.የትራፊክ አደጋን፣የአየር ብክለትንና የነዳጅ ፍጆታን እንደሚቀንስም ተገልጿል
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ሶስት ሳምንት የሆነውና በከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የሰዓት ገደብ በትራፊክ መብራቶች አካባቢ ይታይ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ መቀነሰ እያስቻለ መሆኑን የከተማዋ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በከተማዋ የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ፣የአየር ብክለትንና የነዳጅ ፍጆታን እንደሚቀንስም ኤጀንሲው ገልጿል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂሬኛ ሂርጳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የሰዓት ገደቡ ተግባራዊ መሆን በጀመረበት የመጀመሪያ ሳምንት ያመጣውን ለውጥ አስመልክቶ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተሰራ ጥናት ባይኖርም በተለይ በትራፊክ መብራቶች ላይ ይታይ የነበረውን መጨናነቅ መቀነስ እያስቻለ ነው፡፡ በሥራ መግቢያና መውጪ ሰዓት ላይ ሰዎች ሳይጨናነቁ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ እና ከሥራ ገበታቸው ወደቤታቸው ያለትራፊክ መጨናነቅ እንዲመለሱ እያስቻለ ነው ፡፡
የግል ትራንስፖርት ምልልስ መሻሻሉንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ላይ እንደልብ ትራንስፖርት ያለእንግልት ለማግኘት እንዳስቻለም ገልፀዋል፡፡
የሰዓት ገደቡ የትራፊክ ፍሰቱን ከማሻሻል ባሻገር በመንገድ ደህንነት ላይም ትልቅ ለውጥ ያመጣል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይ በከባድ ተሽከርካሪዎች ምክንያት ይደርስ የነበረውን የትራፊክ አደጋ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አመልክተ ዋል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ በሚያወጡት ጭስና ተሸክመዋቸው በሚሄዱት አቧራ ምክንያት የሚደርሰውን የአየር መበከል እንደሚቀንስም ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤የሰዓት ገደቡ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ስለሚያሳለጥ የተሽከርካሪዎችን የነዳጅ ፍጆታ በመቀነስ በኩልም ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ በዚህም ሀገሪቷ ለነዳጅ ግዢ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስም ይረዳል፡፡
በቀጣይም የከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴ ስርአት እንዲይዝና እንቅስቃሴው ለኢኮኖሚው አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ለማድረግና የትራፊክ አደጋንም ለመቀነስ በአሁኑ ወቅት የተጀመሩትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚወሰዱም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀ ዋል፡፡
ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የከባድ ጭነት ተሽከርካሪ የሰዓት ገደብ ከአሽከርካሪዎች በኩል ቅሬታ እያስከተለ ስለመሆኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 16/2011
አስናቀ ፀጋዬ