
አዲስ አበባ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ሺህ የሚሆኑ የመመዝገቢያ ጣቢያዎች የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ገለጸ፡፡ በበጀት ዓመቱ ለ30 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱ ተመልክቷል፡፡
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮሙኒኬሽን እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቢኔዘር ፈለቀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ለ30 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
አዲስ አበባ ላይ ከፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ጋር ተያይዞ ጥሩ የሆነ መነቃቃት እና የምዝገባ ሂደት መኖሩን ገልጸው፤ በዘንድሮ ዓመት የታቀደውን ቁጥር ለማሳካት በስፋት ወደ ክልሎች የመመዝገብ ሥራ ይሠራል፡፡በተጨማሪም ከዋና ዋና ከተሞች በመውጣት ወደ ገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ለመድረስ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ከክልል ቢሮዎች ፣ ከክልል መስተዳድሮች እና ከአጋር አካላት ጋር በጋራ በመስራት በ2017 በጀት ዓመት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢዎችን 30 ሚሊዮን ለማድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ከአዲስ አበባ ከተማ አልፎ በስፋት በክልሎች ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ነው ያሉት አቶ አቤኔዘር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ሺህ የሚሆኑ የምዝገባ ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ የምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ በዋነኛነት በገቢዎች ሚኒስቴር፣ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በውልና ማስረጃ ተቋም እና በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ በሁሉም የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት በኩል ምዝገባዎች እየተደረጉ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደተናገሩት፤ እስካሁን ድረስ ባለው ሂደት 12 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ መታወቂያን ያገኙ ሲሆን፤ ከ52 ተቋማት ጋር የአሠራር ትስስር በማድረግ ሰዎች አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ መጀመሪያ ላይ የመታወቂያ ፕሮግራሙ ሲጀመር ማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ብዙም እንዳልነበረ አውስተው፤ ምክንያቱም እንደሌሎች ሀገራት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመታወቂያ ሥርዓት ከዚህ በፊት ስላልነበረ መጠራጠር እንደነበር አንስተዋል፡፡
ከግል መረጃ ጥበቃ እና ከአገልግሎት ተደራሽነት ጋር ተያይዞ ማህበረሰቡ የተለያዩ ጥያቄዎች ነበሩት፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተሰራው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የነበረው ጥርጣሬ በሂደት እየተቀረፈ መምጣቱን እና ሕዝቡ ዘንድ መነቃቃት መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
አቶ አቢኔዘር እንደተናገሩት፤ የቀበሌ መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ፣ ፓስፖርት እና ሌሎች የመታወቂያ አይነቶች አገልግሎትን መሠረት ያደረጉ ስለሆኑ ለውስን አገልግሎት ብቻ ነው የሚውሉት እንጂ፤ አንድን ሰው የሚለዩ መታወቂያ አይነቶች አይደሉም፡፡በመሆኑም የተደራሽነት አድማሳቸው በጣም የጠበበ ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንደሀገር ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው ዜጋ ምንም አይነት መታወቂያ የለውም። ይህም ማለት እነዚህ ሰዎች ከየትኛውም አይነት አገልግሎት የተገለሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያም ፋይዳ መታወቂያ እነዚህን የማህበሰብ ክፍሎች መደበኛ ወደ ሆነው የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲገቡ ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም