የሉሲዎቹ ያልተጠበቀ ውጤት ቅልበሳ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ሞሮኮ በ2026 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመቶ ሰማንያ ደቂቃ ፍልሚያ ብቻ ቀርቷቸዋል።

በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ከዩጋንዳ ጋር የተደለደሉት ሉሲዎቹ ከቀናት በፊት ወደ ካምፓላ አቅንተው ሁለት ለምንም መሸነፋቸው ይታወሳል። በሀምዝ ስታድየም በተካሄደው ጨዋታ ሉሲዎቹ ከሜዳቸው ውጪ ጥሩ ተፎካክረው ሙሉውን የጨዋታ ጊዜ ግብ ሳያስተናግዱ ቢያጠናቅቁም በተጨማሪ ደቂቃዎች ሁለት ግብ ማስተናገዳቸው ብዙዎችን ያስቆጨ ነበር። ይሁን እንጂ ከጨዋታው በኋላ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድና አምበሏ ሎዛ አበራ በመልሱ ጨዋታ በሜዳቸው ውጤቱን ቀልብሰው እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ሆነው ነበር መግለጫ ሲሰጡ የነበረው።

የአሠልጣኙና የአምበሏ ሎዛ አበራ በራስ መተማመን ከአስር በላይ በውጪ ሀገራት የሚጫወቱ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን የያዘችው ዩጋንዳን በማሸነፍ እውን ይሆናል ብለው ብዙዎች ጥርጣሬ ነበራቸው። ያም ሆኖ ሉሲዎቹ ቃላቸውን አክብረው ከሜዳቸው ውጪ የገጠማቸውን ሽንፈት በሜዳቸው ቀልብሰው ቀጣዩና የመጨረሻውን ዙር ማጣሪያ መቀላቀል ችለዋል።

ትናንት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም በተካሄደው የሉሲዎቹና የዩጋንዳ የመልስ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ሳይቆጠር ነበር የተጠናቀቀው። በሁለተኛው የጨዋታ ጊዜ ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱም የዩጋንዳ አሸናፊነት ይበልጥ እያደገ በሄደበት ወቅት 65ኛ ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከርቀት ያስቆጠረችው ድንቅ ግብ ሉሲዎቹን ወደ ተስፋ መልሷል። በቀሪዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ሉሲዎቹ የዩጋንዳን መረብ ለማግኘት ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ወደ ግብ ሳይቀየር መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተገባዷል። በተጨማሪ ሰዓት ሉሲዎቹ ያገኙትን ቅጣት ምት እፀገነት ግርማ በአግባቡ ተጠቅማ ያስቆጠረችው ግብ ግን ሉሲዎቹን በድምር ውጤት ወደ አቻነት መመለስ ችሏል።

የሁለቱ ቡድኖች የደርሶ መልስ ጨዋታ 2ለ2 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አሸናፊውን ለመለየት በቀጥታ ወደ መለያ ምት ማምራት የግድ ሆኗል። በተለይም ለኢትዮጵያውያን አስጨናቂ በነበረው የመለያ ምት በመጨረሻም በሉሲዎቹ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና አስደናቂ ብቃት በድል ተደምድሟል። በዚህም ሉሲዎቹ 5ለ4 በሆነ የመለያ ምት ውጤት አሸንፈው ቀጣዩንና የመጨረሻውን የማጣሪያ ዙር ለመቀላቀል በቅተዋል። በቀጣይ ዙር የታንዛንያና ኢኳቶርያል ጊኒን አሸናፊ የሚገጥሙ ይሆናል።

የሉሲዎቹ ድል ለአንጋፋዎቹ የብሔራዊ ቡድኑ ኮከቦች ብርቱካን ገብረክርስቶስና ረሒማ ዘርጋው በጨዋታው በክብር ሲሸኙ ድምቀት ሆኗል። በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከ1995 እስከ 2017 የተጫወተችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ እንዲሁም ከ1999 እስከ 2014 የተጫወተችው ረሒማ ዘርጋው በቅርቡ ራሳቸውን ከብሔራዊ ቡድን ማግለላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሉሲዎቹ ትናንት ከዩጋንዳ ጋር እየተጫወቱ በነበረበት ወቅት በዕረፍት ሰዓት ላይ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ከበርካታ የስፖርቱ ቤተሰቦች እንዲሁም ተጫዋቾች የማስታወሻ ስጦታዎች ተበርክቶላቸው በክብር ተሸኝተዋል።

ሉሲዎቹ በቀጣዩ ዙር ማጣሪያ ከታንዛንያና ኢኳቶርያል ጊኒ አሸናፊ አንዱን ገጥመው በመቶ ሰማንያ ደቂቃ ፍልሚያ ማሸነፍ ከቻሉ ከአስራ ሦስት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚመለሱ ይሆናል። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው እኤአ በ2002 ሲሆን በዚያ ተሳትፎው ከምድብ ጨዋታ ማለፍ አልቻለም ነበር። በቀጣዩ 2004 የአፍሪካ ዋንጫ ግን 4ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በታሪኩ ዛሬም ድረስ ትልቅ የሆነውን ውጤት አስመዝግቧል። የመጨረሻ ተሳትፎው ደግሞ እኤአ 2012 ላይ ሲሆን በዚያ ተሳትፎም ከምድብ ጨዋታ መሻገር እንዳልቻለ ይታወሳል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You