‹‹በተስፋ መራመድ ፍርሃትን ያስወግዳል፤ በጊዜ መጠቀምን ያስለምዳል›› – ዶክተር የሺመቤት ጫንያለው

የወታደር ልጅ በመሆናቸው የሀገር ፍቅር በውስጣቸው ሰርጿል ፤ ሀገር ከምንም ከማንም በላይ መሆኑን በሚገባ ተረድተዋል። በትምህርት አጋጣሚ ባንኮክ እና ኩባ በሄዱበት አጋጣሚ እንኳን የተመቻቸላቸውን የሥራ እድል አሻፈረኝ ያሉትም የሀገራቸውን ጉዳይ ለድርድር የማያቀርቡ በመሆናቸው ነው። ሀገር ላይ መጥተው በፍቅር ሀገርን ማገልገል ለእርሳቸው ትልቅ ትርጉም አለው። እናም በግብርናው ዘርፍ አንቱታን ያተረፉ ሥራዎች ላይ ተሠማሩ። በተለይ የእንስሳት ዘርፉን በሕክምና በማገዝና ለውጥ ያመጡ ሥራዎችን በማከናወናቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ሽልማት እስከ ማግኘት ደርሰዋል።

ዶክተር የሺመቤት ጫንያለው በርካታ ተማሪዎችን በእንስሳት ሕክምና ዘርፍ አፍርተዋል። በተለይም ቀዶ ሕክምና ላይ ብቁ የሆኑ ሰልጣኞችን ለሀገር አበርክተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ሀገር ተንቀሳቃሽ የእንስሳት ሕክምና እንዲኖር ጥንስሱን ያኖሩም ናቸው። በወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በ2009 ዓ.ም በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና በግብርና ሚኒስቴር ተሽላሚ የሆኑ ተመራማሪ በመሆናቸው ይህን መሰል ተግባራቸው ለብዙዎች ተሞክሮ እንደሚሆን በማሰብ የዛሬው የ‹‹ሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል።

የሺዎች እመቤት

በኢትዮጵያዊያን ባሕል ብዙ ጊዜ ስም የሚወጣው በምክንያት ነው። ዶክተር የሺመቤት ስም መውጣት እንዲሁ ምክንያት ነበረው። ነገሩ እንዲህ ነው። አባትና እናታቸው በትዳር ዓመታትን አሳልፈዋል። ነገር ግን በልጅ መባረካቸው ዘግይቷል። ይህንን የሚመለከቱ የአካባቢው ሰዎች ደግሞ ስለ ቤተሰቡ መልካምነት የማያደርገው ነገር አልነበረም። ወደ ፈጣሪው ልጅ እንዲሰጣቸው የማይማጸን ጎረቤት አልነበረም። አለፍ ሲልም ለየታቦቱ የተሳለላቸው ብዙ ነበሩ። አንድ ቀን ይህ ለፈጣሪ የቀረበ ተማጽኖ ፍሬ አፈራ። የሺዎች ልመና ውጤት ይዞ መጣ። ዓይናቸውን በዓይናቸው አዩ፤ የበኩር ልጃቸውን በእጃቸው አቀፉ። በከንፈራቸው ሳሙ። ይህን የምስራች የሰሙ ሁሉ እንኳን ማሪያም ማረችሽ ሊሉ ወደ ሆስፒታሉ አቀኑ ።

ሆስፒታሉ በሰዎች ብዛት ተጨናነቀ፣ አካባቢውም በደስታ ደመቀ። አባትንም ሆነ እናትን እንኳን ደስ አለህ (ሽ) ለማለት ወረፋው ቀላል አልነበረም። በዚህ የተገረሙት አባትም የልጃቸው መወለድ የእርሳቸው ደስታ ብቻ ሳይሆን የሁሉም መሆኑን ሲረዱ ለልጃቸው ገዢ የሆነ ስም ማውጣትን አሰቡ። የሺ እመቤት ሲሉ ጠሯት። ስምን መላክ ያወጣዋል ይባል የለ። ለሺዎች የምትተርፍ በሙያዋ የሺዎች እመቤት ሆነች ።

የዶክተር የሺመቤት አባት ወታደር በመሆናቸው በአንድ ቦታ የመኖር እድል አልነበራቸውና ሆኖም እርሳቸው በተወለዱበት ነገሌ ቦረና ላይ ረጅሙን ጊዜ አሳልፈዋል። በዚያም የማያውቃቸውና የማይወዳቸው ሰው የለምና አሯሷም ልክ እንደ እናት ቤት በአካባቢ ሰዎች በእንክብካቤ ታረሰች። ክርስትናውም ሠርግ ያስናቀ እንደነበር ዛሬ ድረስ ይነሳል።

እንደቤተሰብ ታርሰውና እንክብካቤ ሲደረግላቸው የቆዩት የእንግዳችን አባትና እናት አካባቢውን ለቀው መሄድ ባይፈልጉም የእንጀራ ጉዳይ ሆነና በአባታቸው የሥራ ዝውውር ምክንያት አካባቢውን ሊቀይሩ ግድ ሆነ። ጉዞ ወደ አርሲ ነገሌ። በዚህም የተለየ ነገር አልገጠማቸውም። የአካባቢው ሰው ልክ እንደትናንቱ የነገሌ ቦረና ጎረቤቶች ሁሉ በፍቅር ተቀበሏቸው።

ልጃቸውን እስከ አራት ዓመቷ ድረስ ተንከባክበው ያሳደጉትና የቄስ ትምህርት ያስተማሩትም በዚሁ ስፍራ ነው። ሆኖም ኑራቸው በአርሲ ነገሌ ሆኖ አልቀጠለም። ከዓመታት ቆይታ በኋላ ሁለተኛ ልጃቸውን አስከትለው የተሻለ ኑሮ እኖርበታለሁ ብለው ወዳሰቡበት አዲስ አበባ አቀኑ።

ዶክተር የሺመቤት እና ቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባ ሲገቡ መኖሪያቸውን ያደረጉት ምስካየ ኅዙናን መድኃኔያለም አካባቢ በሚገኘው የወታደሮች ካምፕ ውስጥ ነበር። በካምፑ ውስጥ መኖር ደግሞ ብዙ ዓይነት ልምዶችን ማግኘት ያስችላል።፡ በተለይም የሀገር ፍቅርን ከማጎልበት አንጻር የማይተካ ሚና ነበረው። ማህበራዊ ሕይወቱም ቢሆን የጠነከረ ነውና ልጆችን የተሻለ ስብዕና ኖሯቸው እንዲያድጉ ቀርጿቸዋል።

ይህ ቦታ ዶክተር የሺመቤት ትልቅ ታሪክ ያስታጠቃቸው ስብዕናቸውን የገነቡበት መሆኑን ይናገራሉ። የሚፈልጉትን በሚገባ አውቀው ነጋቸውን እንዲያስተካክሉ እድል ከፍቶላቸዋል። የልጅነት ጊዜያቸውን እስከ አስር ዓመታቸው ድረስ ሲያሳልፉ የማኅበረሰቡን መልካም ግንኙነት፤ ታዛዥነትን፤ ሰውን መውደድን በሚገባ ያወቁበት ነው።

የእንግዳችን ቀጣዩ የልጅነት ቆይታ በኩባ ሀገር ነው። ኩባ የሄዱበት አጋጣሚ ድንገተኛ ነበር። እርሳቸው እሄዳለሁ ብለው የተዘጋጁት ጀርመን ሀገር ሆኖ ሳለ ቀድሞ የመጣው እድል ኩባ በመሆኑ ከሌሎች ልጆች ጋር አብረው ወደዚያ አመሩ።

በጊዜው ‹‹ኩባ ትሄዳላችሁ›› ሲባሉና ከቤት ወደ ሌላ ካምፕ ሲወሰዱ አባታቸው አርፈው እናታቸው ደግሞ ሀዘናቸውን ለመካፈል ወደ ሟቹ ቤተሰቦች ሄደው ነበር። በቤት ውስጥ ያሉት የአባታቸው እህትና ታናናሾቻቸው ናቸው። ማንንም ለማስፈቀድ እድሉን አላገኙም። ይሁንና የትምህርት እድሉን መቼም እንደማያገኙት ስለሚያውቁ በራሳቸው ለመሄድ ወሰኑ።

በአደጉበት ግቢ ውስጥ አብሮነት ግዴታ እንጂ ውዴታ አይደለም። ቤተሰብን መንከባከብም የቤተሰቡ ድርሻ ብቻ ሊሆን አይችልም። ‹‹የእኔ›› የሚሉት ሳይሆን የእኛ የሚለው ነው ጎልቶ የሚታየው። ስለዚህም ታናናሾቻቸው ምንም እንደማይሆኑ ያውቃሉ። ቢሆንም የበኩር ልጅ እንደመሆናቸው የእርሳቸውም ኃላፊነት እንዳለበት ያምናሉ። እናም እስክሄድ ድረስ ማየት አለብኝ፤ ከእኔ ጋር ሊሆኑ ይገባል በሚል ተደብቀው በመውጣት ልጆቹን አሉበት ድረስ ይዘው በመምጣት ከእርሳቸው ጋር አሳድረዋል። ይህ ሲታወቅባቸውም ተገስጸው ልጆቹን ወደ ቤተሰብ መልሰው አርፈው እንዲቀመጡ ሆነዋል።

ዶ/ር የሺመቤት ጭንቀት የታናናሾቻቸው ጉዳይ ብቻም አልነበረም። የአባታቸው ሀዘን ከውስጣቸው ሳይጠፋ እናታቸውን ሳያዩ መሄዳቸውም ረብሿቸዋል። ሆኖም ራሳቸውን አሳምነው ወደ ኩባ ሄዱ።

እንግዳችንን በልጅነታቸው በጣም የሚያስደስታቸው ነገር ማንበብና ታሪኮችን መስማት ነው። ይህ ደግሞ ከአባታቸው አግኝተዋል። በርከት ያሉ አስተማሪ ታሪኮችን እንዲያውቁ አግዟቸዋል። ነገር ግን ከሰሟቸው ታሪኮች የማይረሱትና ከአዕምሯቸው የማይጠፋው የአባታቸው እውነተኛ ታሪክ ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው። የእንግዳችን አባት የባላባት ልጅ ናቸው። ነገር ግን እርሳቸውን የሚያስደስታቸው ከአባታቸው አገልጋዮች ጋር ማሳለፍ ነው። በዚህም ዘወትር ከአባታቸው ጋር ይጋጫሉ። ግጭቱ እየከረረ ሲመጣም ከቤት እስከ መውጣት ይደርሳሉ።

የሀብት ንብረቱ ተረካቢ እና የትውልዱ አስቀጣይ ብቸኛ ወንድ ልጅ ቢሆኑም ለእርሳቸው ሀብት ምንም ማለት አይደለምና ‹‹ከሰው የሚበልጥ ሀብት›› ብለው ለተወሰነ ጊዜ ከአባታቸው ቤት ወጥተው ትምህርታቸውን መማር ላይ አተኮሩ። ቀጥለውም ውትድርናን ተቀላቀሉ። ለሀገራቸው እስከ ሞት ድረስ ተዋደቁ፡፡

ይህ ሁኔታ ለእንግዳችን ብዙ ነገሮችን አስተምሯቸዋል። ለሰዎችና ለሀገር የሚሰጥ ቦታን በአግባቡ እንዲገነዘቡና እንዲኖሩት እድል ሰጥቷቸዋል። ዛሬ ድረስ የእንግዳችን መርህ ‹‹ሰው ከሀብት በላይ ነው›› እና ‹‹ሀገር ከምንም ትቀድማለች›› የሚል ነው።

ከአርሲ እስከ ባንኮክ

እንግዳችን ትምህርታቸውን አሀዱ ብለው የጀመሩት ገና በአራት ዓመታቸው አርሲ ነገሌ ነው። ከዚያ አዲስ አበባ መጥተው ይህንኑ ትምህርት በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ውስጥ ቀጥለዋል። ፊደልን በሚገባ ለይተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ‹‹ኢየሩሳሌም›› በሚባል ትምህርት ቤት፤ እስከ ሦስተኛ ክፍል ተምረዋል። ከዚያ ‹‹ንጋት ኮከብ›› ትምህርት ቤት ገቡ። ይህም እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉበት ነው።

ከስድስተኛ ክፍል በኋላ ያለውን ትምህርታቸውን የተከታተሉት ከባሕር ማዶ ተሻግረው ነው። ኩባ ሀገር ። መጀመሪያ ትምህርት የጀመሩትም ቋንቋ በማጥናት ‹‹ኢስቤክ ኰአርቶ›› ትምህርት ቤት ነው። ብዙ ኢትዮጵያን ተማሪዎችም መምህራንም የሚገኙበት ትምህርት ቤት በመሆኑ ብዙም ሳይቸገሩ የተሻለ አቅማቸውን እያሳዩ የቀጠሉበት እንደነበር ያስታውሳሉ።

በኩባ ሀገር ሲማሩ ብሔራዊ ፈተና የሚሰጠው ዘጠነኛ ክፍል ላይ ነበር። እናም ትምህርቱን ሲጨርሱ የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ በመሆኑም የዓመቱ ተሸላሚ ተማሪ በመሆን አጠናቀዋል:: ከዚያ በኋላ የመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ወደ መከታተሉ ገቡ። የመምህራኑ ፍቅርና እንክብካቤ ከጉብዝናቸው ሊያርቃቸው አልቻለምና ውጤታማነታቸው እስከ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሏል። የዩኒቨርሲቲ የትምህርት ምርጫቸውን ሳይቀር 12ተኛ ክፍል ላይ ወስነው እንዲገቡ ያደረጋቸው ይኸው ጥረታቸውና የመምህራኑ ድጋፍ ነበር።

ዶክተር የሺመቤት በትምህርት ቤት ቆይታቸው መምህራኖቻቸው ብዙ ኃላፊነት የሚሰጧቸው ተማሪ ናቸው። መጀመሪያ የእርሳቸውን ፈተና በማረም ጭምር የሌሎቹን ፈተና እንዲያርሙ እድሉን ይሰጧቸዋል። ኤክስ ሲገባባቸውም ዳግም እንዳይሳሳቱ ለማስተማር ስማቸውን በር ላይ ለጥፈው ያበረታቷቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከተማሪዎች ጋር ተጋግዘው እንዲያጠኑ መደረጋቸው ውጤታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ከፍታ አድርሶታል። በራሳቸው ጥረት በመምህሮቻቸው ርዳታ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ አድርሷቸዋል። በተለይም የኬሚስትሪና የባዮሎጂ መምህራኖቻቸው ለእርሳቸው የሕይወት ጉዞ ትልቅ ዐሻራን ያኖሩ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።

እንግዳችን መጀመሪያ አካባቢ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ መማር የሚፈልጉት ቴሌኮሙኒኬሽን ነበር። የጤና ትምህርት የሚባል ነገር አስበውም፤ አልመውም አያውቁም። አስከሬን በእጅጉ ይፈራሉ። ነገር ግን የባዮሎጂ መምህራቸው ይህንን አመለካከታቸውን አርቃለች። ለትምህርቱ ልዩ ፍላጎት እንዲያድርባቸውም አድርጋለች። በዚህም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኩባ በሃቫና አግሪካልቸራል ዩኒቨርሲቲ ፍሩክቶሶ ሮድሪጌስ ፔሬዝ (Universidad Agraria de la Habana Fructuoso Ro­dríguez Pérez (UNAH)) የእንስሳት ሕክምና አጠኑ።

ባለታሪካችንና ከትምህርት ጋር ዳግመኛ የተገናኙት ከ14 ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ነው። ይህም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር ወደ ደብረዘይት ያቀኑበት ነበር። ይህ የትምህርት ጊዜ ብዙ ነገሮች በጥልቀት የታዩበትና የለፋበት ነው። የትምህርት ምርጫቸው ሳይቀር ታስቦበትና አካባቢ ተኮር ተደርጎ እንዲቀጥል ታልሞበት የተገባበት ነበር። ይህም በሥራ ቆይታቸው ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ማኅበረሰቡ ላይ ችግር እየፈጠሩ ማየታቸው በእጅጉ ስላሳሰባቸው ይህንን የማኅበረሰብ ችግር መፍታት ይሻሉና ትምህርቱን መረጡት።

የመማሪያ ቦታ ምርጫቸው አዲስ አበባ ላይ ቢሆንም መማር የሚፈልጉት ትምህርት ግን የሚገኘው ቢሾፍቱ (በደብረ ዘይት) ነው። ስለዚህም አላማቸውን አንግበው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ባለው ደብረ ዘይት እንስሳት ሕክምና ገቡ። የእንስሳትና ኅብረተሰብ ጤና ትምህርትንም አጠኑ።

ለእንግዳችን ሌላው ይህ ጊዜ ለየት የሚያደርገው ነፍሰጡር ሆነው የተማሩበት ወቅት መሆኑ ነው። የክፍል ትምህርቱን ለመከታተልም ሆነ ቤተ ሙከራ ገብቶ ለመሥራት የአካባቢው የአየር ሁኔታ ለእርሳቸው ተስማሚ አልነበረም። በሙቀት ምክንያት በእጅጉ ይፈተናሉ። ነገር ግን አላማ ነበራቸውና አንድም ቀን እጅ ሰጥተው አያውቁም። እንደ ማንኛውም ተማሪ እስከ መጨረሻዋ ክፍለ ጊዜ ድረስ ይማራሉ። ቤተ ሙከራም ገብተው ይሠራሉ።

ትንሽ የከበዳቸው መውለጃቸው ሲቃረብ ፈተና ላይ መቀመጥ አለመቻላቸው ሲሆን፤ ይህም ቢሆን አልተሳካም የሚባል አይደለም። በወለዱ በሳምንቱ ሄደው በመፈተን ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ ከጓደኞቻቸው ጋር መመረቅ ችለዋል።

የባለታሪካችን አብዛኛው የትምህርት ቤት ቆይታ በውጭ ሀገራት ላይ ሲሆን፤ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ባሕር ማዶ እንድንሻገር ያደርገናል። ይህም ታይላንድ ሀገር ባንኮክ ላይ ካሴትሳርት ዩኒቨርሲቲ ያደርሰናል። በዚህ ዩኒቨርሲቲ ያጠኑት ትምህርት ‹‹ሞሌኩላር ማይክሮ ባይሎጂ›› ይባላል።

ትምህርት በቃኝ የማያውቁት ባለታሪካችን፤ በመደበኛነት ከተማሯቸው ትምህርቶች ባሻገር የተለያዩ ሥልጠናዎችንም ወስደዋል። በፕሮጀክት ፕሮፖዛል፣ በባዮኢንፎርማቲክስ፣ በአስተዳደር፤ በሥርዓተ ፆታ፣ በዲዛይን፤ በዳታ ትንተና፣ በእንስሳት፤ በአሳ ምርምር፣ በኤፒዲሚዮሎጂ፣ በአመራር ብቃት፤ በሥራ ሥነ ምግባር፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም የጥራት ሥራ አመራር ሥልጠናዎችን ክህሎታቸውን አሳድገዋል፡፡

ሀገርን በፍቅር ማገልገል

ዶክተር የሺመቤት ለሕይወታቸው መቀናት የአባታቸው ምክር ከፊት ይቀድማል። ይህም ‹‹ስለ እውነት በእውነት ሂጂ፤ ኑሪ›› የሚለው ነው። እናም እውነታቸውን የሚያገኙት ደግሞ ለእርሳቸው ከሀገራቸው እንደሆነ ተረድተዋል። ኩባ ላይ ሲመረቁ ጀምሮ የነበሯቸውን በርካታ መልካም የሥራ አጋጣሚዎች አሻፈረኝ ብለው ሀገራቸውን የመምረጣቸው ምስጢርም ይኸው ነው።

እንግዳችን ወደ ሀገራቸው የተመለሱት በ1984 ዓ.ም ሲሆን፤ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር በግብርናው ዘርፍ ሀገራቸውን አገልግለዋል። መጀመሪያ የተመደቡትም በግብርና ሚኒስቴር በእንስሳት ሐኪምነት ሲሆን፤ የደረሳቸው ቦታ ደግሞ በአማራ ክልል ነው። ስለዚህም ባህር ዳር ከተማ አሀዱ ብለው ሥራ ጀመሩ፡፡

ከአራት ወር በኋላ ደግሞ ወደ ዳንግላ ከተማ ተመድበው አገለገሉ። በዚህም በእጅጉ ተደስተዋል። ምክንያቱም ሀገራቸውን የማወቅ ጉጉቱ ነበራቸውና እድሉን አገኙ። ዳንግላ ላይ የተለየ ትምህርት ያገኙበትን ሥራ ሠርተዋል። አንዱ ሌሎች ቦታዎች የማይታዩ የሕክምና ኬዞችን በስፋት ማግኘታቸው ነው። ይህም ለመፍትሔ እንዲሠሩ እድሉን አግኝተዋል። ውጤታማም ሆነውበታል።

ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ አዊ ዞን የተዛወሩት ዶክተር የሺመቤት፤ የቀደመውን ሥራቸውን በማስቀጠል በተጨማሪነት የተለዩ አሠራሮችን በመቀየስ ለሀገር ተሞክሮ የሚሆኑ ተግባራትን ፈጽመዋል። አንዱ አርሶ አደሩን በእንስሳት ሕክምና ዙሪያ ማስተማር ሲሆን፤ ይህ ሥራቸው መድኃኒት ገዝቶ መሄድን ያስቀረና ለእንስሳቶቻቸው ድህነትን ያደለ ማድረግን ያለመ ነው። አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ ሕክምና ሳይሆን መድኃኒት ገዝቶ በመሄድ የሚድኑበትን አማራጭ ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ብዙዎቹን አደጋ ላይ የጣለ ነበር። ከትምህርቱና ሥልጠናው በኋላ ግን ነገሩ ተወግዶ አርሶ አደሮችን ደስተኛ ማድረግ ችሏል።

ዶክተር የሺመቤት ቀጣዩ የሥራ ቦታ ደባርቅ ከተማ ነው። እዚህ ከገቡ ጀምሮ አካባቢው ላይ የተለያዩ ለውጦችን ከእንስሳት ሕክምና ጋር በተያየዘ አምጥተዋል። አንዱና ዋነኛው የባለሙያ እጥረቱን የፈቱበት ሁኔታ ነው። ገጠራማው ክፍል ሳይቀር እየወረዱ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሰጥተዋልና ብዙ ብቃት ያላቸው ሐኪሞችን ማፍራት ችለዋል። በተለይም ቀላል የእንስሳት ቀዶ ሕክምና ላይ የሰጡት ሥልጠና ለብዙዎች ተስፋን ያለመለመ ነበር።

ሌላው በዚህ ቦታ የሠሩት ሥራ እንደ ሀገር በተሞክሮነት የሚጠቀስ ነው። አካባቢው ለሕክምና አመቺ አለመሆኑና አብዛኛው ክፍል ገጠራማ መሆኑ አርሶ አደሩን የእንስሳት ሕክምና አገልግሎት እንዳያገኝ ገድቦታል። ስለዚህም ለዚህ ችግር እልባት ለመስጠት አንድ ነገር አሰቡ። ተንቀሳቃሽ የእንስሳት ሕክምና ማድረግ የሚለውም አዕምሯቸው ውስጥ መጣ። እናም ከቅርብ አጋሮቻቸው ጋር በመምከር እውን አደረጉት። ሐኪሞችም በየቀበሌው ተንቀሳቅሰው የሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። ይህ ደግሞ ለብዙዎች ተስፋ ሰጠ። ተሞክሯቸው እንደ ክልል አለፍ ሲልም እንደ ሀገር ተቀመረ።

ከአምስት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ሌላኛውን የሀገሪቱን ክፍል ተመደቡ። ይህም በጎንደር ዙሪያና በጎንደር ከተማ እንዲቆዩ የተደረጉበት ነው። በእነዚህም ቦታ የቀደመ ተግባራቸው አልቆመም። ይልቁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአዳዲስ አሠራሮችም ዳብሯል። ምክንያቱም ኃላፊነታቸው ከፍ እያለ ስለሄደ የተሻሉ ናቸው የሚሏቸውን ተግባራት ወደ ታች ለማውረድ የሚችሉበትን እድል ይሰጣቸዋል።

እስከ 1997 ዓ.ም ከባህር ዳር እስከ ጎንደርና አካባቢው የቆዩ ሲሆን፤ አብዛኞቹን ሥራዎች የእንስሳት ጤና ክፍሉን በመምራት አሳልፈዋል። በተጨማሪም የእንስሳት ጤና፣ የእንስሳት እርባታ፣ የእንስሳት መኖ እና አመጋገብ ቡድንን የማስተባበር ኃላፊነትን ወስደው ሠርተዋል። በዚህ ቆይታቸው ደግሞ የአርሶ አደሩን ኑሮ በመለወጥ የተሻለ ስኬትን አምጥተዋል። የሥልጠና ዕቅድ አውጥቶ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም በማበረታታትና ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግም ጉልህ ሚናን ተጫውተዋል::

የእንግዳችንን ሌላኛውን የሥራ ምዕራፍ ከሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸው በኋላ ነው። ይህም የሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ዙሪያ ላይ የሰሩበት ነው። በቦታው መጀመሪያ ላይ የተመደቡት የእንስሳት እርባታና ብዜት ማዕከል ውስጥ ሲሆን፤ የቴክኒኩ ክፍሉ አስተባባሪ በመሆንም አገልግለዋል። በዚህም ‹‹የአዋሲ›› በጎችን በስፋት እንዲዳቀሉ የማድረግ ሥራን ሠርተዋል።

ከበግ እርባታ ባሻገር መኖ ልማት ማሻሻል ላይ በስፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበርም የተሻሻሉ የበግ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እንዲከፋፈል አድርገዋል። ክትትል በማድረግም የኅብረተሰቡን ኑሮና የእንስሳት ምርትን የማሻሻል ሥራዎችንም አከናውነዋል።

ቀጣዩ የሥራ ላይ ቆይታቸቸው በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኘው የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል ነው። በማዕከሉ በዋናነት የሚሠራው ምርምር ስለሆነ እርሳቸውም በእንስሳት ዳይሬክቶሬት ምርምር ስር የእንሰሳት ጤና ላይ በስፋት ወደ ምርምሩ ገብተዋል። ከረዳት ተመራማሪነት ጀምረውም እስከ ተማራማሪነት ደረጃ ከፍ በማለት አገልግለዋል።

ከሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸው በኋላም የታይላንድ ልምዳቸውን ይዘው በመመለስ ረጅሙን ጊዜ በዚሁ ቦታ ማገልገል ችለዋል። በፓራሳይቶሎጂ፣ ማይክሮባዮሎጂና እንሰሳት እርባታ (ሬፕሮዳክሽን) ላይ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውነዋል። እንዲሁም የእንሰሳት ምርምር ዳይሬክቶሬትን በማስተባበር እና የምርምር ሥራዎችን በመደገፍ ውጤታማ ተግባራትን ፈጽመዋል። ሥልጠናዎችን በማዘጋጀትና በማስተባበር በርካታ ሥራ አከናውነዋል። በተለይ የአካባቢው ወቅታዊ ችግሮች ላይ በጀት በማፈላለግ ውጤታማ ምርምር በመሥራት አንቱታን ያተረፉበት ነው።

አንዳንድ የክትባት መድኃኒቶችን እንዲሻሻሉ በማድረግ፤ የበሽታ ዓይነቶችንና ሥርጭታቸውን በሚመለከት ምርምር በመሥራት መፍትሔ አመላክተዋል። አንዱ የማይረሱት በግብርና ሚኒስቴር መጥቶ የእንስሳቱ መድኃኒቱን በመላመዳቸው የተነሳ የሚፈለገውን ውጤት ያላገኘውን ነበር። በዚህም ምርምር እንዲያደርጉበት ጥያቄ ቀርቦላቸው ለችግሩ እልባት ሰጥተዋል።

በደብረ ብርሃን አካባቢ በነበራቸው የሥራ ላይ ቆይታ በወቅታዊ ችግሮች ላይ ውጤታማ ሥራ በመሥራትና ምርምር ማዕከሉንም አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ በ2009 ዓ.ም በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና በግብርና ሚኒስቴር ተሽላሚ የነበሩት ዶክተር የሺመቤት፤ ከመጋቢት 2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የዛሬውን መሥሪያ ቤታቸውን ተቀላቅለዋል። ይህም ባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ነው።

በኢንስቲትዩቱ በባዮኢንፎርማቲክስ እና ጂኖሚክስ ምርምር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪና ከፍተኛ ተመራማሪ በመሆን ሥራቸውን ጀምረዋል። በዚህም በምርምር እንዲሁም የባዮ ኢንፎርማቲክስ እና ጂኖሚክስ ሥልጠናዎችን በማመቻቸትና በማስተባበር ለተለያዩ የሀገሪቱ ተመራማሪዎች እንዲዳረስ የማድረግ ሥራ በመሥራት እያገለገሉ ናቸው።

በአሁን ወቅት ደግሞ በእንሰሳት ባዮቴክኖሎጂ ዳይሬክተርና ተመራማሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። ችግር ፈቺ የምርምር ፕሮጀክቶችን በማቀድና በሀገር አቀፍና በክልል ወርክሾፕ እና በህትመት መረጃን በማሰራጨት፣ በማስተባበርና በወተት ምርት ላይ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎች ላይ ተሰማርተዋል ።

የሕይወት ፍልስፍና

በእርሳቸው እምነት አንድ ሰው ከምንም በላይ ራሱን ማወቅ፤ አቅሙን መለካት አለበት። በዚህ ባህሪው ደግሞ የማይገባው ላይ እንዳይገኝ፤ ራሱንም ከጫናና ጭንቀት እንዲያቃልል እንዲሁም መጪውን ጊዜ ብሩህ ነው ብሎ እንዲያስብ ይሆንለታል። ከሁሉም በላይ አካባቢውን በምን መልኩ እንደሚያግዝና ዐሻራውን እንደሚያኖር ይረዳበታል ይላሉ።

ሌላው የሕይወት ፍልስፍናቸው ‹‹በተስፋ መራመድ ፍርሃትን ያስወግዳል፤ አላግባብ ነገሮችን ከማድረግ ይቆጥባል። በፍቅርና በጊዜ መጠቀምንም ያስለምዳል›› የሚለው ነው።

አይሬሴው ገጠመኝ

ወቅቱ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እየተማሩ የነበረበት ነው። ትምህርታቸውን አጠናቀው ለፈተና እንዲዘጋጁ ሲነገራቸው ደግሞ እርሳቸው መውለጃ ጊዜያቸው ደርሷል። ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ስለገባቸው ከወለዱ በኋላ ፈተናውን እንዲወስዱ ጥያቄ አቀረቡ። የእርሳቸው እርግዝና ከሚሠሩት ሥራና የትምህርት እንቅስቃሴ አኳያ ያላስጨነቀው የለም። ጊዜው ጭምር የነጎደ የሚመስለው ብዙ ነው። ስለዚህም አቋርጪው፤ ቀጣይ ተፈተኚ፤ አንድ ነገር ብትሆኚስ … የማይላቸው አልነበረም። ግን እርሳቸው ብርቱና ለአላማቸው የቆረጡ በመሆናቸው እስከ መጨረሻው ታግለው ትምህርቱን አጠናቀዋል። የፈተና ጊዜው ሲነገራቸው እንኳን ምንም አልደነገጡም። ‹‹ልጄን በተገላገልኩ በሳምንቱ ተፈትኜ የተሻለ ውጤት አመጣለሁ›› በማለት አራስ ቤት ሳይቀር ተቀምጠው በማጥናት ሃሳባቸውን አሳክተዋል። ይህንን ጊዜ ሲያስቡት ‹‹በሕይወቴ ከሁሉም ጊዜ በላይ በነፃነት ያጠናሁበትና የምደሰትበት የፈተና ውጤት ያመጣሁበት ነው›› ይሉታል።

እንግዳችንን ከዚህ ጋር ተያይዞ በጣም የሚያስደንቃቸው ሐኪሞቹ ገና ነሽ ሲሏቸው ‹‹እኔ ዛሬ እወልዳለሁ፤ ሰዓቱም ይሄ ነው›› ያሉበት ቀንና ሰዓቱ ሳይዛባ ልጃቸውን በሰላም የተገላገሉበት ነው።

ቤተሰብ

ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙት በቤተክርስቲያን ነው። ፍቅራቸው ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ ተጋቢ ሙሽራ ነው። ወንድም፣ ጥሩ የሕይወት አጋራቸውም ናቸው። ለልጆቻቸው አርአያም ሆነዋል። ለልጆቻቸው ያለምንም ጫና የሚፈልጉትን እንዲሆኑ ሲፈቅዱላቸውም እንደ ልጅ ብቻ ሳይሆን እንደ ጥሩ ጓደኛ ጭምር በመሆን ነው። ይህ ደግሞ ቤተሰቡን በደስታ እንዲኖር አስችሎታል።

አምስት ልጆችን አፍርተው እንኳን ልክ እንደ ወጣት ልጆቻቸውን በእድሜያቸው ልክ የሚያወሩ አባትና እናትም መሆናቸው በእጅጉ ያኮራቸዋል። ምክንያቱም ከልጆች ጋር ጓደኛ መሆን ምክርን ለመቀበል፤ ቀጣዩን እጣ ፋንታቸውን ለማስተካከል ይረዳል ብለው ስለሚያምኑ ነው። በርግጥ አሁን ላይ አስቸጋሪ ልጅ በቤት ውስጥ የለም። ሁሉም በሚባል ደረጃ አድገዋል። ራሳቸውን ችለውም የልጅ ልጅ ያሳዩዋቸው አሉ።

የቀጣይ እቅድ

የእርሳቸው ሕልም ባሕላዊ መድኃኒቶችን ከዘመናዊው ጋር በማቀናጀት የተሻለ የመድኃኒት አቅርቦት በሀገር ደረጃ እንዲኖር ማስቻል ነው። በሁሉም ገበያ ላይ እንደ ልብ መድኃኒት የሚሸጥባትን ሀገር መፍጠር ይሻሉ። በዚህም የራሳቸውን ዐሻራ ለማኖር ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። በተፈጥሮ ሀብቷ ምንም እንከን የማይገኝላት ሀገራቸው ደግሞ ለዚህ ምቹ መደላደልን እንደምትፈጥርላቸው ያምናሉ።

ሀገሪቱ ላይ በዚህ ዘርፍ የተሠማሩ ግን ያልታዩና ወደ ዘመናዊው መንገድ ያልገቡ በርካቶች እንደሆኑ ያስባሉ። ስለዚህም እውቀቱን ከእነርሱ በመቅሰምና ከእነርሱ ጋር በመቀናጀት ለመሥራት ይፈልጋሉ። ይህ ጥረታቸው ደግሞ ከብዙ ሰዎች ጋር አገናኝቷቸዋል። ጽፈው የሰጧቸው፤ አብረዋቸው ለመሥራት ቃል የገቡላቸውም በርካታ ናቸው። ስለዚህም የቀጣይ እቅዳቸው ይህንን ሥራ በምርምሮቻቸው መደገፍና ከልጆቻቸው ጋር አብሮ በመሥራት እውን ማድረግ ነው።

መልዕክት

በተፈጥሮ ሀብት ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር የትም የለም። ሆኖም ሁልጊዜ የመድኃኒት አቅርቦትን የምትፈልገው ከውጭ ሀገር ነው። በሀገር ውስጥ በቀላሉ መመረት የሚችሉ በርካታ መድሀኒቶች አሉ። ስለዚህም ያለንን ሀብት ማሳየት ላይ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል።

እንግዳችን በተለያዩ የምርምር ተቋማት የሚሠሩ የምርምር ሥራዎችንም በሚመለከት ያነሱት ነገር አለ። ተቋማት የሚሠራቸው የምርምር ሥራዎች የሚቋጩት ምርምር አድርጎ ውጤቱን በማሳየት ነው። በዚህም ምርቱ ለተጠቃሚው አይደርስም። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ብክነት ነውና ተቀናጅቶ መሥራት ላይ ሊታሰብበት ይገባል። በተለይ መንግሥት ይህንን ከማድረግ አንጻር ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይኖርበታል። ግለሰቦችም ቢሆኑ የምርምሮች ውጤቶች በተሻለ አቅም ወደ ምርትነት ቢቀይሯቸው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ማመን ይገባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You