የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር በአቅርቦት ላይ አጽንኦት ሰጥቶ እንደሚሰራ መንግሥት አስታውቋል፡፡ በአቅርቦት ላይ ለመስራት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትም የግሉን ዘርፍ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ አቅርቦቱ ላይ ለመነጋገር የመንግሥት እቅድ በዝርዝር መውጣት እንደሚኖርበት ጠቅሰው ‹‹ስንዴ፣ ስኳር ፣ዘይት እና በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉትን ሁሉ ማምረት አለብን፡፡››ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ በአቅርቦቱ ላይ ለመስራት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አለማግኘት ትልቁ ተግዳሮት ሊሆን ይችላል፡፡ለእነዚህ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ሀገሪቱ አሁን ከወጪ ንግድ፣ከእርዳታ ፣ከብድር እና ዜጎች ለቤተሰብ ከሚልኩት በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ማሳካት እንደሚያዳግት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይገልጻሉ፡፡
እነ ኬንያ ያላቸው የመሬትና የውሃ መጠን በጣም ትንሽ መሆኑን፣ኤክስፖርታቸው ግን በጣም ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ አብዛኛው ኤክስፖርታቸው ከአግሮ ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዘ መሆኑን በማመልከትም ሀገራችን እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የማትችልበት ሁኔታ እንደማይኖር ይጠቁማሉ፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ግሽበቱን ከፍ አድርገውታል ከሚባሉት አንዱ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ እየጨመረ መምጣት መሆኑን በአብነት ጠቅሰው፣ ‹‹ይሄ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቃለል አይደለም፤ የእህል ዋጋው ሊረጋጋ የሚችለው ገና ተመርቶ እንደመሆኑ አሁን ላለው ችግር መፍትሄ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም›› ይላሉ፡፡
ለአቅርቦቱ መጨመር ግብአቶች፣ መሳሪ ያዎች፣ የውጭ ባለሙያ፣ ቁሳቁስ ፣ወዘተ ሊያስ ፈልጉ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ ለእዚህ ግዥ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የወጪ ንግዱ የወደቀበትን ምክንያት በቅድሚያ ማጥናት እና መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡
ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ አንዱ ምክንያት የዓለም ገበያ ዋጋ መውደቅ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፣ የምርጥ ጥራት ችግር፣የሀገሮች እና ኩባንያዎች የተሻለ ምርት ይዞ መቅረብ፣ባለፉት ዓመታት የተከሰተው አለመረጋጋት ይህን ተከትሎ በኩባንያዎች ላይ የደረሰው ጉዳትም ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ በመጥቀስ እነዚህን ማስተካከል እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አብዛኛዎቹ በንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣በእርሻ እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩት የውጭ ባለሀብቶች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
አቶ ክቡር የዶክተር ቆስጠንጢኖስን ሀሳብ በማጠናከር የሀገሪቱ የግሉ ዘርፍ የተጎዳ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡የግል ዘርፉ ከፍተኛ እድሳት እንደሚያስፈልገው፤የንግድ ምክር ቤቱም አቅም ማማከር የሚችል መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡ ፡በዚህ ውስጥ የመንግሥት ሚና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍተኛ እንደሆነም ነው የሚናገሩት፡፡
እንደ አቶ ክቡር ገለጻ፤ያለመንግሥት ንቁ ተሳትፎ ይህን ኢኮኖሚ ማንቀሳቀስ አይቻልም፡ ፡ በኢኮኖሚ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ አገሮች አሁን ሀገሪቱ ያጋጠማትን አይነት ችግር ሲገጥማቸው መንግሥታቱ ኢኮኖሚውን ማንሳት ባለባቸው ሁኔታ ላይ በትኩረት ይሰራሉ፡፡
የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ የግሉም ዘርፍ እንደገና መንቀሳቀስ እንደሚጀምር አቶ ክቡር ተናግረው፣በዚህም ኢኮኖሚው ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ሀገሪቱ አስፈላጊዎቹ የውጭ ባለሀብቶች እንደሌሏት፣ የመጡትም ጥለው የሚወጡባት መሆኗን ጠቅሰው፣ መንግሥት የውጭ ባለሀብቶች ምንም ሳይሰሩ የሚወጡበትን ሁኔታ በአስቸኳይ ማስተካከል እንደሚኖርበት ያስገነዝባሉ፤‹‹ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር እስከምንፈጽም ድረስ እነዚህ ካፒታል ይዘው የሚመጡ ባለሀብቶች ያስፈልጉናል›› ይላሉ፡፡
ሀገሪቱ የቅባት እህሎች ወደ ውጭ እየላከች የምግብ ዘይት ከውጭ ለማስመጣት ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማውጣት እንደሌለባት የሚናገሩት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ካፒታሊስቶችን በማምጣት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚኖርባትም ያመለክታሉ፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት፤ይህችን ሀገር ሊያሳድጉ የሚችሉ ኢንቨስተሮች መምጣት የሚችሉት በሀገሪቱ ሌላው ዓለም የደረሰበት የፋይናንስ ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡የፋይናንስ ስርዓቱን ማሻሻል ከተቻለ የውጭ ባንኮች ካፒታል ይዘው የሚመጡበት ሁኔታ ይፈጠራል፤በዚህም የግሉን ዘርፍ ማሳደግ እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰሩ ምቹ ሁ ኔታ መፍጠር ይቻላል፡፡
‹‹ኢንቨስተሮች በኪሳቸው ዶላር ጠቅጥቀው አይመጡም፡፡ሊያበድራቸው የሚችል ባንክ እያሰቡ ነው የሚመጡት፡፡››ሲሉ ገልጸው፣ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ካደረጉት አብዛኛዎቹ የቱርክ፣ ቻይናና ህንድ ባለሀብቶች ከልማት ባንክ ለመበደር የመጡ መሆናቸውን ይገልጻሉ ፡፡
አቶ ክቡር ባለሀብቶችን በመሳብ ሂደት ‹‹ምን አይነት የውጭ ኩባንያ ነው እንዲገባ የሚፈለገው የሚለው መጀመሪያ መታየት አለበት›› ይላሉ፡ ፡ የዶክተር ቆስጠንጢኖስን ሀሳብ በማጠናከርም የውጭ ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ ባንኮች መበደር እንደሌለባቸው ይናገራሉ፡፡‹‹የውጭ ባለሀብት ካፒታል ይዞ መምጣት ይኖርበታል፣በስንት መከራ የተጠራቀመውን የውጭ ምንዛሪ መሻማት የለበትም፤ አሁን የተያዘው ግን መሻማት ነው፡፡ ››ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እርሻ በትንሽ ነገር እንደሚበላሽ ጠቅሰው፣በዚህ ዘርፍ ላይ ይበልጥ መስራት የሚቻለው በተለይ የሰፋፊ እርሻ ሥራ ልምድ ካላቸው ሀገሮች ባለሀብቶችን በማምጣት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በእነዚህ ባለሀብቶች ወጣቶችን ማሰራት እንደሚቻልም ይገልጻሉ፡፡
አቶ ክቡር ሀሳብ በማጠናከር እርሻ ለኢንቨስትመንት በጣም አስቸጋሪ ዘርፍ መሆኑን በመጥቀስ የዶክተር ቆስጠንጢኖስን ያጠናክራሉ፡፡ የግሉ ዘርፍ ሊሰማራበት የማይገባ ዘርፍ በማለትም ከዶክተር ቆስጠንጢኖስ የተለየ ሀሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ የግል ባለሀብቱ በራሱ ገንዘብ እርሻ ውስጥ መግባት እንደማይፈልግም ይገልጻሉ፡፡
የእርሻ ኢንቨስትመንት ቢሰጥ የሚሻለው በአካባቢው ለሚኖረው ህብረተሰብ መሆን እንዳለበት አቶ ክቡር ይጠቁማሉ፡፡አርሶ አደሩ ለዘመናት ያካበተው የግብርና እውቀት እንዳለው በመጥቀስ የዶክተር ቆስጠንጢኖስን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ የአርሶ አደሩንና የህብረት ሥራ ማህበሩን አቅም በስልጠናና በመሳሰሉት ድጋፎች በማጠናከር በግብርና ኢንቨስትመንቱ እንዲሰማሩ ማድረጉ የተሻለ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡
‹‹በሀገሪቱ አሁን ብዙ ነገሮች እየተቀየሩ ናቸው፡፡›› የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ የልማት ባንክ አስተዳደር እንደገና በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራ ፣የብድሩ ሁኔታም እየተስተካከለ ነው››ሲሉ ጠቅሰው፣ሀገሪቱ ኢንቨስትመንትና ንግድን በቀላሉ ከመጀመር አንጻር ያለችበትን ዝቅተኛ ደረጃ ለመለወጥ መንግሥት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም መልካም ተግባር ብለውታል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት፤ባለሀብቶች ማስተዳደር ላይ በስፋት መስራት ያስፈልጋል፤የውጭዎቹንም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ብቃት ባላቸው ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያን ከሌሉም የውጭ ሀገር ዜጎች መጥተው እንዲያስተዳድሯቸው ማድረግ ይገባል፡፡
ባለሀብቶቹ ተመልሰው የሚሄዱበት ምክንያት ምንድን ነው፡፡መጀመሪያ ማነው ያመጣቸው?ሲመጡ ምን አይነት ምዘና እና ድጋፍ ያደርግላቸዋል? የሚሉት ጥያቄዎችም መመለስ እንደሚኖርባቸው ይጠቁማሉ፡፡ከመሰረተ ልማት ጀምሮ እስከ ጸጥታ ማስከበር ድረስ ያለው ችግርም መታየት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
የፋይናንስ ሥርዓቱ ይሻሻል ሲባል ልቅ ይሁን ማለት እንዳልሆነም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ጠቅሰው፣ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችሉ ብቃት ያላቸው ትላልቅ ሬጉሌቲንግ ኤጀንሲዎች ሊኖሩ እንደሚገባም ያመለክታሉ፡፡‹‹ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ማለት ማስቆም አይደለም፤ህጉን ተከትለው መሄዳቸውን መከታተል ነው፤ህጉን ከመጣሳቸው በፊት መምከር ነው›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡
‹‹የውጪ ባንኮች ቢመጡ ዝም ብለው አያበድሩም፡፡ካበደሩም በኋላ ይከታተላሉ፡፡የኛም ባንኮች በባንክ ህጉ መሰረት ይህን የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ››ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
አቶ ክቡር ባለፉት ዓመታት ንግዱን ስርዓት ለማስያዝ በሚል ከወጡ ህጎች አብዛኛዎቹ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆናቸውንና መስተካከል እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ አዋጭ በሆነ መንገድ ሰው ወደ ሥራ የሚመልስበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
ባለፉት ዓመታት ምንም እንኳ ገና ሥራ ላይ ባይውሉም ከደንብና መመሪያዎች አንጻር አሰራሮችን ለማቅለል እየተሞከረ መሆኑን ጠቅሰው፣እንደዚያ ሲሆን ወጣቱን ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚቻል፡፡ በቀጣይም የንግድ ማህበረሰቡን ለማሳደግና ንግዱን ለማጠናከር ብዙ መሰራት እንደሚኖርበት ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 16/2011
ኃይሉ ሣህለድንግል