የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛው አቶ ፍቃዱ አሰፋን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ችግኝ ሲተክሉ አገኘናቸው፡፡ ከሐምሌ 22 ሀገር አቀፉ ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› የችግኝ ተከላ አስቀድሞ ተከላውን ሥራውን ለመጀመር በማሰብ መካሄዱን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ችግኝ መትከል ለትውልድ ሀብት ማስቀመጥ ነው›› የሚሉት አቶ ፍቃዱ ‹‹አባቶቻችን የደረቀ ዛፍ እንጂ ለምለም ዛፍ አይቆርጡም ነበር።››ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ለምለም ዛፍ መቁረጥን ልጅ እንደ መግደል አድርገው ያስቡት ነበር ።በአንዳንድ እምነቶችና ጎሳዎች ዛፍ መቁረጥ መጥፎ ባህል ተደርጎ ይታሰባል፤ ይሄን ማጎልበት አለብን።›› የሚሉት አቶ ፍቃዱ፣ዛፍ መትከል ብቻ ሳይሆን መከታተልም እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹የተወሰነ ገንዘብ እያዋጣን ጠባቂና ተንከባካቢ ብንቀጥር ችግኙም ይለማል ፤ሰዎችም ሥራ ያገኛሉ›› ሲሉ ይናገራሉ።
ወይዘሪት መሰሉ አበበ ከዚህ ቀደም በቦሌ ለሚ ፓርክ ከባልደረቦቻቸው ጋር የተከሏቸው ችግኞች ከመጽደቅም አልፎ አድገው ለማየት ችለዋል። ትናንትም በፓርኩ ተገኝተው ችግኞችን ተክለዋል፡፡ለተከላው ጉድጓድ ተቆፍሮ ማግኘታቸውን፣ችግኞቹም በአቅራቢያው ዝግጁ መደረጋቸውን ያመለክታሉ። ሁሉም ከጉድጓዱ ውስጥ ውሃውን እያወጣ በተሰጠው ገለጻ መሰረት ተከላውን ማካሄዱን ተናግረዋል፡፡
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በአትክልት ልማት የሚሠሩት አቶ ዓለሙ ጌታቸው ለሚኒስቴሩ ሠራተኞች ችግኝ ተከላ 15ሺ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ችግኞቹን መንከባከብ ሥራቸው መሆኑንና በየእለቱም ክትትሉን እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
በሚኒስቴሩ የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ቡድን መሪ አቶ አዋሽ ይርጋ በበኩላቸው በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ችግኞቹን መትከል የተፈለገው ግቢው የታጠረ እና ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጸ በመሆኑ ነው ይላሉ። ፓርኩ አትክልት ተንከባካቢ ሠራተኞች እንዳሉትም ጠቅሰው፣ይህም ችግኞቹ በተሻለ መልኩ እንዲጸድቁ እንደሚረዳ ይገልጻሉ።
‹‹እኛ እንተክላለን፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ደግሞ ቀጣይ እንክብካቤ ያደርጋል።››ያሉት አቶ አዋሽ፣በትናንቱ እለትም በቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች 20 ሺ 930 ችግኞች መተከላቸውን ነው ያብራሩት፡፡
ለአካባቢ ስነ ምህዳር የሚስማማ ችግኝ ለመትከል በኮሚቴ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፣ ችግኞቹ በኮተቤ ችግኝ ጣቢያ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የፊታችን ሐምሌ 22 ቀን ለሚካሄደው የአረንጓዴ ልማት ቀንም ወደ ፊቼ ከተማ አካባቢ የመትከያ ስፍራ እየተመቻቸ መሆኑን ጠቅሰው፣ 50ሺ የሚደርሱ ችግኞች ለመትከል መታሰቡን አስታውቀዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ላይ የአረንጓዴ ልማት ሥራው አረንጓዴ አሻራ ማሳረፍን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ይህም ሀገሪቱ የምትከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት አካል መሆኑን ነው የተናገሩት።
‹‹የአረንጓዴ ልማት ሥራው ኢትዮጵያ የምትታወቅበት ጉዳይ ነው›› የሚሉት ሚኒስትሯ፣ ሀገሪቱ በሀገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ፊታውራሪ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም አፍሪካን በመወከል በማደግ ላይ ያሉት ሀገሮች ድጋፍ እንዲያገኙ ስትከራከር መቆየቷንም አብራርተዋል።ችግኝ ተከላው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር የሚረዳ ወሳኝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና 15 የሚሆኑ ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች በቦሌ ለሚና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ችግኞችን መትከላቸው ታውቋል ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 16/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ