰብሰቢያ ቁሳቁሶችም ሆኑ መመርመሪያ ኪቶች እና ስልጠናዎች ወጪያቸው ከማዕከል ነው:: የሰው ኃይል መቅጠር ተንቀሳቅሰው ደም ሲሰበስቡ የሚወጡ ወጪዎች ነዳጅ እና መኪናን ይፈልጋሉ:: ከእርሱ አንፃር በተለይ ክልሎች ላይ በጣም ከባድ ነው:: አዲስ አበባ ላይ ችግር የለም:: ወደ ክልሎች አካባቢ ግን በጣም ችግር አለ:: የማመቻቸት ሁኔታ የለም:: በውስን ገንዘብ መስራት የማይችሉ አሉ::
አዲስ ዘመን፡- መጋቢት የደም ልገሳ ወር ያላችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡- የመጋቢት ወርን የመረጥንበት ምክንያት ደም የሚሰበሰበው ከሰው ነው:: የሰው ልጅ ደግሞ በተለያየ ምክንያት የደም ልገሳ ሁኔታው ሊቀንስ ይችላል:: ደም ከመለገስ ጋር ተያይዞ በተሞክሯችን እንዳየነው የሚለያዩ ወራቶች አሉ:: ለምሳሌ ብዙ ደም የምንሰበስበው ከዩኒቨርስቲ እና ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ነው:: የምንሰበስበውም በሚገኙበት ቦታ በመሔድ ነው:: ተማሪ በሚበተንበት ጊዜ ለምሳሌ ክረምት ላይ ወይም ፈተና በሚኖርበት ጊዜ ጥር ላይ የሚሰበሰበው ደም በጣም ዝቅተኛ ነው::
ሌላው አፅዋማት ሲኖሩ ደም ለማግኘት እንቸገራለን:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛ ነው:: በተለይ ሁለቱም ፆሞች አንድ ላይ ከሆኑ ደም ለማግኘት እንቸገራለን:: ስለዚህ በሁለቱ ወቅቶች ይቀንሳል:: ሶስተኛ የዓደባባይ በዓላት ሲበዙ ደም ለማግኘት እንቸገራለን:: ምክንያቱም ሕብረተሰቡ ትኩረቱ በዓላት ላይ ስለሚሆን ደም ለማግኘት ይከብደናል:: ስለዚህ ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛ ሆኖ ያገኘነው የጾም ወቅት ነው:: ተማሪዎችም ሆኑ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ስለሚፆም ወሳኝ ወቅት ስለሆነ የፆሙን ማዕከል ብዙ ጊዜ መጋቢትን አያጣውም:: ስለዚህ መጋቢትን የደም ማሰባሰቢያ ወቅት ብለን ሰይመናል:: ስለደም ጥቅሞች፣ ስለለጋሽነት፣ ስለበጎ ፈቃድ፣ ስለመልካም አገልግሎቶች ከመፆም ከመፀለይ ባለፈ ልገሳን የምናበረታታበት እንዲሆን በሚል ቅስቀሳ እያደረግን ነው::
አዲስ ዘመን፡- ነገር ግን ሰዎች ፆም ላይ ሆነው መለገስ ይችላሉ?
ዶ/ር አሸናፊ፡- አይችሉም:: ዋናው ጉዳይ መፆም ማለት ምግብ ወይም ውሃን አለመውሰድ ነው:: ቀኑን ሙሉ አይፆምም፤ የማይፆምባቸው ሰዓታት አሉ:: የኦርቶዶክስ ፆም እስከ ምሳ ሰዓት ወይም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ነው:: ከፆሙ በኋላ መለገስ ይቻላል:: ሙስሊሞችም ከአፍጥር በኋላ ፈቃደኛ ከሆኑ መለገስ ይችላሉ:: እኛ የሚለግሱትን ደም ለማግኘት ዝግጁዎች ነን:: በሱማሌ ክልል ጥሩ እየተለመደ ነው:: ሱማሌ ላይ ደም የሚሰበሰበው ከአፍጥር በኋላ መሆኑ ተለምዷል::
በሌላ በኩል በአፅዋሞቹ ላይ የማይሳተፍ ብዙ ሕዝብ አለ:: ስለዚህ እጥረቱን ተገንዝበው ሌላ ጊዜ እንኳ ባይለግሱ ቢያንስ እንደአገር፣ እንደሕዝብ እና እንደወገን ቋሚ ለጋሾቻችን ስለማናገኝ በዚህ ጊዜ ጥሪ አድርገን እንዲለግሱ ለማድረግ ነው:: ስለዚህ አንደኛ ከአፅዋማት ሰዓት ውጪ መለገስ እንዲለመድ፤ ጊዜው በጎ ድርጊት የመፈፀሚያ በመሆኑ፤ ደም በመለገስ መልካም ነገር እንዲፈፅሙ ለማሳሰብ ነው:: ከመፆም ከመፀለይ ባለፈ በጎ ሥራ በፈጣሪ ፊት ተቀባይነትን የሚያስገኝ በመሆኑ፤ ያንን ለማስታወስ ነው:: ሶስተኛ የፆም ተሳታፊ ያልሆኑ ወገኖች እንዲሳፉ ለማስታወስ ነው::
አዲስ ዘመን፡- እንደተቋም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበውን የደም መጠን ለመጨመር ምን ያህል ሠርተናል ትላላችሁ?
ዶ/ር አሸናፊ፡- በተቋም ደረጃ ስትራቴጂክ ፕላን አለን:: በተለይ የሕዝብ ግንኙነት ላይ የማስተማር ሥራዎችን እንሠራለን:: አንደኛ ለሕዝቡ በተለይ መገናኛ ብዙሃንን ማህበራዊ የትስስር ገፆችን በመጠቀም እንቀሰቅሳለን:: ሌላው የፊት ለፊት ትምህርቶች ላይ ሰፊ ገለፃዎችን እናደርጋለን:: ፎረሞች ላይ እንሠራለን:: የትምህርት ቤት፣ የወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች ፎረሞች አሉን:: የአርቲስቶች እና ሌሎችም ወደ መሬት ሊደርሱ የሚችሉ ፎረሞችን በመጠቀም ለማስተማር እና ለመቀስቀስ እንሞክራለን::
መቀስቀስ ብቻ ሳይሆን እነዛ የተማሩ ሰዎች ደም ለጋሽ እንዲሆኑ፤ ደም መለገስ ባይችሉም እና ሌሎች የሚለግሱ ሰዎችን እንዲያመጡ እናሳውቃለን:: በተለያየ መልኩ የማስተማሪያ ፅሁፎችን እናሰራጫለን:: ለመድረስ እንሞክራለን:: በተለይ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ እና ትምህርት ቤቶች አካባቢ በስፋት ስለምንሰራ የልገሳ ክለቦችን እናቋቁማለን:: በጣም በርካታ ክለቦች አሉን:: አዲስ አበባ ውስጥ በቋሚነት በየሶስት ወሩ የሚለግሱ እና ለ50ኛ እና ለ60ኛ ጊዜ እየለገሱ ያሉ አሉ::
ዘንድሮ ሁለት የደም ክለቦችን አቋቁመናል:: የደም ልገሳ አስተባባሪዎችንም አቋቁመናል:: ይህንንም ወደ ክልሎች ለማስፋት እየሞከርን ነው:: ሌላው ደግሞ የተቀበልነውን የምንሰጥበትን ሁኔታም እያሻሽልን ነው:: ከፍት ፍቱ ፊቱ እንደሚባለው እዛም ላይ እየሠራን ነው:: ደም ሊሰጥ ለመጣ ሰው አቀባበላችን የማያስደስት ከሆነ፤ ተመልሶ አይመጣም:: ስለዚህ በዛ ላይ እየሠራን ነው::
በሌላ በኩል ለቋሚ ለጋሾች ምንም ዓይነት የጤና ጉዳት እንዳይደርስባቸው መምከር፤ የምርመራ ውጤቶቻቸውን ማሳወቅ፣ ውጤታቸውን ካሳወቅን በኋላ አስፈላጊ ምክሮችን መስጠት እና ለጋሾችን መንከባከብ ላይ እየሠራን ነው:: በተጨማሪ በቅርቡ ለማሳወቅ ያቀድነው የለጋሾች የማቆያ እና የማትጊያ ስትራቴጂ በመንደፍ የለጋሾችን መረጃ በማጥራት ላይ ነን:: በቅርቡ እንደጨረስን ይፋ እናደርጋለን::
አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን በሰራችሁት ሥራ የተገኘ ለውጥ አለ?
ዶ/ር አሸናፊ፡- አዎ! ቁጥሮች ይናገራሉ:: ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው:: የዘንድሮ እና የአምናው ራሱ ሲወዳደር በተመሳሳይ ጊዜ ከ40ሺህ ዩኒት በላይ ልዩነት አለው::
አዲስ ዘመን፡- ደም በጣም የሚፈለገው በየትኛው ወቅት ነው?
ዶ/ር አሸናፊ፡- ይሄኛው ወቅት ነው:: በአፅዋማት ጊዜ ሆስፒታሎች አካባቢ በሽተኛ ይበዛል:: እርሻ ላይ የከረመውም ሌላ ሌላውም ወደ ሆስፒታል የሚመጣው በዚህ ጊዜ ነው::
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ?
ዶ/ር አሸናፊ፡- አዎ! ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ:: በተለይ በዚህ ወቅት ወገኖቻችን በደም እጥረት ምክንያት ሕይወታቸው እንዳያልፍ እና ሌላ ከባድ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ:: ዕድሜያችን ከ18 በላይ ኪሏችን ከ45 በላይ የሆንን ጤነኛ ሰዎች በደም መለገሻ ተቋማት እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ጣቢያዎች እየተገኘን ደም መለገስ እንችላለን:: ደም መለገስ የማንችል ደግሞ ሰዎችን እንድናስለግስ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን:: በዚህ ወር ላይ ብናተኩርም ደም ሁልጊዜ የሚሰጥ ነገር ነው:: አንድ ጊዜ ተሰጥቶ የሚቆም አይደለም:: አሁንም እንፀልይ፤ እናመስግን፤ ደም እንለግስ እንላለን::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ እናመሰግናለን::
ዶ/ር አሸናፊ፡- እኛም ዕድሉን ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን::
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም