ሩቲ አጋ በትልቁ የሴቶች ማራቶን ትፋለማለች

ሴቶችን ብቻ በማፋለም ዝነኛ ከሆኑ የማራቶን ውድድሮች ቀዳሚው በጃፓን የሚካሄደው የናጎያ ማራቶን ነው። በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጠው ይህ የማራቶን ውድድር ዘንድሮ በቀጣዩ የፈረንጆች ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሲካሄድ፣ ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ አትሌት ሩቲ አጋ ለአሸናፊነት እንደምትፎካከር ተረጋግጧል።

እኤአ በ2018 ከሃያ አንድ ሺ በላይ ሴት አትሌቶችን በማፎካከር በዓለም ትልቁ ሆኖ በድንቃድንቅ መዝገብ ስሙ የሰፈረው የናጎያ ማራቶን ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ ሲካሄድ ከሩቲ አጋ በተጨማሪ የሌሎች ሀገራት ኮከብ አትሌቶች ለድል እንደሚፎካከሩበት አዘጋጆቹ ሰሞኑን ይፋ አድርገዋል።

የ2024 የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊዋ ኬንያዊት አትሌት ሼይላ ቺፕኪሩይ በውድድሩ ፈጣን ሰዓት ይዛ የምትፎካከር ቀዳሚዋ አትሌት ነች። ሼይላ በዚህ ውድድር ቁጥር አንድ የማራቶን ፈጣን ሰዓት ባለቤት ያደረጋትን 2:17:29 ያስመዘገበችው ኒውዮርክ ላይ ባለድል በሆነችበት ውድድር ነበር።

በውድድሩ ሁለተኛውን የማራቶን ፈጣን ሰዓት ይዛ ለአሸናፊነት የምትፎካከረው ሩቲ አጋ፣ የ2019 የቶኪዮ ማራቶንን ያሸነፈችበት 2:18:09 ሰዓት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው። እኤአ በ2013 በሞሪሺየስ ባምበስ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ5ሺ ሜትር ባለድል የነበረችው ሩቲ አጋ፣ ፊቷን ወደ ማራቶን ካዞረች ወዲህ በአርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩ ፉክክር ስኬታማ ከሚባሉ ኮከቦች አንዷ መሆን ችላለች።

ሩቲ አጋ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2019 የቶኪዮ ማራቶንን ካሸነፈች ወዲህ በዚያው ዓመት በኒውዮርክ ማራቶን ሦስተኛ ሆና በማጠናቀቅ በርቀቱ የዓለም ሻምፒዮና ተሳታፊ እንደነበረች ይታወሳል። እኤአ በ2016 የበርሊን ማራቶን ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ በቀጣይ ሁለት የበርሊን ማራቶን ውድድሮች 2017 እና 2018 ላይ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ የርቀቱ ብርቱ ተፎካካሪ መሆኗን አሳይታለች። በተመሳሳይ ዓመት በ2018 በቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋም ይታወቃል።

ሩቲ በዓለም ታላላቅ የማራቶን ፉክክሮች ከስድስት ዓመት በፊት ቶኪዮ ላይ ካስመዘገበችው ድል በቀር ቀዳሚ ሆና ማጠናቀቅ አልቻለችም። ያም ሆኖ በነዚህ ውድድሮች ያካበተችው ከፍተኛ ልምድ ያላት ጠንካራ የተፎካካሪነት አቅም ዘንድሮ ዳግም በጃፓን ምድር በትልቁ የናጎያ የሴቶች ማራቶን ወደ ድል የምትመለስበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ባሕሬናዊቷ አትሌት ኢዩኒስ ቼቢቺ ቹምባ ከሩቲ አጋና ከኬንያዊቷ አትሌት ሼይላ በመቀጠል በናጎያ ማራቶን ለድል የታጨች አትሌት ነች። ይህች አትሌት የ2023 የኤሽያ ጨዋታዎች አሸናፊ ስትሆን ባለፈው ዓመትም በዚሁ በናጎያ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው። ይህም ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ለተሰጣቸው ለኢትዮጵያዊቷና ኬንያዊቷ አትሌት ቀላል ተፎካካሪ አትሆንም የሚል ግምት አሰጥቷታል።

ብዙ ልምድ ያላቸውና ወጣት አትሌቶች በሚፋለ ሙበት የዘንድሮው የናጎያ ማራቶን ለአሸናፊነት ከታጩት ሦስቱ አትሌቶች ባሻገር ያልተገመተ ሻምፒዮን ሊከሰት እንደሚችልም ይጠበቃል። አውስትራሊያዊቷ አይሶቤል ባት-ዶይል፣ ካናዳዊቷ ናታሻ ዎዳክ፣ ቻይናዊቷ ዩዩ ዢአ፣ ጀርመናዊቷ ፋቢን ኮኒግስቴን እንዲሁም አሜሪካዊቷ ናቶሻ ሮጀርስ ውድድሩን ሳይታሰብ የማሸነፍ አቅም አላቸው ተብለው የሚገመቱ አትሌቶች ናቸው።

በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ጃፓናውያን አትሌቶች በመጪው ክረምት በቶኪዮ ለሚካሄደው የዓለም ቻምፒዮና ሀገራቸውን ለመወከል የሚመረጡበት በመሆኑ ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በ2:19:24 የጃፓንን ሦስተኛ የማራቶን ፈጣን ሰዓት የያዘችው አትሌት ሂቶሚ ኒያ እኤአ ከ2009 ወዲህ ከአስራ ስድስት ዓመት በኋላ በናጎያ ማራቶን ለመሳተፍ መመለሷ ትኩረት ስቧል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You