«በኢትዮጵያ የዘመነ እና የዳበረ የንግድ፣ የኮንፈረንስና የኤግዚቢሽን ማዕከል ዕውን ሆኗል» -አቶ ሲሳይ ገመቹ

-አቶ ሲሳይ ገመቹ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል አክስዮን ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የዛሬው ወቅታዊ ጉዳይ እንግዳችን በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ / ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ገመቹ ናቸው፡፡ በቆይታችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /የስብሰባ፣ የኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን ዘርፍን ለማጠናከር ለምናደርገው ጥረት አንድ ተጨማሪ አቅም ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃን እንደጠበቀ ተቋምነቱ የንግድ ቱሪዝምን በማሳደግና ዓለም አቀፍ ኹነቶችን በመሳብ ሀገራችን የስብሰባዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታልሲሉ የመሰከሩለትን የአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዝርዝር ሁኔታን እንመለከታለን። መልካም ቆይታ!

አዲስ ዘመን፡የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል አክስዮን ማህበር ራዕይ እና ተልዕኮ ምንድን ነው ?

አቶ ሲሳይ፡ራዕዩ መዲናችን አዲስ አበባ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች መስተንግዶ በአፍሪካ ቀዳሚ ሆና ማየት የሚል ነው፡፡ ተልዕኮው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ በመገንባት ለዓለም አቀፍና አህጉራዊ ኩነት አዘጋጆች ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኩነት መስተንግዶ በማቅረብ በማዕከሉ ግንባታ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ኢንቨስተሮችን የላቀ ትርፍ ተቋዳሽ ማድረግ ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው ደረጃቸውን የጠበቁ ስብሰባዎች፣ ኮንቬንሽኖችና ኤግዚቢሽኖች የሚስተናገዱበት እንዲሁም ተዛማጅ የሆኑ የንግዱ ኅብረተሰብ የንግድ መረጃ ልውውጥ፤ ድርድርና ትውውቅ የሚካሄድበት ዘላቂ የግንኙነት ሰንሰለት መድረክ በመፍጠር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉ ሲመሰረት እንደ ግብ ያስቀመጣቸውን ጉዳዮች ቢገልጹልን?

አቶ ሲሳይ፡– የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን በማጠናከር የግሉን ንግድ ሴክተር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ልማት ተሣታፊነት ለመጨመር፤

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማጎልበትና ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እና የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማጎልበት፣ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ለኤግዚቢሽን፣ ለዘመናዊ ሬስቶራንት፣ ለስፖርት፣ ለጤና፣ ለመዝናኛ እና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎችን መገንባት፣ መጠቀም እና ማከራየት፤ በሚገነባው ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ማዕከል አማካኝነት የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን አዘጋጆችን፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎችን እና የልዩ ልዩ ትርዒቶች ታዳሚዎችን ማስተናገድ የሚሉ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡የፕሮጀክቱ ሃሳብ ጠንሳሽ የነበረው የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነበርበአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ለመሆን የበቃው እንዴት ነው?

አቶ ሲሳይ፡የማዕከሉ ምሥረታ ሃሳብ አፍላቂ የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ በ1994 ዓ.ም አካባቢ በራሱ ሀብት የንግድ ማዕከል ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምሮ በ1996 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 110ሺ126 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ ተረከበ፡፡ ሆኖም በፕሮጀክትነት በምክር ቤቱ የተዋቀረው ተቋም በተፈለገውና በታቀደው ልክ ሊንቀሳቀስ ባለመቻሉ መፍትሔ የሚያመላክት ሃሳብ እንዲሰበሰብ ተደርጎ ከከተማው አስተዳደር ጋር በትብብር እንዲለማ ለማድረግ አቋም ተወሰደ፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ በከተማ አስተዳደሩና በምክር ቤቱ መካከል የትብብር የመግባቢያ ሠነድ ተፈርሟል፡፡

ይህም ሆኖ የማዕከሉን ግንባታ ለማስጀመር አልተቻለም ነበር፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትብብር ከመገንባት ይልቅ አክስዮን ማኅበር አቋቁሞ በባለቤትነት ሥራውን ማስቀጠል ይሻላል የሚል ውሳኔ ላይ ደርሶ አዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን አ.ማ በሚል መጠሪያ በ2005 ዓ.ም የአክስዮን ማኅበሩ ተመሠረተ። በዚህ መነሻ ማኅበሩ የአዲስ አበባ የንግድ እና የዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤት አካል መሆኑ ቀርቶ ራሱን የቻለ ተቋም ለመሆን በቃ፡፡

አዲስ ዘመን፡የአክስዮን ሽያጭ የተጀመረው መቼ ነው፤ ዋነኛ ባለድርሻ የሆኑት የመንግሥት ተቋማትስ የትኞቹ ናቸው?

አቶ ሲሳይ፡የማዕከሉ አክስዮን ሽያጭ የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ነው፡፡ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ባለፉት ሦስት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልማት ተቋማቶቹ በኩል ከፍተኛ የአክስዮን ግዥ በመፈፀም ዋነኛ ባለድርሻ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት፣ የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደርና ወደ አንድ ሺህ የሚሆኑ የግሉ ሴክተር አካላት ባለአክስዮን ናቸው፡፡ ለተከፈለው ካፒታል ከ96 በመቶ በላይ በመንግሥት ቀሪው በግሉ ሴክተር የተያዘ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡በመጀመሪያው ምእራፍ የማዕከሉ ግንባታ ምን ምን ተካቷል?

አቶ ሲሳይ፡በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን ግዙፍ ማዕከል ለመገንባት የሚያስፈልገውን የገንዘብ ሀብት በአንድ ጊዜ አሰባስቦ የግንባታውን ሒደት ከጅምሩ እስከ ማጠናቀቂያው ዕውን ለማድረግ እንደማይቻል በመታመኑ በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ እንዲከናወን አቋም ተወስዶ ግንቦት 2009 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ። ጥቅምት 2010 ዓ.ም የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ተጀመረ፡፡ በዚህ ምዕራፍ እንዲጠናቀቁ በዕቅድ የተያዙት ግንባታዎች በሙሉ ተከናውነዋል፡፡ በዚህም በጠቅላላው እስከ 10,000 ተሳታፊዎችን የሚያስተናግዱ ሁለት ትላልቅ አዳራሾች እና ስምንት መካከለኛና አነስተኛ የስብሰባ አዳራሾች፣ ትልቅ ጋለሪ፣ 15,000 ካ.ሜ ስፋት ያለው የውጭ ኩነቶች ቦታ፣ ለቢሮዎች፣ ባንኮች፣ ሱቆች፣ ካፍቴሪያዎች ፣ ለሬስቶራንቶች ዝግጁ የሆኑ ቦታዎች፣ ከማዕከሉ ጋር ኩታ ገጠም የሆኑ የሪል እስቴት ሕንፃዎች ተሻሽለው አንድ ሺህ አልጋ ያለው ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል የሚሆኑ፣ ደረጃውን የጠበቀ ሰፊና ለዓይን የሚማርክ የተዋበ አረንጓዴ ቅጥር ግቢ፣ በሕንጻዎች ውስጥና ውጭ ደረጃቸውን ጠብቀው የተገነቡ 2000 የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይዞታ ስፋት 40 ሄክታር ደርሷል፡፡

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉ በአመራር ረገድ ያለው መዋቅር ምን ይመስላል?

አቶ ሲሳይ፡ኩባንያው የተመሠረተው የመንግሥት የንግድ ሕግን ተከትሎና በተዘጋጀ የመግባቢያ ሠነድ አማካይነት ነው፡፡ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ፣ 11 አባላት ያሉት የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ፣ የውጭ ኦዲተር እና የየዕለቱን እንቅስቃሴ የሚመራ ዋና ሥራ አስኪያጅና ማኔጅመንቱ ዋና ዋናዎቹ የአመራር አካላት ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡ሥራውን ማካሄድ የሚያስችሉት ቅድመ ዝግጅቶችስ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀዋል?

አቶ ሲሳይ፡ማዕከሉን የኦፕሬሽን ሥራ ማስጀመር የሚያስችል መዋቅር ፀድቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለዓውደ ርዕይ እና ኮንቬንሽን የሚሆኑ የመገልገያ ቁሳቁሶች ብዛትና ጥራት ተለይቶ ግዥው ተከናውኗል፡፡ ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል መንግሥታዊ የሥራ ፈቃድ ምዝገባ እና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ተከናውነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡በኤሌክትሪክ ኃይል እና ውሃ አቅርቦት እንዲሁም በመንገድ መሠረተ ልማት በኮንቬንሽን ማዕከሉ የሚካሄዱ ኩነቶች እንዳይስተጓጎሉ ምን ያህል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተሠርቷል ?

አቶ ሲሳይ፡– ማዕከሉ በሁለት አቅጣጫ ውሃና ኤሌክትሪክ የሚያገኝ ሲሆን ፤ የራሱ ተጠባባቂ ጄነሬተሮች ስላሉት የትኛውም ሁነት ያለምንም መብራት መቆራረጥ መካሄድ ይችላል፡፡ ከመሰብሰቢያ አዳራሾቹ በተጨማሪ ከአካባቢው ጋር የተሳሰሩት 50 ድርጅቶችን የሚያስተናግዱት የንግድ ቦታዎችም ተመሳሳይ አቅርቦት የሚያገኙ ይሆናል፡፡ በመንገድ ረገድ ማዕከሉ በመገናኛ ብቻ ሳይሆን በጎሮ በኩል በተሳለጠ ሁኔታ ከቦሌ አየር መንገድ ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ እየተሠራ ነው ያለው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ይህን ታሳቢ አድርጎ በመልማት ላይ ይገኛል፡፡ በኮንቬንሽን ማዕከሉ ጀርባ የሚታየው አዲስ መንገድ ከግንባታው ጋር እንዲናበብ ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡

ማዕከሉ ስምንት ዋና ዋና እና ሁለት መጋቢ በሮችን ጨምሮ አስር መግቢያዎች አሉት፡፡

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉ የኮንፍረንስ ቱሪዝምን በማሳለጥ ረገድ ምን አይነት ሚና ይኖረዋል?

አቶ ሲሳይ፡የማዕከሉ ሀገራዊ ፋይዳ በኢትዮጵያ የዘመነ እና የዳበረ የንግድ፣ የኮንፈረንስና የኤግዚቢሽን ማዕከል ዕውን ማድረግ ነው፡፡ ይህ ተሳክቷል፡፡ ከውጭ ሀገራት በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች እና ኮንፈረንሶች ለመሳተፍ በድርጅትና በግለሰብ ደረጃ የሚመጡ እንግዶች እንደሚኖሩ ታሳቢ አድርገን የንግድ ፍቃዳችንን እንኳን በኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ነው ያወጣነው፡፡ ስለዚህ ትኩረታችን በኮንፈረንስ ቱሪዝም ላይ ነው የሚሆነው፡፡ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ወደ ሌላ ከፍታ የሚወስድ ግዙፍ ተቋም ነው የገነባነው፡፡ ሁለት ሺህ የፓርኪንግ ቦታ አለው እያልን ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የፓርኪንግ አገልግሎት የሚሰጥ ሆቴል መዲናችን ውስጥ አይገኝም፡፡ ማዕከሉ በመሃል ከተማ 40 ሄክታር ላይ አርፏል ስንል ምን ያህል ግዙፍ ማዕከል እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡ እኛ በሁሉም ነገር ትልቅ ነን፡፡ እኛ የተፈላላጊዎች መገናኛ መድረክ ነን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በፈጠርነው መድረክ መጠቀም መቻል አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉ ለምን ያህል ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል?

አቶ ሲሳይ፡በግንባታ ሂደቱ በሺህ የሚቆጠር የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ለንግድ ድርጅቶች በተዘጋጁት 50 የሚከራዩ እና የተከራዩ ቦታዎች ውስጥ እየገቡ የሚገኙት እንደ ባንክ ያሉ እና ሌሎች ተቋማትም የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል ይኖራል፡፡

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉ የያዛቸው የተለያዩ አዳራሾች ውስጣዊ አደረጃጀት ምን ይመስላል?

አቶ ሲሳይ፡በድምሩ በአንድ ጊዜ እስከ 10 ሺህ ሰዎችን ይይዛሉ ያልናቸው ትላልቅ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ አዳራሾች ሁለገብ ናቸው። በውስጣቸው ስብሰባዎችን፣ ኤግዚቢሽኖችንና ኮንሰርቶችን ማስተናገድ ይችላሉ፡፡ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የድምጽ ሥርዓትም ተገጥሞላቸዋል፡፡ ዋነኛው ትልቅ አዳራሽ የቪአይፒ መቀመጫዎች፣ የጋዜጠኞች ቦታ፣ ተዘዋዋሪ መድረኮች እና ግዙፍ የሆኑ ተሰቃይ ተንቀሳቃሽ ስክሪን የተሟላለት በመሆኑ ለትላልቅ ስብሰባዎች ብቻ ሳይሆን ኮንሰርቶችንም ለማካሄድ ምቹ ሆኖ የተሰናዳ ነው።

ስብሰባዎችና የተለያዩ ኩነቶች ሲካሄዱ የሚፈጠር የጤና ዕክል የሚኖር ከሆነም የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ርዳታ መስጫ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል። አዳራሾቹ ከምረቃ ሥነሥርዓቱ ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ረቂቅነት ባላቸው ግዙፍ ስክሪኖች በመታገዝ ቴክኖሎጂ ላይ መሠረት ያደረገ ኤግዚቢሽን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በቀጣይ በኮን ቬንሽን ማእከሉ የዓለም አቀፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች አስቀድሞ ወረፋ የተያዘላቸው መሰል ኩነቶች አሉ?

አቶ ሲሳይ፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በገለጹት መሠረት የዓለም አቀፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኤግዚቢሽን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ዝግጅቶች በኮንቬንሽን ማዕከሉ ለማካሄድ ስምምነቶች እየፈጸምን ነው፡፡ እስካሁንም በቀጣዮቹ ሦስትና አራት ወራት የተለያዩ ኩነቶችን ለማካሄድ 10 ተቋማት ተመዝግበው ሰልፍ ገብተዋል፡፡ ማዕከሉ በፍጹም ገበያ ያጣል ተብሎ የሚገመት አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡መንግሥት የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የግንባታ አፈጻጸም ሂደቱን ለመከታተል ያደረገውን ጥረት እንዴት ይገልጹታል፡፡

አቶ ሲሳይ፡ለረጅም ጊዜ ሲጓተት የቆየው የፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት ባለፉት ሦስት ዓመታት ተቀላጥፎ ለአገልግሎት መብቃት የቻለው መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ባስቀመጠው አቅጣጫ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 90 በመቶ በላይ የአክስዮን ድርሻዎችን ከገዛ በኋላ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ያላሰለሰ ክትትል በማድረግ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ቁልፍ የአመራር ሚና ተጫውቷል። የሚደረግለት ክትትልና ድጋፍም ከፍተኛ ነበር። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በወር አንድ ጊዜ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በየሳምንቱ እየመጡ የግንባታ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ እየተመለከቱ አመራር ይሰጡ ነበር፡፡ የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትርና የከተማችን ከንቲባ ለማዕከሉ እውን መሆን የሰጡት ከፍተኛ ትኩረት በግንባታ ሂደቱ የሚሳተፉ አካላት በሙሉ ሥራቸውን በከፍተኛ ትጋት እንዲያከናውኑ ሞራል ሆኗቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉን ስንጎበኝ የተለያዩ ድርጅቶች ለፈለጉት ያህል ጊዜ ተከራይተው ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉበት ምቹ ክፍል መዘጋጀቱን ተመል ክተናል፡፡ ስለ ክፍሉ ትንሽ ማብራሪያ ይሰጡናል?

አቶ ሲሳይ፡– አንድ ድርጅት በርከት ያሉ የሰው ኃይሎችን ይዞ በመግባት ያለምንም ውጣ ውረድ በተሟላ የሥራ ቦታ በተቀላጠፈ መንገድ ሥራውን ማከናወን የሚችልበት ቦታ ለመፍጠር አቅደን ነው የሠራነው፡፡ በዚህም አንዳች ሥራ ኖሮት የሥራ ቦታ ተከራይቶ መሥራት የሚፈልግ ድርጅት ካለ ሊገለገልበት የሚችል ሙሉ ለሙሉ የቢሮ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችልና በርካታ ሠራተኞችን የሚያስተናግድ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት የተደራጀ ክፍል ማዘጋጀት ችለናል፡፡ የሚከራዩ ድርጅቶች ቁልፉን ተረክበው ሥራቸውን እስከሚያጠናቅቁ ድረስ የሚያስተዳድሩት ክፍል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉ ያካተታቸው ለውጭ ኤግዚቢሽን አገልግሎት የሚውሉ ቦታዎች ምን አይነት አገልግሎቶችን መስጠት ይችላሉ?

አቶ ሲሳይ፡15 ሺህ ካሬ ሜትር የሚሆን ቦታ ለውጭ ኤግዚቢሽን አገልግሎት የሚውሉ ቦታዎችን አካትቷል፡፡ የማዕከሉ የምርቃት ሥነሥርዓት በዕለቱ በተካሄዱ ኤግዚቢሽኖች ጭምር የታጀበ ነው፡፡ በግቢው በሚገኘው የከባድ ማሽነሪዎች ኤግዚቢሽን ማካሄጃ ቦታ ላይ የከባድ መኪኖች ኤግዚቢሽን ቀርቧል፡፡የፋብሪካ ውጤቶች የቀረቡበት ኤግዚቢሽን ተካሂዷል፡፡ ምድረ ግቢው አሁን ባለበት ደረጃ ሳቢና ምቹ መሆን የቻለው ሁሉ ነገር ታስቦ ስለተሠራ ነው። የኮንቬንሽን ማዕከሉ ያረፈበትን ቦታ አቋርጦ የሚሄድ ወንዝ ነበረ፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ አካባቢው መጥቶ የነበረ ሰው እንደሚረዳው አካባቢው በጣም ቆሻሻ ነበር፡፡ አሁን ግን እንደምትመለከቱት አረንጓዴ ስፍራ ሆኗል። ወንዙም ከስር እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉ ያቀፈው ግዙፍ ጋላሪ ውስጣዊ አደረጃጀቱ ምን መልክ አለው?

አቶ ሲሳይ፡አንድ ወጥ የሆነ የስዕል ጋላሪዎች የሚቀርቡበት ግዙፍ አዳራሽ አለ፡፡ በአንዱ የግድግዳ ክፍል ላይ ብቻ የሚገኙ በቁጥር የተሰየሙ ስድስት የመግቢያ በሮች አሉት፡፡ ሁሉም ክፍሎች በሚፈለገው መጠን መስፋትና መጥበብ እንዲችሉ የሚያደርጋቸው ተንቀሳቃሽ ግድግዳ ይኖራቸዋል፡፡ እያንዳንዳቸው አንድ ሜትር ከሃያ ሴ.ሜ ስፋት ያላቸው በአዳራሽ ቁመት ልክ የተመጠኑ ተንቀሳቃሽ ግድግዳዎች በቻይና ሀገር ተመርተው በአሁኑ ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ በመጓጓዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ ተንቀሳቃሽ ግድግዳዎቹ ሲገጠሙ ግዙፉ የስዕል ጋላሪ እንደተፈለገው እስከ ስምንት ወደ ሚደርሱ የየራሳቸው በር ያላቸው አነስተኛ ክፍሎች መቀየር ይችላል፡፡ ግድግዳዎቹ በማያስፈልጉበት ጊዜ ተጣጥፈው ሲቆሙ ውበት ያላቸው ናቸው፡፡ ምንም አይነት ድምጽ ከአንዱ ክፍል ወደሌላው እንዳይተላለፍ የሚያደርግ ቴክኖሎጂም ተገጥሞላቸዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ክፍል ሁለት ሜትር በአራት ሜትር የሆነ ስክሪን እና የድምጽ ሥርዓት ታዟል፡፡ ሙሉ አዳራሹን መጠቀም ሲያስፈልግ ደግሞ የመጀመሪያውና የመጨረሻው በሮች ብቻ ተከፍተው ሌሎቹ ዝግ እንዲሆኑ ተደርጎ ተመልካቾች በአንዱ በር በመግባት በሌላኛው በር እንዲወጡ ይደረጋል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሥነጥበብ ሥራዎች ማሳያ ጋለሪውን በጣም ወደውታል፡፡

አዲስ ዘመን፡የኮንቬንሽን ማዕከሉ ያቀፋቸው የፓርኪንግ ቦታዎች እና ሆቴሎች ግዝፈት በሚያስተናግዱት መኪና እና በሚይዙት የመኝታ ክፍል ብዛት በቁጥር ሲገለጽ ሰምተናል፡፡ ዝርዝር መረጃዎችን ሊያካፍሉን ይችላሉ?

አቶ ሲሳይ፡– ዲዛይናቸው ተከልሶ ወደ ሆቴልነት እየተቀየሩ ያሉ ከኖህ ሪልስቴት እና ካንትሪ ትሬዲንግ የተገዙ ስድስት ሕንጻዎች አሉ። ውስጣዊ አደረጃጀታቸውን እና ዲዛይናቸውን ወደ ሆቴሎች የመቀየር ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ሥራቸው ሲጠናቀቅ 1000 አልጋዎችን ይይዛሉ። የሚተዳደሩትም በማዕከሉ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ስም ባላቸው የሆቴል አስተዳደሮች ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በኮንቬንሽን ማዕከሉ ለሬስቶራንቶች የተዘጋጁ ሰፋፊ ክፍሎች ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት ኩሪፍቱ እና አዲስ ካተሪንግ ሥራ ጀምረዋል፡፡ አሁን መጠነኛ አገልግሎት እየሰጡ ነው የሚገኙት። በሂደት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ ማዕከሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሬስቶራንቶችን ያቀፈ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ፓርኪንግን በተመለከተ በሆቴሎቹ ምድር ቤት በርካታ መኪኖችን የሚያስተናግድ ፓርኪንግ አለ። በግዙፉ የማዕከሉ ሕንጻ ስር፣ በግቢው ውስጥ ባሉ ሰፊ ቦታዎች እንዲሁም ከግቢው ውጪ መንገዱን ተሻግሮ በሚገኘው የፓርኪንግ ስፍራ ላይ ያለው የመኪና ማቆሚያ ተደምሮ ነው ማዕከሉ የተጠቀሰውን ያህል ያለው መኪና ማስተናገድ የሚችል ፓርኪንግ አለው እየተባለ ያለው፡፡

አዲስ ዘመን፡የኮንቬንሽን ማዕከሉን የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች እና የኅብረ ተሰብ ክፍሎች እየጎበኙት ነውምን አይነት አስተያየቶች እያገኛችሁ ነው?

አቶ ሲሳይ፡በሀገራችን እንዲህ አይነት ማዕከል ተገንብቶ በማየታችን እጅግ በጣም ደስተኞች ነን ነው የሚሉን፡፡ እናንተን እንዳስጎበኘኋችሁ ሁሉ በተለይ ከተለያዩ ተቋማት የሚመጡትን አብዛኞቹን እንግዶች እኔ ራሴ ነኝ እየዞርኩ የማስጎበኛቸው። ማዕከላችንን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶች ከሚያነሱልን ጥያቄዎች አንዱ፣ ማዕከሉ በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም ስንተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው የሚል ነው፡፡ በሀገራችን የመጀመሪያው ነው። በምሥራቅ አፍሪካም ቀዳሚ ነው፡፡ በአፍሪካም በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ከሚጠቀሱት መካከል ይሆናል የሚል ግምት አለን። አሁን ላይ ጥናቶች ስላላደረግን በእርግጠኝነት የምንሰጠው መረጃ የለንም፡፡ ትክክለኛውን መረጃ ወደፊት የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡በቀጣይ ምዕራፍ የማዕከሉ ግንባታ ምን ይከናወናል?

አቶ ሲሳይ፡– አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በቀጣይ ምዕራፍ ግንባታዎቹ በቅጥር ግቢው ውስጥ ያረፈውን ግዙፍ ሕንጻ የሚያህል ተጨማሪ ግንባታ የሚያከናውን ይሆናል፡፡ አሁን በግቢው ውስጥ የሚታዩ ሰፋፊ ባዶ ቦታዎች ወደፊት የማዕከሉ ማስፋፊያ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ቀጣይ የግንባታ ምዕራፎቹ በሚጠናቀቁበት ጊዜ ከአፍሪካ አንደኛ ነው የሚሆነው።

አዲስ ዘመን፡ማዕከሉን ስላስጎበኙን እና ጊዜ ወስደው ለጥያቄዎቻችን የተብራራ መልስ ስለሰጡ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፡፡

አቶ ሲሳይ፡እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You