አሜሪካና ዩክሬን በውድ ማዕድናት ዙሪያ ስምምነት ላይ ደረሱ

አሜሪካና ዩክሬን በውድ ማዕድናት ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ። አሜሪካና ዩክሬን በረቂቅ የውድ ማዕድናት ስምምነት ላይ መስማማታቸውንና ይህም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦርነቱን በፍጥነት ለማስቆም ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት ኪዬቭ የዋሽንግተንን ድጋፍ እንድታገኝ እንደሚያስችላት ተገልጿል።

ረቂቅ ስምምነቱ የአሜሪካን የደኅንነት ዋስትና ወይም ቀጣይነት ያለው የመሣሪያ አቅርቦት ጉዳይን በግልጽ አለመጥቀሱንና ነገር ግን አሜሪካ ዩክሬን “ነፃ፣ ሉዓላዊ፣ ደኅንነቷ የተጠበቀ እንዲሆን ትፈልጋለች” የሚል ይዘት ማካተቱን ሮይተርስ ዘግቧል። ዋሽንግተንና ኪዬቭ ወደፊት ሊኖር በሚችል የመሣሪያ አቅርቦት ጉዳይ እየተወያዩ መሆናቸውን ሮይተርስ ስምምነቱን በቅርብ የሚያውቅ አንድ ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ በቀጣይ ዓርብ “ትልቅ ስምምነት” ለመፈረም ወደ ዋሽንግተን እንደሚመጡ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ይህ የሆነው ሁለቱ መሪዎች ኃይለ ቃል ከተቀያየሩ በኋላ ነው። ስምምነቱን አሜሪካ ለዩክሬን ላደረገችው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ እንደክፍያ የሚያዩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ በዩክሬን የሰላም አስከባሪ ኃይል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በዩክሬን ላይ ዘመቻ የከፈተችው ሩሲያ ምንም የኔቶ ኃይል እንዲሠማራ አትፈልግም። የተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት ወደ ዩክሬን ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ሰኞ ሞስኮ ይህን እንደምትቀበል ቢገልጹም፣ ክሬምሊን ማክሰኞ እለት አስተባብሏል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦርነት በፍጥነት የማስቆም ፍላጎትና ለሞስኮ በጎ የሆነ አዝማሚያ ማሳየት ዩክሬንንና አውሮፓውያንን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል። ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት ዘለንስኪን የማይወደድ “አምባገነን” ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን ዘለንስኪ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተሳሳቱ መረጃዎች ተከበዋል የሚል ምላሽ ሰጥተው እንደነበር አል ዐይን ዘግቧል፡፡

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You