አዲስ አበባ፡- ዩኒቨርሲቲዎች ሀገሪቱ የምትፈልገውን የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት በልማቱ ዘርፍ የምታሳየው ለውጥ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን እያበረከቱ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ገለጹ፡፡
አድማስ ዩኒቨርሲቲ ከትናንት በስቲያ የዕለቱ የክብር እንግዳ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በተገኙበት በተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮች ያስተማራቸውን 7ሺ ተማሪዎች አስመረቀ፡፡
ፕሮፌሰር ጣሰው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ባለፉት 28 ዓመታት ወደ 50 የሚጠጉ የመንግሥትና ከ170 በላይ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከፍተው ሀገሪቱ የምትፈ ልገውን የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት በልማቱ ዘርፍ የምታሳየውን ለውጥ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
ፕሮፌሰር ጣሰው፣ መንግስት ባመቻቸው ዕድል ተጠቅመው በግሉ ሴክተር ከተሰማሩ በርካታ ተቋማት በተለይ ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ካሉት 4ቱ የግል ተቋማት አንዱና አንጋፋው አድማስ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ አስረድተ ዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እስካሁንም ያስመዘገበውን አመርቂ ውጤትና የገነባውን መልካም ስም በማስጠበቅ ለጥራት፣ ለማህበራዊ አገልግሎትና ለጥናትና ምርምር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋዬ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን ሕዝብ በማገልገል፣ በመደገፍና በማልማት ከዚህን ቀደም ሲያደርገው የነበረውን እንቅስቃሴ አሁንም እያጠናከረ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ የማህበረሰብ አገልግሎት ስትራቴጂ ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተው፤ በዚህ መሰረት የተለያዩ የህብረተሰቡን ችግር የሚዳስሱ ጥናቶችን በማካሄድ የተለያየ የነፃ ስልጠናዎችንና ድጋፎችን መስጠቱንም አስረድተዋል፡፡
በዕለቱ የማዕረግ ተሸላሚ በመሆን ዋንጫ የተሸለመችው የአካውንቲንግና ፋይናንስ ክፍል ትምህርት ተማሪ ሩታ አካለወልድ እንደተና ገረችው፤ ለዚህ ውጤት የበቃችው ጠንክራ በመማሯ ነው፡፡ በተማረችው የትምህርት መስክ ለሀገሯና ለወገኗ በታማኝነት ማገልገል ትፈልጋ ለች፡፡
ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ሰባት ሺ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሐ ግብሮች ያስመረቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዲግሪና በቴክኒክና ሙያ በመደበኛና በርቀት ትምህርት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በሶማሌ ላንድና በፑትላንድ ከ30 ሺ በላይ ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ ይገ ኛል፡፡ ላለፉት 20 ዓመታትም በመደበኛና በርቀት ትምህርት በዲግሪ፣በዲፕሎማና በሰርተፍኬት ከ70 ሺ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወ ሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 16/2011
ሐይማኖት ከበደ