• በተሳሳቱ ትርክቶች አንድን ህዝብ መፈረጅ ተገቢ አለመሆኑም ተጠቁሟል
ባህር ዳር፡- የአማራ ክልልና ሱማሌ ክልል ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ በአማራ ህዝብ ዙሪያ ያለውን የተዛበ ትርክት በማጥራት እውነታውን ለማስገንዘብ እገዛ እንደሚኖረው የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡
ስለአማራ የተሳሳቱ ትርክቶች የህዝቦችን አብሮነትና ሀገራዊ አንድነቱን የሚጎዱ በመሆናቸው አንድን ህዝብ በጅምላ መፈረጅ ተገቢነት የሌለው መሆኑንም የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጠቁመዋል፡፡
የአማራና ክልልና የሱማሌ ክልል ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ በባህርዳር ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ላቀ አያሌው እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ውስጥ የአማራ ህዝብ ጨቋኝ ተደርጎ ተስሏል፡፡ ይህ ግን የተሳሰተ ትርክት ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ተከባብሮና ተዋዶ የሚኖር ህዝብ እንጂ ጨቋኝ አይደለም፡፡
ይህ የተሳሳተ ትርክት እንዲስተካከል የሱማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት መልካም ሚና እየተጨወቱ ናቸው፡፡ በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል የተደረገው የህዝብ ለህዝብ የውይይት እውነታውን ለማስገንዘብ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በሶማሌ ክልል ባለፈው ዓመት ግጭት የወደሙ ቤተክርስቲያኖችን መልሶ በማስገንባት ረገድ የክልሉ መንግሥት የፈጸመው ተግባር በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው ያሉት አቶ ላቀ፤ በክልሉ የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ የክልሉ መንግሥት እየወሰደ ያለው ተግባራዊ ዕርምጃ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ላቀ ማብራሪያ ሁለቱ ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ በጋራ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ለዚህም የአማራ ህዝብና የክልሉ ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሱማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው፤ ስለአማራ የተሳሳቱ ትርክቶች የህዝቦችን አብሮነትና ሀገራዊ አንድነቱን የሚጎዱ በመሆናቸው አንድን ህዝብ በጅምላ መፈረጅ ተገቢነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ታሪክ የሚገኝባት የብዝሃነት ስብጥር የሚስተዋልባት ሃገር መሆኗን ያነሱት አቶ ሙስጠፌ ብሄራዊና ሃገራዊ ማንነት አንዱ የሃገሪቱ ደጀን እና ዋልታ መሆኑን በመገንዘብና በጋራ በማስተሳሰር የህዝቦችን ሐተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የጋራ እና ብሄራዊ ማንነት ተፈጥሯዊ ተቃርኖ እንዳላቸው በማስመሰል የብሄር ፅንፈኝነት በመፍጠር የሃገርን ሰላም የሚያውኩ አካላትን እያንዳንዱ ግለሰብ በያገባኛል መንፈስ ሊከላከላቸው ይገባልም ብለዋል።
በመድረኩ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲና የጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ለዘመናት የቆየውን የሁለቱን ህዝቦች አብሮነትና ለሀገር አንድነት ብሎም ሉዓላዊነት መከበር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዳስሱ ጽሐፎችን አቅርበዋል፡፡
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ዶክተር ዋጋው ቦጋለ፤ “የኢትዮጵያ ሱማሌና የአማራ ህዝቦች አብሮነት ታሪካዊ ልምድ’’ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፋቸው እንዳብራሩት ሁለቱ ህዝቦች በጋራ አኩሪ ገድሎችን ፈጽመዋል፡፡ ሁለቱ ህዝቦች የመካከለኛ ዘመን ስልጣኔ መስራች ህዝቦች ናቸው፡፡
በመካከለኛ ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ አሻራ አኑረዋል፡፡ ለዚህም ከጂግጅጋ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውንና ብዙ ያልተነገረለትን “ደርጊ በላምል” የተሰኘውን መስጊድ፣ ቤተመንግሥትና ትክል ድንጋዮችን አጠቃሎ የያዘውን ቅርስ እንደማሳያ አንስተዋል፡፡ በተመሳሳይ በአማራ ክልልም ላሊበላና ፋሲል የመሳሰሉ የመካከለኛ ዘመን ቅርሶችንም ለማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
በመካከለኛ ዘመን እነዚህን ተዓምሮችን የሠሩ ህዝቦች በዚህ ዘመንም በጋራ መሥራት ከቻሉ ተዓምር መሥራት ይችላሉ፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የቀደመ ስልጣኔያቸውን ለማስቀጠል ይረዳል ብለዋል፡፡
ዶክተር ዋጋው አክለውም፤ ሁለቱ ህዝቦች ለሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት መስዋዕትነት የከፈሉ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ የአድዋ ጦርነትና ሌሎች ታላላቅ ጦርነቶች ላይ ከመላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በመሆን ሁለቱ ህዝቦች የከፈሉትን መስዋዕትነት አንስተዋል፡፡
እንደ ዶክተር ዋጋው ማብራሪያ፤ ሁለቱ ህዝቦች በጸረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ታሪክ የሠሩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጅ በሆኑት በሰዒድ ሞሃመድ የተደራጀው የደርቡሽ እንቅስቃሴ ረጅሙና እልህ አስጨራሽ የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል በአፍሪካ ተጠቃሽ ነው፡፡
ሌላኛው ጽሑፍ አቅራቢ ዶክተር ንማን አብዱላሂ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ህዝቦች በሀገር ምስረታ ላይም የላቀ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ የያዘቺውን ቅርጽ ከማስያዝ አኳያ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ግንኙነታቸው ተፈጥሯዊና አንዱ በሌላው ላይ የተደገፈ ከመሆኑም ባሻገር ሁለቱ የተጋቡና የተዋለዱ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ግንኙነታቸው የበለጠ ቢጠናከር ለሀገር አለኝታ ይሆናል ያሉት ዶክተር ንመን የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት እንዳይጠናከር የሚያደርጉ የፖለቲካ እንቅፋቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
የራሳቸውን የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የሚፈልጉ ኃይሎች የፈጠሩት የተዛበ ትርክት የህዝቡ ግንኙነት እንዳይጠናከር አድርጓል፡፡ በመሆኑም የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማስተካከል የተዛቡ ትርክቶችን ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ንመን ማብራሪያ፤ የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የሱማሌ ባለሀብቶች በአማራ ክልል በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፡፡ የአማራ ህዝብ በሱማሌ ክልል ከተሞች መዋዕለ ንዋዩን ማፍሰሱን መቀጠል አለበት፡፡ ከዚያ ጎን ለጎን እኩይ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ልህቃንም ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2011
መላኩ ኤሮሴ