የችግሮቻችን መፍቻ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር ምን ያህል እየተጠቀምንበት ነው?

በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ተጀመረ ተብሎ ከሚታሰብበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የፖለቲካ ባህል ስናይ ከሀገር ይልቅ የራስን ጥቅም ፤ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ የራስን ስሜት፤ ከሀገር ሕልውና የፓርቲ ሕልውና ማስቀደም ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ላልተገባ እሰጥ እገባና ግጭት አልፎ ተርፎም በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድትዘልቅ አድርጓታል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ጉድለት የመነጋገር ባህል አለመለመዱ ነው፡፡ ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተን ልማድ ነው፡፡ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰረት ሌሎችን አጥፍቶና አንቋሾ፤ ጥላቻ ዘርቶና አኮስምኖ የራሱን ስብዕና ለመገንባት ሲሞክር ማየት የተለመደ ነው፡፡

በጋራ ሰርቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ከማላቀቅ ይልቅ በየጊዜው ጥላቻና ግጭትን በመፈብረክ ሀገርን የኋሊት እንድትጓዝ ማድረግ አንዱ ፖለቲካ ታሪካችን ነው፡፡

ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባኅልም ስለሌለን ችግሮች ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው እየተሻገሩ የጥላቻ፣ የቂም በቀልና የሴረኝነት መነሻ ይሆናሉ፡፡ ቀላል የሚባሉ ችግሮች ሳይፈቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወሳሰቡ ስለሚሄዱ መፍትሄ ለመስጠት እንኳን አዳጋች እስከመሆን ይደርሳሉ፡፡

ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሀገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ሦስት ዓመታት እንደ ሀገር ችግሮቻችንን በምክክር ለመፍታት በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በአብዛኞቹ ክልሎች የተሳኩ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡

እንደ ሀገር ምክክር ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ መሆን ሲገባው አሁንም ጥያቄዎችን በመሳሪያ ኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸው ሁኔታውን ግራ አጋቢ ያደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ከአዲስ ዘመን ወቅታዊ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባኅላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል። ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፤ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግ የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ከሦስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት እጅግ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ኮሚሽኑ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የሀገራዊ ምክክር በተለያዩ ሀገራት ሲከናወን ሊያሳካ የሚፈልጋቸው የተለያዩ ዓላማዎች እንደሚኖሩት ዕሙን ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክርን ማድረግ በራሱ ግብ ሳይሆን ችግሮችን ለመፍታት እና የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት የሚያገለግል መሳሪያ ነው፡፡ ሀገራት ይህንን ሲያደርጉ የሀገራዊ ምክክር ዓላማ እና በሂደቱ ሊገኙ የታሰቡ ውጤቶችን በተለያዩ ዓውዶች ውስጥ በግልፅ ደንግገው ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም የሀገራዊ ምክክሩን ዓላማ በሦስት የተለያዩ ዓውዶች ከፍሎ እነሱንም ለማሳካት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ውጤት መር ዓላማዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ሲጠናቀቅ የሚያስገኛቸው ተጨባጭ ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህም በተለያዩ ቡድኖች መካከል ያሉ አለመግባባቶችን መፍታት እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ምክረ-ሀሳብ ማቅረብን ይጨምራሉ፡፡ በዚህ መሰረት ሀገራዊ ምክክር ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ውጤቶችን እንደሚያስገኝ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

የፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያዎች፣ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎች፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች፣ ቀደም ሲል ለተፈፀሙ በደሎች መፍትሔ ማበጀት እና የመሳሰሉት በሀገራዊ ምክክሩ ሊገኙ የሚችሉ ቀጥተኛ የሆኑ ውጤቶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካና የዲሞክራሲ ባኅልን ማሳደግ፣ የሀገራዊ ምክክር ዕውቀቶችን እና ልምዶችን መቅሰም፣ የንግግር እና የምክክር ባህል እንዲጎለብት ማድረግ እና የመሳሰሉት የሀገራዊ ምክክሩ ቀጥተኛ ያልሆኑ ውጤቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የሀገራዊ ምክክር ቀላል የማይባል መዋዕለ-ነዋይ (ገንዘብ፣ ጉልበት፣ ጊዜ እና ቁሳቁስ) ፈሶበት የሚከናወን ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ በግለሰቦች፣ በቡድኖች እና በተለያዩ የሀሳብ መሪዎች መካከል በመተማመንን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እና መንፈስ እንዲገነቡ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የምክክር ሂደቱ አንደኛው ወገን ስለሌላኛው ወገን በጥልቀት በማወቅና በመረዳት ሁሉም ወገኖች ለጋራ ችግሮቻቸው የጋራ መፍትሔን ለመፈለግ ምቹ አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚከናወነው ሀገራት ግጭቶችን ከማስተናገዳቸው በፊት፣ በግጭቶች ውስጥ ሆነው እና ግጭቶች በተከሰቱ ማግስት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ በግጭት መሀል ሀገራዊ ምክክር ሲካሄድ ግጭቶቹን ለማርገብ እና የተለያዩ ቡድኖች ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ ሂደቱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የፖሊቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በምክክር የማመን የፖለቲካ ባህል ለመገንባትና ለዲሞክራሲ ስርዓት ማደግ መደላድል በመፍጠር የዲሞክራሲ ልምምድን እንዲያዳብሩ ያረዳቸዋል፡፡

ይህንንም መሰረት በማድረግ ኮሚሽኑ በሰላማዊ መንገድ ትግል ለሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን የትጥቅ ትግል ውስጥ ለገቡትም ጭምር ጥሪ አድርጓል፡፡ ደህንነታቸው ተጠብቆ ምንም አይነት ስጋትና ጥርጣሬ ሳይኖራቸው መጥተው ተነጋግረው እንዲሄዱ መልእክት ማስተላፋቸውን ያስረዳሉ። ከዚህ አንጻር ከመንግሥትም ጋር ተነጋገረን ፈቃደኝነቱን ገልጾልን በማስ ሚዲያ አሳውቀናል። ምንም አይነት የደህንነት ሥጋት ሳይኖርባቸው መጥተው መሳተፍ እንደሚችሉ፤ ስጋትም ካደረባቸው ይሄንን የሚያመቻቹ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስላሉ በእነርሱ አማካኝነት ተሳትፈው አለን የሚሉትን ጥያቄ በምክክር እንድንፈታው ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በበኩላቸው አለመግባባቶችን በሀገራዊ ምክክር በመፍታት ወደ ተሻለ ምዕራፍ መጓዝ አለብን ማለት እንግዲህ ሂደቱ ሁሉን ያማከለ፣ ግልፅና ውጤታማ መሆን አለበት ማለት ሲሆን ሁሉም አካላት የበኩላቸውን የሚሳተፉበትም ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው።

በሌላ በኩል አሁንም ይሁን ከአሁን በፊት በነበሩት ጊዜያት እንዲሁም ወደፊት ያላግባቡንን የማያግባቡንን ነገሮች እልባት እየሰጠን መስመር እያስያዝን ሄድን ማለት ነው። እንዲሁም እነዚህን አለመግባባቶቻችንን በውይይት ከፈታን በኋላ ወደቀጣይ ምዕራፍም ለመሸጋገር ድልድይ እናገኛለን፤ ለምሳሌ ሕዝበ ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፍን መፍጠርም ሊያስፈልግ ይችላል፤ ተቋማት እንዲዋቀሩም የሚጠይቁ ሥራዎች ይኖራሉ።

ዋናው ግን ምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመበትንና ያስፈለገበትን ነገር መጀመሪያ ማጠናቀቅ ቀጥሎም ቀጣይ ሥራዎችን በመስራት አገራችን ተጨማሪ ፈተና እንዳይኖርባት ማድረግ ስለሚጠቅም ሂደቱን ችግር ፈቺ አድርጎ መመልከቱ ይጠቅማል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንደሚሉትም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ዓላማ አገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ዘላቂ ልማት እንዲሁም ዘላቂ እድገት እንድታገኝ ማስቻል ነው። መሰረታዊ የሆኑ ችግሮቻችን በሰላማዊ መንገድ ተወያይተን የኢትዮጵያን ከፍታ ማየት ትልቁ ዓላማችንም ሕልማችንም ነው፡፡

ስለዚህም እያንዳንዷ የሰላም ጠብታ ለኮሚሽኑ ሥራ በጣም ጠቃሚ ናት፡፡ እኛ ሕዝብን በማወያየት ረገድ ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልል አዳርሰናል። በመጨረሻም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተረባርቦ በሚያደርገው ጥረት ለዘመናት የነበሩትን ጦርነቶች እንዲገቱ ማድረግ ነው፤ በዚህም ወጣቶቻችን ተስፋ የሚያደርጉበት ሁኔታ በመፍጠር ወደልማትና ሰላማዊ ወደሆነው ኑሮ ሕዝቡን መመለስ ዋናው ዓላማችን ነው፡፡

ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣትን ባህል ማድረግ፣ የምንጥረው በኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ሁሉም አሸናፊ መሆን እንችላለን ወደሚለው ከፍታ ለማድረስ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ አካሄድ በተደረገው ስምምነት ሁላችንም ተጠቃሚዎች ነን፡፡ ምክንያቱም ጦርነት እንቅፋት ነው፡፡

አቶ ሰማነህ ታምራት የተባሉ ምሁር በዚሁ ገዳይ ላይ እንደተናገሩት ሀገር ከምክክርና ውይይት ውጪ የሚታደጋት ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ምክንያቱም በመቀራረብና በመወያየት ችግሮች በሙሉ መፍትሄ ያገኛሉ፡፡ ምክንያታዊ ሀሳቦች ከምንጩ ይፈልቃሉ። ወደ አንድ አስተሳሰብ መምጣትም ይቻላል፡፡ አንድ መሆን ባለመቻላችን የትናንቱን፣ የአባቶቻችንን ብርቅዬ ገድሎች መፈጸም አልቻልንም፡፡ እናም ይህ ኮሚሽን ይህንን የሚፈጥር ሥራ ይሰራል ብዬ አስባለሁ፡፡

በኮሚሽኑ በኩል በሚደረግ ምክክር አንድነት ይጠነክራል፤ አዳዲስ ሀሳቦች ይመነጫሉ፤ ዝምድና ይዳብራል፤ አለመረዳቶች በእውቀት ይቀየራሉ፡፡ ቁስሎችና ቅሬታዎች ገሀድ ስለሚወጡ ይታከማሉ። ይህ ማለት ደግሞ ጫና ፈጣሪዎች ጥጋቸውን ይይዛሉ፡፡ አጣልተው ገንዘብ የሚሰበስቡም ቦታቸውን ይቀይራሉ። ምክንያቱም አስተሳሰቦች ሁሉ ልማትና እድገት ላይ ይሆናሉ፡፡ ሀገርም ያሰበችው የብልጽግና ደረጃ ላይ ትደርሳለች፡፡ በሰላም የሚፈቱ ነገሮች ስለሚበራከቱ መገፋፋትና ግጭቶች ይቆማሉ። እድገት መሪ ይሆናል ብዬ አስባለሁ ሲሉ ያላቸውን እምነት ያስረዳሉ፡፡

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደሚናገሩት የኮሚሽኑ ዋና ተግባር በየአካባቢው ለግጭት የዳረጉን ጉዳዮችን እጅግ መሠረታዊ የሚባሉትን ወደ ሀገራዊ ምክክር አጀንዳነት ማምጣት ነው። ኮሚሽኑ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን እየሠራ ቢሆንም መንግሥትም ሆነ በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች በተቻለ መጠን ወደ ድርድርና መነጋገር መጥተው ወደ ግጭት ያስገቧቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይትና ምክክር በማድረግ ችግሮቻቸውን ሊፈቱ ይገባል ሲሉ ጥሪ ያቀርባሉ ፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ምሁራኑ እንዳብራሩት የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ደግሞ ለዚህ ምቹ መደላድልን የሚፈጥር ነው፡፡ ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል። ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፤ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው፡፡

ስለዚህም በዚህ ታሪካዊ የምክክር መድረክ መሳተፍ አዲስ ታሪክ የመጻፍ ያህል ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር ነፍጥ የሚያነሱ ቡድኖች ከግል ስሜትና ፍላጎት በመውጣት ኢትዮጵያን በምክክርና በውይይት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ዳር ተመልካች ሆኖ መተቸትና ማጥላላት ሀገርን ወደ አዘቅት ከመክተት በስተቀር እንደሀገር የሚፈይደው ቁም ነገር አይኖርምና ችግሮቻችንን በምክክር የመፍታት ባህል ልናዳብር ይገባል፡፡

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You