‹‹በችግር መቆዘም ለለውጥ ራስን መስጠት አለመቻል ነው›› – ወይንሸት ግርማ (ዶ/ር)

ወይንሸት ግርማ (ዶ/ር) የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት

መስማት የተሳናት ነች። ይህ የአካል ጉዳቷ ግን ከምንም አልገደባትም። ይልቁንም ልቃ የምትወጣበትን ዕድሎች ሰጥቷታል። አንዱ በትምህርቷ ገፍታ እስከ ዶክትሬት ድረስ መማር መቻሏ ነው። ሌላው ደግሞ የእርሷ ዕጣ ሌሎች ላይ እንዳይደርስ ለማድረግ እንደ ሀገር በምልክት ቋንቋ ”አፕ” ሠርታ ማበርከቷ ነው። ከዚያ ባሻገር በተሠማራችበት ዘርፍ ሁሉ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችላለች።

ወይንሸት ግርማ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በመምህርነት እዚያው ማገልገል የቻለች ጠንካራ ሴት ስትሆን፤ 15ኛው ዓለም አቀፍ የምልክት ቋንቋ ጉባዔ በኢትዮጵያ እንዲዘጋጅ ከጅምሩ ከለፉትና ስኬታማ እንዲሆን ከአስቻሉት መካከልም ነች። ዛሬ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች።

ይህና መሰል ተሞክሮዋ ደግሞ ለብዙ ሴቶች ጠቃሚ ሃሳቦችን እንዲጋራ ያደርጋልና በልዩ ዕትማችን እንግዳ አድርገናታል። ሙያዋ፤ ያላት ቦታና መሰል ተሞክሮዎቿ አንቱታን ቢያስቸሯትም ወጣት በመሆኗ በጽሑፋችን ውስጥ አንቺ እያልን ታሪኳን የምናጋራችሁ ይሆናል።

የእናቷ ልጅ

ትውልዷ አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ጎላ ሚካኤል በሚሰኘው አካባቢ ነው። ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ስትሆን፤ እናቷ ወይዘሮ ብዙነሽ ጎበና ያለ አባት አንቀባረው አሳድገዋታል። እንደ አዲስ አበባ ልጅ ቤት ተቀመጭ ሳትባል እንደፈለጋት ከእኩዮቿ ጋር ቦርቃ አድጋለች። ከልጆች ጋር እንደ ልጅነቷ ሱዚ፤ ጢባጢቤ፤ ገመድ ዝላይና መሰል ጨዋታዎችን ተጫውታለች። በሰፈሩ እናትና አባቶች እንዲሁም በታላላቆቿ ተቆንጥጣም አድጋለች። ለጎረቤቱ ሁሉ የመታዘዝ ጣዕሙን አይታም የሰዎችን ፍቅር ቀምሳለች።

የትናንቷ ልጅ የዛሬዋ ወጣት ወይንሸት በልጅነቷ በጣም የምትወደው ጨዋታ ጢባጥቤና ዝላይ ነበር። ሆኖም በዝላይ ጨዋታቸው ብዙ ጊዜ መመታት ይገጥማቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ሰፈሩ በአቧራ የተሸፈነ መሆኑ ነው። ገመዱን ሲያወዛውዙት ሰዎች ቤት ይገባና ይረብሻቸዋል። በዚህም መመታታቸውና መባረራቸው ግድ ይሆናል። ግን በሁኔታው ጥፋታቸው ስለሆነ አንድም ቀን ተከፍተው አያውቁም። ይልቁንም ደጋግመው ያደርጉና ለራሳቸው ደስታን ይፈጥራሉ።

በእነርሱ መጫወት ማንም እንደማይናደድ ይገባቸዋል። ነገሩን በአግባቡ እንዲያደርጉት ስለሚፈልጉ ነው የሚመቷቸውም። ስለዚህም በሚሆነው ሁሉ ደስተኛ ናቸው። የአካባቢው ሰው ሁሉም እናትና አባት እንደሆኑም ያስባሉ። በእነርሱ ሕይወት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፉም ይገነዘባሉ። ምክንያቱም ትናንት ባይሆንም ዛሬን ሲያዩት ለእነርሱ በመታዘዛቸው ሰው አክባሪነትን፤ ታዛዥነትን ተምረዋል። በምርቃታቸው የነገ ተስፋቸውን አለምልመዋል። የምርቃትን ዋጋ አይተዋል።

እንግዳችን ሌላው ልጅነቷ ላይ ማድረግ የሚያስደስታት ነገር መጽሐፍትን ማንበብ ነው። በአብዛኛው የታሪክ መጽሐፍት ይመቿታል። ለዚህ ደግሞ ጎረቤታቸው የቤተመጽሐፍት ኃላፊ በመሆኗ በብዙ መንገድ ታግዛታለች።

በባሕሪዋ ተደባዳቢና በጥባጭ የሆነችው ባለታሪካችን፤ ካልነኳት ማንንም አትነካም፤ የምትናገረውም ሆነ የምትጣላው በምክንያት የምታደርግ ልጅ ነች። በሁሉም እንቅስቃሴዋ ላይ ለምንን? ታስቀድማለች። መልስ ካላገኘችበትም በምንም መልኩ አትተውም። ይህንን ባሕሪዋን የሚያውቁ ሁሉ እርሷ የማትፈልገውን ነገር ከማድረግ ይቆጠባሉ። ይህ ደግሞ ተከባሪ ልጅ አድርጓታል።

ወይንሸት (ዶ/ር) አርዓያዋ ሁሌም እናቷ ናቸው። እናቷ በአለችበት ላይ ቆማ ነገን አሻግራ እንድታይ የሚያበረቱ፤ ቋሚ ንብረት እንዲኖራት የሚገፋፉ፤ ንባብ ሕይወቷ እንዲሆን የሚያተጉ፤ ከራሷ ውጪ ማንም እንደሌላት እንዲሰማት የሚያደርጉና ነፃነት ከምንም በላይ ለሥራዋ ሁሉ መሠረት እንደሆነ የሚያስረዱ ናቸው። በዚህም ሁሌም ልክ እንደእርሳቸው መሆንን ታልማለች። በራስ መተማመናቸው የእርሷ ብርታትን ይሰጣታል። በእንቅስቃሴዋ ሁሉ እችላለሁ እንጂ አልችልምን እንዳታስብ አድርጓታል።

የሚገጥማትን ፈተና ሁሉ በድል መወጣትን እንድታውቅበት ረድቷታል። ከሁሉም በላይ በትንሽነቷ ሳይቀር እልኸኛና ያሰበችውን ከግብ ሳታደርስ የማታቆም መሆንን አላብሷታል። በነፃነት ነገሮችን እንድታደርግም መደላደሎችን ፈጥሮላታል። ለዚህም አብነት የመሆንን ድንገት በማጅራት ገትር ወረርሽኝ ብዙዎች መስማት የተሳናቸው ሲሆኑና የተለያዩ ችግሮች ሲገጥማቸው እርሷ ግን ነገሮችን በማስተዋል ተቀብላው እንድትኖርና ወደፊት እንድትራመድ ሆናለች። ከጓደኞቿ ጋር ጭምር ምንም እንዳልተፈጠረ ሆና ጊዜዋን ተጠቅማለች።

የተሰጣት ነፃነት፤ የተሰጣት ወኔና ጥንካሬ ጠዋት በሰላም ወጥቶ ማታ ላይ በኃይለኛ ትኩሳት መጥለቅለቅና ከዚያ አልፎም መስማት አለመቻል እጅጉን ይከብዳል። ጠንካራና የሚረዳ ቤተሰብ ከሌለ ደግሞ ነገሮችን በቀላሉ ለመቋቋም ያዳግታል። ወይንሸትንም የገጠማት ይህ ነበር። ጠዋት እናቷ በሚገባ ስማትና የምትፈልገውን ሁሉ አሟልታላት ትምህርት ቤት ሰዳታለች። ማታ ስትመለስ ግን በወረርሽን በሽታው ተይዛ ኃይለኛ ሙቀት ውስጥ ገብታለች።

ከተማ ላይ ያለች በመሆኗ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወሰደችና በሕክምና ርዳታ የተወሰኑ ችግሮቿ ተፈታላት። ነገር ግን ሁሉም ችግር ወዲያው የሚፈታ አልነበረምና እያደር የመስማት ችግር እንዲገጥማት ሆናለች። ይህ ግን ለእርሷ ዱብዕዳ አልነበረም። የመጣ ትልቅ ፈተና እንጂ። ስለዚህ በችግሩ ውስጥ ከመቆዘም ይልቅ ወደ መፍትሔው መሻገር እንደሚያዋጣ ታውቃለችና ችግሩን ከመቀበል ጀምራ በራሷ ላይ መሥራቱን ቀጠለችበት።

የከንፈር እንቅስቃሴዎችን መልመድና ለንግግር ራስን ብቁ ማድረግንም በሚገባ በራሷ ተማረች። ይህ ደግሞ ጠንካራዋንና ለምንም ነገር የማትበገረዋን ወይንሸትን ፈጠረ። ባለታሪካችን በልጅነቷ መሆን የምትፈልገው ራሷን መቻልና የተደላደለ ኑሮ መኖር ነው። ይህንን ደግሞ ዛሬ ላይ እንዳሳካችው ታምናለች። ነገም ይህ እንዲሆን ትለፋለች።

ከአዲስ አበባ እስከ ኦስሎ

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተማረችው በዚያው በአቅራቢያቸው በሚገኘው ዘርዓይ ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በትምህርቷ መካከለኛ ተማሪ ነች። ነገር ግን ኤክስ የሚባል ነገር ማየት አትሻም። ሁለቱን ነገሮች ማጣጣም ሲሳናትም የተለየ ነገር ታደርጋለች። ይህም ኤክስ የገባበትን ቦታ ነጥላ ደብተሯን መቀዳደድ ነው። በዚህ ደግሞ ዘወትር ትደበደብ ነበር። በተለይ መምህሮቿ በእጅጉ ይቆጧታል። እናቷም በሆኑ ውጤታማ ለመሆን መሥራት እንጂ ደብተር መቅደዱ መፍትሔ እንዳልሆነ ይመክሯታል። በዚህም ብዙ መሻሻሎችን እንዳሳየች ታወሳለች።

እንግዳችን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን መከታተል የጀመረችው ደግሞ በአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ይህ ወቅት ትልቅ የሚባል አደጋ የገጠማት ጊዜ ነው። መስማት የተሳናት ተማሪ በመሆኗ ለመማርና ውጤታማ ለመሆን እጅጉን ከብዷት አሳልፈዋለች። በተለይም መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለመኖሩ ችግሩን ከአከበዱባት መካከል የሚጠቀስ ነው።

ከጉዳት አልባው እኩል እንድትማርና እንድትፈተን ትሆናለች። ነገር ግን ቆራጥና የጀመረችውን ነገር ከግብ ማድረስ የምትችል በመሆኗ ፍላጎቷን ለማሳካት ብዙ ለፍታለች። የከንፈር እንቅስቃሴዎችን በማየት ሌሎች ጋር ተወዳድራ የተሻለች ተማሪ በመሆን ቀጥላለች። በቃል የሚጻፉ ነገሮች ሲኖሩ ይከብዳታል እንጂ ሌሎቹን በሚገባ ጽፋ አንብባ ትፈተናለች። በቃል የሚጻፈው የሚከብዳት አንድ ጊዜ ያለውን ለመጻፍ ጎንበስ ስትል ሌላው ስለሚያመልጣት ነው። ይህም ቢሆን ከጓደኞቿ ጋር በማስተያየት የተሻለ ማስታወሻ ይዛ ወደ ቤቷ ትሄዳለች።

እንግዳችን ከትምህርቶች ሁሉ የምትወደው የታሪክ ትምህርትን ነው። ምክንያቷ ደግሞ መምህሩ ናቸው። መምህሩ በትምህርቱ የተሻለ አቅም ያላቸው፤ ለተማሪ ሥነምግባር መሻሻል የሚለፉ፤ ትሕትና ያላቸውና የተሻለ ተማሪዎችን ማፍራት የሚችሉ ናቸው። በፈጠሩት መልካም ተፅዕኖም ብዙዎች ወደ ታሪክ ትምህርት ተስበዋል። የእንግዳችንም ምርጫ እዚያ ላይ ቢያርፍ ያስደስታት ነበር። ሆኖም በጊዜው የትምህርት መስኩ ስለተዘጋ ሌላ መስክ ላይ ማረፍ ግድ ሆኖባታል። በእርግጥ በዚህም አትቆጭም። ምክንያቱም መስማት የተሳናት በመሆኗ ለብዙዎች የምትተርፍበትን ሥራ እንድትሠራ ያግዛታል።

ወይንሸት (ዶ/ር) የዩኒቨርሰቲ ትምህርቷን የተከታተለችው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ የትምህርት መስክ ምርጫዋም ሥነ ቋንቋ ጥናት (ሊንጉስቲክ) ነው። ይህ ምርጫዋ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የዘለቀ ሲሆን፤ በትምህርቷም የማዕረግ ተመራቂ እስከመሆን የደረሰችበት ነው። ሁለተኛ ዲግሪዋን መማር የጀመረችው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት እያገለገለች ሳለ ነበርም። ሦስተኛ ዲግሪዋን ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኖርዌይ ውስጥ ከሚገኘው ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በከፈተው ፕሮግራም አማካኝነት ተከታትላለች።

ትምህርቱ ጥሩ ልምድ ያገኘችበት እንደነበር በተለይም ከምልክት ቋንቋ ጋር በተያያዘ የተሻሉ መምህሮችንና የተሻለ የግብዓት አቅርቦት አግኝታ እንድትማር ስለሆነችበት ጥሩ የመሥራትን አማራጭ፤ ዜጎቿን የማገዝ ዕድል እንዳጎናጸፋት ታስረዳለች። ትምህርቱ በቤተ ሙከራ ጭምር ይሰጥ ፤ ኖርዌይ ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ሳይቀር እየሄደች የተከታተለችው በመሆኑም ከሰዎች ጋር የመተዋወቁን፤ ሀገሯን የማስተዋወቁን ዕድል ጭምር እንደሰጣትም ትናገራለች።

እንግዳችን ‹‹የትምህርት ምርጫችን ከጫናና ችግር ያላቅቀናል። ተስፋችንንም ያለመልመዋል። ይህ ችግር አለብኝ ማለትና መቀበልን ይጠይቃል። የሆነብንን ችግር መቀበል እድገትን ያመጣል፤ ነገን የተሻለ ለማድረግ ያስችለናል፤ ራስን ከጫና ውስጥ ለማላቀቅና የራስ ጌታ  ለመሆንም ይበጀናል። ለነገዎቹ ተስፋን ለመስጠት፤ አዳዲስ ፍሬያማ ተማሪዎችን ለማውጣት፤ ‹ከችግር መላቀቅ እና የተሻለ ነገን መሥራት ይቻላልን› የሚሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመፍጠር ያስችላል›› የሚል እምነት አላት።

እንደ እርሷ አመለካከት፤ የደረሰባቸውን ችግር መቀበል መቻል ምንም ችግር ካልደረሰበት እኩል መራመድ እንዲቻል ያደርጋል። ለዚህም አብነት ራሷን ታደርጋለች። ዛሬ መሆን የምትፈልገውን እንደሆነች፤ መስማት የተሳናት በመሆኗ የተነጠቀችው ነገር እንደሌለና ወደፊትም እንደማትነጠቅ ታስባለች። ችግሯን እያየች፤ ለመፍትሔው እንደምትፋጠንና ነገዋን በራሷ እንደምትሠራም ታምናለች። ሁሉም ሰው ይህንን እንዲያደርግም ትመክራለች።

የሥራ ሀሁ

ወይንሸት (ዶ/ር) የመጀመሪያ ሥራዋን የጀመረችው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በዚያው ያስቀር ነበርና እርሷም በዚያው ቀርታ የመጀመሪያ ሥራዋን በምልክት ቋንቋና በቋንቋ ጥናት ዙሪያ መምህርት ሆና እንድታገለግል ዕድሉን አግኝታለች። ለሰባት ዓመታትም በመምህርነት አገልግላለች። የአትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ጥናትና ምርምር ላይ በስፋት ሠርታለች።

ቀጣዩ የሥራ ቦታዋ የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ነው። ከሰባት ዓመታት በላይ የቆየችበት ሲሆን፤ ብዙዎችን ተግባሯን ስታከናውን የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ በመሆን ነው። ሥራው የሚሠራው ከፊላንድ መንግሥት በሚደረግ ድጋፍ አማካኝነት ሲሆን፤ ሴቶችን ማብቃትና ኤች አይቪ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። በዚህም በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። በየክልሉ ያሉ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጫናዎች የሚፈቱባቸውን አሠራሮችን ጭምር በመዘርጋት ነበርና ሥራው እንዲከናወን የምታደርገው በርካታ ሴቶች የራሳቸው ጌታ እንደሆኑም ዕድል ሰጥታቸዋለች።

ሴቶች ተከፍሏቸው የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠሩ ሲመለከቱ ወንዶች ሥራውን ከእጃቸው ለመንጠቅ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጉ እንደነበር የምታስታውሰው ባለታሪካችን፤ ይህንን በአሠራርና በሕግ ጭምር መምራት እንደቻለች ታነሳለች። ይህ መሆኑ ደግሞ እንደ ሀገር ቋሚ ንብረት ማስቀመጥ እንደተቻለ፤ ቢሮዎች ጭምር አሁን ድረስ ክፍት ሆነው እንዲሠራባቸው እንዳደረገ ትናገራለች።

ወይንሸት (ዶ/ር) ሥራዎቿ ሁል ጊዜ ቋሚ ለውጥ ከሚያመጣ ነገር ጋር ማስተሳሰር ትፈልጋለች። በዚህም ዜጎች በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ምን ያህል እንደሚሰቃዩ ታውቃለችና ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ የምልክት ቋንቋ አፕ እስከ መሥራት ደርሳለች። አሁንም ትኩረት እንዲያገኝና የምልክት ቋንቋ እውቅና እንዲሰጠው ለማድረግ ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር እየሠራች ትገኛለች።

ወደ አዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንትነት መጣች በኋላም ቢሆን የተለያዩ የለውጥ ሥራዎችን አከናውናለች። ከእነዚህ መካከልም ማኅበሩ ለዓመታት ኦዲት ሳይደረግ የቆየውን እርሷ ስትመጣ መተግበሯ የሚጠቀስ ነው። በተመሳሳይ የአሠራር ማሻሻያዎችም በብዙ መልኩ ተደርገዋል። 15ኛው ዓለማቀፍ የምልክት ቋንቋ ጉባዔ በአትዮጵያ እንዲዘጋጅ ከጅምሩ ከለፉትና ስኬታማ ካደረጉት መካከልም ነች።

በሥራዋ ሁል ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሶ ሳልሠራሁ ብላ መቆጨትን የማትፈልገው ባለታሪካችን፤ ከተሰጣት ሕግና መመሪያ ጎን ለጎን ተጨማሪ ተግባራትን ማከናወን ትወዳለች። ሕግ እስካልጣሰች ድረስ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችንም መተግበር ይመስጣታል። በዚህ ደግሞ ቋሚ አሠራሮችን ሳይቀር መዘርጋት ችላለች።

የሕይወት ፍልስፍና

ሰው ሁሉ በተፈጥሮው በጎ ነው የሚል አቋም አላት። በጎውን ተፈጥሮ የሚቀይሩት የኑሮ ጫና፤ የሰዎች መጥፎ አመለካከትና ችግሮችን አለመረዳት ሲኖሩ ነው ነገሮች ተለውጠው መጥፎውን መስመር የሚይዙት ብላ ታምናለች። ይህንን ችግራቸውን የምንረዳ ከሆነ ወደ መልካም ሰውነት እንቀይራቸዋለን። የምንወዳቸውን ሰዎች በብዛት ማግኘትም እንችላለን ብላ ታስባለች። ይህንን በማድረጓ ደግሞ እንደተጠቀመችም ታነሳለች። ሰው ሁሉ በጎ ነው ብለን ስናስብ ጠላት ጋር ጭምር በሰላም መኖር እንችላለን፤ በስኬቶቻችን የሚደሰቱ ሰዎችን እናበራክታለን የሚል እምነትም አላት።

የማይረሳው ገጠመኝ

እስከ ሦስተኛ ዲግሪዋ ስትማር ፈታኝ የሆነባት አንድ ነገር ብቻ ነበር። ይህም የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለማግኘቷ ነው። በተለይም የምርምር ሥራዎቿን ስታከናውን ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን አንድ ዓመቷን ጭምር በልቶባታል። ይህ ገጠመኝዋ መቼም የማትረሳው ሆኖ አልፏል። ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው።

አንድ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ቢያንስ አንድ የምርምር ሥራዎችን በታዋቂ ጆርናሎች ላይ ማሳተም አለበት የሚለው እነርሱ ለምረቃ እየተሰናዱ ባለበት ወቅት ተቀየረና ወደ ሁለት ከፍ እንዲል ተደረገ። ይህ ደግሞ ለወይንሸት (ዶ/ር)ና ሌሎች ተመራቂዎች በእጅጉ አስደንጋጭ ክስተት ነው። ምክንያቱም በሦስት ወር ውስጥ አይደለም ሁለት የምርምር ሥራ አንዱንም ማሳተም አይቻልም። መሥራቱም ቢሆን በቀላሉ የሚሳካ አይደለም።

ወይንሸት (ዶ/ር) ግን ከሌሎች ተቋማት ጋር አብራ በመሥራቷ የተነሳ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በታዋቂ ጆርናሎች ላይ አሳትማለች። እንደተባለው ሁለት የምርምር ሥራዎችንም ማቅረብ ችላለች። ይሁንና አንዱ በትምህርት መስኩ ዙሪያ የተሠራ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በሴቶች ዙሪያ የተሠራ ነው። ስለዚህም ተቀባይነት ያገኘው አንዱ ብቻ ነበር።

በዚህ ወቅት ሁሉም በሚባል ደረጃ ምንም ሳያቀርቡ እርሷ ሁለቱን አቅርባ በመገኘቷ የቅርብ መምህሮቿና አንዳንድ የትምህርት ቤቱ አመራሮች እንድትመረቅ መግባባት ላይ ደረሱ። አንድ የትምህርት ቤቱ አመራር ግን አይሆንም አለ። ጥፋቱ የተቋሙ ሆኖ ሳለ ‹‹የትም ፍጨው ዱቄቱን አምጪው›› የሚለውን አባባል ማራመዱን ቀጠለ። በዚህም ሁለቱም አርቲክሎቿ ውድቅ ተደረጉ።

ወይንሸትም (ዶ/ር) በሁኔታው ብትበሳጭም ሠርታ ማሳየት እንደምትችል ግን እምነት አላትና በቀጥታ ወደ ሥራዋ ገባች። ሁሉም መመረቅ ባለመቻላቸውም በአንዱ አርቲክል እንዲሄድ ሲፈቀድ እርሷም እንድትሳተፍ ቢነገራትም አሻፈረኝ አለቻቸው። በአዲስ መልኩ ሁለቱንም ሠርታ ማንነቷን አሳይታ በዓመቱ መመረቅ ቻለችም።

በእርግጥ ዩኒቨርሲቲው ያለአስተርጓሚ አስተምሯት በሦስት ወር ውስጥ የጥናትና ምርምር ሥራ ሠርተሸ አቅርቢ ብሏት ያላትን ሥራ ሊቀበላት አለመውደዷ በጣም አበሳጭቷታል። ግዴታቸውን ሳይወጡ ግዴታ እንዳለብሽ ማለታቸው ተገቢነት የሌለው ጉዳይም እንደሆነ አስረግጣ ትናገራለች። በዘህ አጋጣሚም ይህ ዓይነት ተግባር ዳግም እንዳይደገምም ስትል መልእክቷን ታስተላልፋለች።

ስለሴትነት

ሴት ልጅ በአፈጣጠር ባሕሪዋ ካልሆነ በስተቀር ከወንዶች አትለይም። ሴት ቤትንም ሆነ ውጪ ላይ ያሉትን ሥራዎች በአግባቡ መምራት፤ ማስተዳደር የሚሳናት አይደለችም። ይልቁንም ሁሉንም በተሻለ ጥበብና እይታ ታቆመዋለች። ሴት ልጅ ርኅሩህና ብልሃተኛ፤ የማኅበረሰብ መሠረት ጣይም ናት። ሴት ልጅ ሕይወት፤ ሀገርም ናት። ሴት ልጅ እናት ናት የልጆቿን ነገ የምታነጋ። ሴት ልጅ መንገድ መሪም ናት ልጆችን ለተተኪነት የምታበቃ። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ራሷን በብዙ መንገድ ማብቃት ይጠበቅባታል። አንዱ በትምህርት ሲሆን፤ ሌላኛው በኢኮኖሚ ነው።

ሴት ልጅ በራስ መተማመን ካላትና የተሰጣትን ኃላፊነት በመቀበል ሠርታ ካሳየች የማኅበረሰቡንም ሆነ የመንግሥትን ምልከታ መቀየር ትችላለች። ከዚያ ባሻገር ደግሞ በኢኮኖሚ ራሷን አብቅታ ስትገኝ ማንንም ቀና ብላ መናገርም ማዘዝም ትችላለች። ስለሆነም ቢያንስ ማኩረፊያ የሚሆናት የራሷ ገቢ ማመንጨት ያስፈልጋታል።

ለሴት ልጅ የራስ ገቢን ማግኘት ክብርን በእጅ ማስገባት ነው። የፈለገችውን ቦታ በፈለገችው ጊዜ መፈናጠጥም ነው። ትችላለችን ወደ ራሷ መሳብም ነው። አሁን ደግሞ ዘመኑ ይህንን እንድታደርግ ያግዛታል። ልማር ብትል፤ ልሥራ ቴክኖሎጂው የረቀቀ በመሆኑ የትም ሳትሄድ ቤቷ ቁጭ ብላ ማድረግ ትችላለች።

ሁሌ ከማማረር መውጣት አለባት። ጨለምተኛ የሆነ አስተሳሰቧንም ማስወገድ ይገባታል። ወደ ውጭ ወጥታ ብርሃኗን ልትፈልግ ያስፈልጋል። በእርግጥ እነዚህን ተግባራት እንዳትከውን የሚያደርጓት በርካታ ነገሮች አሉ። አንዱ ራሷ ሴቷ ወደ ለውጥ ውስጥ ላለመግባት የምታደርገው የአመለካከት ችግሯ ነው።

አሁን ዘመኑ በሠለጠነበትና መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ስለ ሴቶች እየሠራ ባለበት ጊዜ ሴቷ ሴቶች ደካማ ናቸው፤ ሴት ልጅ ከወንዶች እኩል አይደሉም ትላለች። ማኅበረሰቡ ኃላፊነት ሲሰጣትም ለራሷ ቦታና ጥሩ ግምት ስለማትሰጥ ለሌሎች ቦታውን አሳልፋ ታስረክባለች። የራሷ ገቢ ሳኖራት ትዳር ትመሠርታለች። ልጄ በሚል ተልካሻ ምክንያት ራሷን ታስራለች። እንዲህ ያሉ ሴቶች ደግሞ ስንፍናቸውን ላለማሳየት የሚጥሩ ናቸው ስትል ታነሳለች።

ሴት ልጅ ለልጆቼ ነው የምትለውን ማታለያ ቃላት በፍጹም መተው አለባት። እየተደበደበች ለልጆቼ ነው፤ ሳትሠራ ቤት ውስጥ ተቀምጣ ማሳለፉ ለልጆቼ ነው ትከክል አይደለም። ለልጆቿ ወጥታ ሠርታ ስትገባና ደስተኛ ስታደርጋቸው ነው ነገን የምትገነባላቸው። መደብደቧን እያዩ ከሚያዝኑ ልጆች ይልቅ ሠርታ የምትገባና ጠንካራነቷን እያሳየቻቸው የምትጓዝ እናት ልጆቿ ላይ የምትፈጥረው አመለካከት እኩል አይደለም። እናም ከፍታዋን ለልጆቿ ማሳየት ያለባት በቤት ውስጥ ተረግጣ በመኖር ሳይሆን የራሷ ጌታ በመሆን ነው። ለልጆች ራስን ገሎ ሳይሆን ራስን ለውጦ ማሳየት የበለጠ ያበረታታቸዋልና ሴቶች ይህንን እያሰቡ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም በዚህ አጋጣሚ ትገልጻለች።

ወይንሸት (ዶ/ር) ሌላው ያነሳችው ነገር ሴቶች ላይ ማኅበረሰቡና በመንግሥት ዘንድ የሚመጣውን ጫና ነው። በተለይ ሴትና አካል ጉዳተኝነት ተሳስረው ሲመጡ ያለው ችግር በዋናነት የመወያያ አጀንዳ መሆን እንደሚገባው ታብራራለች። ምክንያቱም ሴት ልጅ እውቀትና አቅም ስላላት ብቻ የትም መድረስ አትችልም። መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮች ያስፈልጓታል።

እነዘህም የቤተሰብ ድጋፍ፤ የመንግሥት ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ግድ ይላል። ለአብነት ምቹ የመማሪያ ቦታ፤ የመሥሪያ ስፍራ ሳታገኝ እምቅ አቅሟን ልታሳይ አትችልም። ከቤት ውስጥ እንድትወጣ ካልተፈቀደላት የትም ሄዳ ማንነቷን ልታሳይ አይቻላትም። በዚህ ደግሞ ሀገር የሚጠቅሙ ሴቶች ዐሻራቸውን እንዳያሳርፉ ተፈርዶባቸዋል።

ለሌሎች አርዓያ የሚሆኑ ሴቶችም እንዳይወጡ ገድቧቸዋል። ተከታዮችም እንዳይኖሩ፤ ማኅበረሰቡም ባለው አመለካከት ጸንቶ እንዲቀጥል አድርጎታል። ስለሆነም ሴትነት ብዙ ነገር ቢሆንም የገደቡት በርካታ ተግዳሮቶች አሉና ከራሷ ከሴቷ ጀምሮ እስከ ላይኛው መንግሥት ድረስ መሠራት ይኖርበታልም በማለት ትመክራለች።

ውሃ አጣጭን ለመከታ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለጥንዶቹ ባለውለታቸው ነው። በተለይ ሁለቱም አንድ የትምህርት ክፍል ውስጥ መማራቸው በትምህርት ጥናታቸው ውስጥ የትዳር ምርምርም እንዲሠሩ መሠረት ሆኗቸዋል። እርሷ ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ ብትመደብም የእርሱን ያህል ግን አይደለችም። ስለዚህም በጉብዝናው ጠርቶ እንዲያስጠጋት ሆኗል። አንተ ትብስ አንቺ ትብሱም በትምህርቱ ብቻ ሳይሆን በፍቅር ጭምር ተጠናክሯል። ይህ ደግሞ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገውን ቤት መሥርቷል። አሁን ሁለት ልጆችን አፍርተው በፍቅር እንዲኖሩም መደላድልን ፈጥሯል።

እርሷ ፈጣን ነች። ቶሎ የመቆጣትም ባሕሪ አላት። እርሱ ግን ከእርሷ በተቃራኒው ወገን ይቀመጣል። ነገሮችን በሰከነ መልኩ ያያል፡ በዚህም ዘወትር ከችግሮቿ ይታደጋታል፤ ይጠብቃታልም። ይህ ባሕሪው ደግሞ እርሱን ስታነሳው መከታዬ፤ ጠባቂዬ እንድትለው ያስችላታል። አሁን በሥራ ምክንያት ወደ ውጭ ሀገር በመሄዱ ብዙ ነገር እንደጎደለባት ይሰማታል። ጎኗ ባለመኖሩ ቶሎ መፍትሔ ለማግኘት የማትችልባቸው ነገሮች በመኖራቸው ቢከፋትም በስልክ ቢሆን ከስሯ እንዳራቀ እንዲሰማት ስለሚያደርጋት በእርሱ ደስተኛ ነች።

በዚህ አጋጣሚም አንድ መልዕክት ለሌሎች ባሎች ታስተላልፋለች። ለሚስቶቻችሁ አጋዥ፤ መከታና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው አመላካች ሁኑላቸው። የዚህን ጊዜ የእነርሱ ስኬት የእናንተም ይሆናል። ለሀገርም የምታበረክቱት ነገር ይበራከታል።

መልዕክት

ማንም ሰው ጠንካራ ለመሆን መሥራትና መፈተን አለበት። በእነዚህ ሁለት ክስተቶች ውስጥ ማለፍ ካልቻለ ነገን አሻግሮ ማየት አይችልም። የተሻለ ሆኖም ለመውጣት ይገደባል። ተተኪ ማፍራትም ይሳነዋል። ይህ ደግሞ ትውልድን ጭምር ለማስቀጠል ፈተና ይሆናል። ሰዎች ሠርቶ ለመለወጥ በሚያደርጉት ግብግብ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም። ተፈተንኩ ብለውም እጅ ሊሰጡ አይገባም። ይልቁንም ነገን አሻግረው በማየት ወደፊት መጓዝ ይኖርባቸዋል። ያን ጊዜ አሸናፊነት፤ ብርታትና የተሻለ ቦታ ማግኘትን ይቆናጠጡታል። ሀገርን በማሻገር ላይም ዐሻራቸውን እንዲያኖሩ ይሆናሉ ትላለች።

ሌላው መልዕክቷ ሴቶች እኔ ዕድለኛ አይደለሁም፤ እኔ መሥራት አልችልም፤ እኔ ይህ የለኝም ወዘተ ማለት የለባቸውም የሚለው ነው። ሴቶች ችግሮችን ከመዘርዘር ይልቅ ያላቸውን ማሳደጉ ላይ ሊጠመዱ ይገባል። እነርሱ የባሰ ችግር ያለባቸውን እያዩ ወደፊት መጓዝ አለባቸው። በችግር መቆዘም ችግርን ይጠራል። በችግር መቆዘም ለለውጥ ራስን መስጠት አለመቻል ነው። በችግር መቆዘም ከጭለማ ጋር ራስን ማዋሓድ ነው። ከችግር ራስን በፍጥነት ለማውጣት መትጋት ያስፈልጋል። በብርሃን ለመመላለስ ቆፍጣና መሆን ያስፈልጋል ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You