
ጣሊያን ኢትዮጵያን ከወረረች ከ65 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያዊው ወታደር ሮምን ብቻውን በባዶ እግሩ ወረረ። የዓለም መገናኛ ብዙሃንም አስቀድሞ ያልተገመተ አበበ ቢቂላ የተባለ ጥቁር አትሌት በባዶ እግሩ ማራቶንን በመሮጥ አባቶቹ በጣሊያን ላይ የተቀዳጁትን ድል መድገሙን አወጁ። አሸናፊ የሆነበትን የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አደባባይ በክብር ተወለበለበ። በጣሊያን ጎዳናዎች ያሳረፈውን ዐሻራ ተከትሎም ትውልድ ለዘመናት እየተቀባበለ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከውጤታማነት ማማ ሳያወርድ አሁን ካለበት አድርሷል።
ቅኝ ግዛትን አልሞ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ጣሊያን ከ129 ዓመታት በፊት ድል በተደረገበት ሥፍራ ስመጥሮቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት የማራቶን ዱላ ቅብብል ፉክክር አድርገዋል። ከዓድዋ ድል ቀጥሎ ኢትዮጵያ ስሟ በክብር የሚነሳው በአትሌቲክስ ነው። ጀግኖች አባቶች የተዋደቁለት የኢትዮጵያ ክብር በጀግኖች አትሌቶች የትውልድ ቅብብል ለዘመናት ቀጥሏል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ጀግንነት በተገለጠበትና ታሪክ በተሠራበት ዓድዋ 20ኛው የኢትዮጵያ የማራቶን ሪሌ ውድድር ተካሂዶ የድል በዓሉን አድምቋል።
የአፍሪካና የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነውና ኢትዮጵያውያን አባቶች ጣሊያንን ድባቅ በመቱበት የዓድዋ ጎዳናዎች ላይ በተደረገው በዚህ ውድድር ላይ ሀገራቸውን ወክለው በዓለም አቀፍ ቻምፒዮናዎች ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩ አትሌቶች ተሳትፈዋል። ከእነዚህም መካከል በኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ባለሜዳሊያው ሃጎስ ገብረህይወት፣ የቀድሞው የዓለም የቤት ውስጥ ክብረወሰን ባለቤቱ ሳሙኤል ተፈራ፣ የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ያለምዘርፍ የኋላው፣ የዓለም ቻምፒዮን የሜዳሊያ ባለቤቷ እጅጋየሁ ታዬ፣ የዓለም ቻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ኮከቧ ወርቅውሃ ጌታቸው፣ ተስፈኛዋ ወጣት አትሌት ለምለም ኃይሉ፣ አብርሃም ስሜ፣ ኃይለማሪያም አማረ፣ ገመቹ ዲዳ፣ አይናዲስ መብራቱ፣ አሳየች አይቼውና ሌሎችም ትልልቅ ስም ያላቸው አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ተሳትፈዋል።
ጠዋት 2፡00 ሰዓት የጀመረው ውድድር በየ 10፣ 7 ነጥብ 1 እና 5 ኪሎ ሜትር ልዩነት ወንድና ሴት አትሌቶች ዱላ በመቀባበል የአሸናፊነት እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ አድርገዋል። በዚህም ውድድር ከሶስት ክልሎች፣ አንድ ከተማ አስተዳደርና አምስት ክለቦች የተውጣጡ አትሌቶች ተካፋይ ነበሩ። አጓጊ ፉክክር በሚስተናገድበት የሪሌ ውድድሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀዳሚነት በማጠናቀቅ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል። በውድድሩ የመጨረሻውን ርቀት የሸፈነችው እአአ የ2023 የለንደን እና የ2024ቱ የአምስተርዳም ማራቶን አሸናፊዋ ኮከብ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው ክለቧን ቀዳሚ ልታደርግም ችላለች። በሩጫውም አስደናቂ አጨራረስ በማሳየት በሥፍራው የተገኙ የስፖርት ቤተሰቦችን አስደምማለች።
በውድድሩ ይጠበቅ የነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አትሌት ሃጎስ ገብረክርስቶስ በደረሰበት መጠነኛ ጉዳት በሩጫው አለመሳተፉም ከቦታው የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
በ20ኛው የማራቶን ሪሌ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ክለብ ሸገር ከተማ ሲሆን፤ በመጨረሻው ርቀት በመሰለፍ ክለቧን ለብር ሜዳሊያ ያበቃችው አትሌት ደግሞ በቡድን ስራ የምትታወቀው አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ናት።
የበርካታ ድንቅ አትሌቶች ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽሟል። ባለፈው ዓመት በቤልግሬድ በተካሄደው የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና በወጣቶች ዘርፍ ተሳትፋ በግሏ የብር በቡድን ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ወጣቷ አትሌት አሳየች አይቸው ክለቧ የነሃስ ደረጃን እንዲይዝ አድርጋለች።
ለአሸናፊዎቹም እንደየደረጃቸው ከሚያገኙት ሜዳሊያ ባለፈ የ40 ሺህ፣ 20 ሺህ እና 15 ሺህ ብር ሽልማት በፌዴሬሽኑ የተበረከተ መሆኑም ታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም