ድሬዳዋ፡- በኢትዮጵያ ብሄረ ግንባታ (ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት) እርስ በርስ ከሚያቃርነን ማንነት ድርብ ወደሆነ ማንነት መሄድ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ መድረክ ትናንት “ሀገረ መንግሥት ግንባታና ብሄራዊ መግባባት በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ ሲካሄድ በፀጥታ ጥናት ተቋም የምርምር ባለሙያ ዶክተር ሰሚር ዩሱፍ “የብሄረ ግንባታ ውጣ ውረድ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ፀሁፍ እንደገለፁት፣ የብሄረ ግንባታ በሰዎች መካከል ወጥ እና ብሄራዊ ማንነት እንዲፈጠር የሚሰራ ነው። ስለሆነም ድርብ ወደሆነ ማንነት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት።
“የብሄረ ግንባታ ሥራ የመንግሥት ሥራ ሆኖ ቀጥሏል” ያሉት ዶክተር ሰሚር፣ “በሀይለስላሴ ፣ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን የተሰራው ሥራ ግን ውጤታማ አልሆነም። ስለሆነም አሁንም ቢሆን ወጥ የሆነ ብሄራዊ ማንነት ያስፈልጋል፣ ለዚህ ደግሞ የሚያስተሳስር ገመድ ያስፈልገናል ብለዋል።
የብሄረ ግንባታው ያልተሳካው ተገዳዳሪ የሆኑ ንዑስ ብሄርተኝነቶች እያደጉ በመምጣታቸው መሆኑን ገልፀው፣ ለዚህ መንስዔው ደግሞ የአውሮፓ ቅኝ ግዛት፣ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል እና የማርክሲዝም ሀሳብ መሆኑን ጠቅሰው፣በዚህም መንግሥታዊ ብሄረ ግንባታው ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የንዑስ ብሄር ክስመት ስጋት መሆኑን አመልክተዋል።
በኢህአዴግ (ቀዳማዊ) ዘመን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ከመንግሥት ወደ ህዝብ መውረዱን አስታውሰው፣ በዚህ ሂደት መንግሥት ንዑስ ብሄርተኝነቶች የሚፋፉበትን መንገድ ዘርግቷል ብለዋል። ንዑስ ብሄርተኞች በተማከለ አስተዳደር እንዲያድጉ መደረጉን የገለፀት ዶክተር ሰሚር ፣በዚህም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትና ንዑስ ብሄርተኝነት በጋራ ያደጉበት ሁኔታም ተፈጥሯል ብለዋል።
የንዑስ ብሄርተኝነት ማደግ በአንዳንዶቹ የመቀንጨር ስሜት ፈጥሮባቸዋል ያሉት ዶክተር ሰሚር፣ በዚህም የራሳቸውን ብሄር ከስርዐቱ ውጨ የሚያደርግ ዝንባሌ መፈጠሩን አስታውሰዋል።
ንዑስ ብሄርተኝነቶቹ በርካታ ፍልሚያዎች ያሉባቸው ናቸው ያሉት ዶክተር ሰሚር፣ ግጭቶቹም ከአገዛዙ ጋር፣ ሁለቱም ብሄርተኝነቶች (ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነቶችና ንዑስ ብሄርተኝነቶች ) መካከል እንዲሁም በንዑስ ብሄርተኝነቶች መካከል የነበሩ ቢሆንም መንግሥት ጠንካራ በመሆኑ ከቁጥጥር ውጪ መውጣት አልቻሉም ብለዋል። በ’’ዳግማዊ ኢህአዴግ’’ ደግሞ ሁሉም ገንፍሎ ከቁጥጥር ውጭ የሚሆንበት ሁኔታ መከሰቱን አስታውሰው፣ ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ምሽግ የነበረው አካባቢም ወደ ንዑስ ብሄርተኝነት ወርዷል ብለዋል።
እንደ ዶክተር ሰሚር ገለፃ፣ ለብሄረ ግንባታ መፍትሄው እርስ በእርስ ከሚያራርቀን ማንነት ይልቅ ወደ ድርብ ማንነት መሄድ ነው፡፡ ይህ ሲደረግ ግን ብሄረ ግንባታው ለንዑስ ብሄር ክስመት ስጋት መሆን የለበትም፡፡ ይልቁኑ ሌላውንም የማያጠፋና ሁሉንም አቅፎ የሚሄድ መሆን አለበት ፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ፈርጀ ብዙ እና የሰለጠነ ውይይት ያስፈልጋል።
የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ በበኩላቸው፣ ብሄረ ግንባታ የሚሳካው የጋራ እሴቶቻችን ሲጎለብቱ እንደሆነ ጠቅሰው ፣እነዚህ እሴቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ይጠቅማሉ ሲሉ አመልክተዋል።
ለብሄረ ግንባታው ፍትሀዊ የሀብትና የስልጣን ክፍፍል ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ኮንቴ ፣ የህግ የበላይነትን ማስከበር፣ ማህበራዊ ካፒታልና የህዝብ ተሳትፎ ማሳደግ ፣አስተማማኝ ፍትህ ማስፈን ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ ሀገር መገንባት የሚቻለው በመግባባት፣ በምክክርና ግጭቶችን በማስወገድ መሆኑን አመልክተው፣ የህግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊ ስርዐት ማስፈን ሳይነጣጠሉ የሚሄዱበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰዋል። ልዩነት ተፈጥሯዊ ቢሆንም በሰለጠነና በመወያየት መፍታት እንጂ ጥይትና ድንጋይ ለማንሳት መነሻ መሆን የለበትም ሲሉም አሳስበዋል።
ከአዲስ አበባ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው በዚህ መድረክ ከሶማሌ፣ አፋር፣ ድሬዳዋ፣ ሐረሪና ኦሮሚያ የተውጣጡ ምሁራንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 16/2011
ፍቃዱ ሞላ