ሀገር አቀፍ የፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል እየተካሄደ ነው

በዘመናዊው የኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ትልቅ ሚና ካላቸው ተቋማት መካከል የሚሊተሪ ተቋማት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። እንደ ኦሜድላ ያሉ የስፖርት ማህበራት ደግሞ እንደ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ኮማንደር ጌጤ ዋሚ እና በላይነህ ዴንሳሞን የመሳሰሉ ድንቅ አትሌቶችን አፍርቷል። በተለያዩ ስፖርቶች ተፎካካሪና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቁልፍ የሆኑ ተጫዋቾችን ያፈራው የፖሊስ ሠራዊት ከመደበኛ ሥራው ባለፈ በስፖርት ያለው ተሳትፎ ጠንካራ መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና በሀገር አቀፍ ደረጃ ይህንን መሰል ውድድሮች ተቋርጠው ቆይተው ዘንድሮ በደማቅ ሁኔታ ተመልሰዋል።

በዚህም ሀገር አቀፍ የፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል። ‹‹በላቀ የስፖርት ተሳትፎ ብቁ እና ንቁ የፖሊስ ሠራዊት እንገነባለን›› በሚል መሪ ሃሳብ ከቀናት በፊት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት መክፈቻውን በማድረግ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ተወዳዳሪዎችን እያፎካከረ ነው። ሁሉንም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚያሳትፈው ይህ ውድድር አትሌቲክስና እግር ኳስን ጨምሮ በ10 የስፖርት አይነቶች ይደረጋል። አስቀድሞ በየክልሉ ሲከናወኑ የቆዩ የፖሊስ ውድድሮች መጠናቀቃቸውን ተከትሎም ከቀናት በፊት ከ1ሺ600 በላይ ተፎካካሪዎችን በማሳተፍ ሀገር አቀፉ ውድድር የተጀመረ ሲሆን፤ እስከ መጋቢት 02/2017 ዓ.ም ድረስም የሚቆይ ይሆናል።

በመክፈቻው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ መንግሥት ስፖርት ለሀገር ያለውን ፋይዳ ከግምት በማስገባት በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከተሰጠው ሕግን የማስከበር ኃላፊነት ጎን ለጎን በስፖርቱ ዘርፍም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ የኦሜድላ ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ ውለታ ከዋሉ ክለቦች መካከል አንዱ መሆኑንና ወደ ቀደመ ገናና ስሙ ለመመለስም በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። በቀጣይ በኢትዮጵያ በሚደረገው 5ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ከስፖርታዊ ውድድሩ ጎን ለጎንም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በትብብር በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርገዋል። ፖሊስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞችን እያፈራ በመሆኑ ተቋርጦ የነበረው የፖሊስ ስፖርት ውድድሮችን በማስጀመሩ እና ስፖርቱን ለማልማት ሠራተኞች ከደመወዛቸው በፐርሰንት እየተቆረጠ ለሠሩት ሥራ ምስጋና እንደሚገባቸውም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። ስፖርት ሰላምን፣ ፍቅርንና አብሮነትን ለማስፈን ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን የተረዳው ፖሊስ፤ ስፖርትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ስፖርትንና ኪነጥበብን በማስተሳሰር የውስጥ ውድድሮችን በማጠናከር እንዲሁም በስልጠናና በውድድር በጋራ እንደሚሰሩና ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ሚኒስትሯ ቃል ገብተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ከአንድ ቤተሰብ በላይ በመተሳሰብ የሚሰሩ አባላትን የያዘ ትልቅ ተቋም መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ናቸው። በመሆኑም የውስጥ አንድነትን ለማጠናከር ስፖርት በተቋሙ ዓይነተኛ ሚና አለው። ተቀራርቦ በመስራትም ባህል፣ ኪነጥበብ እና ስፖርትን በመጠቀም ትስስሩን በማጠናከር ሀገር ማቅናት የሚችል ተቋም ከመመስረት ጋር ውጤት ይመጣል። ስፖርት ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቅ እንደመሆኑም በመንግሥት በጀት ማስኬድ ስለማይቻል ከሠራተኞች ደመወዝ በመቁረጥ ስፖርቱን ለማሳደግ እየተሰራ ነው። የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ ስፖርት ውድድርን በትብብር ለማካሄድ እንደሚሰራም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሃመድ በበኩላቸው፤ ፖሊስ ውጤታማ ስፖርተኞችን በማፍራት ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። የስፖርት ጸረ አበረታች ቅመሞች ምርመራ በሀገር ውስጥ ለማድረግ ላቦራቶሪ ለማቋቋምና የወንጀል ህግ አፈጻጸም ዙሪያ በትብብር ቢሰራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም አመላክተዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You