ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት በትዊተር ገጻቸውና ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫቸው ኤልሀን ኦማር፣ አሌክሳንድሪያ ኦካሲዮ-ኮርቴዝ፣ አያን ፕሬስሌይ እና ራሺዳ ትላይብ የተሰኙትን አራት የምክር ቤት ሴት አባላትን ‹‹ሀገራችንን ይጠላሉ፤ እንደ አልቃኢዳ ያሉ የአሜሪካ ጠላቶች ወዳጆች ናቸው፤ ደስተኛ ካልሆኑ ሀገራችንን ለቀው ይውጡ” ሲሉ መወረፍና መወንጀላቸው የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ መሆኑ ቀጥሏል፡፡
‹‹ዘ ስኳድ›› በሚል ቅጽል ስም ከሚጠሩት አራቱ የኮንግረስ አባላት መካከል ሶስቱ የተወለዱት አሜሪካ ውስጥ ሲሆን ኤልሀን ኦማር ሶማሊያ ውስጥ የተወለዱ አሜሪካዊ ናቸው። አራቱም አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሲሆን፣ የኮንግረሱ አባል ሆነው የተመረጡት ደግሞ ባሳለፍነው አመት ነው፡፡
ትችቱ የተሰነዘረባቸው የምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ በሰጡት መገለጫ፣የፕሬዚዳንቱ ተግባር አገሪቱን ለመከፋፈል ያለመ እና የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች አጀንዳ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ትውልደ ሶማሊያዊቷ የአሜሪካ የህግ አውጭ ምክር ቤት አባል ኤልሃን ኦማር ‹‹ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአራቱ ሴት የምክር ቤት አባላት ላይ ቀለምን መሰረት ያደረገ ዓይን ያወጣ የዘረኝነት ጥቃት ፈፅመዋል፣ይህ ደግም የነጭ ብሔርተኛነት አጀንዳ ነው›› ስትል ወቀሰች።
አያን ፕሬስሌይ ተግባሩን ‹‹የኮንግረስ አባላቱን ለማግለልና ድምጻቸውን ለማፈን የተቃጣ ፣ መጤ ጠልና ጽንፈኛ ንግግር›› በሚል ስትገልፀው›፣አሌክሳንድያ ኦስካዝዮ- ኮርቴዝ በበኩሏ፣ ንግግሩን አዕምሯቸው ያልበሰለ መሪዎች ፓሊሲ ላይ ማተኮር እንደሚሳናቸው የሚያሳይ መሆኑን ተናግራለች፡፡
ተግባሩን ‹‹ከፕሬዚዳንቱ ዘረኛ አመለካከት የተቀዳ›› ያሉት››ራሺዳ ቲላይብ፤ የአገሪቱን ሕግ ተመርኩዘው ፕሬዚዳንቱን ተጠያቂ ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳማይሉም አስታውቀዋል። አራቱም ሴቶች፤ የአሜሪካውያን ትኩረት ፖሊሲ ላይ እንጂ የፕሬዘዳንቱ ንግግር ላይ እንዳይሆን በማሳሰብ፣ የትራምፕን ንግግር ከቁብ እንዳይቆጥሩት አሳስበዋል፡፡
በዚህ መልክ ፕሬዚዳንቱ ዘረኛ ተብለው ተግባራቸው ውግዘት የገጠመው በሰለባዎቹ ሴቶቹ ብቻም አይደለም፤ተግባሩ ሌሎችንም አስቆጥቷል፡፡ ዴሞክራቱ ጆን ልዊስ፤ ‹‹በከፍተኛ የመንግስት አስተዳደር መቼም ቢሆን ለዘረኛነት ቦታ የለንም›› ሲሉ፣የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ ናንሲ ፒሎሲም፤ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ‹‹ዘረኛ፣ ክብረ ነክና አስቀያሚ›› ብለውታል። የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሪሳ ሜይ፣ የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን እንዲሁም የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሮዶ የፕሬዚዳንቱን ንግግር በእጅጉ ነቅፈውታል።
የአሜሪካ የሕዝብ እንደራሴዎችም በአብላጫ ድምፅ ፕሬዚዳንቱን የሚያወግዝ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡ ዴሞክራቶች የበላይነቱን በያዙበት ምክር ቤት በተካሄደው ድምፅ አሰጣጥ በ240 ድጋፍ ና በ187 ተቃውሞ ያለፈው የምክር ቤቱ ውሳኔ፣ ተግባሩም ‹‹በአሜሪካውያን መካከል ፍርሀትና ጥላቻን የነዛ ዘረኛ ንግግር›› በሚል ተችቷል። ‹‹አሜሪካ በስደተኞች ጀርባ ላይ የቆመች አገር እንደሆነችና አገር ወዳድነት የሚገለጸው ህገ መንግስት በማክበር እንጂ ሰዎችን በዘራቸው ምክንያት በማንቋሸሽ አይደለም›› ሲል ማመላከቱም ታውቃል፡፡
ይህን የተከታተሉ በርካታ የመገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙዎችም ‹‹ዘረኛ›› ከተባለው የፕሬዚዳንቱ ተግባር ጀርባ ምን ፖለቲካዊ አንድምታ ይኖር ይሆን ? አላማና ጠቀሜታውስ ምን ይሆን? በሚል በስፋት በማተት ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶች ‹‹ሰውየው መሰል ዘረኛና ጸረ ስደተኛ ንግግር ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው አይደለም፣ ሰውየው አልፎ አልፎም ህጋዊ ስደተኛ እንደሚወዱ ሲያስመስሉና ሲናገሩ ቢደመጡም ከመጋረጃው በስተጀርባ እነዚህን ስደተኞች ሳይቀር ሲያንቋሽሹ በተደጋጋሚ ታይተዋል፤የሰሞኑ ተግባራቸው ምንም ሊያስገርም አይገባም›› ሲሉ ተደምጠዋል። ከዚህ በአንጻሩ‹፣የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖራቸውም አሜሪካውያንን ወደመጣችሁበት ተመለሱ ማለት መስመር ያለፈ ነው›› ብለውታል።
ከሁሉም በላይ ከስተቱ የወለደው ሰፊ ልዩነት በሪፐብሊካንና በዲሞክራቶቹ መካከል እየታየ መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ዴሞክራቶች ‹‹ድንበር ላይ የስደተኞች ሰብአዊ መብት እየተጣሰ ነው›› ሲሉ የትራምፕን አስተዳደር ከፉኛ መተቸታቸውና እቅዳቸውም ተግባራዊ እንዳይሆን በምክር ቤቱ ጠንክረው በመሞገታቸው ሳቢያ የተከሰተ ነው›› ሲሉ የሚገልጹት ቁጥር በርካታ ሆኗል፡፡
በእርግጥ የትራምፕ አስተዳደር ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገሪቱ ሊገቡ የሚችሉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ሊገቡ የሚችሉበትን በር ዘግቷል፡፡ የሚቀበሏቸውን ስደተኞች ቁጥር እንደሚቀንስ በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ ቆይታል፡፡ ይሁንና የስደተኞችን ጉዳይ ፈር ማስያዝ የሆነለት ግን አይመስልም፡፡ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ድንበር ማቋረጣቸውን ቀጥለዋል፡፡ መግባት ያቃታቸው በርካታዎች ደግሞ ድንበር ላይ ተከማችተዋል፡፡
ይህን ያስተዋሉ ዴሞክራቶች ታዲያ ድንበር ላይ የስደተኞች ሰብአዊ መብት እየተጣሰ ነው›› በሚል የትራምፕን አስተዳደር ከፉኛ ይተቹታል››፣ የሚለው የኤፒ ኒውሱ ኮለን ሎንግ፣ሪፐብሊካኑ በአንፃሩ ዲሞክራቶቹ የትራምፕን አጀንዳ ለመቀበል ዳተኛ መሆናቸው ለዚህ ቀውስ መባባስ ሁነኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ሰለመሆኑ እንደሚሞግቱ አትቷል፡፡ ይህ ልዩነት ፕሬዚዳንቱን እንዳበሳጫቸውና ከተግባራቸው ጀርባ ያለው ምክንያትም ምናልባት ይህን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
ጉዳዩ የዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኑ ፍልሚያ ሳይሆን የፕሬዚዳንቱ የግል ፍላጎትና ተግባር ውጤት ስለመሆኑ የሚያስረዱም አልጠፉም፡፡ በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ማዕከል የበላይ ሃላፊ ላሪ ሳባቶም ይህን ሀሳብ ያጠናክሩታል። የግሎባል ባለሙያው ለኤፒ ኒውስ ጸሃፊው ጃክሰን ፐሮስኮ በሰጡት አስተያየት ‹‹ሰዎችን መከፋፈል በጣም ቀላል ነው፣ከባዱ ሰዎችን አንድ ማድረግ ነው፣ ዶናልድ ትራምፐ ደግሞ ሁልጊዜ የሚከውኑት ቀላሉን ነው፣ ተግባሩም የዚህ ማሳያ ነው›› ብለዋል፡፡
በእርግጥ ይህ ተግባር ሙሉ በሙሉ ከዘረኝነት ጋር ሊዛመድ ይችላል፡፡ ይሁንና ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ግድ የላቸውም፡፡ ሰውየው በተግባራቸው የነጭ የበላይነት አቀንቃኝ መሆናቸውን በማረጋገጥ ሊያስተቻቸው እንደሚችል ሲጠየቁና የዘረኝነት ጥቃት ፈፅመዋል በሚል ለቀረበባቸው ውንጀላ ሲመልሱ ቆፈጠን ብለው ‹‹አያሳስበኝም፤ ብዙዎች በሀሳቤ ተስማምተዋል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ትራምፕ ከዚህ ድርጊታቸው በስተጀርባ ከባድ ቁማር ስለመጫወታቸውና አነጋጋሪነታቸውን በመጠቀም ስማቸውን ይበልጥ ከማሰማት ጀምሮ በተለይም ዲሞክራቶቹ መልስ ለመስጠት ሲጣደፉ የፓርቲው ወቅታዊ ተጽእኖ ፈጣሪነትና ቁመና ምን እንደሚመስል ለመሳል ፈልገው መሆኑን የሚናገሩም አልጠፉም፡፡ የታይም ጸሃፊው ብሪያን ቤንት ያነጋገራቸው በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪው ቲሞቲይ ናፍታሊ፣ የፕሬዚዳንቱ ግብ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላትን በመከፋፈል በምርጫው ፍልሚያ አሸናፊ መሆን ነው›› ብለዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ተግባር የታቀደበትና ስትራቲጂክ ሰለመሆኑ የሚሞግቱት የእሳቤው አቀናቃኞች፣ ተግባሩን በርካቶች ቢቃወሙትም ሪፐብሊካኑ ሳይቀሩ የተስማሙበት ስለመሆኑ አስቀድሞ የታቀደበት ነው ለማለት በቂ ማስረጃ ሆኗል›› ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ የኤቢሲ ኒውሱ ዞይ ዳንኤልና ኤምሊ ኦልሰን ባሰፈሩት ሰፊ ትንታኔ ፣ፕሬዚዳንቱ ከ2015 ምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ በሚያ ደርጓቸው ዘረኛ ንግግሮች ከሚቃወሟቸው ብቻም ሳይሆን ከሚወክሉት ፓርቲ አባላት ሳይቀር ‹‹አበዙት›› በሚል ትችት ሲገጥማቸው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን ‹‹አበዙት›› የሚል ትችት አለመስተዋሉን አትተዋል፡፡
ፍራንስ 24 ያስነበበው ዘገባም ይህን ያጠናክራል፡፡ ከሪፐብሊካኑ መካከል በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ተግባሩን እንደተቹትና በተለይም ‹‹የቴክሳሱ ተወካይና በምክር ብቱ ብቸኛው አፍሪካ አሜሪካዊ ዊል ሃርድና የሴኔቱ ብቸኛ ጥቁር ቲም ስኮት ተግባሩን ዘረኛ›› ማለታቸውን ዘግቧል፡፡
ሌሎች በአንጻሩ የ2012 የሪፐብሊካን ዕጩ ፕሬዚዳንት ሚት ሮምኒ እንዲሁም የ2016 እጩ ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ንግግሩን ቢያወግዙትም ከዘረኝነት ጋር ማዛመዱን እንዳልወደዱት ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የአብላጫ ወንበር ያለው የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ኬቨን ማካርቲ ፕሬዚዳንቱን አለመውቀሳቸውና ዘረኛ አይደሉም ማለታቸው ጉዳዩን ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል። ይህም ከሁሉም በላይ ‹‹ዘረኛ›› የተባለው የፕሬዚዳንቱ ተግባር የታቀደበትና ስትራቴጂው ስለመሆኑ ለሚያስቡት ሁነኛ ማስረጃ ሆኗቸዋል፡፡
ዋነኛ የፖለቲካ መርህ ከሆኑት መካከል አንዱ እንዴት ደጋፊዎችን ማብዛት እንደሚገባ ማጤን ብቻም ሳይሆን በሌላ አቅጣጫ ተቀናቃኞችንም እንዴት መቀነስ እንደሚቻል ማወቅ እንደመሆኑ ፣ሰሞኑን ፐሬዚዳንቱ የፈጸሙት ተግባርም ከሁሉም በላይ ደጋፊዎቻቸውን ማብዛትን ታሳቢ ያደረገ ነው የሚሉም በርካቶች ሆነዋል፡፡
የዠንዋው ማቲው ሩሰሊን ያነጋገራቸው ባለሙያዎችም፣ፕሬዚዳንቱ ስምና ዝናቸውን ከፍ አድርገው የገነቡት ሁነኛ ደጋፊዎቻቸው የሚፈልጉትን ሆኖም አደባባይ ላይ ለመናገር የሚሰጉበትን በገሃድ በመግለጻቸው ነው ብለዋል። ‹‹ይህም በማድረግም ሁሌም ከደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ነጥብ ያገኛሉ፣ ይህም በቀጣዩ ምርጫ ይረዳቸዋል›› ሲሉ ተደምጠዋል። ዘጋቢው ካነጋገራቸው ባለሙዎች አንዱ የሆኑት የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ከሌይ ራምሴ፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ በዚህ አይነት መንገድ ከቀን ወደ ቀን ራሳቸውን ቁጥር አንድ አብይ ጉዳይ ማድረግ ዋነኛ ስትራቴጂአቸው ነው‹‹ ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 16/2011
ታምራት ተስፋዬ