
‹‹ልጆች የፈጣሪ ስጦታዎች ናቸው›› ፤ የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በብዙዎች ልብ የሚመላለስ ነው:: ማናችንም ብንሆን ከእገሌ መወለድ አለብን ብለን ፈልገንና ፈቅደን ከፈለግነው ሰው፤ በምንፈልገው ሁኔታ አልተወለድንም:: በወላጆቻችን አማካኝነት መምጣታችን ግን እውነት ነው:: ልጆች ምንም ይሁኑ ምን ለወላጆች በአደራ የተሰጡ የፈጣሪ ስጦታዎች መሆናቸው የሚካድ አይደለም::
እናቶች በተፈጥሯቸው ለልጆቻቸው ስስ ልብ ያላቸው እንደመሆኑ በችግር፣ በሕመምና በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ቢሆኑም እንኳ ዓይናቸው ከልጆቻቸው ላይ አይነቀልም:: ድሮውንም በእትብት የተሳሰረው የእናትና የልጅ ቁርኝት እትብቱ ከተበጠሰ በኋላም ቢሆን በፍቅር ጸንቶ የሚኖር መሆኑን ሁሉም ከራሱ ተሞክሮ ሊረዳው የሚችል ነው::
‹‹ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች›› እንዲሉ እናት ለልጇ ስትል የማትከፍለው መስዋዕትነት የለም:: እርሷ እየራባት ለልጇ ከማጉረስ ጀምሮ የራሷን ሕመምና ስቃይ ትታ ልጇን የምታዳምጥ፤ ስለልጆቿ ስትል የማይቻለውን የምትችል፤ የማይከፈለውን ዋጋ የምትከፍልም ነች::
በየጓዳው ስለልጆቻቸው ሲሉ ከሰው አቅምና ከአዕምሮ በላይ የሆኑ ችግሮችን እየተጋፈጡ የሚኖሩ እናቶች በርካቶች ናቸው:: ብቻቸውን የወለዷቸውና ወደዚህ ምድር ያመጧቸው ይመስል ያለ ልጆቻቸው አባት እገዛ የልጆቻቸውን መከራ ተሸክመው የሚኖሩትን እናቶች ቤት ይቁጠራቸው::
ወይዘሮ እየሩስ ተስፋዬ ነዋሪነቷ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ነው:: ትውልድና እድገቷም እዚያው ነው:: ከልጆቿ አባት አቶ ፀሐዬ ጋር በፍቅር ለሶስት ዓመት ያህል አብረው ከቆዩ በኋላ ነበር በ2008 ዓ.ም ትዳር የመሠረቱት:: የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአይቲ የትምህርት ዘርፍ በሥራ ላይ የነበረችው ወይዘሮ እየሩስ የመጀመሪያ ልጇን ስትወልድ ገና የ22 ዓመት ወጣት ነበረች:: በትዳር ውስጥ ልጅ አንዱ በረከት ሲሆን ለእናት ደግሞ ትልቅ ስጦታ እና ሕይወትን በተለየ መንገድ እንድትመለከት የሚያደርግ ነው:: እየሩስም ትዳር ከመሠረተች በኋላ ይህንን ክብር ለማየት በቅታለች::
እየሩስ አሁን ላይ የዘጠኝ ዓመት እና የአራት ዓመት ከስድስት ወር ወንድ እና ሴት ልጆች እናት ነች:: ሁለቱም ልጆቿ በጭንቅላት ላይ በሚፈጠር ጠባሳ በሕክምናው አጠራር cerebral palsy(cp) ተጠቂ ናቸው :: በዚህም ምክንያት የልጆቹ የመንቀሳቀስ እና የንግግር እንዲሁም አጠቃላይ እድገት ላይ መዘግየት ይታያል:: እየሩስ የልጆቿን ሕመም መንስኤ ለማወቅ እስከሄድኩበት የሕክምና ርቀት ድረስ በምን ምክንያት ሊመጣ እንደቻለ ማወቅ አልተቻለም ስትል ትገልጻለች:: በዚህም ምክንያት ትዳሯን እስከ ማጣት እና ልጆቿን በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ብቻዋን ለማሳደግ ተገዳለች::
‹‹የመጀመሪያ እርግዝና አዲስ እንደመሆኑ በቂ የሕክምና ክትትል አድርግ ነበር::›› የምትለው እየሩስ መውለጃዋ በደረሰበት ወቅት ከሁለት ቀናት የምጥ ቀን በኋላ ልጇን ተገላገለች:: ልጇ ላይም ምንም ችግር ሳይታይ ወደ ቤቷ አመራች:: ነገር ግን የመጀመሪያ ልጇ ናታን እንደሌሎች ሕፃናት ፈጣን እድገት አልነበረውም::
እናት ይህ ስጋት እና ጥያቄ ቢፈጥርባትም ልጇ ክብደቱ ከፍ ያለ በመሆኑ ለዚያ ነው የሚሉ ከቅርቧ ሰዎች የሚሰጧት አስተያየት ችግሩን ገፍታ እንዳትመለከት አድርጓት እንደነበር ታስታውሳለች:: ልጇ ናታን ስምንት ወራት ከሆነው በኋላ በዓይኑ ላይ መንሸዋረር ያስተዋለችው እናት የዓይን ችግር ይሆናል በሚል ወደ ሕክምና ተቋም አቀናች:: ‹‹ብዙ ጊዜ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ሐኪሞች የሚታይ ነገር ይፈልጋሉ፤ በዚያ ምክንያት በቂ ምላሽ ሳናገኝ ወደቤታችን ተመለስን›› ትላለች::
‹‹ሕፃናት እንደየእድሜያቸው በየቀኑ እድገት ይስተዋልባቸዋል::›› የምትለው እየሩስ፤ ይህንን እድገት ልጇ ናታን ላይ ማስተዋል አልቻለችም:: አንድ ዓመት ሲሆነው እየሩስ ከባለቤቷ ጋር ለተሻለ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ይዛው ትመጣለች:: በአዲስ አበባ የተለያዩ ሕክምናዎችን ካደረጉ በኋላ ሰረብራል ፓሊሲ (cerebral palsy) (cp) የተሰኘ በጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠር ጠባሳ መሆኑ ተነገራቸው:: ሰረብራል ፓሊሲ (cp) በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚከሰት ከባለሙያዎች እንደተገለጸላቸው ትናገራለች::
ይህ በጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠር ጠባሳ ያጋጠማቸው ልጆች አዕምሯቸው ንቁ ሲሆን የሚጥል በሽታን ማስከተል፣ እንደ ሌሎች ልጆች በቶሎ ከመናገር እና ከመንቀሳቀስ መገደብ፤ አልያም መዘግየት እንዲከሰት ያደርጋል:: ‹‹ ሐኪሞቹ በወቅቱ ይህንን ቀለል አድርገው ስለነገሩን በቶሎ ለውጥ ያመጣል በሚል ተስፋ አድርገን ተከታታይ ሕክምና ለማድረግ ወስነን ተመለስን›› ትላለች::
ናታን ከጊዜ በኋላ የሚጥል ሕመም በተደጋጋሚ ይገጥመው ጀመር፤ ራሱን በሚስትበት ወቅትም እናት እና አባት ለሳምንታት ልጃቸውን ይዘው በሆስፒታል ውስጥ ለማሳለፍ ይገደዱ ጀመር፤ ይህም እጅግ በጣም ከባድ ድንጋጤ፣ መረበሽ እና መጉላላት ፈጠሮባቸው እንደነበር እየሩስ ታስታውሳለች:: በሀገራችን አንድ ልጅ ብቻ መውለድ በብዙም የሚመከር ባለመሆኑና ባለትዳሮቹ ይህ ሃሳብ የሚስማሙበት በመሆኑ ሁለተኛ ልጃቸውን ለመውለድ ይስማማሉ::
እየሩስ የመጀመሪያ ልጇ የገጠመው ችግር በምጥ ወቅት በሚፈጠር መታፈን ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ከመስጠት በስተቀር ይህ ነው የሚባል የሕክምና መደምደሚያ ከባለሙያዎች አለማግኘቷን ትናገራለች:: ሁለተኛ ልጇን በምትወልድብት ሰዓትም በእርሷ የክትትል ክፍተት እና የጥንቃቄ ጉድለት ችግር እንዳይፈጠር በርካታ ጥንቃቄዎችን አድርጋለች:: የቅድመ ወሊድ ክትትል በማድረግ፣ የእርሷና የባለቤቷን የሆርሞን፣ የጄኔቲክ እና ተያያዥ ምርመራዎችን ካደረገች በኋላ ሁለተኛ ልጇን ነፍሰጡር ሆነች::
ከሐኪሞች ባገኘችው መረጃ በመጀመሪያ ልጇ ላይ እንደተፈጠረው የምጥ ወቅት መታፈን ችግር እንዳይከሰትም በኦፕራሲዮን መውለድን የተሻለ አማራጭ አድርጋለች:: የመውለጃዋ ወቅት እስኪደርስም ተገቢውን ክትትል ማድረጓን ቀጠለች፤ አንዲት ነፍሰጡር እናት በጽንስ ወቅት ለልጆች እድገት የሚረዳ አመጋገብ እንደምትመገብ ሁሉ እርሷም አመጋገቧን በአግባቡ ትከታተለው ነበር:: የመውለጇ ሰዓቷ በሚደርስበት ወቅት ሁለተኛ ሴት ልጇን ኢቫና ፀሐዬን በኦፕራሲዮን ወለደች::
ሕፃናት ሲወለዱ በጤና ተቋማት ውስጥ ያላቸው ጤንነት በቅድሚያ በጥቂት ሕክምናዎች ይረጋገጣል፤ እናቲቱም ሰላም መሆኗ ሲረጋገጥ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ:: ‹‹ኢቫና ስትወለድ እንደማንኛውም ሕፃን አልቅሳለች:: ወደቤት ከሄድን በኋላ ግን የመጀመሪያ ልጃችን ላይ ያሉ ምልክቶችን እርሷም ላይ ማየት ጀመርን::›› የምትለው እየሩስ በመጀመሪያ ልጇ ላይ የገጠማት ችግር በሁለተኛ ልጇ ላይም መፈጠሩ አስደንግጧታል:: ይህ እንደ አንድ እናት እና ወላጅ በጣም ከባዱ ጊዜ ነበር:: ታዲያ በዚህ ጊዜ ከሕክምናው ይልቅ ወደ እምነት ቦታዎች ፊታቸውን በማዞር ምህረትንና ድህነትን ይጠባበቁ ነበር::
ልጃቸው ኢቫና ለአንድ ዓመት ከሁለት ወር ያህል ለውጥ አለማሳየቷ ፤ ለምን ይህ በሁለቱም ልጆቻቸው ላይ ሊፈጠር ቻለ የሚለው ጥያቄ ያልተመለሰለት አባትም ኃላፊነቱን ለእርሷ ሰጥቶ ቤቱን ትቶ ሄደ::
በፍቅር ሶስት ዓመት አብራው ያሳለፈችው፤ እንዲሁም የዘጠኝ ዓመት የትዳር አጋሯ በልጆቹ ጉዳይ የሆነውን መቀበል ከብዶት ተስፋ ቆርጦ መሄድና በወቅቱ በክልሉ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር ተዳምሮ ለእየሩስ የሕይወቷን ከባዱን ጊዜ እንድትጋፈጠው አደረጋት::
‹‹ባለቤቴ ጥሎኝ ከሄደ በኋላ በነበረው ጦርነት እንኳን ለእንደኔ ዓይነት ልጆችን ለያዘ ይቅርና ለማንኛውም ሰው ቢሆን ከባድ ነበር:: በየቀኑ መውሰድ የነበረባቸው መድኃኒትም ተቋርጦ ነበር፣ መብራት አልነበረም፣ የማበላቸው እንኳን አልነበረኝም::›› የምትለው እየሩስ ለምን ይህ በእኔ ሆነብኝ በሚል ፈጣሪዋን በመጠየቅ ብዙ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ማሳለፏን፤ ለቀናት በር እየዘጋች ማልቀሷን እና ራሷን ለማጥፋት መሞከሯን ታስታውሳለች::
እየሩስ በአይቲ የትምህርት ዘርፍ ተመርቃ በሥራ ላይ ነበረች:: ጦርነቱ አብቅቶ ሰዎች ወደ ሥራቸው መመለስ ቢጀምሩም እየሩስ ግን ያንን ማድረግ አልቻለችም:: የልጆቿን ኃላፊነት የሚወስድ አደራ የምትጥልበት ባለማግኘቷ ሥራዋን ትታ ቤት ውስጥ ለመቀመጥ ተገድዳለች ፤
‹‹ ሌሎች እህትና ወንድሞቼ ጤነኛ ልጆች ነው የወለዱት:: በእኔ ላይ ለምን ተፈጠረ በሚል ከመጨነቄ የተነሳ የቤተሰቦቼን የኋላ ታሪክ የአያቶቼን እና ቅድመ አያቶቼን በሕይወት ያሉትን ሁሉ ገጠር ድረስ ሄጄ አጣርቻለሁ፤ ነገር ግን እንደ እኔ የገጠመው የቤተሰብ አካል አላገኘሁም::›› የምትለው እየሩስ በሁለቱም ልጆቿ ላይ የተፈጠረው ሕመም ከምን እንደመጣ ዛሬም ድረስ ጥያቄ የፈጠረባት ጉዳይ ነው::
እየሩስ አለ ወደ ተባለ የምርመራ ማዕከል ብትሄድም መፍትሔ አላገኝችም፤ የመጨረሻው መፍትሔው የተለያዩ የፊዝዮቴራፒ እና የንግግር ቴራፒ ማግኘት መሆኑን ስታውቅ ወደ መፍትሔው ማተኮርን ወሰነች:: ‹‹ሁሉንም የሕክምና ዓይነት ከሞከርኩ በኋላ ያደረኩት ሁኔታውን በመቀበል ፈጣሪዬ እንደሰጠኝ እንዲያበረታኝ በመጸለይ ልጆቼ ላይ በመሥራት ለትልቅ ነገር ማብቃት እንዳለብኝ በማመን ራሴን ማስተማር ጀመርኩ›› ትላለች::
እየሩስ ከዚያን ጊዜ በኋላ በልጆቿ ጉዳይ የምታለቅስበት ጊዜ አበቃ:: የተለያዩ ድህረ ገጾች ላይ ራሷን በማስተማርና የልጆቿን ለውጥ ያግዛሉ የተባሉ ክህሎቶችን በማዳበር ሙሉ ጊዜዋን ለልጆቿ ሰጠች:: ባላት እውቀት የተለያዩ ቴራፒዎችን ታደርግላቸው ጀመር:: ምንም ሥራ ሳይኖራት በእድሜ ከገፉ ወላጅ እናቷ ጋር በመሆን፤ የአካባቢዋ ማኅበረሰብ እና ጎረቤቶቿ በሚያደርጉላት ድጋፍ ክፉ ጊዜዎቿን እያለፈች ስለመሆኑም ትገልጻለች::
‹‹ልጆቼ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የማይችሉ በመሆናቸው ዳይፐር ያስፈልጋቸዋል ፣ በየቀኑ የሚወስዱት መድኃኒት አለ፤ በቅርቤ ያሉ ሰዎች ባያግዙኝ ሥራ ሳይኖረኝ ይህንን መወጣት አልችልም ነበር›› የምትለው እየሩስ፤ ራሷን ባስተማረችበት መንገድ ቤት ውስጥ የምታገኛቸውን ቁሳቁሶች በመጠቀም ልጆቿ እንዲንቀሳቀሱ እና አዳዲስ ነገሮችን እንዲለምዱ ታደርጋለች::
ይህ ጥረቷ ምናልባት ለሌሎች እናቶች ትምህርት ከሆነ በሚል እና በዘርፉ ላይ የበቁ ባለሙያዎች ሊያግዙኝ ይችላሉ በማለትም የተለያየ ስፍራ ያሉ ሰዎችን በአንድ የሚያቀራርብ የማህበራዊ ገጽ ተሳታፊም ሆናለች:: በቲክቶክ የማህበራዊ ገጽ ላይ ለልጆቿ የምታደርጋቸውን ድጋፎች በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጻ በማጋራትም ዛሬ ላይ ከራሷ አልፋ ለብዙ እናቶች ብርታት እና አማካሪ መሆን ችላለች::
በማህበራዊ ገጽ ላይ በርካታ የሚያግዟትን ሰዎች ማግኘት እንደቻለች የምትገልጸው ወይዘሮ እየሩስ፤ በዚህ ችግር ውስጥ የሚገኙ እናቶችን በስልክ በማግኘት፤ ያላትን ልምድ በማካፈል እና እሷም ልምድ በመውሰድ በተለይም በመቀሌ ከተማ ያሉ በርካታ እናቶችን በአካል ለማግኘት ችላለች:: እየሩስ ምናልባትም የተፈጠርኩበት ዓላማ በልጆቼ ምክንያት ሌሎች በርካታ ሰዎችን እንዳግዝ ይሆናል ስትል ብዙ ቤተሰብ ማፍራቷን ትገልጻለች::
በዚህ መልኩ የተፈጠሩ እና መሰል ችግር ያለባቸው ሕፃናት ከተሠራባቸው ለውጥ ማምጣት የሚችሉ እና ለሀገር የሚጠቅሙ በመሆናቸው እናቶች በዚህ ተስፋ እንዳይቆርጡ መልዕክቷን ታስተላልፋለች:: ‹‹እንደ እኔ ዓይነት ልጆች ያላቸው እናቶች ሊረዱት የሚገባው መጀመሪያ እኛ አዕምሯችን ደህና ሲሆን አስተሳሰባችን ሲቀየር ነው ልጆቻችንን መርዳት የምንችለው ፤ ጥረት ስናደርግም ለውጥ የምናየው:: የምናየው ለውጥ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ትዕግስት ያስፈልጋል የምናየውን እያንዳንዱን ትንንሽ ለውጥ ልጆቻችን እንዲያውቁት ማድረግ ይገባል::››
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም