
ሴትን ልጅ የሚያግዝ፤ ሊያበረታታ የሚችል ሥርዓት ከተዘረጋ አይደለም ከተረጋጋ ሕይወት ከወደቀችበት ተነስታ አጀብ የሚያሰኝ ስኬት ታስመዘግባለች:: ነገዋን አሻግራ በማየት ለሕልሟ ትዋደቃለች:: ለዚህ ነው ‹‹ሴትን መደገፍ ሀገርን ማገዝ ነው›› የሚባለው። ሴቶች በብልሃት፣ ጥንካሬና ዓላማ መርህ በመሆን የሚገዳደራቸው እንደሌለም ይታመናል። ከእነዚህ ብርቱ ሴቶች መካከል ለምለም ሰለጋ አንዷ ነች::
ለምለም ገና በሰባት ዓመቷ የቤት ሠራተኛ ሆና ነው የኑሮ ውጣውረድን የጀመረችው:: ልጅ ሆና ልጅ አዝላለች፤ ልጅ ሆና ልክ እንደ እናት ልጆችን መግባለች፤ ልጅ ሆና መጫወት ሲገባት የልጆች አጫዋች ሆናለች:: ለዚህ መራራ ሕይወት የዳረጋት የቤተሰቦቿ የኑሮ ሁኔታ ነበር:: እናት አባቷ በግብርና ይተዳደራሉ:: ሆኖም ቤተሰቡን ሊመግብ የሚችል ምርት አያገኙም:: በዚህ ምክንያት ለምለምን ጨምሮ ሌሎቹ ልጆች ገና በታዳጊነታቸው ሥራን መፈለግ ግድ ብሏቸዋል::
የለምለም ወንድም አዲስ አበባ ነው የሚሠራው። እርሷም የእርሱን ፈለግ ለመከተል በማሰብ ወደዚሁ መጥታለች:: ታላቅ ወንድሟ ያለበት የኑሮ ሁኔታ ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑም እስከ 13 ዓመቷ በቤት ሠራተኝነት ለማገልገል ተገድዳለች:: ለምለም ኑሮ በብዙ መልኩ ያስተማራት ልጅ በመሆኗ ከሠራተኝነት ወጥታ ራሷን ነፃ ለማድረግ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም:: በግል የጀመረችው የመጀመሪያ ሥራዋ ድንች ቀቅሎ መሸጥ ነበር፤ ንግዱ አላሳፈራትም በቶሎ ትርፋማ አድርጓታልም::
ድንች በመቀቀል የጀመረችው የንግድ ሥራ ጥሩ ልምድን የቀሰመችበት በመሆኑም ወደ ተሻለ ሥራ ለማሳደግ አሰበች:: ጉልት ላይ በመቀመጥ በዝቅተኛ ዋጋ የአትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምጣት በችርቻሮ መልክ ለወጭ ወራጁ መሸጡን ተያያዘችው:: ይህ ደግሞ የእለት ገቢዋን በእጅጉ ጨመረላት:: ሌላ የሥራ እቅድም እንድታወጣ አገዛት::
በንግድ ሥራዋ ገቢዋን ከፍ እንደምታደርግ ያመነችው ለምለም ሌሎች የተሻሉ የሥራ አማራጮችን መመልከት ጀመረች:: ከጉልቱ ሊያስነሳት የሚችል ሥራ ደግሞ የእቅዷ አንዱ አካል መሆን እንዳለበት አምናለች:: ሀሳቧ ሱቅ መክፈትና ጎን ለጎን ተባራሪ ሥራዎችን ማከናወን ነበር:: ሆኖም ለሱቅ የሚሆን ቦታ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም፤ ተስፋ ሳትቆርጥ ብዙ በሮችን አንኳኳች::
አንድ ቀንም ጥሪዋ ተሰማና በቀበሌ አመራሮች በኩል ‹‹የምስራች›› ተባለች:: ‹‹ምስር ብሉ›› ብላ አብራ ከተደራጀቻቸው ሰዎች ጋር ለሱቅ የሚሆናትን ስፍራ ተረከበች:: የምታገኘውን ገንዘብም ላለማባከን በአካባቢው ከሚገኙ ሴቶች ጋር እቁብ ገባች:: ውጤታማ ሆናም ቤተሰቦቿን እያገዘች ቆየች:: በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች ነበር በውሳኔዋ ዛሬ ላይ የምትፀፀትበትን ርምጃ የወሰደችው።
በስደት የባከኑ ዓመታት
ለምለም ሀገሯ ላይ የተሻለ አቅም ብትፈጥርም፤ የበለጠ መሥራት እንዳለባት ታምናለች:: ይህንን ፍላጎቷን ለማሳካት ስትል ባሕር ማዶ ለመሻገር አሰበች:: ያጠራቀመችውን ገንዘብ ይዛ በደላላ በኩል ወደ ሱዳን ጉዞ ጀመረች፤ ነገር ግን እቅዷ እንዳሰበችው አልተሳካም:: የስደት ምርጫዋ ስቃይ እንጂ በረከትን ይዞላት አልመጣም:: በስደት ወቅት ርሃብና ጥሙን እንደምንም ልታልፈው ብትሞክርም ሌሎች የማትቋቋማቸው ነገሮች ገጠሟት::
‹‹በስደት ቆይታዬ ወደ ውጭ መውጣት ፍፁም የተከለከለ ነበር:: የውሃም ሆነ የሳሙና ነገር አይታሰብም:: ልብስ ማጠብ የለም፤ ገላ መታጠብ የለም፤ የሴት ግዴታ መጥቶ ሳይቀር እንደ ልብ ወጥቶ መጸዳዳት አይቻልም:: በዚህም የራስ ጠረን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ጠረንን መቋቋም ግድ ነው:: አትጠጉኝ ማለትም አይቻልም:: በመሆኑም በሽታ ሳይቀር አብሮ ያምሳል:: በቃ ያለውን ስቃይ ብቻ ነው ከማለት በስተቀር ቃላት አይገልጸውም›› ትላለች ጊዜውን ወደ ኋላ መለስ ብላ ስታስታውሰው::
በስደት በቆየችባቸው የመጀመሪያዎቹ ወራቶች ቶሎ ወደ ሥራ የሚያስገባት ሰው አላገኘችም:: በዚህ ምክንያት ርሃብና ጥሙ አሰቃይቷታል:: ይህ ፈተና ራሷን ለማጥፋት እንድታስብ ሁሉ አድርጓት ነበር:: ከዚህ ከባድ ድባቴ ለማምለጥ ስትል ጫት ቅማለች፤ ሺሻ አጭሳለች ሌሎች አደንዛዥ እጾችን አብዝታ ተጠቅማለች፤ ሁኔታዎች ሲከብዱ ወደ ሀገሯ ለመመለስም ሞክራ ነበር፤ ነገር ግን ሁለቱም እቅዷ አልሠራም። የፈሰሰ ውሃ የሆነባት ባለታሪካችን ከገባችበት ወጥመድ እስክትወጣ በስደት ሕይወት ቆይታለች:: በቆይታዋ ከአንድም አምስት ሰው ቤት ገብታ ሠርታለች::
ከአራቱ ቀጣሪዎቿ ጋር በጽዳት ሠራተኝነት ስትሠራ በቋንቋ ፤ በጫና እና መሰል ችግሮች ምክንያት ቶሎ ቶሎ ለመቀየር ተገድዳለች፤ በአምስተኛው ግን በተወሰነ መልኩ የተረዷት ቀጣሪዎች በማግኘቷ ከስድስት ዓመት በላይ ቆይታለች:: በርግጥ በዚህም ቢሆን ጫናዎቹ የበረቱ ነበሩ:: ነገር ግን ትናንት ከሆነባት ነገር ስለማይበልጥ ትእግስት አድርጋ ለዓመታት ሠርታለች:: ለምለም ከሥራና የባሕሪ ጫና በማይተናነስ መልኩ የአየር ፀባዩን ለመልመድም ተቸግራ እንደነበር ታስታውሳለች።
‹‹በሱዳን ያለው ሙቀት ከምድርም ከሰማይም እሳት የሚዘንብ ያህል ይሰማል:: ግድግዳ እንኳን ነክቶ ራስን ማቀዝቀዝ አይቻልም:: ስለዚህ ቅዝቃዜ ካሻሽ የግድ ቬንትሬተር ያስፈልግሻል:: ይህ ደግሞ ለሠራተኛ የማይታሰብ ነው:: ስለዚህ ምርጫሽ እየተቃጠሉ መተኛት ነው:: ይህም በሥራ ብዛት የደከመ አዕምሮሽንና ጉልበትሽን እንዳታሳርፊ ያደርግሻል:: ነገሩ ከከባዱ ጸባያቸው ጋር ሲዳመር ምን ማድረግ እንዳለብሽ ግራ ይገባሻል›› ስትልም ያሳለፈችውን የስደት መከራ ዘመን ታወሳለች::
ለምለም ወደ ሀገሯ እንዴት እንደተመለሰች ስትናገር ‹‹የምሠራበት ቤት ባለቤቶች ልጆችን በአልበላ አንጀቴ ደጋግሜ ፎቅ ድረስ እየወጣሁና እየወረድሁ ምግብ እንዲበሉ ጠየኳቸው:: እነርሱ ግን እምቢታን መረጡ:: በመጨረሻም ለእናትና አባት ተናገርኩ:: ምላሼ ግን የሆነው ስድብ ነበር:: ያውም እኔን ሳይሆን ሀገሬን የሚያዋርድ ስድብ:: መጀመሪያ የስድቡ ናዳ የወረደው በእኔ ላይ ስለነበር ምንም አላልኩም:: ነገር ግን ስድቡ ወደ ሀገሬ ሲሻገር መቋቋም ተሳነኝ:: ‹ገረዳችሁ እኔ፤ የምትሰደበው ሀገሬ ለምን› ስል ተሟገትኳቸው:: እነርሱ ግን ማቆም አልቻሉም:: በዚህም ግጭታችን ከረረና ወደመጣሁበት ቦታ እንዲመልሱኝ ጠየኳቸው:: ደመወዝ እንኳን ሳይሰጡኝ ወደ አየር መንገድ ወስደው አሳፍረው ወደ ሀገሬ ሸኙኝ:: በዚህ ግን አንዳች ነገር አልተቆጨሁም:: ምክንያቱም ሀገሬ ናፍቃኛለች:: ሠርቼ ለመለወጥም ጓጉቻለሁ:: እናም ህልሜ ተሳካ እንጂ አልተደናቀፈም:: ትናንት የተመኘሁትን ወደ ሀገር የመመለስ ፍላጎቴ እውን ስለሆነልኝም ተደስቻለሁ›› ትላለች የሰው ሀገር ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ስትናገር::
‹‹ማንም ሰው ስድብንና የሥራ ጫናን ሊቋቋም ይችል ይሆናል:: ነገ ያልፍልኛል ብሎ ርሃብን፤ የጉልበት ብዝበዛውን ሊቋቋመውም ይችላል:: አንድ ነገር ግን መቋቋም ይሳነዋል:: ይህም ሀገሩን የሚነካበትና የሚሳደብ ሰውን በቀላሉ ሊያልፈው አይችልም:: እኔም ያደረኩት እርሱን ነበር›› ያለችን ለምለም፤ የሀገሯን ምድር ከረገጠች በኋላ ቁጭቷን ለመወጣት ምንም ዓይነት ሥራ ሳትመርጥ ነበር የምትሠራው:: መጀመሪያም ሥራዋን አሀዱ ያለችው በሰፈር ውስጥ ጋዜጣ በማዞር ነው::
መለወጥ ግዴታዋ እንደሆነ ታውቃለችና በምንም መልኩ ጉልበቷን አትቆጥብም:: ቀድሞ የተሰጣት ሱቅን በሚገባ እየተጠቀመችበት ጎን ለጎን የጉልበት ሥራ ሳይቀር ትሠራለች:: ሀገሯ ምንም ዓይነት ተልዕኮ ስትሰጣትም ቀድማ ትደርሳለች:: ለአብነት እርሷ የሰላም ሠራዊት በመሆን ለሀገሯ ዘብ እየቆመች ትገኛለች:: ከዚያ ባሻገር የተለየ ስብሰባ ካለ ሁሉንም ሰው በጡርንባዋ እንዲንቀሳቀስ ታደርጋለች:: ይህ ሥራዋ ደግሞ ድቅድቅ ጭለማውን ጭምር መጋፈጥን የሚጠይቅ ነው::
ለምለም ቅዳሜ የገበያ ቀኗ ቢሆንም ጽዳት ላይ ከመሳተፍ አትቦዝንም:: ሁሉን ቀስቃሽ፤ ሁሉን አሳታፊ በመሆን አካባቢያቸውን ጽዱና የተዋበች እንዲሆን ትታትራለች:: ጽዳት ራስንና ቤተሰብን ከበሽታ በመከላከል ጤናማ ትውልድን ለሀገር ያበረክታል ብላ ስለምታምንም ያለምንም ክፍያ ተግባሩን ትፈጽማለች::
ለምለም በስደት ካየችው ስቃይ አንጻር የተለየ ትርጉም አለው:: በእርሷ አገላለጽ ሀገር ‹‹ንጹህ እንቅልፍ የሚተኛበት፤ መሬቱ የሰጡትን አብቅሎ የሚመግብበት፤ ጥሩ አየር የሚተነፈስበት፤ በነፃነት ሃሳብ የሚገለጽበት፤ ስጡኝ ቢባል የማይታፈርበት፤ የሚዘረጉ እጆች የበዙበት ነው:: ሰው ደካማ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ምድር ንፉግ አይደለም:: በአንዳንድ ቦታዎች ያሉ ግጭቶች በማስቀረት ይህንን እድል የበለጠ ማስፋት ይቻላል:: በመሆኑም የሀገርን ጥቅም እንደዋዛ ማየት ተገቢ እንዳልሆነ ትመክራለች:: በሀገራችን ኮርተን በሀገራችን ሠርተን መለወጥ ይኖርብናል ትላለች።
ከጅብ ጋር እስከ መፋጠጥ
ለምለም ዘወትር ጥንካሬዋን ማሳየት ትፈልጋለች:: በዚህም ድቅድቅ ጭለማ ሳይቀር ተጋፍጣ የሰላም ሠራዊትነት ተልዕኮዋን ትወጣለች:: ሠራዊቱን ለመቀስቀስ ጡሩንባዋን ይዛ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት በመነሳት ጭምር ለሀገሯ ያላትን ፍቅር ትገልጻለች:: ይህንን ስታደርግ ደግሞ ጥበብ በተሞላበት መንፈስና በወኔ ነው:: ለሀገሯና ለባንዲራዋ ሕይወቷን አደራ በመስጠት ነው::
በጭለማ መሥራት ብዙ ጣጣ አለው፤ ድፍረትና፣ ጥንቃቄና ኃላፊነት መውሰድን ይጠይቃል። ከቀን ይልቅ በጭለማ ብዙ አጋጣሚዎች ይኖራሉ:: ለምለም ግን እንደ እድል ሆኖ የከፋ ነገር አልደረሰባትም። በሀገር ፍቅር ታጥራ፤ በእምነት ለመጋደል ወስና ስለምትወጣ ብዙ ገጠመኞች የሏትም:: የደረሱባት ችግሮችም እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም:: የገጠሟትንም ችግሮች በጥሩንባዋ እንደፈታቻቸው ታነሳለች::
በአንዱ የሥራ ሌሊት ውሾች ከያሉበት ተሰባስበው የከበቧትና ጡሩንባ ስትነፋባቸው አንዱ ብቻ ቧጭሯት የተበተኑበት አጋጣሚን አትዘነጋውም:: ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጅብ ጋር ተፋጥጣለች፤ ይህንንም በጡሩንባዋ በማስደንገጥ ሕይወቷን ታድጋለች::
ሴትነት በለምለም ዕይታ
ሴት ልጅ ዝቅ ብሎ መኖርንም፤ ማኖርንም ትችልበታለች:: ለልጆቿ የሰው ቤት ታጸዳለች፤ ልብስ ታጥባለች፤ እንኩሮ አንኩራ ለእለት ጉርስ የሚሆን ገቢን ታመጣለች:: ለልጆቿ መከታም፤ መምህርም መሆንን ጠንቅቃ ታውቅበታለች:: ማንም ላይ ጥገኛ መሆንን አትሻም:: ይልቁንም ተደግፋ ቀና ማለትንና ለተሻለ እድገት መትጋትን ትችልበታለች::
እድል ካልገፋት በስተቀር ሁሌም ከፍታን እንጂ ዝቅታን አትመርጥም:: በምትሠራው ሥራ ወደኋላ ይሉት ነገርም አታውቅም:: እየራባት አጉራሽ፤ እየከፋት አጽናኝ፤ የቤቷ እያረረባት የሰው ገበናን ሸፋኝ ናት:: ልጆች ቢሉ ሀገር በእርሷ ማንነት ይቆማሉ፤ በእርሷ ጥረት ዛሬን አልፈው ነገን ያያሉ:: በአጠቃላይ ሴት ልጅ የቤት እመቤትም፤ የውጭ መብራትም ፤ የሀገር ምሰሶም ነች ብሎ መውሰድ ይቻላል ትላለች::
ለምለም ‹‹እኔ ሴት በመሆኔ ፍላጎቴን ጭምር ገትቼ ለሌሎች መኖርን መርጫለሁ:: በመኪና አደጋ አካል ጉዳተኛ የሆነች እናቴን የወንድሜን እንዲሁም የእህቶቼን ልጆች እየተንከባከብኩ የምገኘው ሴት በወሰነችበት ጉዳይ ላይ ወደኋላ እንደማትል የሚያረጋግጥ ነው›› በማለት፤ እኛ ሴቶች ላሰብነው ነገር ሁሌም ቆራጥ መሆናችንንም ያሳያል ትላለች:: በመሆኑም ሴትን በጎደላት ቦታ እየተገኙ መደገፍ ሀገርን ከማቅናት አይተናነስም ትላለች። በመሆኑም የሴቶችን አቅም ለማጎልበት ሁሉም የበኩሉን ማበርከትም ይኖርበታል ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች:: ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም