
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ጨምሮ ሌሎች የስፖርት ውድድሮችን ለማስተናገድ ምቹና ተመራጭ ናት። በእንግዳ ተቀባይነቷ ስመጥር የሆነችው የምስራቋ ኮከብ ድሬዳዋ ሕዝብም ስፖርት ወዳድነቱን በብዙ መልኩ አስመስክሯል። ኢትዮጵያን በታላላቅ የውድድር መድረኮች ከመወከል ባለፈ ለውጤታማነትም ጉልህ ሚና የነበራቸው በርካታ ስፖርተኞችን አፍርታለች፤ በማፍራት ላይም ትገኛለች። ለስፖርቱ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እጥረት ለመቅረፍ ጠንካራ ሥራ በማከናወንም ተመስጋኝ ከተማ ናት፡፡
ባለፉት ስድስት ወራትም በስፖርት ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም በማሳየት ለሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሞክሮ መሆን ችላለች። በዚሁ ምክንያት ከተማ አስተዳደሩ ያቀረበውና በመጪው ዓመት የሚካሄደው 7ኛው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ምዘና ውድድር አዘጋጅነት ጥያቄዋ ተቀባይነትን አግኝቷል። በመሃል መቀዛቀዝ ገጥሞት የነበረው የስፖርት እንቅስቃሴ የስፖርቱ የበላይ ጠባቂ በሆኑት የከተማዋ ከንቲባ አነሳሽነት ወደነበረበት ሊመለስ እንደቻለ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማስፋፋትና ማልማት ዳይሬክተር ኢብሳ ዱሪ ይጠቁማሉ። ለዚህ ማሳያ የሆነው ደግሞ በከተማዋ የሚገኙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በሳምንት ሶስት ቀን በስታዲየም ተገኝተው አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው እንዱም ከአጎራባች ክልሎችን ጨምሮ ከጅቡቲ ከሚመጡ ልኡካን ጋር ውድድሮችንም ማከናወናቸው ነው።
ሕዝባዊ የስፖርት እንቅስቃሴውም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይገኛል። ድሬዳዋ ካላት የአየር ሁኔታ አንጻር ተላላፊ በሽታዎች በስፋት የሚስተዋል እንደመሆኑ አስቀድሞ የመከላከል ሥራዎች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ይገኛሉ። የታዳጊዎች የስፖርት ሥልጠና ፕሮግራምም በተነቃቃ ሁኔታ እየተሰጠ ይገኛል። በእግር ኳስ ከፊፋ በተገኘው ድጋፍ መሠረት በየትምህርት ቤቶች ዕድሜያቸው ከ8 ዓመት ጀምሮ የሆኑ ታዳጊዎች ይሠለጥናሉ፡፡
በአጠቃላይ 68 የታዳጊ ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን ታዳጊዎችም እንዳሉበት ሥፍራ ተስማሚ ለሆኑበት ስፖርት (ለገሃሬ አካባቢ ለቅርጫት ኳስና ቮሊቦል፣ ሳቢያን አካባቢ ለእግር ኳስ፣ ገንደቆሬ ለባህል ስፖርት፣…) ተለይተው የሚመለመሉ ይሆናል። ታዳጊዎችን ተቀብሎ በተቀናጀና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ አሠልጥኖ ለብሄራዊ ቡድን ለማብቃትም አካዳሚ እየተገነባ ሲሆን፤ በቀጣዩ ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። በመጀመሪያ ዙርም 120 ታዳጊ ወጣቶች ተቀብሎ ወደ ሥልጠና እንደሚገባም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ እግር ኳስ ወዳድ እንደመሆኑ እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ድረስ ሊያጫውት የሚያስችል ብቃት አለው። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግም በከተማዋ ለማካሄድ ምቹ ከመሆኑ ባለፈ ከሶማሌ ክልል በመቀጠል በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (VAR) ተግባራዊ ማድረግም ተችሏል። በዲቪዚዮን በሚደረጉ ውድድሮች ጭምር ይኸው ዳኝነት የሚተገበር ሲሆን፤ ከ25ሺህ እስከ 30ሺህ ሕዝብ የሚይዘው ስታዲየም ጨዋታዎች በሚኖሩበት ወቅት በተመልካች ተሞልቶ ይታያል። ከተማዋ በካፍ ዕውቅና ያገኘ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ያላት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ልምምድም ሆነ ውድድር በዚሁ ስታዲየም ማድረግ እንዳለበትም ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ በ2029 ለማዘጋጀት ያቀደችው የአፍሪካ ዋንጫ በድሬዳዋ እንዲካሄድ ለማድረግም ተጨማሪ የስታዲየም ግምባታ (ከዓመታት በፊት መሠረተ ድንጋይ የተጣለ) እቅድ መኖሩንም አንስተዋል፡፡
በየትምህርት ቤቶቹ የቤት ውስጥ ስፖርት ማካሄጃ እንዲሁም እንደ እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ እና ቮሊቦል ስፖርቶች የሚዘወተሩባቸው ሜዳዎችም እየተስፋፉ ይገኛሉ። እያንዳንዱ ወረዳ ቢያንስ አንድ የስፖርት ማዕከል ያለው ሲሆን፤ ከከተማዋ መስፋትን ታሳቢ ያደረጉ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግንባታም እንዲሁ ነዋሪዎችንና ባለሀብቶችን በማካተት እየተሠራ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የማስተናገድ ዕድልን ያገኘችው ከተማዋ ከስፖርቱ ባለፈ ኢኮኖሚው ላይም የማነቃቃት ሚናም ነበረው። ከዚህም ጋር በተያያዘ ከተማዋ ቀድሞ የነበራትን ሁኔታ እንድትላበስ የተለያዩ ሥራዎችም በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ነው ዳይሬክሩ ያብራሩት።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም