ዩክሬን እዳዋን በማዕድን ክፍያ የማወራረድ ፍላጎት እንዳላት ተገለጸ

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በነገው እለት ወደዋሽንግተን በማቅናት አሜሪካ ዩኩሬን ላይ አለኝ የምትለውን የገንዘብ እዳ በማዕድን ክፍያ ለማወራረድ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ይመካራሉ እየተባለ ነው።

ዘለንስኪ ወደ አሜሪካ በመሄድ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የሚመክሩት ያለባቸውን የአሜሪካ እዳ የሀገራቸውን ማዕድን ለማጋራት እንደሆነ የትራምፕ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ዘለንስኪ ስምምነቱን በመታከክ አሜሪካ ከአዲስ የተቀናጀ የሩሲያ ጥቃት እንደምትከላከላቸው ማስተማመኛ እንደሚፈልጉ ማሳሰባቸውም ታውቋል። ሆኖም ግን ዩናይትድ ስቴት ምንም አይነት ማስተማመኛ እንደማታቀርብ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የገለጹ ሲሆን የማስተማመኛ ኃላፊነቱን የሚወስዱት የአውሮፓ ሀገራት እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አባል ለመሆን እያሳየችው ያለው ፍላጎት የማይታሰብ ነው ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ የዘለንስኪን የረጅም ጊዜ ምኞት አጣጥለዋል። ረቡዕ እለት በካቢኒያቸው ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ፤ አሜሪካውያን ማዕድን አውጪዎች በዩክሬን ተገኝተው ውድ የሚባሉ የመሬት ውስጥ ማዕድናትን እንደሚያወጡ ተናግረው፤ ይህም ለዩክሬን ትልቅ ደህንነትን ያጎናጽፋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

ትራምፕ አክለውም ኪየቭ ኔቶን ለመቀላቀል የጀመረችውን ሃሳብ መርሳት አለባት ብለዋል፤ ይህ ጉዳይ ለሩሲያ ጦርነት መጀመር ምክንያት ነው በማለት የሞስኮን አቋም አንጸባርቀዋል። ትራምፕ በንግግራቸው በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ለሶስት ዓመታት የሰነበተው ጦርነት በተኩስ አቁም ስምምነት ሊገታ መቃረቡን ጠቁመው ‹‹የንጹሀን መገደል እንዲቆም ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጋር ስምምነት እንፈጽማለን›› ማለታቸው ታውቋል፡፡

የትራምፕን ንግግር ተከትሎ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ‹‹የዩክሬን ደህንነት የሚረጋገጥበት ማስተማመኛ ከሌለ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዋስትና አይሰጠንም ስለሆነም አናደርግም›› የሚል አቋማቸውን መግለጻቸው ታውቋል። ‹‹በኔቶ በኩል አሊያም በተመሳሳይ መንገድ መፍትሄ መፈጠር አለበት›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ዩክሬን ኔቶን ልትቀላቀል ይገባል የሚለውን ሀሳብ አጥብቃ የምትቃወመው ሩሲያ ይህ ከሆነ የኔቶ ኃይሎች ወደ ድንበሬ ይቀርባሉ የሚል ስጋቷን ገልጻለች። የጦር ቃልኪዳኑ በአውሮፓውያኑ 2008 ዩክሬን ኔቶን ልትቀላቀል ትችላለች ማለቱ አይዘነጋም። ትራምፕ የአውሮፓ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በዩክሬን ይሰፍራሉ የሚል ጥቆማ መስጠታቸውን ተከትሎ ሩሲያ ይሄን እንደማትቀበለው ማስታወቋ ተገልጿል፡፡

አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በምታደርገው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የአውሮፓ ተወካዮች አለመኖራቸው አውሮፓውያኑን ያስቆጣ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ ጉዳይ ላይ ሃሳብ ያጋሩት የአውሮፓ የውጪ ጉዳይ ከፍተኛ ልዑክ ካጃ ካላስ ‹‹በአውሮፓ ምድር ለሚፈጸም ለየትኛውም ስምምነት አውሮፓውያን ሊሳተፉ ይገባል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አክለውም ‹‹ዩክሬን ማዕድኗን በተመለከተ የምታደርገው ውል የግሏ ቢሆንም የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ አውሮፓውያንን ማካተት አለበት›› ብለዋል። በተያያዥ ጉዳይ ላይ ቃላቸውን እንዲሰጡ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ረቡዕ እለት ቀጠሮ የነበራቸው ካጃ ካላስ በጊዜ መጣበብ ምክንያት ውይይቱ መሰረዙ ታውቋል።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ላይ በዋሽንግተን የሚያደርጉት የማዕድን ስምምነት ውል ከትራምፕ ጋር በሚኖራቸው ውይይት ላይ የሚመሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል። የማዕድን ውል የሚለውን ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረቡት የዩክሬኑ መሪ ዘለንስኪ ሲሆኑ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ለማስቀጠል የታሰበ እቅድ መሆኑ ታውቋል፡፡

ላለፉት ሶስት ዓመታት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በህይወት እና በንብረት ላይ በርካታ ኪሳራን በማድረስ ዛሬም ድረስ ስጋት መሆኑ እንደቀጠለ ሲሆን አሜሪካ በአዲሱ ፕሬዚዳንቷ ትራምፕ በኩል ጦርነቱን ለማስቆም ከሩሲያ ጋር ሰላም ተኮር እንቅስቃሴን በማድረግ እየመከረች እንደሆነ ይታወቃል። የመረጃ ምንጫችን ቢቢሲ ነው።

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You