የማህጸን ወደ ውጭ የመውጣት አደጋ

ከማህጸን ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ሕመሞች በርካታ ናቸው:: እነዚህ ሕመሞች ግን ከጥቂቶቹ በስተቀር የሚታወቁ አይደሉም:: በዚህም ብዙዎች በከፋ ችግር ውስጥ እንዲገቡና እንዲሰቃዩ ሆነዋል:: ይህ እንዳይሆን ደግሞ ስለ ሕመሞቹ ምንነት እና ሕክምናው ማሳወቅ ያስፈልጋል:: እኛም ከዚሁ ሃሳብ በመነሳት በስፋት የማይታወቀውን የማህጸን ወደ ውጭ መውጣት ምንነትና ሕክምናው ዙሪያ በ‹‹ማህደረ ጤና›› አምዳችን ልናስነብባችሁ ወደናል:: ስለሕመሙ ምንነትና ሕክምናው ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡን ደግሞ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የማህጸንና ጽንስ ትምህርት ክፍል ዩሮጂኔኮሎጂ ፎሎ ዶክተር መስፍን ፍስሃ ናቸው::

እንደ ዶክተር መስፍን ማብራሪያ፤ የማህጸን ወደ ውጭ መውጣት ሕመምን ለማንሳት መጀመሪያ በሕክምናው ቋንቋ ‹‹Pelvic organ›› የሚባሉት ዘርዝሮ ማየትን ይጠይቃል:: ‹‹ሰርጂክ ኦርጋን›› የሚባሉት ማህጸንን ጨምሮ በአቅራቢያው ያሉትን ሌሎችን የአካል ክፍሎች የሚይዝ ነው:: ለምሳሌ፡- የውሃ ሽንት ፊኛ፤ የሽንት ቧንቧ፤ ማህጸን( ጽንስ የሚቀመጥበት)፤ ከማህጸን እስከ ውጪኛው ክፍል ያለው (ብልት)፤ ፊንጢጣ፤ የላይኛው አንጀት የሚሉት ናቸው:: እነዚህ ክፍሎች የተፈጥሮ ቦታቸውን ትተው ሲወጡ የተለየ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ:: ይህ የሚሆነው ደግሞ የማሕጸን ወለል መላላት ሲፈጠር ነው::

ማህጸን በተፈጥሮው ያገኘውን መደገፊያ ጥንካሬ በሚያጡበት እና በሚላሉበት ወቅት ማህጸን ወደ ብልት እየተገፋ ይመጣል። በዚህ ጊዜ ማህጸን ብቻም ሳይሆን የሽንት ፊኛና ደንዳኔውን ደግፎ የሚይዘው ብልትም ወደ ውጭ ይወጣል:: የዚህ ጊዜ የማህጸን መውጣት አጋጠመ ይባላል:: ይህ ችግር የሚታየው በአብዛኛው እድሜያቸው ከ50 እስከ 79 ዓመት በሚደርሱ ሴቶች ላይ ሲሆን፤ የሚከሰተውም ከነበረበት ወይንም ከተፈጠረበት እና ከሚቀመጥበት ቦታ ለቆ ሲወጣ እንደሆነ ዶክተር መስፍን ይናገራሉ::

የማህጸን መውጣት መንስኤዎች

የማህጸን ወደ ውጭ መውጣት ችግር የሚያጋጠመው በዚህ ምክንያት ነው ተብሎ ማስቀመጥ ያዳግታል:: ችግሩን ሊፈጥሩት የሚችሉት በርካታና የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉና መንስኤውን ከመዘርዘር ይልቅ አጋላጭ ምክንያቱ ምንድነው የሚለው ቢታይ የተሻለ ግንዛቤ መያዝ ይቻላል:: ከአጋላጭ ምክንያቶቹ መካከል አንደኛው በምጥ መውለድ ነው:: በተለይ በወሊድ ጊዜ የማህጸን በር መጥበብ ሲያጋጥም ሰፋ ለማድረግ የሚወሰዱ የመፍትሔ ዘዴዎች ማህጸንን ደግፈው የያዙትን ጡንቻዎችና ጅማቶች ሊያላሉት ይችላሉ:: በዚህም የማህጸን መውጣት ችግር ይከሰታል::

ሌላው በወሊድ ጊዜ የልጁ መታፈን ሲያጋጥም ልጁን ለማውጣት በመሳሪያ የታገዘ ወሊድ እንደ አጋላጭ ምክንያት ይወሰዳል:: በተመሳሳይ በተደጋጋሚ መውለድም የማህጸን በርን ስለሚያሰፋው ሌሎች የዳሌን ወለል አካባቢ በማላላት የችግሩ ሰለባ ሊያደርግ ይችላል:: ከዚህ በተጨማሪ የእድሜ መግፋትም አካላጭ ከሚባሉት መካከል የሚመደብ ነው::

የወር አበባ መቋረጥ ላይ ያሉ ሴቶች ኢስትሮጂ የሚባለው ንጥረ ነገር በሰውነታቸው ውስጥ መመረት ስለሚያቆም የጡንቻዎች መላሸቅ ያጋጥማቸዋል:: ጡንቻዎች ላሉ ማለት ደግሞ ማህጸንን የሚደግፉ አካላት ላሉ እንደ ማለት ይወሰዳልና የማህጸን ወደ ውጭ መውጣት እንዲያጋጥም ሰፊ መደላደልን ይፈጥራል::

በመውለድ ጊዜ ካሏቸው ከበድ ያሉ ልጆችን መውለድ ወይንም ለረጅም ጊዜ በምጥ ላይ መቆየትም እንዲሁ ለችግሩ ተጋላጭ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ይካተታል:: በሌላ በኩል ከፍተኛ የሆነ ውፍረትም ለማህጸን መውጣት ሊያጋልጥ ከሚችል ምክንያት ውስጥ አንዱ ነው:: ውፍረት በራሱ በማህጸን አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን እንዲላሉ ማድረግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል:: የሆድ ውስጥ ግፊት መብዛት፤ ከባድ ሳል፤ የሆድ ድርቀትን የመሳሰሉትም ሕመሙን ከሚፈጥሩ አጋላጭ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ::

የሚፈጠሩ ስሜቶች

የማህጸን መውጣቱ ያጋጠመው በፊኛው ክፍል ከሆነ ከሽንት መሽናት ጋር ተያይዞ በርካታ ስሜቶችን ልናስተናግድ እንችላለን:: አንዱ ሽንት ማምለጥ (ጭርቅ ጭርቅ) ዓይነት ስሜትን ማስተናገድ ሲሆን፤ ሌላኛው የመሽናት ሁኔታ መዘግየት ነው:: በተጨማሪም ውሃ ሽንት ለመሽናት አለመቻልም ያጋጥማል:: ከዚያም ባሻገር በትንሽ ኳስ ላይ እንደተቀመጡ ወይንም ከብልት ውስጥ አንድ ነገር እየወደቀ እንዳለ ያለ ስሜት እንዲሰማም ያደርጋል::

ሌላው ወሲባዊ ግንኙነት ሲደረግም የመቸገር ሁኔታ ይፈጠራል:: በብልት አካባቢ ያለው ስሜት ሴቷን ወሲብን እንደማትፈልግ ወይንም ያ የፍላጎት ስሜቷ እንደተቋረጥ ሊሰማት ይችላል:: በተጨማሪም እንቅስቃሴ የመከልከል ስሜቶችም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ስሜቶች ናቸው::

የማህጸን መውጣቱ ከኋለኛው ክፍል ሲያጋጥም ደግሞ የሚኖሩ ስሜቶች የሆድ መድረቅ፤ የሰገራ እንቢ ማለት፤ ሰገራ ለመውጣት መቸገርና መሰል ችግሮች ናቸው:: እነዚህ ስሜቶች አብዛኛውን ጊዜ ቶሎ ላይታዩ የሚችሉ ሲሆን፤ ምልክቱ መታየት ሲጀምሩ ግን ዋነኛው ምልክት ይሆናል ተብለው የሚታመኑት የውስጠኛው ልጅ የሚይዘው ማህፀን ወደ ውጪ መውጣት፤ ታማሚዋ በብልቷ በኩል የወጣ ሥጋ መሰል ነገር መታየት፤ የሽንት ምንም ሳይታወቅ መፍሰስ፤ ከማህፀን አካባቢ ያበጠ ነገር መፈጠር፤ የወገብ ህመም፤ የዳሌ አጥንት አካባቢ የግፊት ስሜት መሰማት ዋና ዋናዎቹ ናቸው::

የሕመሙ ደረጃዎችና ክፍሎች

የማህጸን ወደ ውጭ መውጣትን ለሕክምና አላማ ሲባል በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል:: አንደኛ ደረጃ የሚባለው ‹‹Pelvic organ›› ወይም ማህጸን ክፍል ከተፈጥሮ ቦታው ወርዶ ግን በውጭ በኩል የማይታይ ደረጃ ላይ የደረሰውን ነው:: ከብልት በር ‹‹ hymenal ring›› አንድ ሴንቲ ሜትር በላይ ሲከፈትና ሲታይ የሚቀመጥበት ደረጃ ነው::

የብልት በር ‹‹ hymenal ring›› ከአንድ ሴንቲ ሜትር በላይ ወይም በታች ወጣ ብሎ የሚታይ ከሆነ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል:: በተመሳሳይ የብልት በር ‹‹ hymenal ring›› ከአንድ ሴንቲሜትር በታች ሁለት ሴንቲሜትር ሳይደርስ እስከ የማህጸን ርዝማኔ ወይም በብልት በኩል መውጣት ሲጀምር ያለውን ደረጃ ሦስት ላይ ይመደባል:: ከሁለት ሴንቲሜትር በላይ ብልትን ተያይዘው ሙሉ በሙሉ ወደ ውጭ ከወጡ ደግሞ ደረጃ አራት ላይ ይቀመጣል:: ይህንን ማድረግ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ሁኔታውን አውቆ ሕክምናውን በአግባቡ ለመስጠት ነው:: ለአብነት ደረጃ አንድና ሁለት ላይ የተቀመጠው ምድብ የተለየ ችግር ካልገጠማቸው በስተቀር የቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው አይደሉም:: ሦስትና አራት ግን ሕክምናው ተለይቶ እስከ ቀዶ ሕክምና ድረስ የሚደርሱ ሕክምናዎች መውሰድ የግድ ሊሆን ይችላል::

የማህጸን ወደ ውጭ መውጣት ችግር በክፍልም ደረጃ ይቀመጣል:: ይህም የሚሆነው የትኛው የማህጸን ክፍል ወደ ውጪ ወጥቷል የሚለውን ለመለየት ነው:: ከዚህ አንጻርም የፊተኛው፤ የኋለኛውና የላይኛው የማህጸን ክፍል መላላት በሚል ደረጃ ይወጣለታል:: ለምሳሌ፡- የሽንት ፊኛን እና የሴት ብልትን የሚይዙ ጡንቻዎች ወይም ጅማቶች ድክመት ወይንም መላላት፤ መሳሳት ሲገጥማቸው የሽንት ፊኛው በማበጥ ወደ ብልት ሊንሸራተት ይችላል:: ይህም የፊተኛው ግርግዳ መላላት ‹‹ anterior defect (systocele)” በመባል ይታወቃል:: የሽንት ፊኛ መንሸራተት በሚልም ሊጠራ ይችላል::

ሌላው በሕክምናው ቋንቋ የኋለኛው ግድግዳ መላላት ‹‹Posterior defect (rectocele)›› የሚባለው ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ፊንጢጣን እና ብልትን የሚደግፉ ጡንቻዎች ወይንም ጅማቶች መላላት ወይንም መድከም የሚያመጣው የብልት መንሸራተት ችግር ነው::

መከላከያ ዘዴዎች

የማህጸን መውጣት ችግርን ከምንከላከልባቸው ዘዴዎች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው:: በተለይም በብልት አካባቢ ወይንም በወገብ አካባቢ ያሉ የሰውነት ክፍሎችን መርዳት፤ ማጠንከር በመሳሰለው ሁኔታ በብልት አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን ለማጠንከር መሞከር ጠቃሚ ነው :: ልጅ ከወለዱ በኋላ በማህጸን ዙሪያ ያሉ ጡንቻዎች እንዲጠነክሩ ማድረግ ላይ መሥራትም ጠቃሚ ነው::

የሆድ ድርቀትን ለመከላከል ፈሳሽን መጠጣት፤ ምቹ የሆኑ ሆድን የሚያለሰልሱ (ፍራፍሬ፤ አትክልት፤ ባቄላ፤ የመሳሰሉ ምግቦችን መመገብም እንዲሁ ይጠቅማል:: ከፍተኛ ሳልን መቆጣጠር፤ እንደ ብሮንካይትስ ያለ ህመምን መታከም፤ ሲጋራ ማጤስን ማቆምና ከፍተኛ ውፍረትን ማስወገድ ለችግሩ መፍትሄ ከሚሰጡት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው::

ከማህጸን ወደ ውጭ መውጣት ጋር በተያያዘ መከላከል የማንችላቸው ችግሮችም አሉ:: ለአብነት እርግዝናን ማስቆም፤ እድሜ በአለበት እንዲቀጥል ማድረግ አይቻልም:: ስለዚህም መስተካከል የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ መስተካከል የማይችሉም መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል::

ሕክምናው

ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚደረጉ ሕክምናዎች በሁለት መልኩ የሚታዩ ናቸው:: አንደኛው ያለ ቀዶ ሕክምና የሚሰጥበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በቀዶ ሕክምና የሚከናወነው ነው:: የመጀመሪያው ሕክምና የሚሰጠው የማህጸን ወለሉ መላላት፤ የጡንቻዎች መዳከም ሲኖር የሚከናወን ነው:: የላላው ክፍል እንዲጠነክር ለማስቻል የሚሰጡ ሕክምናዎች ናቸው:: ለአብነት የዳሌ ወለል ጡንቻዎችን ሊያጠነክሩ የሚችሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጠቃሚ ነው::

ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሕክምና የወጣውን ክፍል ደገፍ አድርጎ የሚይዝልን ከፕላስቲክ የተሠራ መሳሪያዎችን መጠቀም ነው:: ተግባራቸው የወጣውን ክፍል በመደገፍ ወደነበሩበት ተፈጥሯዊ ሁኔታ መልሶ መያዝ ነው::

ሁለተኛው ዓይነት ሕክምና በቀዶ ሕክምና የሚሠራው ነው:: በዚህ ሕክምና ዋናው አስፈላጊ ነገር የእናትዬዋ ፍላጎት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የወሰደቻቸው ሕክምናዎች መፍትሔ እንዳልሰጧትና ቀዶ ሕክምና እንደምትፈልግ ስትገልጽ ሕክምናው ሊሰጥ ይችላል::

ሌላው ተጓዳኝ ሕመሞች ካሉ በቀዶ ሕክምና ችግሩ እንዲፈታ ይደረጋል:: ለምሳሌ፡- ማህጸን ከካንሰር ጋር ተያይዞ ችግሮች ከታዩበት፤ የማህጸን ደም መፍሰስ ካለ ቀዶ ሕክምናው እንዲደረግ ይወሰናል:: ሌላው ደግሞ በቀዳሚዎቹ ሕክምናዎች ለውጥ ያላሳዩ ችግሮች ካጋጠሙ እንዲህ ዓይነት ሕክምናዎች ይደረጋሉ:: የሽንት፤ የሰገራ ችግሮች ካሉና ምልክቶቹ እየባሱ ከመጡ ቀዶ ሕክምናው ይሰጣል::

የቀዶ ሕክምና ሲደረግ ሁለት ዓይነት አማራጮች አሉ:: ጥሩና የተሻለ አማራጭ ነው የሚባለው ማህጸን ሳይወጣ የላላውን ክፍል ብቻ ወደ ነበረበት መመለስ ነው:: ይህም የሚሠራው በማህጸን በኩል አለያም በሆድ በኩል በመክፈትና የላላውን አካል ተመልክቶ መፍትሔ በመስጠት ነው:: በእኛ ሀገር ደረጃም ያለው አማራጭ ይህ ነው:: ይህ ግን በውጭው ዓለም የተለየ የሕክምና ደረጃ ላይ ደርሷል:: ሆድ ወይም ማህጸን ሳይከፈት የላላውን ክፍል ብቻ ለይቶ የሚስተካከልበት ሕክምና ማድረግ ተችሏል::

ሁለተኛው የቀዶ ሕክምና ዓይነት ብልትን የመዝጋት ሕክምና ‹‹ Obliterative surgeries›› የሚባለው ሲሆን፤ ማህጸንን (ጽንስ የሚሸከመውን) አካል አውጥቶ የላላውን ክፍል የሚስተካከልበት ሕክምና ነው:: ይህ ሕክምና ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ነው ለማለት ያስቸግራል:: ስለዚህም ሕክምናው ሲደረግ የታካሚዋን ፍቃደኝነት መነሻ በማድረግ ነው የሚከናወነው:: አሁን ላይ ከእነዚህ ሕክምናዎች ውስጥ በስፋት የሚመከረው ከሚወስደው ጊዜ፤ ጤናማ ከሆነ እሳቤው፤ ቶሎ የመዳኑ ሁኔታም የተሻለ ነው የሚባለው ሆድ ሳይከፈትና ማህጸን ሳይወጣ የላላውን ቦታ ብቻ ማስተካከል ላይ የሚያተኩረው ነው::

የማህጸን ወደ ውጭ መውጣት ተፈጥሯዊ አቀማመጡ የተዛባ ስለሚሆን አዕምሮ ላይ የሚፈጥረው ጫና ካልሆነ በስተቀር ብቻውን እንደ ችግር ተወስዶ ሕክምና ካላገኘሁ የሚያስብል አይደለም:: ስለዚህም የማህጸን መውጣትን ተከትሎ የሚከሰቱ ችግሮች ለአብነት የሰገራ መውጣት ችግር፤ የሽንት መሽናት ችግርና መሰል ነገሮች ካላጋጠሙ በስተቀር ሕክምና የግድ መወሰድ አለበት አያስብለውም::

ከማህጸን መውጣት ጋር በተያያዘ መወሰድ ያለባቸው ነገሮች አሉ:: አንዱና ዋነኛው የማህጸን መውጣት እርግማን ወይም የማይድን በሽታ አድርጎ መውሰድ አይገባም:: በተጨማሪም ማህጸንን የማይታከም የሰውነት አካል አድርጎ መውሰድም ተገቢነት የለውም:: ማህጸን እንደ ማንኛውም የሰውነት ክፍል የሚታመም፤ ከዚያም ሕክምና አግኝቶ የሚድን ሕመም ነው:: ከታከሙ በኋላ ደግሞ ልጅ አይገኝም፤ ማርገዝ አይቻልም የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት መቀየር ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ታክመው ማርገዝ የቻሉ፤ የወለዱና ልጃቸውን ያቀፉ በርካቶች ናቸውና::

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You