ላለፉት 28 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየው የኢህአዴግ አስተዳደር አገራችን አሁን ለደረሰችበት በጎም ሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ድርጅቱ በአራት ብሔራዊ ድርጅቶች የተዋቀረ ሲሆን በውስጠ ደንቡም መሰረት አገሪቷንና ክልሎችን ሲያስተዳድር ቆይቷል። በእነዚህ የአመራር ዘመኑ ከሚታወቅባቸው ገጽታዎቹ ውስጥ ዋነኛው ደግሞ ጠንካራ ውስጠ ድርጅታዊ አሠራርና አመራሩ ነው፡፡
በርግጥ ድርጅቱ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በውስጡ ካጋጠሙት አንዳንድ ፈተናዎች የተነሳ ሊወድቅ የደረሰባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በተለይ በ1993 ዓ.ም በህወሓት አመራሮች መካከል የተነሳውን ልዩነት እና ይህንንም ተከትሎ በተፈጠረው ውስጣዊ ችግር ድርጅቱ ለመፈረካከስ ተቃርቦ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ያንን ወቅት አልፎ ወደመረጋጋትና አገሪቷንም በተሻለ ሁኔታ ለመምራት ወደሚያስችለው ቁመና ተሸጋግሯል፡፡
ድርጅቱ በአገሪቷ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ብሎም ዘላቂ ልማትን ለማምጣትም የተጓዘባቸው መንገዶች ቀላል አልነበሩም፡፡ በአገራችን ትላልቅ ስኬቶች የተመዘገቡት በዚሁ ኢህአዴግ አገሪቷን ባስተዳደረባቸው ዓመታት እነደሆነ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ በተለይ በመሰረተ ልማት፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች የልማት ዘርፎች ያከናወናቸው ተግባራት ትልቅ ዕውቅና የተቸራቸው ናቸው።
ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ ማድረግ ችሏል፡፡ በቀጣው አገራት አካባቢ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጓዘባቸው መንገዶችም በዓለም አቀፍ መድረክ ጭምር ትልቅ ዕውቅና የተቸራቸው ናቸው፡፡
ያም ሆኖ ግን ድርጅቱ ያልተሻገራቸውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያበላሻቸው የመጡ ችግሮች ድርጅቱን ብቻ ሳይሆን አገሪቷንም ወደመበታተን አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚል ትልቅ ስጋት የተፈጠረበት ሁኔታ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
በተለይ የፍትሐዊነት መጥፋት፣ የሌብነትና ብልሹ አሠራሮች መበራከት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ የህግ የበላይነት መርህ መጣስ፣ ወዘተ ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፉ የመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም የተነሳ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱት የህዝብ ቅሬታዎችና አመፆች ለኢህአዴግ ትልቅ ፈተና፤ ለአገሪቱ ህዝቦችም ከፍተኛ ስጋት ሆነው ቆይተዋል፡፡
በመከራ ውስጥ በመጓዝ ችግሮችን የማለፍ ትልቅ ተሞክሮ ያካበተው ኢህአዴግ ግን በዚህ ወቅትም ቢሆን ይህንን አደጋ በከፍተኛ ጥበብ ማለፍ ችሏል፡፡ በወቅቱ በራሱ ከኢህአዴግ ውስጥ የወጡ የለውጥ ኃይሎች ከድርጅታቸው ጋር ከፍተኛ የውስጥ ትግል በመግጠም በአገሪቷ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ጭምር ትልቅ ተስፋ መሆን የቻለ ለውጥ ማምጣት ችለዋል፡፡ አሁን የምናየው የዴሞክራሲና የዕድገት ተስፋም የመጣው በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠሩ የለውጥ አመራሮች ነው፡፡
ይህም በመሆኑ በኢህአዴግ ውስጥ የሚከሰቱ በጎም ሆኑ ክፉ ነገሮች መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ የሚፈጠር ችግር አሁን የተጀመረውን የለውጥና የተስፋ ጭላንጭል ወደኋላ ሊመልስ የሚችልባቸው ዕድሎች አሉት፡፡ በመሆኑም በኢህአዴግ ውስጥ የሚታዩ ማናቸውም ችግሮች በወቅቱና በስርዓቱ የሚፈቱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡
ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ ውስጥ የሚታወቀው ውስጣዊ አንድነትና ውሳኔዎችን በጋራ የማሳለፍ ሂደት ተሸርሽሮ ርዕስ በርዕስ የመወነጃጀል ሁኔታዎች መስፋፋት ድርጅቱን አደጋ ላይ ሊጥሉት የሚችሉ በመሆኑ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡
በተለይ ሰሞኑን በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል የተከፈተው የቃላት ጦርነት አገሪቷን ከሚያስተዳድር ድርጅት የሚጠበቅ ሳይሆን ለፍልሚያ የተዘጋጁ የሁለት አገር መንግሥታት መሪዎች ያስመስላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ስጋት ነው፡፡ ህዝብን ለመምራት በቅድሚያ ራስን በአግባብ መምራትና ከቅርብ አጋር ጋር በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ባህልን ማዳበር ይገባል፡፡
ርዕስ በርዕሳቸው የማይስማሙና መሰረት በሌለው ሁኔታ የተጣመሩ አካላት አገርን መምራት አይችሉም፡፡ በመሆኑም በድርጅቶቹ መካከል የተፈጠሩ ውስጣዊ ቅራኔዎች ተፈትተው በሚስማሙባቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚሠሩበትን መንገድ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ለራሳቸው ህልውና ሲሉ በህዝብ ፊት ድንጋይ መወራወራቸውን ማቆም ይገባቸዋል፡፡
አሁን አገራችን በለውጥ ጎዳና ላይ ናት፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ ለህዝብ የሚጠቅምና ለዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም ጭምር ትልቅ ተስፋን ይዞ የመጣ ነው፡፡ ይህንን ለውጥ ለማስቀጠልና የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ኢህአዴግ ከሁሉ የበለጠ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡
ለዚህ ደግሞ አዳዲስ ችግሮችን እየፈጠሩ ወደህዝብ ማውረድ ሳይሆን የነበሩ ችግሮችን ፈትቶ ለጋራ ዕድገት በትብብር መሥራት ከእያንዳንዱ ድርጅት ይጠበቃል። በመሆኑም ይህ ትልቅ ታሪካዊ ኃላፊነት የተጣለባቸው የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችም ይህ ታሪክ እንዳይበላሽና ለውጡም እንዳይቀለበስ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ቁጭ ብለው በመፍታት ለህዝቡም አርኣያ መሆን አለባቸው፡፡ ኢህአዴግም እንደድርጅት በአህት ድርጅቶቹ መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር አበክሮ ሊሠራ ይገባል። የራሱን ችግር መፍታት ያልቻለ ድርጅት የአገርን ችግር ሊፈታ አይችልምና፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2011