አዲስ አበባ፡- ለኢትዮጵያ ሰላምና ለኢትዮ ያውያን አንድነት እውን መሆን ለዓመታት የታገሉለት ዓላማ አሁን በመጣው አገራዊ ለውጥ ምላሽ እያገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር የብላክ ላይን ባታሊዮን አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ጃኮብ ፖል ኡጁሉ ገለጹ። በቀጣይም ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎቿ ያለምንም ችግር በአንድነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን እርሳቸውና በእሳቸው ስር ያሉ አባላት ከኢህአዴግ ጎን ሆነው ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ኮሎኔል ፖል ኡጁሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን የአንድነት መላላት ተከትሎ በህዝቦች መካከል አንድነትና ሰላምን ለመፍጠር የሚስችል ዓላማን ይዞና ብሔራዊ ገጽታን ተላብሶ ለዓመታት ሲታገል ቆይቷል።
በትግል ላይ እያሉም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውይይትና ድርድር ጀምረው የነበረ ቢሆንም ሂደቱ ውጤት ሳይመጣ ተቋርጧል።አሁን ላይ የመጣውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎም ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደመሆኑ፤ እርሳቸውና አባሎቻቸው ከኢህአዴግ ጋር ለመሥራት ተዘጋጅተዋል።
እንደ ግንባር ሰላሟ የተረጋገጠላት አንድ አገርና ህዝብ የመመስረት ዓላማን ይዞ የተነሳና በሂደትም ከመንግሥት ጋር ተነጋግሮ ለመፍታት የጣረ ቢሆንም፤ በሊቀመንበራቸው በኩል የሚስተዋለው ተግባር ግን ከግንባሩ ዓላማ እያፈነገጠ መምጣቱን የሚናገሩት ኮሎኔል ፖል ኡጁሉ፤ ይሄም ሊሆን በማይገባው የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ጣልቃ እስከመግባት የደረሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።እአአ ከ2016 ጀምሮ ሊቀመንበሩ የሚሰጧቸው መግለጫዎችም ሆኑ የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች ፓርቲው ከቆመለት ዓላማ አኳያ ሳይሆን ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት አኳያ እንደነበረ ያብራራሉ፡፡
ይህ ሂደት ደግሞ የህዝብንም ሆነ የአገርን ጥቅም የሚጎዳ እንጂ ፓርቲው የተነሳለትን ሰላማዊ የሆነ አንድ አገርና ህዝብ የመፍጠር ዓላማ ከዳር የሚያደርስ ሆኖ እንዳላገኙት ይገልጻሉ።በዚህ መልኩ የግንባሩን ዓላማ ባዛባ አካሄድ ደግሞ ከእርሳቸው ጋር ፓርቲው ውስጥ ሆነው መሥራት እንደማይፈልጉ ጠቁመዋል።አሁን የመጣው አገራዊ ልውጥ ደግሞ እርሳቸው ከተከታዮቻቸው ጋር በመሆን ከግንባሩ ወጥተው ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አንድነትና ጥቅም ሲሉ ከኢህአዴግ ጋር ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
እንደ ኮሎኔል ፖል ኡጁሉ ገለጻ፤ ለውጡን ተከትሎ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሰላምና አንድነት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ተስተውሏል።ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በህዝቦች መካከል ሰላምና አለመረጋጋትን ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት አሉ። ላለፉት ዓመታት በነበረው ሂደትም ዜጎች በብሔርና ክልል አጥር ውስጥ ሆነው አንዱ አንዱን የሚገፋበትና የሚያፈናቅልበት ሂደት ተበራክቷል።ከክልልና ከብሔር ያለፈ ስለ አገርና ህዝብ ማሰብ እና ኢትዮጵያን የሚታደግ አንድ ሰው ከየትኛውም ቦታ ሊወጣ እንደሚችል ተገንዝቦ በኢትዮጵያዊነት ስሜት መሥራት ተዳክሟል።
ይህ ደግሞ በለውጡ አመራሮች ሥራ ላይ የራሱን ጫና የሚያሳድር ሲሆን፤ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የለውጥ አመራሮቹም ሊታገዙ የሚገባቸው ወቅት ላይ ናቸው ብለዋል።በመሆኑም ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ምቹ እንድትሆን፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገሩ በየትኛውም ክፍል በነፃነት ተንቀሳቅሶ መሥራትና መኖር እንዲችል እርሳቸው ከተከታዮቻቸው ጋር በመምከር ከኢህአዴግ ጋር ሆነው ለመሥራትና ለማገዝ እንደተዘጋጁ ኮሎኔል ኡጁሉ ተናግረዋል።
ይሄንን ፍላጎታቸውም ለኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ ያሳወቁ ሲሆን፤ በቀጣይም በሚያስማሟቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን በማያስማሟቸው ጉዳዮች ላይም በመመካከር ልዩነታቸውን ለማጥበብ እና በሂደትም ኢህአዴግን ተቀላቅለው የሚሠሩበትን አቅጣጫ እንደሚከተሉ ጠቁመዋል።
ወደ ትግል የገቡት ለስልጣን ሳይሆን ለአገርና ለህዝብ አንድነትና ሰላምን ለማምጣት መሆኑን የሚገልጹት ኮሎኔል ፖል ኡጁሉ፤ በዚህ መልኩ ከኢህአዴግ ጋር ለመሥራት ሲወስኑም ከተከታዮቻቸው ጋር መምከራቸውንና ተከታዮቻቸውም ይሄንን ሃሳብ መቀበላቸውን ተናግረዋል።
እሳቸው የሚመሩት ጦርም የትጥቅ ትግል ያቆሙ መሆናቸውንና አባሎቻቸውም በዚሁ መሰረት በፈለጉት አማራጭ በሰላማዊ መንገድ አገርና ህዝባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2011
ወንድወሰን ሽመልስ