ጥናታዊ ጽሑፏን ወደ ቢዝነስ የለወጠች ወጣት

ብዙዎች የወጣነትነት ዕድሜያቸውን ለቁምነገር ከማዋል ይልቅ በዋዛ ፈዛዛ ሲያባክኑ ይስተዋላል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ወደ ዩኒቨርሰቲ ገብተው ተመርቀው ሥራ አጣሁ እያሉ ማማረርና ራስን ለሥራ ዝግጁ አለማድረግ የተለመደ ጉዳይ ነው።

የወጣትነት ዕድሜን በአግባቡ በመጠቀም ለመለወጥ መፍጨርጨር ነገን የተሻለ ያደርጋል። የዛሬ የወጣትነት ዓምዳችን የወጣትነት ዕድሜን በአግባቡ በመጠቀም ስኬታማ የሆነች የ35 ዓመት ዕድሜ ወጣት እንስትን ተሞክሮ ያስነብበናል።

ወጣት ኬኔሳ ሙሉነህ ትባላለች። የተወለደችው በምሥራቋ ፈርጥ ድሬዳዋ ከተማ ሲሆን በሦስት ዓመቷ ቤተሰቦቿ ለኑሮ ወደ ኔዘርላንድ ይዘዋት ስለሄዱ ዕድገቷ አውሮፓ ኔዘርላንድስ ነው። የማኅበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳታፊ ስትሆን፣ የሥራ ፈጠራ ክህሎት እና የሕይወት ልምዷን በበይነ መረብ (ኦንላይን) ሥራ ለመፍጠር ለሚታትሩ ዜጎች ከራሷ ልምድ በመነሳት ታስተምራለች።

ወጣቷ ገና በጨቅላነቷ ወደ ኔዘርላንድ ብትሄድም አማርኛን አቀላጥፋ ትናገራለች። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኔዘርላንድስ በማጠናቀቅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ በቤተሰቦቿ ምርጫ ሕክምና ዘርፍ እንድታጠና እንዳደረጓት ትገልጻለች፡፡

ዩኒቨርሰቲ ገብታ በወላጆቿ ምርጫ የሕክምና ትምህርቷን በስኬት ስታጠናቅቅ ሁሉም ተማሪ የመመረቂያ ጽሑፍ እንደሚያዘጋጀው ሁሉ እሷም በሕክምና ዘርፍ በገጠማት ችግር ላይ በማተኮር መፍትሔ እንድትፈልግለት የጥናት አማካሪዋ አስተያየት ይሰጣታል። የጥናቷ መነሻም ሆስፒታል ላይ ብዙ ጊዜ ሕክምና ሲሰጡ የሚታዩት ወንዶች መሆናቸውና ከዶክተሮቹ አጠገብ ድጋፍ የሚሰጡት ነርሶች፤ ረዳትና መሰል የሙያ ዘርፎች ላይ የሚሠሩት አብዛኛዎቹ ሴቶች ናቸው፡፡

ስለዚህም ይህ ለምን ሆነ ስትል ጉዳዩን ለማጤን አሰበች። ሴቶች ብዙ ጊዜ በቤተሰብ ደረጃ ከፍተኛ የኃላፊነት ድርሻ አላቸው። በመሆኑም ልጆቻቸው ሲታመሙ ወይም አንድ ነገር ሲፈጠር ቀድመው ቤት የሚደርሱ ሴቶች ስለሆኑ ሥራቸውን ትተው የማስታመም ሥራ እንደሚሠሩ መገንዘቧን ትናገራለች።

ኬነሳ ሁነቱ በወቅቱ ሴቶች ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው አንዱ ምክንያት የቤተሰብ ኃላፊነት ስላለባቸውና ለመመራመር ጊዜ እንደሚያንሳቸው የጥናቷ መነሻ ሆነ። ቤት ሆኖ ሥራን መሥራት ለምን አልተቻለም በማለት ራሷን መጠየቅ የጀመረችው የኮቪድ 19 ከመከሰቱ ቀደም ብሎ የነበረ ሲሆን ጥናታዊ ጽሑፏ እንደተጠናቀቀ አማካሪዋ ሀሳቡን አደራጅታ ብትሸጠው ስኬታማ እንደሚያደርጋት አሰተያየት ሰጧት። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከአባቷ ሦስት ሺ ዩሮ በመበደር አጎልብታ ከአንድ ሚሊዮን ዩሮ በላይ መሸጡን ትናገራለች።

ጥናቱን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ ለአማካሪዋ ባስረከበችበት ወቅት ለምን ይህን አደራጅተሽ ወደ ቢዝነስ አትለውጭውም የሚል ምክረ ሀሳብም በተጨማሪ ቀረበላት። እሷም ጥናቷን አደራጅታ ወደ ቢዝነስ ገባች። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ለኢንሹራንስ ድርጅት በመሸጥ ትርፋማ መሆን ችላለች።

ይህን ጥናት ስታደርግ ኬነሳ ዕድሜዋ 20 ነበር። በወቅቱ ከትምህርት ውጭ ምንም ዓይነት ሥራ አልነበራትም። ስለዚህም በእጇ ያላትን ጥናት በመጠቀም ሥራ መፍጠር ችላለች፡፡

ኬነሳ እንደምትለውም ‹‹አቅምን መጠቀም፤ ችግርን ወደ ዕድል መቀየር እና አስተሳሰብ ጭምር ማስተካከል ያስፈልጋል። ስለዚህ የቢዝነስ ሰው መሆን ማለት ችግር ሲያጋጥም ችግሩን በጥናት ወደ ገንዘብ መቀየር እንደሚቻል ራስን ማሳመን ይጠይቃል ትላለች፡፡

ሀሳቡ በስልክ በርካታ ታካሚዎችን የማማከር እና የመደገፍ ሥራ የሚሠራበት ቴክኖሎጂ ነው። የጤና እክል ያለበትን ሰው በአካል ማግኘት ሳያስፈልግ በስልክ በመስማት ሕመሙን መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው። ስለዚህ የሕክምና ሥራ ቤት ላይ ሆኖ መሠራት እንደሚቻል አፕሊኬሽኑ ወደ ቤት ስልክ ወይም ወደ ስማርት ስልክ በማገናኘት ‹‹redirect›› በማድረግ ቤት ቁጭ ብሎ በኮምፒውተር ሲስተም ውስጥ መግባት ነው።

ይህ ሲወራ ቀላል ወይም ቀልድ ይመስላል። ነገር ግን ሥራው ከስልክ ውጭ የሆስፒታሎች የኮምፒውተር ሲስተም ለሁሉም ሰው ተደራሽ አይደረግም። ይህ ለጥናቷ እና አሁን መሠረት ለሆናት ሥራ ፈተና ነበር። ፈተናው ባታልፍ አሁን ለደረሰችበት ቦታ እንደማትበቃ እና ጥናቱን ወደ ውጤት ለመቀየር ብዙ ፈተና ይገጥማት ነበር። መጨረሻ ግን ችግሩን መፍታት መቻሏን ትናገራለች።

የሥራ ፈጠራው ዓለም ለእሷ አዲስ ነበር። ወደ ተግባር በለወጠችው ሥራ የፍቅር ጓደኛዋን የዛሬው የሁለት ልጆቿ አባት የሆነውን ባለቤቷን የተዋወቀችበት ስለነበር ከራሷ ጥንካሬ ባሻገር ወላጅ አባቷና ባለቤቷ በሀሳብ እና በምክር ውጤታማ እንድትሆን አድርገውኛል ስትል ትናገራለች።

‹‹አንድ ችግር ካገኘሁ በችግሩ ላይ ጥናት በማድረግ መፍትሔ እንዲኖረው እና ብዙዎች ወደ ቢዝነስ እንዲገቡ እፈልጋለሁ። ስለዚህ እኔ ራሴ ለአንድ ነገር መነሻ (founder) መሆን እና ለችግሮች መፍትሔ ፈልጎ ወደ ሥራ ማስገባት ለእኔ ሙያዊ ሥራ ነው። እኔ የተረዳሁት ብዙ ሰው ገንዘብ አለው ነገር ግን ሀሳብ የለውም። ስለዚህ ሃሳቤን ብር ይዘው ሃሳብ ለሌላቸው በመሸጥ ሥራ ላይ በሰፊው እየሠራሁበት ነው›› ስትል ገልጻለች።

ለምሳሌ ብዙ ሰው የልብስ ብራንድ ሥራ መጀመር ይፈልጋል። ምን ዓይነት የሚለው የማርኬቲንግ ሥራው ግን ሲከብዳቸው ይስተዋላል። ስለዚህ በዚህ ላይ ያለውን ክፍተት በጥናት በመለየት የሥራ መንገዱን በማሳየት ውጤታማ ለመሆን እንደምትጥር ትናገራለች። የጃኬት፤ የሸሚዝ እና መሰል ልብሶች ብራንድ በመሥራትና በመሸጥ ብዙ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውናለች።

ፓኪስታን ውስጥ ከ30 በላይ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች የብራንድ ልብስ ፋብሪካ አላት። አውሮፓ፣ አሜሪካ፤ ዱባይ ለሚገኙ የልብስ ብራንዶች እያመረተች እያከፋፈለች ነው። እስካሁን አምስት የሚደርሱ ችግር ፈቺ ጥናቶችንም ሠርታ ወደ ቢዝነስ ለውጣለች፡፡

ኔዘርላንድ ውስጥ የአሜሪካ እግር ኳስ ልብስ ብራንድ በመሥራት መሸጧን የምትናገረው ኬነሳ፤ በቴክኖሎጂው መስክ ኤአይ ውስጥ ወደ ኢንቨስትመት ገብታለች። በትውልድ ሀገሯ ኢትዮጵያ ብዙ የቢዝነስ ዕድሎች አሉ የምትለው ወጣቷ፤ በቀጣይ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ኢንቨስት ለማድረግ ካቀደችው መካከል የሪል ስቴት ዘርፍ አንዱ ነው። ይህ ዘርፍ የብዙ ዜጎች ችግር ሆኖ አይቸዋለሁ። በተመጣጣኝ ዋጋ ለዜጎች ቤት ማቅረብ ቀጣይ እቅዷ ነው። በተጨማሪም በኦንላይን ለሥራ ፈጣሪ ዜጎች ተሞክሮና አጫጭር የግንዛቤ ፈጠራ ሥልጠና እንደምትሰጥ ገልጻለች።

ብዙ ሰው የሥራ ዕድል ይፈልጋል፤ ነገር ግን በዚህ በሠለጠነ እና ቴክኖሎጂ በዘመነበት ወቅት ችግር ለመፍታት አይጥሩም። ያለ ጥረት ደግሞ የሥራ ዕድል አይገኝም። በር ካላንኳኩ አይከፈትም፤ ሥራም ሳይፈልጉት አንኳኩቶ አይመጣም። ብዙ ጊዜ ለሥራ ፈላጊ ችግሩ ራሱን ለሥራ ጥረት አለማዘጋጀት ነው። ስለዚህ የሰው አስተሳሰብ እንዲለወጥ የቻለችውን ሁሉ ለትውልድ ሀገሯ እንደምትሰጥ እቅድ ይዛ እየሠራች መሆኑን ጠቅሳች።

የቢዝነስ ሥራዋን አሐዱ ብላ የጀመረችውም እ.ኤ.አ በ2021 የተለያዩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሀሳብ በማፍለቅ ነው። በሥልጠና ወቅት ‹‹ኢተርንሽፕ›› በወጣችበት ሆስፒታል በተመለከተችው ችግር ላይ የሠራችው ጥናታዊ ጽሑፍን በመሸጥ ዛሬ ላይ ለደረሰችበት ስኬት በቅታለች። በአሁኑ ወቅት ከ10 በላይ ሀገራት የሚሸጥ “ሙሉ” የተሰኘ ብራንድ ልብስ (የፋሽን መለያ) ድርጅት ባለቤት ናት።

የእሷ የሥራ ካፒታል በዋናነት ገንዘቡ እንዳ ልሆነ የጠቀሰችው ኬነሳ፤ ካፒታሏ በየጊዜው የምትፈጥረው አዳዲስ ሀሳብና መፍትሔ ነው። አሁን ላይ 190 ሚሊዮን ዶላር የሥራ ካፒታሏ ገብቷል።

‹‹እኔ የጨዋታ ታሪክ የለኝም፤ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ስትሆን ዓድዋ በታሪክ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው። ስለዚህ ዓድዋን ታሪኩን መሠረት ያደረገ ትምህርት ሰጭ የሚሆን ጌም (ጨዋታ) አፕ እየሠራሁ ነው፡፡›› የምትለው ኬኒሳ በአውሮፓውያን ጨዋታ ወይም ጌም ጊዜያችን ስናጠፋ ኢትዮጵያውያን እንደ ኢትዮጵያዊ ብሎም እንደ አፍሪካዊ የራሳችን የሆነ ጨዋታ አለመኖሩ እንደሚያስቆጫት ትናገራለች።

ስለሆነም ጥናት ስታደርግ ፊሊፒንስ ሀገር ውስጥ በ4 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የኪሪብቶ ጨዋታ መኖሩን ተገነዘበች። እንዴት ይህን ያህል ገንዘብ ሊሠራ ቻለ የሚል ጥያቄ በማጫር የዳሰሳ ጥናት ባደረገችበት ወቅት የጨዋታው ይዘት በሀገሪቱ ላይ መሠረት ያደረገ ነው። እየተጫወቱ ገቢም ያገኙበታል። ስለዚህ እሷም ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ኩራት በሆነው ዓድዋ ድል ስም ጨዋታ ለምን አይሠራም በሚል እሳቤ ጨዋታውን ለመተግበር እየሠራች መሆኗን ተናግራለች።

ችግሩንና መፍትሔው በማበጀት ዓድዋ የተሰኘ ጨዋታ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ማክበሪያ ዕለት ይፋ እንደሚደረግ የጠቀሰችው ኬነሳ፤ ሁሉም ጨዋታ የጨዋታ ታሪክን ይፈልጋል። ጨዋታው በጦርነቱ ወታደሮች የሚመገቡት ሬሽን፤ በዓድዋ ጦርነት የነበረው አለባበስ የትግል ስልት የተላበሰ ጨዋታ ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑን ትናገራለች።

ዋና ሀሳቡ አዲስ የኢኮኖሚ ስልት ለአፍሪካ ማስተዋወቅ ነው። ከተዋወቀ በኋላ በሚሰጠው ምክረ ሀሳብ እየተጫወቱ ገቢ የሚያገኙበት ይሆናል። ጨዋታው የኢትዮጵያ ምርት እንዲባል የምትፈልገው ለመላው አፍሪካና በኋላም ዓለም ላይ እንዲተዋወቅ ነው። ስለዚህ ለሥራ ብቻ ሳይሆን ለአዲሱ ትውልድ ‹‹ጌም ፈጣሪዎች ዲቬሎፐርስ›› በሚል ሥራ የመፍጠር ዓላማ አላት። ይህም የራሳቸውን ድርጅት እንዲያደራጁበት እና እንዲያድጉ የሚያደርግ ነው ስትል አስረድታለች።

ስኬታማ ለመሆን ዋናው እና ቁልፉ ምስጢር አቅምን ማየትና መለወጥ እንደሚቻል ለራስ መንገር ነው። የሰውን ችግር መገንዘብና መፍትሔ መፈለግ የራስም ችግር ቢሆን ምንድነው የጎደለኝ ብሎ ማየት ከዛም መፍትሔ መፈለግና ችግሩን መፍታት ነው። እንዴት ትርፋማ መሆን እችላለሁ፤ በምን መልኩ ለገበያ ባቀርብ ገቢ ያስገኛል፤ ደንበኛ ይስባል፤ የሚለው ሁልጊዜም ራሷን የምትጠይቀው ጥያቄ ነው። ስለዚህ ችግርን ወደ ውጭ ማውራት ብቻ ሳይሆን መፍትሔ በመፈለግ ያን መፍትሔ ለሰው ለመሸጥ መጣር ነው።

በ‹‹ማይንድሴት›› ሲታይ ደግሞ ‹‹እኔ ሁልጊዜም የራሴን ስሜት እከተላለሁ። ሰውን ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ሰውን መምከር ጥሩ ነገር ነው። ግን ምክሩ ለእኔ ወይም ለእናንተ ይሠራል ማለት አይደለም። የሰው ምክር ‹‹ጋይድላይን›› ሊሆን ይችላል። ግን መፍትሔ ነው ማለት አይደለም። ስለዚህ የራሴን ስሜት አዳምጣለሁ አንድ ነገር ለማድረግ ደስ የሚል ስሜት ከፈጠረብኝ ወደ ተግባር እለውጠዋለሁ። እናም ሁልጊዜም ከራሴ ጋር መክሬ ደስ ካላለኝ አላደርገውም። ሰው ምን አለኝ የሚል ነገር መኖር የለበትም። ግልፅ የሆነ ቢዝነስ የሚያዋጣ ነገር ከሌለው ወይም ደስ ካላለኝ ጊዜዬንም አላባክንም፤ አላደርገውም። ለዚህም ነው ከሜዲካል ዓለም ወደ ቢዝነሱ ዓለም ያሻገረኝ›› ስትል ተሞክሮዋን ገልጻለች፡፡

ፈተና የማያጋጥመኝ ጊዜ የለም፤ ዓለም በፈተና የሞላች ናት። ነገር ግን ፈተናውን የመሻገሪያ ጥበብ ማፍለቅ ያስፈልጋል። ለእኔ የሕክምናው ዘርፍ በጣም ትልቅ ዓለም ነው። ከፈረንጆች ጋር መሥራት በጣም ያስፈራኝ ነበር። ምክንያቱም በእኛ ባሕል ፈረንጆች ከእኛ አልቀን እናያቸዋለን። ሥራ ስትጀመር ራሷን የምታየው ከፈረንጆች በታች ነው። ስለዚህ ራስን ማመን እና ዝቅ አለማድረግ ማንም ከማንም ጋር የበታች ሳይሆን እኩል እንደሆነ መገንዘብና መረዳት እንደሚያስፈልግ ምክር ትሰጣለች፡፡

ጥናት ስትሠራ ብዙ መረጃን በነፃ እንዳገኘች የገለጸችው ወጣቷ፤ ሰዎቹ ታሳዝናላች ምንም አታውቅም ብለው እሷን ዋጋ እንደሌላት አደረጓት። ግን እሷ አልተናደደችም። ይልቁንም መረጃዎችን ለመሰብሰብ ተጠቅማባቸዋለች፡፡

ሁሉን ነገር እንደማታውቅ በመምሰል የበለጠ መረጃ መሰብሰቧ ለአሁኑ ደረጃ እንድትደርስ ትልቅ ግብዓት ሆኗታል። እናም ማንም ዝቅ ሲያደርግ ማቀርቀር ሳይሆን ብልህ በመሆን ወደ ዕድል መቀየር ያስፈልጋል።

ከአምስት ዓመት በኋላ አውሮፓ ያለውን እውቀት ይዛ ኑሮዋን በትውልድ ሀገሯ ኢትዮጵያ ማድረግ ምኞቷ እንደሆነ የጠቀሰችው ኬነሳ፤ የምትፈልገው የራሷ የሪልስቴት ልማት ካምፓኒ በመጀመር አውሮፓ ያየችውና የለመደችው ጥራቱን የጠበቀ ምቹ የመኖሪያ ከባቢን መፍጠር ምኞቷ መሆኑን አስረድታለች።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You