የአገራችን ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው 2011 በጀት ዓመት የ9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። ይህ ዕድገት ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ7 ነጥብ 75 በመቶ እንዲሁም በቀደሙት ጥቂት ዓመታት ከተመዘገበው አማካይ የ8 ነጥብ 65 በመቶ አንጻር ሲታይም ከፍተኛ ነው፡፡ በቀጣይም ከ12 በመቶ በላይ እንደሚያድግም እየተጠበቀ ነው፡፡
የኢኮኖሚው በዚህ ልክ ማደግ በርካታ አንድምታዎች ቢኖሩትም፣ በዋናነት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለም ማደግ የሚችል እንደሆነና በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ለሀገሪቱ ችግር እየሆነ ያለው ግን የዋጋ ግሽበት ማሻቀብ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ግሽበቱን ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎች ቢሰሩም፣ ከሁለት አሀዝ ንቅንቅ ሊል ካለመቻሉም በተጨማሪ በግንቦት ወር ወደ 16 በመቶ አሻቅቦም ነበር፡፡ ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ያለበት ሁኔታም የዚሁ ችግር ሌላው መገለጫ ነው፡፡
መንግስትም ይህን የዋጋ ግሽበት በሚቀጥለው በጀት ዓመት ለመቆጣጠር በትኩረት እንደሚሰራ በድጋሚ አረጋግጧል፡፡ ውሳኔው ተገቢም ወቅታዊም ነው፡፡
በመሰረቱ አቅርቦት ከስንዴ፣ዘይት፣ስኳር አንስቶ በጣም ሰፊ እንደመሆኑ ስራውም እጅግ ሰፊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ለአቅርቦትና ለመሰረታዊ ፍጆታ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬም እንዲሁ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ አቅርቦቱን በአጭር እና በረጅም ጊዜ ለይቶም መስራትን ይጠይቃል፡፡
እንደሚታወቀው ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬን በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልጉ እና ልማቷን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ግዙፍ የሀይል ማመንጫዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የባቡር መስመሮችን፣ ዩኒቨርስቲዎችን፣ ወዘተ እየገነባች ትገኛለች፡፡ ከተለያዩ አበዳሪ ተቋማት የተበደረችውን እየከፈለችም ነው፡፡ እነዚህ ስራዎች በራሳቸው ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬን ይጠይቃሉ፡፡
ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ከወጪ ንግድ፣ ከብድር፣ እርዳታ፣ ስጦታ፣ ከውጪ ከሚላክ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝ ቢሆንም፣ይህ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንደበፊቱ የሚታለብ አይደለም፡፡ የወጪ ንግዱ ባጋጠሙት ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ተግዳሮቶች የተነሳ ተቀዛቅዟል፡፡ አበዳሪ ተቋማት በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ብድር እንድትከፍል እንጂ እንድትበደር ብዙም አይፈልጉም፡፡
በእዚህ ወሳኝ ወቅት ነው እንግዲህ ግሽበቱ የውጭ ምንዛሬን የሚጠይቅ የአቅርቦት ስራ ውስጥ ሀገሪቱ በስፋት እንድትሰማራ እያስገደደ ያለው፡፡ ይህን ብርቱ ስራ ለማከናወን በወጪ ንግዱ፣በብድር ጥያቄው እና በመሳሳሉት ላይ አሁንም በትኩረት መስራቷን አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል፡፡
ብድር መመለስ መጀመር በራሱ ጥሩ ለውጥ ነው፡፡ ጥሩ ተበዳሪ መሆንን ያመለክታል፡፡ በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ብድር የሚከፍለበትን ዘመን ያስረዘመችባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ የብድር ወለድ ላይ የተሰራም አለ፡፡ በወጪ ንግድ ላይም እንዲሁ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፡፡
ሀገሪቱ የቅባት እህል ወደ ውጪ እየላከች በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ዘይት ከውጭ እያስገባች ትገኛለች፡፡ የዳቦ ስንዴ፣ ስኳር እና ዘይትም አሁንም የሀገሪቱ መሰረታዊ ችግሮች ሆነው በውጭ ምንዛሬ እየተገዙ ናቸው፡፡
የሚያሳዝነው እነዚህንና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ሊያለማ የሚችል ሰፊ ለም መሬትና ለመስኖ ሊውል የሚችል የውሃ ሀብት እያለ ነው ይህ ችግር ክፉኛ እንደተጣባን የቀጠለው፡፡ አቅርቦትን ለማሳደግ እና ግሽበቱን ለመቆጣጠር በእርሻ ስራው ላይ ሰፋፊ ስራዎችን መስራት ቀጣይ አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል፡፡
የግብርና ስራ ዘለው የሚሳፈሩበት አይደለም፤ ልምድ ይጠይቃል፡፡ አርሶ አደሩንና ማህበራቱን እየደገፉ በመስኖና በመሳሰሉት ስራዎች በስፋት የሚያመርቱበትን ሁኔታ የመፍጠሩ ስራ እንዳለ ሆኖ የውጭ ባለሀብቶችን መሳብም ይገባል፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ ባለሀብቶች እየተመለመሉ እንዲሰሩ እንደሚደረገው ሁሉ በግብርናው መስክም እንዲሁ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው በስፋት የሚሰማሩበትንና ምርታቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡበትን መንገድ መፍጠር ይገባል። ይህም የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያስችል ሌላ መንገድ ይሆናል፡፡
በስኳር በኩል የተጀመሩትን ፋብሪካዎች በመጨረስ አንድ እርምጃ ወደፊት መውሰድ ይቻላል፡፡ በዘይት ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ግን አይስተዋልም፤ ገና ውሃውም አልሞቀም፡፡ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በዘይት ላይ ፈጥኖ መንቀሳቀስንም ይጠይቃል፡፡ ከእዚህ አኳያ ሊከናወኑ የታሰቡት ስራዎች ‹‹የስኳር ወሬ›› ሆነው በማይቀሩ መልኩ በአጭርም በረጅምም ታቅደው ሊሰራባቸው ይገባል፡፡
የውጭ ባለሀብቶቹ እስከ አሁን ባለው መንገድ ከልማት ባንክ ብድር የሚቀላውጡ ሳይሆን የራሳቸውን ካፒታል ይዘው የሚመጡ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህም የፋይናንስ ስርአቱን ከማሻሻል አንስቶ ያለውን የገበያ ስርአት መቃኘት ይገባል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች የራሳቸውን ካፒታል ይዘው እንዲመጡ ማድረግ እንጂ የልማት ባንክን የውጭ ምንዛሬ የሚቀላውጡ እንዳይሆኑ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡
በሀገራችን በግብርናውና በአንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ላይ የተሰማሩ አንዳንድ የውጭ ኩባንያዎች ከልማት ባንክ ተበድረው ወደ ልማቱ ከገቡ በኋላ ለሀገሪቱ ምንም ሳይፈይዱ ከሰርን እያሉ ከሀገሪቱ እየወጡ ያሉበት ሁኔታ በሚገባ ሊጠናና የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፣ በቀጣይ ባለሀብቶችን ለመሳብ ለሚደረገው ጥረት መደላድል ማስቀመጥም ያስፈልጋል፡፡
ለአቅርቦት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ እና የሀገር ውስጥ ምርት ፍላጎትን ለማሟላት የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ ወቅታዊም ተገቢም ነው፡፡ ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ከካፒታል፤ ከልምድ፣ ከውጭ እና የሀገር ውስጥ ገበያ አኳያ በእርግጥም ተገቢ ነውና!!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 16/2011