ጠብታ-ታገል ሰይፉ ከታገለው

የሰው ልጅ ለመኖር ሲፈጠር አንድም ከሕይወት እጣ ፈንታው ጋር ትግል ለመግጠም ነው፡፡ ትንሹም ትልቁም፣ ሊቁም ደቂቁም፣ የራሱን ትግል ገጥሞ ያልፋል፡፡ ከዚህ አለፍ ያለውም ታግሎ ያታግላል፡፡ ታዲያ ትግልም የጦርና የነጻነትን ዓለም ፍለጋ ብቻ አይደለም፡፡ ምናባዊ የሆነ ትግልም አለ፡፡

ጥበብም በራሷ የትግል ሜዳ ናት፡፡ ታገል ሰይፉን ያገኘሁትም ከዚሁ ነበር፤ ከውስጥ ሆኖ ለሌላው ከሚታይባት የሕይወት እንቅብ ውስጥ፡፡ ጠብታውን ብቻ ልመለከተው ፈለኩኝ፡፡ በሀገራችን ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ትግሉን የጀመረው ገና አፍላ ልጅ ሳለ ነበር፡፡ ያኔም ብዕሩን ሲጨብጥ ጀምሮ ለወትሮው የምናውቃቸውን ቃላት እንዳናውቃቸው የማድረግ ልዩ አስማት ያለው ይመስለኛል፡፡ ተምሳሌታዊ የምናብ ወግ በብዕሩ ያለማማሯ ለየት ያለ ነው፡፡

ታገል ሰይፉ ምን እያለ ነው? ብቻ ሳይሆን፤ ምን ለማለት ፈልጎ ነው? ማለትም ጥሩ ነው፡፡ ለአንዳንዶቹ ሊያስለቅሰን የሚችለውን ጉዳይ፣ እያስነበበ በሳቅ ሊያጅበን ይችላል፡፡ ስለ ፍቅር ነው ስንል ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ነው ያልነውን ደግሞ የፍቅር ሽልጦ አድርጎ ሲያወጣውም እንመለከታለን፡፡ “ግጥም ሲጥም እንደ ዶሮ ቅልጥም!” እያሉ መግመጥ ነው፡፡ የብዕሩ አቅም አንድም ምናባዊ ትግልን ማታገል ነውና፡፡

ሃይ! ገባህ አይደል?

እንዲህ ሲደላደል፡፡

የጨዋታው ሜዳ

ከጀግኖች መደዳ፡፡

የኛ ዶሮ ጮሆ

ሆሆሆ ሆ፡፡

ወይኔ !

አላመነም ዓይኔ፤

አገባሁት እንዴ፤

አይ ሳተናው ጓዴ፡፡

…እያለች የምትቀጥለው የግጥም ሥራው፣ በውል እስከማላስታውሰው ጊዜ ድረስ ልቤን በትዝታ ቀጥ አድርጋው ቆይታለች። ልክ በእግር ኳሱ አውድማ ያውም በዓለም ዋንጫ ዚነዲን ዚዳን የማቴራዚን ልብ በቴስታ ቀጥ አድርጎ ሲጥለው እንዳለው ዓይነት፡፡ በ1998ዓ.ም (በ2006 ዓለም ዋንጫ) ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ይህ አይረሴ ትውስታው ነው፡፡ ታገልም ያንን የሜዳ ላይ ፍልሚያ በድምጽና ምስል የተቀናበረ ግጥም አድርጎ ሲሠራው ራሱን የቻለ ፊልም ወጣው፡፡ ይህን መሳጭ ትርኢት ከማራኪ ድምጽ ጋር፣ አዲስ ፈጠራዊ የግጥም ፊልም መስሎ እንደኔው ዓይንና ጆሮ አልጠግብ ያሉ ብዙ ናቸው።

ግጥምን የማንበብ ብቻ ሳይሆን ግጥምን የመስማት ሱስም እንዳለ የታገል ሰይፉ ሲዲዎች አስመለከቱ፡፡ ፊልም ተከራይቶ፣ በዲቪዲ ማጫወቻ በሚመለከቱበት ዘመን፣ የግጥም ሲዲዎቹን እንደ ፊልም ተከራይተው የተመለከቱት ብዙዎች ናቸው፡፡ ቅንብሩን ስንመለከትም ታገል ሰይፉ ግጥሙን የሚጽፈው የተንቀሳቃሽ ምስሉን ታሪክ ተመልክቶ? ወይንስ ለጻፈው ግጥም የሚሆን ምስል አስቀርጾ ነው? ያስብለናል፡፡ ምክንያቱም፤ በገሀድ ከሆነው በላይ በግጥም ማስረዳትን ይችልበታል፡፡ ብዙዎችም “ታገል ይጻፈው! ታገል ይናገረው!” ቢሉ እውነታቸውን ነው፡፡ የውስጥን ስሜት በቃላት አንጀት ማራሱን ስለሚያውቅበት ነው፡፡

ደራሲና ገጣሚ ታገል ሰይፉ፤ ከኋላ የአንድ ዘመን ትውልድ አስከትሎ የተሻገረ ሰው ነው፡፡ “ማን ያውራ የነበረ…” እንዲሉ፣ በዋናነት በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ አካባቢ ለጥበብ ቅርብ የነበረ ማንም ይናገርለታል፡፡ በተለይ ደግሞ የቅርቡ የሆነው ጸሐፊ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ውስጥ አዋቂውም ጭምር ነው፡፡ በአንዳች ነገሩ እርሱን የሚመስለው በእውቀቱ ስዩምም የጋራ የሆነ ሕይወት ነበራቸው፡፡ ታገል ሰይፉ፤ እውቅ ከምንላቸው ከበርካቶች ጋር በአብሮ አደግነትም ሆነ በሌላ ተሳስሯል፡፡ ለዚህም ይመስላል በብዛት የታገልን የሕይወት አጋጣሚዎች የምንሰማው ከራሱ ሳይሆን ሌሎች ስለርሱ ሲያወሩ ነው፡፡

ልጅነቱ ከሥነ ጽሑፍ ጋር ትግል የገጠመበት ሜዳ ነበር፡፡ የተወለደው በጎጃሟ እቴጌ በባህርዳር ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ወላጆቹ እንዳወጉት፣ እርሱም ለወዳጆቹ እንዳወጋው ከሆነ በልጅነቱ በየጊዜው እየመጣ የሚያሰቃየው አንዳች ሕመም ነበረበት፡፡ ይኸው መከረኛ በሽታው በመጣ ቁጥርም ወላጆቹ ሐኪም ቤት ይዘውት ይሮጣሉ፡፡ ለብዙ ጊዜያት ቢመላለስም ሊድን ቀርቶ በሽታውም ራሱን አልገልጥ አለ፡፡ በልጃቸው የሕመም ሁኔታ መጨነቃቸውን የተመለከቱ ጎረቤቶችም፣ ጠጋ ብለው ለወላጆቹ አንድ ነገር ሹክ አሏቸው፡፡ “ለምን ወደ አዋቂ ቤት አትወስዱትም” የሚል ነበር፡፡ በጊዜው በአብዛኛው ማህበረሰብ ውስጥ እንዲህ ያለው የጨነቀ ዕለት ውሳኔ የተለመደ ነውና ወላጆቹም ተስማሙ፡፡ ታገልን አንጠልጥለው ከጠንቋዩ ቤት ያደረሱትም እኚሁ መካሪ ጎረቤቶች ነበሩ፡፡

ከጥቂት ቆይታ በኋላም አድባሩን መጅነው ፣ ክታባቸውን አስረው፣ ውቃቢውን ቀስቅሰው፣ በአቦል በእጣኑ ከራማቸውን ተማጽነው ሲያበቁ እንዲህ አሉ “አዬ!…ይሄ ልጅ ዋጋ የለውም፡፡ አይተርፍም፡፡ እንዲያውም ከአሁን በኋላ የልጁ እድሜ 40 ቀናት ብቻ ናቸው” በማለት፣ በጊዜው ለታገል ያልገባውን መርዶ ላመጡት ጎረቤቶቹ ነግረው ሰደዷቸው፡፡ የያዙትን በሆድ ይዘው በጭንቀት ሊፈነዱ የተቃረቡ ጎረቤቶችም፣ አንዳችም ለወላጆቹ ትንፍሽ አላሉም፡፡ ብቻ በውስጣቸው በፍርሃት ሲጠባበቁት የነበረው ቀንና ሰሞን ደረሰ፡፡ ታገል ግን እንኳንስ ሊሞት ሕመም ሳይታይበት ይበልጥ ይቦርቅ ነበር፡፡ ጊዜው ከማለፉም እርቆ ሄደ፡፡ አርባ ቀናት የተቆጠሩለት ታገል ሰይፉ ግን ከ40ዎቹ የእድሜ ክልሎች ጋር ወደፊት በመገስገስ ላይ ነው፡፡ የቅርብ ወዳጆቹ፤ እንዲያውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጠና ታሞ እንኳን አያውቅም ይላሉ፡፡

ከዚያ የጠንቋዩ የሞት ትንበያ አምልጦ ደህና የሆነው ታገል ሰይፉ፣ ቀጣይ የልጅነት ሕይወቱ የጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ እንደ ሌሎች ልጆች ሁሉ ተማሪ ቤት ገብቶ ትምህርቱን በመከታተል ላይ በመሆኑ ወላጆቹን ቢያስደስትም፣ ወዶ ይሁን ተይዞ የገባበት ሌላ አባዜ ግን አዋቂ ጠፋለትና ያስጨንቃቸው ነበር፡፡ በዚያ ትንሽ እድሜው እንደ አቻዎቹ ከቁጥርና ፊደላት ጋር መታገሉን ትቶ፣ በልቦለድና በግጥም መጻሕፍት ላይ ማፍጠጥ አበዛ። የረገጠውን ምድር ረስቶ ያለ ዕድሜው ሰማይ ሰማዩን እየቧጠጠ፣ ቤት ይዞት የማይመጣው የመጽሐፍ ዓይነት አልነበረም፡፡ ወላጆቹም ትምህርቱን ችላ ብሎታል ብለው መክረውም፣ ተጨንቀውም አልፈውታል፡፡ ታዲያ ድንገት አንድ ሰሞን ላይ ታገል ሁሉን ትቶ ወደ ትምህርቱ የመመለስ ምልክቶችን ማሳየት ጀመረ፡፡ በለውጡ ወላጆቹ በጣም ተደሰቱ፡፡

“አላልኩሽም! አንድ ቀን በራሱ ጊዜ ወደ ትምህርቱ ማዘንበል ይጀምራል ብዬሽ አልነበር…” እየተባባሉ እናትና አባት በልጃቸው ደብተር ላይ አቀርቅሮ መዋል ኩራት ተሰማቸው፡፡ መቶ ቅጠል ደብተሩን ገልጦ፣ ያለዚህ ሌላ ዓለም የለኝም በሚመስል መልኩ ቀናቱን የሚያሳልፈው በተመስጦ ንባብ ነው፡፡ ወላጆቹም፤ ከልቦለድና የግጥም መጻሕፍት አስጥሎ የሂሳብና ሳይንስ ደብተሮቹን ለማንበብ ስላበቃላቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ፣ ለታገልም እንክብካቤውን በእጥፍ አደረጉት፡፡ ጉድና ጅራት ከኋላም አይደል…ታገል ለቀናት ተጥዶበት የነበረው ደብተር ሳይሆን የበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” ነበር፡፡ ከላይ በመቶ ቅጠል የደብተር ሽፋን፣ መጽሐፉን ለብጦት የነበረውም በጊዜው በነበረው የፖለቲካ ሸፍጥ፣ በደርግ መንግሥት የታገደና ይዞ መገኘትም የሚያስቀጣ የነበረ በመሆኑ ነው፡፡

ይኼው ታገል ሰይፉ በ16 ዓመቱ “ፍቅር” የተሰኘ የግጥምና አጫጭር ልቦለዶች ስብስብ የሆነ መጽሐፍ ጻፈ። ጊዜውም 1982ዓ.ም ነበር፡፡ ይሁንና ታገል ትንሹ ዝነኛ ለመሆን የቻለው ከዚህ አራት ዓመታት ቀደም ብሎ ነበር። የሆነውም በመጽሐፍ ሳይሆን በአንድ ረዥም የግጥም ሥራው ነው፡፡ የ12 ዓመት ታዳጊ ሳለ “ሰላም” በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን ዕውቅ ግጥም ደረሰ፡፡ ቢመለከት አንዱ ግጥም ለመድብልነት የቀረው አልነበረም፡፡ አንዱን ግጥምም ለሦስት ከፋፈለው፡፡ የመጀመሪያውንም በለገዳዲ የትምህርት ስርጭት የሬዲዮ ጣቢያ አቀረበው። ቀጥሎ ሁለተኛውን ክፍል በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ላይ አስደመጠ፡፡ “ሰላም” ይቀጥላል…እያለ የሚሄደው የግጥም ሥራው፣ ሦስተኛውንም በዚያው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የሕጻናት ዝግጅት ላይ አቀረበው፡፡ ታገል ሰይፉ ቆንጆ ግጥም መጻፍ ብቻ ሳይሆን የራሱ የሆነ ቆንጆ የግጥም አቀራረብ እንዳለውም አሳየ፡፡

ታገል ምናባዊ ትግል ገጠመው፡፡ ትንሽ ልጅ ሆኖ ለማንበብ ከቻለበት ጊዜ አንስቶ፣ በመጻሕፍት የተለከፈ ቢሆንም ትምህርቱንም አልጣለውም ነበር፡፡ 8ኛ ክፍል እስኪደርስ ድረስም ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች መካከል አንደኛው ነበር፡፡ እዚህ ሲደርስ ግን የገጠመው የትምህርት ትግል እየተረታበት መጣ፡፡ ውስጡ ያለው የጥበብ ኃይል እየጨመረ በመሄዱ፣ የትምህርቱን ነገር ችላ እያለው መጣ፡፡ ፊቱ ቆሞ ከሚያስተምረው የመምህሩ ድምጽ፣ ከውስጥ ይሁን ከውጭ የምትጣራውን የጥበብን ድምጽ እየሰማ፣ በለሆሳስ አቤት ማለቱን ተያያዘው፡፡ “ለተንኮሉ አዳዲስ ሃሳቦች የሚመጡልኝና ልውጣ ልውጣ እያሉ የሚያስጨንቁኝ ክፍል ውስጥ ሆኜ አስተማሪ ማስረዳት ሲጀምር ነበር” በማለት በአንድ ወቅት ተናግሮት ነበር፡፡

“ፍቅር” የተሰኘውን መጽሐፉን ለአንባቢ ለማድረስ የገጠመው ትግል ቀላል አልነበረም፡፡ የመጽሐፉን የማተሚያ ክፍያ ለመክፈል ባለመቻሉ፣ ተከሶ የፍርድ ሸንጎ ላይም ቆሟል፡፡ ከዚህ በመነሳትም እንደዋዛ እያዋዛ ከ12 በላይ መጻሕፍትን ለማስነበብ በቃ፡፡ በግጥም ተነስቶ፣ በአጫጭር ልቦለዶች እያሟሟቀ፣ ረዥም ልቦለዶችንም ለመድረስ በቅቷል፡፡ ሁለተኛው መጽሐፉ “ቀፎውን አትንኩት” በ1986ዓ.ም ያሳተመው የግጥም መድብል ነው።

በ1989ዓ.ም ደግሞ “ሌዋታን” በተሰኘው የልቦለድ መጽሐፉ ሠለሰ፡፡ ይህ ሥራውም ወደ ራሺያ ቋንቋ ተተርጉሟል፡፡ ሌላኛው በ1990ዓ.ም ለንባብ ያበቃው “ሃምሳ አለቃ ገብሩ” የሚለው ተከታታይ የግጥም ሥራው ዝነኛ ነው፡፡ የሰዶም ፍጻሜ(ግጥም)፣ በሚመጣው ሰንበት(ግጥም)፣ ተልባና ጥጥ(ረዥም ልቦለድ)፣ ጉባኤ ለቅሶ(ወግ)፣ የልቤ ክረምቱ እና ክፍት ነው የተሰኙ የግጥም መድብሎቹን አስነብቧል፡፡ የታገል ሰይፉ የቅርብ ጊዜ ስጦታው፣ በ2016ዓ.ም ያሳተማት “ዝንቡላና ካሮት” የሚለው ረዥም ልቦለዱ ናት፡፡

ለሕጻናት ልጆች ከሚሳሱ ደራሲያን መካከልም አንዱ ነው፡፡ የአንድ ዘመን ሙሉ ትውልድ በሥነ ጽሑፍ ይዞ ሲጓዝ፣ ዓይኖቹ በልጆች ላይ ነበሩ፡፡ እጅግ የተወደደለትን “የእንቅልፍ ዳር ወጎች” የተሰኘ የተረት መጽሐፍ ለልጆች አቅርቧል፡፡ “አራቱ ውሾችና ትልቁ ውሻ” ሌላኛው የተረት መጽሐፍ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በአማዞን የመጻሕፍት ዓለም ለመካተት በቅቷል፡፡

በሥራዎቻቸው ዝነኛ ከመሆን አልፈው ብዙዎችን ለማስከተል የቻሉ የጥበብ ሰዎች አብዛኛዎቹ የራሳቸው የሆነ ቀለም ያላቸው ናቸው፡፡ በልዩነት እነርሱ ብቻ የሚታወቁበት አንድ ነገር አይጠፋም፡፡ ታገል ሰይፉን ከተመለከትነው ግን ያለው አንድ ብቻ አይደለም፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ ጽፎ ሲያበቃ በሁለት ነገሮች ያስገርመናል። አንደኛው ግጥሞቹን ስዕላዊ በማድረግ፣ በተምሳሌታዊ የአገላለጽ ስልቱ ውስጥ የሚጠቀማቸው ማንነቶች ናቸው። ሁለተኛው ደግሞ እኚህን ማንነቶች ከታሪካቸው ጋር አገጣጥሞ፣ በቃላት የሚያሰፍርበት መንገድ ነው። ግጥሞቹን ከላይ ስንመለከት አብዛኛዎቹ ቧልትና ፌዝ ይመስላሉ፡፡ ሁሉንም ፈገግ የሚያስብሉ ቢሆኑም፣ ቁም ነገራቸው ለሁሉም በእኩል ደረጃ ላይገለጥ ይችላል። በሥራዎቹ ውስጥም ሁለት ዓይነት አድናቂዎች ያሉት ይመስለኛ፤ ሳቅን ሽተው የሚጠጉና ቁም ነገሩን ሸልቅቀው የሚጠረጥሩ፡፡

“ሰውን ማመን ቀብሮ” ያለችን ቀበሮ ጸሎት፣ ድንገት ታገል ሰማት፡፡ እናም እርሱ እንደሰማውም፣ እንደጻፈውም እንዲህ ነበር…

እባክህ አምላኬብትሬን ቀባና፤

እኔም ልወዝውዘውየሙሴን ጎዳና፡፡

ያላንዳች ፍርሃትያለምንም ችግር፤

ባህሩን ከፍዬሕዝቤን እንዳሻግር፡፡

አደራህን ታዲያጭንቅ አትወድም ነፍሴ፤

ልመናዬን ሰምተህካደረግከኝ ሙሴ፡፡

ነብዩ ዮናስንአርገህም ስትፈጥረኝ፤

የባህሩን ፍዳያሳውን ሆድ ማረኝ፡፡

የዳዊትም ኮከብበኔ ላይ ሲወጣ፤

እባክህ አምላኬጎልያድ አይምጣ፡፡

ታገል ሰይፉ እንዳልነው ነው… ስለማይረባ ጉዳይ እየተረከ፣ ወሳኙን የሕይወት ትምህርት ሊሰጠን ይችላል። ከጻፋቸው 7 የድርሰት መጻሕፍቶቹ፣ መካከል ሰባተኛዋ “ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር” ነው፡፡ ‘የቃላት ኩዋሻኮር’? ወይንስ ‘ልሳን?’ አሁን ይህን ምን ልንለው እንችላለን? መጽሐፉን ገልጠን ከመሃል አካባቢ ስንደርስ፣ ሀገራችን ውስጥ ከሚገኝ ከአንድ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተማሪዎች መካከል ስለ ተቀሰቀሰው ጸብ ይነግረናል። በእርስ በርስ ጸቡም 27 ተማሪዎች ቆስለው፣ አራት ተማሪዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የዚህ ረብሻ መንስኤ ታዲያ፣ ከዶርም የጠፋው የአንድ ተማሪ አንድ እግር ጫማ ነው፡፡ እንግዲህ ታገል እየነገረን ያለው ስለ ተማሪው የአንድ እግር ጫማ አይደለም፡፡ ቅልጥ ያለ የፖለቲካ መንደር በሆኑት ዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ የሚታየውን በዘር ፖለቲካ የጠበበ መንገድን ነው። ለመጽሐፉ የተጠቀማቸው ስምና መቼቶች በገሀድ ከወዴትም የሌሉ ቢሆኑም፣ ሁሉም የኛን ጉድ የተሸከሙ ናቸው፡፡

ከመጻሕፍት ዓለም ውጪ በሌላም ሌላም ቦታዎችም ትግሉን ቀጥሏል፡፡ በቁም ነገር መጽሔት ላይ ራሱን የሚመስሉና የሚመጥኑ ቆንጆ አምዶችን ሲያዘጋጅ ይታወቃል፡፡ በ1980ዎቹ መካከልም በፋና ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እዚህ የሚያውቁትም፤ በጊዜው ቀጭን ጌታ ነበር ይላሉ፡፡ ውስጥ አዋቂው እንዳሾለከበትም፣ አሜሪካ ውስጥ የነበሩት ፍቅሬ ቶሎሳን ጠቅሶም “በወር አንድ መቶ ዶላር ይጸድቁበታል” ይላል። ታዲያ የሥራ ባልደረቦቹ ሁሉ ተቸግረው ይመለከታል፡፡ የችግራቸው መንስኤ ደግሞ፤ መሥሪያ ቤቱ ደመወዛቸውን በጊዜ እየከፈላቸው አለመሆኑን ብድር በጠየቁት ቁጥር ይነግሩታል፡፡ በወቅቱ ኃላፊ የነበሩትም ሴኮ ቱሬ ነበሩ፡፡

አንድ ቀን ታዲያ ሴኮ ሁሉንም ሠራተኛ ስብሰባ ጠሩ። ሁሉም ከየክፍሉ መጥቶ ቦታ ቦታውን ይዟል፡፡ ሴኮ ቱሬም “ዛሬ የአምስቱን ዓመት የኤክስቴሽን ፕሮግራም እንዴት እንደምናሳካ እንወያያለን…” ከማለታቸው፤ ታገል አስከትሎ “እነዚህ ሠራተኞች ደመወዝ ለ15 ቀን አልተከፈላቸውም። እናንተ የ5 ዓመት ኤክስቴሽን ፕሮግራም ትላላችሁ። በመጀመሪያ ደመወዛቸውን ክፈሏቸው” ይላል፡፡ ሴኮ ቱሬም “እንዲህ ዓይነት ችግር መኖሩን አላውቅም ነበር” በማለት፣ ሠራተኞቹን አንድ በአንድ እየተመለከቱ፣ የሆነውን መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ሠራተኞቹ ግን “ዓላማችን የአምስት ዓመቱን የኤክስቴሽን ፕሮግራም ማስፈጸም ነው፡፡ ጥያቄያችንም የገንዘብ አይደለም” በማለት ፈርተው ታገል ሰይፉን አሳጡት፡፡

ይሄኔ ታዲያ አለቃ ሴኮ ቱሬም “ለምን ትዋሻለህ? ዛሬ እውነቱ ሳይወጣ ከዚህ አዳራሽ ንቅንቅ አንልም” በማለት በቁጣ ይናገራሉ፡፡ ስብሰባው ውስጥ ከነበሩት አንዱ ሙሉጌታ ተስፋዬ ነበር፡፡ መቋጫ ያጣው ስብሰባዊ ንትርክ ጭንቅ የሆነባቸው፣ ሙሉጌታና ሌሎችም በቀስታ ወደ ታገል ሰይፉ ጠጋ እያሉ “እባክህን ውሸቴን ነው ብለህ እመንና ከዚህ ገላግለን” እያሉ ተማጸኑት፡፡ በሠራተኞቹ ሁኔታ ያዘነው ታገል ግን፤ እውነት ምንም ጊዜም እውነት ናትና አልዋሽም አለ፡፡ ሽንፈትን ሳይሆን ህሊናውን መደለል ስለከበደው፣ በዚያው ሰሞን ሥራውን ለቀቀ፡፡ በወቅቱ የታገል ትግል ለራሱ አልነበረም፡፡ ችግሩ ግን የተቸገሩትን ተመልክቶ ለማለፍ አለመቻሉ ነበር፡፡ በየትኛውም ጊዜና ቦታ፣ እውነት ስትካድ ቆሞ ለመስማት አይወድም። ጉዳያቸው ነው፤ ከሚል ፈሊጥ ርቆ፣ የሁሉንም የራሱ ጉዳይ የማድረግ ባህሪ ያለው ሰው ነው፡፡ ታገል እንዲህ ያለውም ጭምር ነው!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You