
ወቅቱ በጋ ቢመስልም የወይዘሮ ብርቅነሽ ቀልቦሬ ግቢ አረንጓዴ ከመሆን የከለከለው ነገር የለም:: ወዲህ ሸንኮራው፣ ወዲያ ደግሞ ጎመኑ፣ ዴሾ በመባል የሚታወቀው የሳር አይነቱ፣ ዝሆኔው፣ ብቻ ሁሉም አለ ማለት ያስደፍራል:: በሌላ በኩል ደግሞ በግቢው ውስጥ በራቸው ክፍት የሆኑ ውስን ቤቶች ይታያሉ፤ በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ገለባ መሳይ ነገር ታጉሮባቸዋል:: ልብ ተብለው ሲታዩ ግን የከብቶች ቡፌ የሚያሰኝ የተለያየ የመኖ አይነት መሆኑን ተረዳን::
አብዛኛውን ጊዜ ሰው ለምግብ ፍጆታነት የሚጠቅመውን የጓሮ አትክልት በቅጥር ግቢው እንደሚያለማው አይነት ወይዘሮ ብርቅነሽ ደግሞ ለሚያረቧቸው የወተት ላሞች አስፈላጊ ናቸው የተባሉትን የመኖ አይነት በግብርና ባለሙያዎች እየታገዙ በማልማታቸው ግቢያቸውን በከብቶች መኖ ሞልተውታል:: ስለዚህም ለከብቶች መኖነት ተፈላጊ የሆኑ የሳር እና የስራስር አይነቶች በስፋት ይታያሉ፡
የዛሬው የልዩ ዕትም እንግዳ ያደረግናቸው ወይዘሮ ብርቅነሽ ቀልቦሬ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሃድያ ዞን፣ ሆሳዕና ከተማ አራዳ ቀበሌ የመንደር ሶስት ነዋሪ ናቸው:: እንደማንኛውም ሰው ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል ቆጠረው ሥራ ይዘው ይተዳደሩ የነበረ ቢሆንም፤ ተቀጣሪ ሆኖ መዝለቁን ልባቸው በጀ አላለም::
በአሁኑ ጊዜ ሥራቸውን ለቀው መተዳደሪያቸው ያደረጉት መንግሥት በያዘው የከተማ ግብርና ኢንሼቲቭ መሰረት ነው:: ስለዚህም ወር ጠብቀው የሚሰፈርላቸውን ጥቂት ብር ከሰው እጅ ከመቀበል ይልቅ በወተት ላም እርባታ መተዳደርን መርጠው በማኅበር ተደራጁ::
እርሳቸውን ጨምሮ ጥቂት ሰዎች መንግሥት ባመቻቸው ሁኔታ በማኅበር ቢደራጁም፤ ሌሎቹ በቁርጠኝነት ለመዝለቅ የእርሳቸውን ያህል ብርቱ መሆን አልቻሉም:: ማኅበሩ ጅማሬውን ያደረገው በ2002 ዓ.ም ላይ ነው:: ወደ ሥራ መግባት የቻሉትም በአንዲት ላም ብቻ ነበር:: በወቅቱ አብረዋቸው የጀመሩ የማኅበሩ አባላት እንዲሁ እንደዋዛ ብር ከመንግሥት የሚገኝ መስሏቸው ሥራውን ለመሥራት ቢጀምሩም በሥራ እና በሒደት የሚመጣ ብር እንጂ ወዲያው የሚታፈስ ብር አለመኖሩን እያደር አጤኑ:: እነርሱ የጠበቁት ነገር ባለመሳካቱም ብዙም ሳይቆዩ ማኅበሩን ትተው ወጡ::
ወትሮም ቢሆን ሰርቶ እንጂ ተቀምጦ የሚመጣ ሀብት የልማና ማኀበሩን ትተው ሲወጡ ምንም አይነት የመከፋት ስሜት አይታይባቸውም ነበር:: ለእነዚህ የማኅበሩ አባላት ዋና ግባቸው የነበረው በመሥራት ከሚገኘው ገቢ መጠቀም ሳይሆን፤ መንግሥት ስላደራጀ ብቻ ፍላጎታቸው የነበረው የጎደለውን ነገር ሁሉ እየሞላላቸው ተቀምጠው መቆጣጠር ነበር:: ይሁንና አባላቱ እንዳሰቡት አንዳች የሚሰጥ ነገር አለመኖሩን በማየታቸው ምርጫቸው ለቅቀው መሄድ ነበርና አደረጉት::
በወቅቱ ወይዘሮ ብርቅነሽ፣ ከእነርሱ ጋር በመሆን ለከብት እርባታ የሚያስችል ቦታ ተከራይተው መሥራት የጀመሩ ሲሆን፣ እንደሌሎቹ ብር ለምን አልተሰጠም በሚል ማኅበሩን ለቅቀው መውጣትን አልፈለጉም:: ወይዘሮዋ፣ “እኔ ግን የመንግሥትን እጅ ማየትን ምርጫዬ አላደረግኩም::” ይላሉ:: ስለዚህም የማኅበሩ አባላት የማኅበሩን ደንብ ተከትለው የመልቀቂያ ደብዳቤ ካስገቡ እና ከተሰናበቱ በኋላ ማኅበሩን በቁርጠኝነት ለማስቀጠል ታተሩ:: ደግሞም ተሳካላቸው:: በእርግጥ በእነዚህ መሃል ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩም በመጋፈጥ ሥራቸውን ለማስኬድ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል::
በአሁኑ ወቅት እርሳቸው ጥጆች፣ ገና በማደግ ላይ ያሉ ጊደሮች እና ላሞችን ጨምሮ 28 ከብቶች ያሏቸው ሲሆን፣ ሁለት ተጨማሪ በሬዎችም አሏቸው:: ካሏቸው የወተት ከብቶች በቀን የሚያገኙት የወተት መጠን ተለዋዋጭ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ብርቅነሽ፣ አንዳንዴ በርከት ያሉ ከብቶች ወተት የሚሰጡበት ጊዜ ላይ ሲሆኑ፣ በርከት ያለ ሊትር ወተት ይገኛል ይላሉ፤ አንዳንዴ ደግሞ በመታለብ ረዘም ያለ ጊዜ ያስቆጠሩ የወተት ላሞች በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ አነስ ያለ የወተት ምርት እንደሚያገኙ ነው የሚያስረዱት::
እንዲያም ሆኖ ወይዘሮ ብርቅነሽ በአሁኑ ጊዜ በቀን እስከ 70 ሊትር ወተት ያገኛሉ:: ይህን ተከትሎም ለአራት ሰው የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል:: የከተማ ግብርና ላይ በመሥራታቸው በእጅጉ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይናገራሉ:: መንግሥትም ዘርፉን በዚህ መልክ ማመቻቸት በመቻሉም አንደኛዋ ተጠቃሚ እርሳቸው ቢሆኑም፤ ለሌሎችም መልካም አጋጣሚ መፍጠር መቻላቸውን ያመለክታሉ::
እርሳቸው እንደሚናገሩት ከሆነ፤ የገበያ ትስስር ችግር የለባቸውም:: እንዲያውም የእርሳቸው ወተት ተመራጭ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ የሚወስዱት ሕጻናት ያሏቸው ሰዎች ናቸው:: በሚያቀርቡት የወተት ምርትም ሁሌ ተመስጋኝ ሲሆኑ፣ ተመራጭነታቸው የመጣውም ሁሉን በንጽህና ስለሚይዙት እንደሆነ አውግተውናል::
በእርግጥ በቤተሰብ ደረጃ ብዙውን ጊዜ ኃላፊነቱ ከፍ የሚለው ሴቶች ላይ ነው:: ከዚህም የተነሳ ተደራራቢ የሥራ ጫና አለባቸው:: ከዚህ ውስጥ አንዱ ልጆቻቸውን በማሳደጉ ረገድ ሚናቸው ጉልህ መሆኑ ነው:: እናት ለልጇ የምትሳሳ እንደ መሆኗ ለልጇ ምርጡ የተባለውን ነገር ሁሉ ብታቀርብ ምኞቷ ነው ይላሉ:: ከዚህም የተነሳ እርሳቸው የሚሸጡትን ወተት ሕጻናት ላሏቸው እናቶች መሸጥን ይፈልጋሉ:: እያደረጉ ያሉትም ያንኑ ነው::
ወይዘሮ ብርቅነሽ፣ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደርም ሆነ የሃድያ ዞን ግብርና ቢሮ ምስጋና እንዳላቸው ይናገራሉ፤ እርሳቸው ወደ ከተማ ግብርና ሲገቡ ምንም እንኳ ብዙዎቹ ምንም ሳይሠራ በቀላሉ የሚታፈስበት የሥራ መስክ አድርገው በመቁጠራቸውና እንዳሰቡት ሆኖ ባለማግኘታቸው ማኅበሩን ትተውት ቢወጡም ከጎናቸው ሆነው ሲያበረታቷቸው የነበሩ የግብርና ባለሙያዎችን ከልባቸው ያመሰግናሉ::
በተለይ ከከብት መኖ ጋር ተያይዞም ሆነ ከከብቶች ጤና ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጋቸውን ከማማከር እስከ ማቅረብ እየተደረገላቸው ያለው ክትትል በሴትነታቸው ጠንክረው እንዲሠሩ ምርኩዝ እንደሆናቸው ያስረዳሉ:: እርሳቸውም ለሥራ ቁርጠኛ በመሆናቸው የከብቶቻቸው ቁጥር በጨመረ ቁጥር የሚያስፈልጋቸው መኖ የዚያኑ ያህል የሚጨምር በመሆኑ ከሌሎች ቁጭ ብሎ መጠበቅን አይፈልጉም:: በራሳቸው ተንቀሳቅሰው የጎደለውን ለመሙላት ይጣጣራሉ::
ሁሌም ከብቶች እያረቡ ወተት በማከፋፈል መወሰንን አይፈልጉም፤ ሥራቸውን ከፍ ለማድረግ ወደ ወተት ማቀነባበር ብገባ ደስ ይለኛል ይላሉ:: ወተት ብቻ ከመሸጥ የወተት ተዋጽኦን ለገበያ ማቅረብ ይናፍቃሉ:: ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ንብ በማነብ ሥራ ለመሰማራት እቅድ እንዳላቸው ይገልጻሉ:: እርሳቸው ሥራቸውን ሲያከናውኑ ያለ እቅድ የሚያደርጉት ነገር የለም:: ስለሚሠሩት ሥራ አስቀድመው ያቅዳሉ፤ እቅዳቸውንም ይተገብራሉ:: ይህ መለያ ባህሪያቸው ነው:: የገቢ እና የወጪ መዝገብ ደብተር ያላቸው ሲሆን፣ የመንግሥትን ለመንግሥት፤ የግላቸውን ደግሞ ወደ ግል ካዝናቸው ያደርጋሉ:: እኔ ሥራው በጣም ተመችቶኛል ይላሉ:: እንዲያም ሆኖ በዚህ ብቻ መወሰንን አልፈልግም ሲሉ አጽንኦት ይሰጣሉ::
ቀደም ሲል ይሰሩ የነበረው ከፈረንጆች ጋር ነው፤ የቅርብ አለቃቸው በጣም ሥራ ወዳድ ስለነበሩ ከእርሳቸው የወሰዱት ልምድ ዛሬ እርሳቸውንም ሥራ ወዳድ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: ካገኙት ልምድ በመነሳት ሥራ አይንቁም፤ ምንም እንኳ አራት ያህል ሰራተኞች ቢኖሯቸውም የሚያረቧቸውን ከብቶች ንጽህናቸውን የሚጠብቁላቸው እርሳቸው ናቸው:: የከብቶቻቸውን ንጽህን መጠበቅ ከሚያስደስታቸው ተግባራቸው መካከል ግንባር ቀደሙ ነው:: ከብቶቹን በንጽህና ስለሚይዟቸውም ብዙ ጊዜ የእርሳቸው ከብቶች ለበሽታ ሲጋለጡ አይስተዋልም::
ሴት ሥራዋን ስታከናውን የመጀመሪያ መስፈርቷ ጽዳት ነው የሚሉት ወይዘሮ ብርቅነሽ፣ መኖሪያ ቤታቸውን ከማጽዳት ጀምሮ ያሉበትም አካባቢ ንጽህናው የተጠበቀ እንዲሆን ይመርጣሉ:: ከዚህም የተነሳ እርሳቸውም እንኳን የቤታቸውን እና የግቢያቸውን ውበት መጠበቅ ቀርቶ የሚያረቧቸውን የወተት ላሞችን ንጽህና በመጠበቃቸው ሊያመጣባቸው ካለው ኪሳራ ራሳቸውን መታደግ ችለዋል:: ምክንያቱም የከብቶቹ ንጽህና መጠበቅ ባይችል ኖሮ እንደሌሎቹ ከብቶች በተለያየ በሽታ ተይዘው ከጥቅማቸው ይለቅ የኪሳራ ምንጭ ይሆኑባቸው እንደነበር ያስረዳሉ::
ተቀጥሮ መሥራት የሌላን ሰው እጅ እንደ መጠበቅ የሚቆጠር ነው:: የራስን ሥራ መሥራት የመፍጠር አዕምሮን የሚያሰፋ ነው:: ከዚህ በተጨማሪም የባለቤትነት ስሜት ስላለው ሰዓት ተጠብቆም ሳይጠበቅም ለመስራት ምቹ ነው ይላሉ:: ከራስ አልፎ ሌሎችን ለመርዳት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርም ጭምር ነው:: ወደዚህ ሥራ ለመግባት መተዳደሪያ የሆናቸውን ሥ ራ ጨክኖ መልቀቅ ግድ የሚል ነበርና ሳያቅማሙም በማድረጋቸው በአሁኑ ጊዜ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል::
ወይዘሮዋ፣ አንድ የቸገራቸው ነገር ቢኖር ከብቶቻቸውን ከሚያረቡበት ቦታ ጥበት ነው:: እንደ ልብ መግባት እና መውጣት የሚያስችል መንገድ አለመኖሩ ደግሞ ሌላው ተግዳሮት ነው ሲሉ ይናገራሉ:: በእርግጥም ለእርሳቸው ትልቁ ማነቆ መንገድ መሆኑን በወቅቱ በስፍራው ተገኝተን ያስተዋልነው መሆኑን መጥቀስ የሚቻል ነው፤ ለከብቶቻቸው መኖ ሲመጣ ወደ ውስጥ ለማስገባት ፈተና ይሆንባቸዋል:: መንገዱ ቀና ቢሆን አንድ መኪና ገዝተው ወተት ለከተማ ነዋሪው ማመላለስ እንደሚቻልም አውግተውናል::
እርሳቸው ከቤተሰባቸው ባለፈ ሌሎችን የመርዳቱ ርዕይ ነበራቸውና በአሁኑ ወቅት ከሚያገኙት ገቢ የእርሳቸውን ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች በማጋራት ላይ ይገኛሉ:: በተለይም ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን ለአራት ተከታታይ ዓመት ደብተር እና እስከሪብቶ ዓመቱን ሙሉ በመቻል እንዲማሩ የማድረግ ድርሻቸውን በመወጣት ላይም ናቸው:: ይህን ቀጥሎም የሚያደርጉት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸው እንደሆነ ያስረዳሉ:: ይህንን ለማድረግ የታደሉትም ስለሠራሁ ነው ሲሉ ይናገራሉ::
ወይዘሮ ብርቅነሽ ዛሬም ከስራቸው ጋር በተያያዘ አሻግረው ያልማሉ:: አሁን ካላቸው ቦታ በተጨማሪ ቢሰጣቸው በተሻለ ሠርተው በሆሳዕና እና በክልሉ ብቻ ሳይወሰኑ የወተት ተዋጽኦ ማከፋፈልን ያልማሉ:: ምርታቸውን ካሉበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፈ እስከ አዲስ አበባ ድረስ መውሰድን ይናፍቃሉ:: ይህ እንደሚሳካላቸውም ባለሙሉ ተስፋ መሆናቸውን ይናገራሉ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም