
በዓለማችን በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ከተወለዱበት ሀገር ወደ ተለያዩ ሀገራት ይፈልሳሉ። አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና የመሬት አቀማመጥ ያለባቸውን አካባቢዎች በማቆራረጥ ከተፈጥሮና ከድንበር ጠባቂዎች ጋር ግብግብ በመግጠም ከሀገር ሀገር ለመሻገር በሚደረግው ሙከራ በርካቶች በመንገድ ይቀራሉ፤ ለተለያየ አይነት የአካል እና የአዕምሮ ጉዳትም ይጋለጣሉ።
በለስ ቀንቷቸው ያሰቡትን የተስፋ ምድር የረገጡ ስደተኞችም በስደት በተጠለሉባቸው ባዕድ ሀገራት ለረሃብና ለጉስቁልና ይዳረጋሉ፤ ከባድ የመከራ ጊዜያትን ያሳልፋሉ። ፈታኙን ጉዞ አጠናቀው የሚፈልጉት ሀገር ከገቡ በኋላም ቀጣይ ጉዟቸውን ለማመቻቸት በሰዋራ መንደሮች ውስጥ ለወራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ተደብቀው ይቆያሉ። በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ከሃምሳ እስከ መቶ የሚደርሱ ሰዎች ሊታጎሩ ይችላሉ። ምግብና ውሃ የሚያገኙት በቀናት ልዩነት ውስጥ በመሆኑም ሰውነታቸው ይከሳል፤ ይጎሳቆላሉ።
በዚህ መንገድ በርካታ ኢትዮጵያውያን በደላሎች እና የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በሕገወጥ መንገድ ድንበር ይሻገራሉ። ወጣቶቹ የተሻለ ኑሮን በማለም ከሀገር ለመውጣት ካላቸው ጉጉት የተነሳ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በዚህ ልክ ስደትን እንዲከጅሉ የሚገፋፋቸው አንዱ ምክንያት በወላጆቻው ዘንድ ያለ ስደትን ከድህነት መውጫ መንገድ አድርጎ የመቁጠር አመለካከት ጭምር ነው። ልጄ ወደ ሌላ ሀገር ከሄደ ኑሮዬን ይቀይርልኛል፤ ያልፍልኛል የሚለው የወላጆች ምኞት ለወጣቶቹ ፍልሰት ራሱን የቻለ አስተዋፅዖ አበርክቷል።
ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ ሲሉ ያላቸውን ጥሪት አሟጠው ለሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ክፍያ ያውላሉ። የእርሻ በሬያቸውን አሊያም መሬታቸውን ቆርሰው በመሸጥ ልጆቻቸውን ይሸኛሉ። በሕገወጥ መንገድ ከሀገር መውጣት እንደ ልማድ በተያዘባቸው አካባቢዎች የሀገር ሽማግሌዎች ተጓዦቹን መርቀው ይሸኛሉ፡፡
በዛሬው የወጣቶች ዓምድ የምናነሳው ወጣት ይህን የስደት ታሪክ ቀምሶ የተመለሰ ነው። ሀገሩን ጥሎ ተሰዶ ኬኒያ ናይሮቢ ኖሯል። የስደት ሕይወት እንዳሰበው ቀላል አልሆነለትም። ከሀገሩ ለምን እንደወጣና እየገፋ ያለው የስደት ሕይወት ከቀድሞ እጅግ የከፋ እንደሆነ በማሰብ ብቻውን ሲብሰለሰል ኖሯል። በመጨረሻም ወደ ሀገሩ ለመመለስ ወሰነ። አደረገውም። በኬኒያ ናይሮቢ በስደት መኖር በቃኝ ብሎ ወደ ትውልድ ቀዬው ድሬዳዋ ተመለሰ። ይህ ወጣት ማን ነው? እንዲህ በጋዜጣ ለመነገር የበቃ ታሪኩስ ምንድን ነው? እንዴት እና የትስ አገኘነው የሚለውን ለማወቅ ንባብዎትን ይቀጥሉ።
ለሥራ ጉዳይ ወደ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባመራሁበት አጋጣሚ አንድ ዕለት በፍራፍሬ የምትታወቀውን ከተማ ትሩፋት የመመልከት ዕድል ገጠመኝ። በፍራፍሬ ልማት ተሠማርቶ ውጤታማ በመሆን በሀገር ደረጃ ሞዴል ተብሎ የተሸለመ የአንድ ወጣት ማሳን ለመጎብኘት ወደ ስፍራው አመራን። በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ በፍራፍሬ ዛፎች የተሞላ የተንጣለለ ማሳ በማየቴ እየተገረምኩ ሳለሁ፣ እጁ በደረቀ ጭቃ የቆሸሸ አንድ ወጣት ከማሳ ውስጥ ብቅ አለ፡፡
የሱፍ አብዱ ኡመሮ ይባላል። በሀገሩ ሠርቶ ለመለወጥ ቆርጦ ተነስቶ ሕልሙን በትጋት ማሳካት የቻለ ጀግና ነው። የማንንም እገዛ ሳይፈልግ በራሱ እጆች 20 ሜትር ርቀት ያለው ጉድጓድ ቆፍሮ ውሃ አወጣ። ከዚያም ማሳውን ቆፈረ። በድሬዳዋ አካባቢ በስፋት የሚመረተውን ጣፋጭ ብርቱካን ተከለ። ሳይታክት ከቆፈረው ጉድጓድ ውሃ በማውጣት የፍራፍሬ ዛፎቹን በመንከባከብ ራሱን ጠመደ። የሰጧትን እጥፍ ድርብ አድርጋ የምትሰጥ ምድር ፊቷን አላዞረችበትም። የልፋቱን ፍሬ ማጣጣም ቻለ። ነገር ግን በጥቂቱ አልረካም። ማሳው ከፍራፍሬ ዛፎች በሰጠው በረከት ብቻ መጥገብን እምቢ አለ።
የብርቱካን ዛፎቹ ደርሰው ከተለቀሙ በኋላ ለራሱም ሆነ ለማሳው ዕረፍት መስጠትን አልመረጠም። ከፍራፍሬ ዛፎቹ ስር ቃሪያ፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም በመትከል ራሱንም ማሳውንም በሥራ ያዘ። የአትክልት ምርቱን ሰብሰቦ ሲያበቃ ደግሞ በቆሎ ይዘራል። እንዲህ እንዲህ እያለ ከአንድ ሄክታር ማሳው በዓመት ሦስት ጊዜ የተለያየ ዓይነት ምርት ይሰበስባል።
ኦሮምኛ ቋንቋ ስለሚናገር አስተርጓሚ መያዝ ነበረብኝ። በአስተርጓሚው አንደበት ተነጋገርን። ‹‹በኬንያ ናይሮቢ የስደት ኑሮን ስገፋ ከቆየሁ በኋላ ወደ ሀገሬ ተመልሼ ጉድጓድ በመቆፈር ይሄን ውሃ ላወጣ ቻልኩ። ከዚህ በኋላ እኔ ድህነትን በሥራ እንዳሸነፍኩ ሁሉ ሌሎች ወጣቶችም ሀገር ጥሎ ለመሰደድ ማሰባቸውን ትተው በሀገራቸው ላይ ሠርተው መለወጥ እንደሚችሉ ከእኔ መማር እንዳለባቸው ተረዳሁ። ስለዚህም በአካባቢያችን ያሉ ወጣቶችን ፈለጌን እንዲከተሉ ማበረታታት ተያያዝኩ›› አለኝ፡፡
ቀድሞ በአካባቢው ስትኖር ያልታየህ የሥራ ዕድል ከስደት ከተመለስክ በኋላ እንዴት ተገለጸልህ ስል ጥያቄ አቀረብኩለት። ‹‹በሌላ አካባቢ መሬት ቆፍረው ውሃ በማውጣት የፍራፍሬ ልማት የሚያካሂዱ ሰዎችን ተመልክቼ ነው ወደሥራ የገባሁት። እነሱን ተመለከትኩና ለካ በዚህ መንገድ ማልማት ይቻላል ብዬ ወደ ሥራ ገባሁ። ይህን የምታየውን መሬት ቆፈርኩ። ከዚያ በኋላ እረፍት ለምኔ ብዬ ጠንክሬ ሠራሁ። ሕይወቴ ተቀየረ›› አለኝ።
‹‹ሠርተን መለወጥ እንደምንችል አየሁና ወደ ሥራ ገባሁ ከዚያ ውጤታማ ሆንኩ›› የሚለው ወጣት የሱፍ፤ ሥራውን ከጀመረ ሰባት ዓመት እንደሆነውና መሬቱ አንድም ጊዜ ያለምርት ተቀምጦ እንደማያውቅ ይናገራል። ‹‹አንድ ጊዜ ብርቱካን ሌላ ጊዜ አትክልት በኋላም በቆሎ እያልኩ እየቀያየርኩ አመርትበታለሁ›› ይላል።
“በመጀመሪያ ብርቱካን እናመርታለን። ብርቱካኑ ሲነሳ ደግሞ ሌሎች እንደ ሽንኩርት እና ቲማቲም ያሉ አትክልቶችን እንዘራለን። ከአትክልት ምርት ብቻ በዓመት ከአምስት መቶ ሺ ብር በላይ አገኛለሁ። ከብርቱካን ምርት ደግሞ በዓመት አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ አገኛለሁ” ሲል በኩራት ይናገራል።
የሱፍ በቆፈረው ጉድጓድ ከራሱ አልፎ የአካባቢውን ወጣቶች ተጠቃሚ አድርጓል። እርሱ ጉድጓድ ቆፍሮ ውሃ በማውጣት ማሳውን ሲያለማ የተመለከቱ የእድሜ ዕኩዮቹ ሌላ ጉድጓድ መቆፈር ሳያስፈልጋቸው የየሱፍን ውሃ በመጠቀም መሬታቸውን በማልማት በዓመት በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር ገቢ ማግኘት ችለዋል።
ለዚህ አንዱ ምስክር ሙክታር አብዶ ኢብራሂም የተባለው በአካባቢው የሚኖር ወጣት ነው። ከየሱፍ ጉድጓድ ውሃ በመጥለፍ ሁለት ሔክታር መሬት በፍራፍሬ ዛፍ እና በአትክልት አልምቷል። አሁን ላለበት ደረጃ የበቃበትን ሁኔታ ሲያስረዳ፤ ‹‹የሱፍ ብቻውን 20 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ቆፍሮ ውሃ አውጥቶ ምርት ሲያገኝ ካየሁ በኋላ እኔም እንደ እርሱ ውጤታማ የመሆን ጉጉት አደረብኝ። ተጠግቼ ጓደኛ አደረግኩት። የሱፍ ቀና ሰው ነው ያለውን ተሞክሮና እውቀት ያለስስት ለአካባቢው ወጣቶች ያካፍላል። ወጣቶች ሠርተው እንዲለወጡ ይፈልጋል። ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል ከእኔ ማሳ ተመልከቱ እያለ ይመክረናል። ምክር በመስጠትና በማበረታት ብቻም አልተወሰንም። በራሱ ላብ ብቻውን ቆፍሮ ያወጣውን የጉድጓድ ውሃ ተጠቅመን ማሳችንን እንድናለማ ፈቅዶልናል›› ይላል፡፡
ሙክታር ከየሱፍ ጉድጓድ የጠለፈውን ውሃ በመጠቀም ሁለት ሄክታር ማሳውን በማልማት ከብርቱካን ብቻ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚያገኝ ተናግሯል። ቃሪያ፣ ቲማቲምና ሽንኩርት በመትከል ደግሞ ተጨማሪ ገቢ ያገኛል። ልክ አርዓያ እንዳደረገው ጓደኛው የሱፍ ሁሉ እሱም ከአትክልቱ በኋላ በቆሎ በመዝራት ሌላ ሦስተኛ ምርት ይሰበስባል።
የሱፍ ጉድጓድ ቆፍሮ ውሃ አውጥቶ ማምረት ከጀመረ በኋላ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን ማቅረብ ጀምሯል። የሱፍን ተከትለን ወደ ሥራው የገባን ሌሎች ወጣቶችም ከመንግሥት አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገልን ይገኛል። እኔ ያለኝ መሬት ሁለት ሄክታር ስለሆነ ነው ከብርቱካን ብቻ ሁለት ሚሊዮን ብር የማገኘው እንጂ በጥረት እና በትጋት ከየሱፍ በልጬ አይደለም። እዚህ ደረጃ የደረስኩት እሱ ምሳሌ ሆኖኝ ነው ሲልም ያክላል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሱፍ ሌሎች ወጣቶች ላይ መፍጠር የሚችለውን ተፅዕኖ በመረዳት ከግብርና ሥራው ጎን ለጎን በአካባቢው ባለው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ በአመራርነት እንዲሳተፍ አድርጎታል። ይህ በመንግሥት የተሰጠው እውቅናም በአካባቢው ወጣቶች ዘንድ ያለው ተሰሚነት እንዲጨምርና የተፅዕኖ አድማሱ እንዲሰፋ አድርጓል። እርሱም ከግብርና ሥራው በተጨማሪ ለሚኖርበት ማኅበረሰብ ተጨማሪ አስተዋፅዖ ማድረግ የሚችልበት ዕድል ስለተፈጠረለት ደስተኛ ነው።
ወጣቶች አማላይ ዜናዎችን በመስማት ወደ ውጭ ሀገራት ለመሰደድ ከመወሰናቸው በፊት አካባቢያቸውን መመርመርና አጠገባቸው ባለው የሥራ ዕድል ለመለወጥ ምን ያህል ጥረት እንዳደረጉ ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። ሥራ ሳይንቁ ለመሥራትም መቁረጥ ይገባቸዋል። በእምነትና በትጋት ከተፍጨረጨሩና ከደከሙ ደግሞ ፈጣሪም ይረዳቸዋል። የድካማቸውን ፍሬም ያገኛሉ ሲል ይመክራል።
የሱፍ ከስደት መልስ በሀገሩ ላይ ጠንክሮ በመሥራት ስኬታማ በመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ተችሮታል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ከተማዋን የረገጡና የድሬዳዋን የልማት እንቅስቃሴ ለመመልከት የሚሹ እንግዶች ከሚደርሱባቸው ደጆች አንዱ የየሱፍ ማሳ እንዲሆን ማድረጉ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። የሱፍ እንደሚናገረው ሕልሙ ብዙ ነው፤ ወደፊት ይበልጥ ርቆ የመጓዝ ውጥን አለው። የእርሱ ለመላው የኢትዮጵያ ወጣቶች አርዓያ የሚሆን የስኬት ታሪክ ከዚህም በላይ መዘመርና ተደጋግሞ መነገር አለበት፡፡
ከስደት ተመላሾችን ለማደራጀት የሚደረገው ጥረት እና የሥልጠና ሂደት እንደ የሱፍ ያሉ ወጣቶችን ሕይወት አስረጂ አድርጎ በማቅረብ ሊታጀብ ይገባል። መግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት ሕገወጥ ስደት በርካታ ገፊና ሳቢ ምክንያቶች አሉት። የኅብረተሰቡ የአመለካከትና አስተሳሰብ ችግሮች፣ ድህነት፣ የደላሎች ባልተጨበጠ ተስፋ ማታለል፣ የአቻ ለአቻና የቤተሰብ ግፊት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። በእነዚህ ምክንያቶች ሀገር ጥለው የኮበለሉ ዜጎች ወደ በተለያየ ምክንያት ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ መልሰው የስደት ጉዞን አማራጭ እንዳያደርጉ እንደ የሱፍ ያሉ ወጣቶች ታሪክ ተስፋ እንዲሰንቁ ያደርጋቸዋል።
በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና መቆጣጠር የሥራ ሂደት በያዝነው ዓመት ታኅሣሥ መጨረሻ ላይ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ከ2014 እስከ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ምክንያት ከተመለሱ 133ሺህ ዜጎች ከ60ሺህ በላይ የሚሆኑትን ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቁሟል፡፡
ተመላሾቹን በሴፍቲኔት ፕሮግራም ለማደራጀት እንቅስቃሴ ሲደረግ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሊገኙ አልቻሉም። ከተጠቀሰው ቁጥር ግማሽ ያህሉ በለመዱት መንገድ ዳግም ወደ ሌሎች ሀገራት ተጉዘዋል። መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ተጎጂ የሆኑ ተመላሽ ዜጎች ተመልሰው ከመሄዳቸው በተጨማሪ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሌሎችንም ይዘው መሄዳቸው ነው።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከስደት ተመላሽ ዜጎች ዳግም በሕገ ወጥ መንገድ እንዳይሰደዱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ሕግን ማስፈጸምና የድንበር ቁጥጥር ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን መናገራቸው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም