
ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ስፖርት ትልቁ መሣሪያ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሰውነት ማጎልመሻና ስፖርት ኢንስቲትዩት ዲን ወገኔ ዋልተንጉሥ (ዶ/ር) ገለፁ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሁለተኛ ምዕራፍ ሁለተኛ መድረክ “ስለኢትዮጵያ” የፓናል ውይይትና የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ ትናንት በሐረር ከተማ ሲካሄድ፣ አብሮነት ስለኢትዮጵያ በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የፓናል ውይይት በተለያዩ ምሑራን ባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ስፖርት ለአብሮነት የሚጫወቱትን ሚና በተመለከተ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ስፖርት ለአብሮነት የሚያበረክተውን ሚና በተመለከተ በመድረኩ ጽሑፍ ያቀረቡት ወገኔ ዋልተንጉሥ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ብዝኃ ባሕልን ለማጎልበትና የጋራ እሴትን ለመገንባት ትልቁ መሣሪያ ስፖርት ነው።
የሌሎችን ስሜት የሚረዳ ኅብረተሰብ ለመገንባት ስፖርት ትልቅ ሚና እንዳለው የጠቆሙት ወገኔ ዋልተንጉሥ (ዶ/ር)፣ ስፖርት የውድድር ባሕልን በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ የሚያስችል ትልቅ መሣሪያ በመሆኑ አንድነትን፣ ትብብርን አብሮ መነሳትን የማስተማር አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
“የስፖርት ቡድን ስብስብ የኅብረ ብሔራዊነት ማሳያ ነው” ያሉት ወገኔ (ዶ/ር) የጋራ ማንነታችንን በስፖርት አማካኝነት ማጎልበት ይቻላል ብለዋል። ስፖርት ብዝኃ ባሕልን ለማጠናከር ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ወገኔ (ዶ/ር) ገለፃ፣ ስፖርት ሁሉንም ሰው የሚያግባባ የዓለም ቋንቋ ነው። በዚህም ሰላምን መስበክና ማስፈን ይቻላል። ስፖርት ባሕል ውስጥ የምናከናውነው በመሆኑ ስፖርትን ከሠላም ሰላምን ከስፖርት መነጠል አይቻልም። ምክንያቱም ስፖርት በራሱ ዲሞክራሲን ስለሚሰብክ። ስፖርት በራስ መቆምን፣ መወዳደርና ማሸነፍን የሚያሳድግ ነው። አሸናፊ እንዲኖር ደግሞ ተሸናፊ ወይም ተገዳዳሪ መኖር አለበት። አሸናፊውም ለተሸናፊው ክብር መስጠት ያለበት ለዚህ ነው።
ስፖርት የውድድር ባሕልን በማኅበረሰቡ ዘንድ ለማስረጽ እንደሚያስችል ያስረዱት ወገኔ (ዶ/ር)፣ በሕግና ሥርዓት መመራት የምንችለው በስፖርት ነው ብለዋል። በዚህም ስፖርት የማኅበረሰብ እሴቶችን የማሻሻል ኃይል እንዳለው ጠቅሰው መተጋገዝን ለማጎልበት ትልቅ መሣሪያ መሆኑን አብራርተዋል።
ስፖርት አንድነትን በመፍጠር ለጋራ ዓላማ ለመቆም የሚያስችል መሆኑን በመግለጽ የሰላም መልክዓ ምድር ለመፍጠር ያለው ጠቀሜታ ትልቅ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም የስፖርት እሴትን ለሀገር ግንባታ መጠቀም ለነገ የማይተው ወሳኝ ጉዳይ ነው በማለት አፅንዖኖት ሰጥተዋል።
ስፖርት በዚህ ረገድ ያለውን ጥቅም ብናውቅም ማኅበራዊ ጥቅሙን ወደ መሬት አውርደን በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች እንዳሉብንም ወገኔ (ዶ/ር) ተናግረዋል። እነዚህን ክፍተቶች ለመድፈንና ከማኅበራዊ ፋይዳው በብዙ ለመጠቀም አንዱ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማስፋት መሆኑንም አንስተዋል።
በእርግጥም ስፖርት ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ትልቅ ተፅዕኖ እንዳለው ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱና እግር ኳሱ ውጤት ሲቀናት በሕዝብ ዘንድ የሚፈጠረው ስሜት ማሳያ መሆኑ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ሀሳብ ተሰንዝሯል። ስፖርት በሕዝብ ዘንድ አንድነትን ከመፍጠርና ማጠናከር በተጨማሪ ውጤት የሚመዘገበውም በስፖርተኞች አንድነት መሆኑም ተጠቅሷል። ለአብነትም ኢትዮጵያ ወርቃማ ውጤት ያስመዘገበችባቸው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በአትሌቶች አብሮነትና መተጋገዝ የተገኙ ናቸው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአትሌቶች ዘንድ አብሮ ልምምድ መሥራት እየቀረ በመምጣቱ እንደ ሀገር ውጤት እየቀነሰ በመሆኑ በቀደሙት ዓመታት አትሌቶች በጋራ የሚለማመዱበትና የሚወዳደሩበት ሁኔታን መመለስ እንደሚያስፈልግ ተወያዮች አስተያየት ሰጥተዋል።
የመድረኩ አወያይ የነበሩት የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በሰጡት አስተያየት፣ ስፖርት ምክንያታዊና የሰከነ ትውልድ ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳለው ጠቁመው፣ ለሕዝቦች አንድነትና አብሮነትም ከፍተኛ አቅም አለው ብለዋል። ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውድድሮችን ለማስፋት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ተቋርጠው የቆዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮችም ዘንድሮ መካሄድ እንደጀመሩ አስታውሰዋል። ለዚህም ለዓመታት ተቋርጠው የነበሩት ሀገር አቀፍ የታዳጊዎች የምዘና ውድድርና የዩኒቨርስቲዎች ውድድርና ፌስቲቫል ከሳምንታት በፊት ዳግም ተጀምረው መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም