
ስፖርት በዘመናችን ሳይንስ ብቻ ሳይሆን እጅግ በረቀቀ ሳይንስ የሚደገፍ ዘርፍ ሆኗል። በተለያዩ ስፖርቶች ልህቀት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት አትሌቶቻቸው ወደ ውስጥ የሚያስገቡት አየር ሳይቀር በሳይንስ የተመጠነ እስከ መሆን ደርሷል። ከሥልጠና ጀምሮ እያንዳንዱ የስፖርተኞች እንቅስቃሴ ሳይንስ በሆነበት በዚህ ዘመን የአትሌቶች አመጋገብ ጉዳይ በሥነ-ምግብ ባለሙያ የታገዘ መሆኑ የስፖርቱ ዓለም “ሀሁ” ነው።
ኢትዮጵያ ስኬታማ የሆነችበት አትሌቲክስን ጨምሮ በሌሎች በርካታ የስፖርት አይነቶች ውጤታማ ለመሆን በተቻለ አቅም ዘርፉ በሳይንስ እንዲደገፍ ጥረት ከጀመረች ሰንብታለች። ስፖርቱን በብዙ መልኩ ሳይንሳዊ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ከሚገኙ ተቋማት አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ነው።
አካዳሚው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ታዳጊና ወጣት ስፖርተኞችን ከምልመላ ጀምሮ እስከ ሥልጠና በሳይንሳዊ መንገድ ኮትኩቶ በማሳደግ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲወክሉ እያደረገ ይገኛል። በዚህም በቂ ነው ማለት ባይቻልም አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል።
አካዳሚው ባለፉት ዓመታት አበረታች ውጤቶችን ሲያስመዘግብ ግን ነገሮች ሁሉ ሜዳ ሆነውለት አይደለም። በብዙ ፈተናዎች ውስጥ መጓዝ ግድ ብሎታል። አሁንም በፈተናዎች ውስጥ መገኘቱን ማስተባበል አይቻልም። ከፈተናዎቹ አንዱ ደግሞ ከስፖርተኞች አመጋገብ ጋር የተያያዘ ነው።
በአካዳሚው ውስጥ ለአራት ዓመታት ሥልጠናቸውን በተለያዩ ስፖርቶች የሚከታተሉ አትሌቶች እያንዳንዳቸው ለምግብ በቀን የተበጀተላቸው ገንዘብ ስልሳ ስምንት ብር ብቻ ነው። ይህ ደግሞ እንኳን ለስፖርተኛ ለማንኛውም ሰው በቂ ሊሆን እንደማይችል አከራካሪ አይደለም። ያምሆኖ አካዳሚው በተቻለው መጠን ስፖርተኞቹን በቀን ሦስት ጊዜ እየመገበ ይገኛል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው በሩጫም፣ በእግር ኳስም፣ በቦክስም ይሁን በብስክሌት ስፖርቶች የሚሠለጥኑ አትሌቶች አመጋገባቸው አንድ አይነት መሆኑን ነው። ይለያያል ቢባል እንኳን በጀቱ ስፖርተኞቹ የሚያስፈልጋቸውን እንዲመገቡ ይፈቅድላቸዋል ብሎ ማሰብ ለማንም አይዋጥም።
ይህ ጉዳይ ብዙውን አሠራሩን በጥናትና ምርምር አስደግፎ በሳይንሳዊ መንገድ ከሚራመድ ሀገር አቀፍ የስፖርት አካዳሚ ጋር አብሮ ሊሄድ አይችልም። ከምልመላ እስከ ሥልጠና በሳይንሳዊ መንገድ ተጉዞ ሥነ-ምግብ ላይ ያለው ችግር በአካዳሚው ስኬት እንዲሁም በስፖርተኞች ብቃት ላይ እንከን መፍጠሩ እንደማይቀር ግልፅ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፎ ከተቀረው ዓለም ጋር ተፎካካሪ ሆኖ የሚያሸንፍ ስፖርተኛን ማፍራትም ተአምር ይፈልጋል። ስለዚህ መፍትሄው ምንድነው?
አካዳሚው ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ በአርባምንጭ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ከተነሱ ነጥቦች አንዱና ዋነኛው፣ አካዳሚው ከምግብና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያለበትን የበጀት ውስንነት ለመቅረፍ የራሱን የገቢ ምንጭ መፍጠር እንዳለበት የሚጠቁሙ ናቸው።
አካዳሚው አዲስ አበባና አሰላ በሚገኙ ሁለት የማሠልጠኛ ማዕከሉ ብዙ ሀብት አለው። በውይይቱ ወቅት አንድ አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት “በአሰላ የሚገኘው የተንጣለለ ግቢ እያለ አካዳሚው ለስጋ፣ ወተትና እንቁላል ብዙ ገንዘብ ይዞ ገበያ መውጣት የለበትም”። ለስፖርተኞች የምግብ ግብዓት የሆኑ ነገሮችን አካዳሚው በራሱ ለማምረት አስፈላጊው ሁሉ እንዳለው አከራካሪ አይደለም። በአዲስ አበባው ማሠልጠኛ ማዕከልም የንግድ ቦታዎችን እንዲሁም የተለያዩ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በማከራየት የገቢ ምንጭ የመፍጠር አቅም አለው።(የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማከራየት በሥልጠና ሂደቱ ላይ የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም።)
እነዚህንና መሰል ሌሎች ሀብቶቹን ተጠቅሞ አካዳሚው ገቢ የማግኘት አቅም እንዳለው ቢታመንም ይህን ለማድረግ እንቅፋት አለበት። ይህም አካዳሚው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲቋቋም ገቢ የመሰብሰብ ዓላማ የሌለው መሆኑ ነው። ስለዚህም አካዳሚው ከመንግሥት በጀት ተላቆ “ራስ ገዝ” ለመሆን የሚመለከተውን አካል ውሳኔ የግድ ነው። በዚህ ረገድ ጥናቶች ተሠርተው ውሳኔ እየተጠበቀም ይገኛል።
አካዳሚው “ራስ ገዝ” እንዲሆን ውሳኔ ላይ እስኪደረስ ግን እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ለምሳሌ ያህል በአሰላው ማሠልጠኛ ማዕከል የተለያዩ ሰብሎችንና ለምግብ የሚሆኑ ተክሎችን በማልማት፣ ንብ በማነብና በመሳሰሉት ራስ ገዝ የመሆን አቅም እንዳለው የሚጠቁሙ ሥራዎችን ማሳየት ከጀመረ ሰነባብቷል። ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም