አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በምክር ቤቱ አባላት ፊት ቃለ መሃላ ፈፅመዋል፤ ባህር ዳር፡- የአማራ ክልል ምክር ቤት የአቶ ተመስገን ጥሩነህን የርእሰ መስተዳድርነት ሹመት አጸደቀ ፡፡ ‹‹ሰላም በማስጠበቅ የኢኮኖሚ እድገት ለማሳካትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የህግ የበላይነትን ማስፈን የክልሉ መንግሥት ተቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል›› ሲሉ አዲሱ የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ፡፡
የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ እንደሚሰሩም ገለፁ፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 5ኛ ዙር፤ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤው ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድርነት በእጩነት የቀረቡትን የአቶ ተመስገን ጥሩነህን ሹመት መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
አዲሱ ርዕሰ መስተዳድርም ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ‹‹የፖለቲካችን ምሰሶና የኑሯችን ዋስትና የሆነውን ሰላማችንን በማስጠበቅ የኢኮኖሚ እድገታችንን ቀጣይነት ለማሳካትና የህዝቦቻችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የህግ የበላይነትን ማስፈን ለነገ የማንለው ተቀዳሚ አጀንዳችን ይሆናል” ብለዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት በከፍተኛ ደረጃ ተናግቶ መቆየቱን አቶ ተመስገን አስታውሰው፣ ‹‹የተለያዩ የውጭና የውስጥ ሰበቦችና የመጠቃት ስሜቶችን እያስተጋባን በአቅማችን ሰላምና ጸጥታችንን በማረጋገጥ ረገድ ሊከናወኑ የሚገባቸውን ሥራዎች በአግባቡ ሳንሰራ ቆይተናል፡፡›› ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ተመስገን ማብራሪያ፤ ስርዓትን በማስፈንና የተረጋጋ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር በማረጋገጥ ረገድ በክልሉ ከፍተኛ ክፍተቶች ተስተውለዋል፡፡ ክልሉ የብጥብጥና የሁከት ማዕከል እንዲሆን ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት በሚፈልጉ ኃይሎች ገፊነት በዘፈቀደና በስሜት በሚነዱ ውስን ግለሰቦችና አካላት አስተባባሪነት በቀልን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ተፈፅመዋል፡፡ ግድያዎች፣ የንብረት ውድመቶችና መፈናቀሎች የህዝቡን ሰላም፣ ነጻነትና የኑሮ ዋስትናን የሚያናጋ ሂደት ተስተውሏል፡፡ በድምሩ ስርዓተ አልበኝነትን የማንገስ የታለመና የተጠና አካሄድም ታይቷል፡፡
የሰላም ችግሮች የህዝቡ ቅሬታ እንዲበራከት ማድረጋቸውን ርእሰ መስተዳድሩ ጠቅሰው፣ በየአጋጣ ሚውና በየአካባቢው የሚፈጸሙ ተራ ወንጀሎችም ያለማንም ተጠያቂነት ስፋታቸው እየገዘፈ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ላይ ተጨማሪ ስጋት በመደቀኑ ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው ለመግባት የሚሳቀቁበት ነባራዊ ሁኔታ ተፍጥሯል፡፡›› በማለትም የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የክልሉ መንግሥት፣ የጸጥታ አካላትን አቅም ከመገንባት ጎን ለጎን የመላውን ህዝብ ተሳትፎ በማሳደግ ህዝቡን የሚመጥን አመራር ለመስጠት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ፣ ‹‹የአማራ ክልል ህዝቦች ከመላው የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በአብሮነት መንፈስ ለረጅም ዓመታት ቢኖሩም፣ በተዛባ የፖለቲካ አስተምህሮ ምክንያት አንድነታችንና ሰላማችን አደጋ ተደቅኖበታል፡፡›› ሲሉ ገልፀው፤ ‹‹የተዛባ የፖለቲካ አስተምህሮውን ለማስተካከል እየተደረገ ያለው ትግል ስኬታማ እንዳይሆን የሴራ ፖለቲከኞች የአማራን ህዝብ ለፖለቲካ ትርፍ ለማዋል ባላቸው ፍላጎት ሳቢያ ውጤቱ አዝጋሚ ከመሆኑም በላይ ህዝቡን አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለው ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
የክልሉ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የክልሉን የውስጥ ሰላም ከማስፈን ባሻገር የአማራ ክልል ህዝቦች ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል የተለየ ትኩረት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ተመስገን ገለፃ፤ በክልሉ ህዝቦች የሚነሱ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መፈታት የሚገባቸው መሆኑን የክልሉ መንግስት ያምናል፡፡ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው የለውጥ አካላት ጋር በትብብርና በባለቤትነት ስሜት ለመስራት ዝግጁ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 16/2011
መላኩ ኤሮሴ