የዓባይ ልጆች

ዓባይ የሚለው የአማርኛ ቃል አባት ማለትም የወንዞች ሁሉ አባት ከሚለው የመጣ መሆኑን የተለያዩ መዝገበ ቃላት ያትታሉ። አለፍ ሲል በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 2፤ ቁጥር 13 ላይ ወንዙ ፈለገ- ግዮን በሚልም ይጠራል። ይህ የሚያመላክተው ወንዙ ያለውን ግዝፈት እና ኢትዮጵያ በተነሳች ቁጥር አብሮ የሚነሳ ታላቅ ወንዝ መሆኑን ነው፡፡

የዓባይ ተፋሰስ የአፍሪካን አንድ አስረኛ ግዛት የሚሸፍን ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያዩ የአየር ፀባዮችን ያስተናግዳል። በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ የኢኳቶሪያል አየር ንብረት፣ ከምሥራቅ አፍሪካ የታችኛው ክፍል ሲነሳ የትሮፒካል፣ ከዚያም ነፋሻማውን የኢትዮጵያ ከፍታ አምባ አቋርጦ በረሃማና ምድረበዳማ በሆነው የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ክልል ዘልቆ ሜዲትራኒያን ባሕር በመግባት ጉዞውን ያከትማል። በዚህ ረዥም የጉዞ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ደቡብ ሱዳን ዓባይ አቋርጦ የሚያልፍባቸው ሀገራት ናቸው።

ኢትዮጵያ የዓባይ ንዑሰ ተፋሰስ የሆነው ጥቁር ዓባይ ምንጭ ነች። እስከ 86 በመቶ የሚደርሰውም የናይል ወንዝ ውሃ የሚመነጨውም ከዚችው ሀገር ነው። ይህ የውሃ ድርሻዋም እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ ባለሙሉ መብትና ባለብዙ ተፅዕኖ አሳራፊ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡

ሆኖም በተዛቡ ዕሳቤዎች እና በተለይም የቅኝ ግዛት ውሎችን መሠረት ተደርጎ በተፈጠሩ ኢ-ፍትሐዊ አካሄዶች ኢትዮጵያ 86 በመቶ ድርሻ ካላት ዓባይ ውሃ እንዳትጠቀም ማዕቀብ ተደርጎባት ዘመናትን የበይ ተመልካች ሆና ኖራለች፡፡

በዓለም ላይ ወደ 276 የሚጠጉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አሉ። እነዚህን ወንዞች 145 የሚሆኑ ሀገራት ይጋራሉ። አንዳንድ ሀገራት ወንዞቹን የሚመለከት ሕግ አላቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የጋራ የውሃ አጠቃቀም ሕግ የላቸውም። ነገር ግን ሕጉ ያላቸው ሀገራት ውሃን ዘላቂና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ።

ወደ እኛ ጉዳይ ስንመጣ ግን በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ በርካታ መሰናክሎች እና እልህ አስጨራሽ ክርክሮች ሲደረጉበት ቆይቷል። ኢትዮጵያ ከ86 በመቶ በላይ የናይል ወንዝ ምንጭ ብትሆንም በቅኝ ግዛት ውሎች የተነሳ መብቷ ለዘመናት ተጥሶ ኖሯል፡፡ከ86 በመቶ በላይ የውሃ ባለቤት እየሆነች 1 በመቶ እንኳን የመጠቀም መብት አልነበራትም።

ግብፅ እና ሱዳን የ1929 እና የ1959 የቅኝ ግዛት ውሎችን ምክንያት በማድረግ ከቀሪዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል። ግብፅና ሱዳን የፈረሙት የቅኝ ግዛት ውሎች የዓባይን ውሃ ሀብት ከአሥር የተፋሰሱ ተጋሪ ሀገሮች ለሁለቱ ብቻ የሚያከፋፍል በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ ስምምነት ሆኖ ሌሎቹን ተጋሪ ሀገሮች ለማስገደድ እንደማይችል የሕግ ሊቃውንቱ እና ፀሐፍት ሲወተውቱ ኖረዋል። ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሁሉም ዘንድ የሚነሳ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር ተከታታይነት ያላቸውን ድርድሮች በማድረግና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ አካሄድን በመከተል ዛሬ ላይ ደርሳለች። እግረ መንገዷንም የህዳሴ ግድብ ግንባታን ወደ ማገባደዱ በማድረስ መጪውን ብሩህ ተስፋ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። በተለይም የናይል የትብብር ማሕቀፍ ወደ ኮሚሽን ደረጃ መሸጋገሩ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ መስሎ የቆየው ውዝግብ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በእኔነት ስሜት እንዲሟገቱበት እና እንዲከራከሩበት ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡

አንዱ ሕጋዊ ማሕቀፍ ሆኖ በቀጣይ የናይልን የውሃ አጠቃቀም ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጠው የናይል የትብብር ማሕቀፍ ነው፡፡

የናይል የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት የዓባይን ውሃ በጋራ፣ በእኩልነትና ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ ውሃውን መጠቀምና አብሮ መንከባከብ የሚያካትትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚተዳደሩባቸውን መርሆዎችን ጭምር ያካተተ ማሕቀፍ  ነው። ይህም በአሥራ አንድ ሀገራት መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው።

ጉዳዩን የኢትዮጵያ መንግሥት የቅርብ ክትትል ያደረገበት በመሆኑ የተሳካ እየሆነ መጥቷል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን በሚያገኙበት አጋጣሚ የውሃ ሀብትን በጋራ ማልማትና መጠቀም የሚቻልባቸውን መንገዶች ያነሳሉ። ይህም የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ ሥራ ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ ቀድማ ማሕቀፉን ያፀደቀች ሲሆን፤ ከዛ በኋላ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ ገብተውበት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ የመጣውም በጋራ ለመልማት ካለ ፍላጎት አንፃር ነው። በቅርቡ ደግሞ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን በምክር ቤቶቻቸው አፅድቀውታል።

ይህ መሆኑ ደግሞ ለዘመናት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የላይኛው ተፋስስ ሀገሮች ከውሃው በፍትሐዊነት የመጠቀም መብታቸውን ከማረጋገጡም ባሻገር ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ስታደርገው የነበረውን ፍጥጫ ሌሎች ሀገራት እንዲቀላቀሉና ክርክሮችንም የሚያካሂዱት ሀገራት ሳይሆኑ ኮሚሽኑ እንዲሆን ያስችላል። ይህ ማለት ጉዳዩ የኢትዮጵያ እና የግብፅ ብቻ ሳይሆን የ11ዱም ሀገራት ጉዳይ እንዲሆን ያስገድዳል። በአጠቃላይ የናይል ትብብር ማሕቀፍ ወደ ኮሚሽን ማደጉ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይዞ ይመጣል፡፡

የመጀመሪያው እና ዋናው ነገር የናይልን ውሃ በትብብር ለመጠቀምና ለማልማት ያስችላል። በቅኝ ግዛት ውሎች ውሃውን ከመጠቀም ተገለው ነበሩ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ውሃውን በፍትሐዊነት የመጠቀም መብት ይጎናጸፋሉ፡፡

የናይል የትብብር ማሕቀፍ ወደ ኮሚሽን ደረጃ ማደጉ በአጠቃላይ በተፋሰሱ ሀገራት ዘንድ የሚታየውን አለመግባባት እና ውዝግብ የሚያረግብ ይሆናል። በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም የማይተካ ሚና አለው፡፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ሀገር ነች። የሕዝብ ቁጥሯም በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ የያዘ እና በቀጣይም እያደገ የሚሄድ ነው። ስለዚህም የዚህን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት መጠነ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ያስፈልጋታል። ይህንን ለማሳካት ደግሞ በዋነኝነት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እና የባሕር በር ጥያቄዎቿ ሊመለሱላት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይል እጥረት የሚሰቃይ ሕዝብ ነው። 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኝም። አብዛኞቹ ፋብሪካዎች በኃይል እጥረት ምክንያት በተገቢው መጠን ለማምረት የሚቸገሩ ናቸው፡፡

ስለዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ የኃይል ፍላጎቷን ማሟላት ለነገ የማትለው ጥያቄ ነው። ይህን መሠረት በማድረግም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ዛሬ ላይ ወደ ማጠናቀቁ ደርሳለች። እስካሁንም ባለው ሁኔታ አራት ተርባይኖች ወደ ኃይል ማምረት የገቡ ሲሆን ቀሪ ሥራዎችም በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ባመነጨበት ቅጽበትም ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አልፎ ለጎረቤት ኬንያ እና ሱዳን ጭምር የኃይል አማራጭ መሆን ችሏል። በጎረቤት ሀገራትም ዘንድ የትብብር እና የወዳጅነት ማህተም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ሆኖም ይህ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል። በተለይም በውሃው ላይ የቅኝ ግዛት ውሎችን ጭምር በማንሳት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ ሀገራት ግንባታውን ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። በሀገር ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ቅጥረኞችን ከማሰማራት አንስቶ በፀጥታው ምክር ቤት ጭምር በርካታ ጫናዎች ተደርገውበታል፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የያዙት ፍትሐዊ የመልማት ጥያቄ በመሆኑ ልማቱን ለማስተጓጎል የቻለ አንዳችም ኃይል የለም፡፡

ስለዚህም ለቀጣናው ሀገራትም ሆነ ቀጣናውን ተሻግረው ለሚመጡ የተፋሰሱ ሀገራት የሚበጀው በጋራ ተባብሮ የዓባይን ውሃ መጠቀም እና አብሮ ማደግ ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ የውሃ ግዛትን ውሎች እየጠቀሱ ኢ-ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማንገሥ መሞከር ጊዜው ያለፈበት ዕሳቤ ነው፡፡

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You