“የክልላችንን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት የመገደላቸውን ዜና ከሰማሁ በኋላ ስጋት አድሮብኝ ነበር፡፡ከተማዋም ሆነች ክልሉ በአጭር ጊዜ ይረጋጋል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ጦርነት የሚከሰት መስሎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደፈራሁት አልሆነም፡፡በአሁኑ ወቅት ከተማዋም ሆነ ክልሉ ሰላም የሰፈነበት ነው” ሲል ያብራረው የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ዮሴፍ ተስፋዬ ነው፡፡
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከአማራ ክልል መዲና ባህርዳር የተሰማው ዜና እጅግ ዘግናኝ ነበር፡፡ የአማራ ክልል አስተዳዳሪ ዶክተር አምባቸው መኮንንን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት ላይ በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡ከተማዋ ክልሉ እንዲሁም ሀገሪቱ ወደ አስከፊ ሁኔታ እንዳትሸጋገር በሚል በርካቶች ስጋታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ስላለችበት ሁኔታ አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ዮሴፍ አንዱ ነው፡፡ከጓደኞቹ ጋር በእግር በመጓዝ ላይ ሆኖ ነበር የተኩስ ድምፅ የሰመው፡፡የተኩስ ልውውጡ እየበረከተ ሲመጣ ግን ወደ ቤቱ አቅንቶ ቴሌቪዥን እንደከፈተ እና በቴሌቪዥን መስኮት ሲተላለፍ ነበረው ዜናም እጅግ እንዳስደነገጠው ይናገራል፡፡
“ዜናውን ስሰማ ከተማዋ የጦርነት አውድማ ሆና መቅረቷ ነው የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር፤ ከተማዋ በአጭር ጊዜ ወደ ሰላሟ በመመለሷ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤ ከተማዋ ወደ ሰላሟ ልትመለስ የቻለችው የመንግሥት ጸጥታ ኃይልና የከተማዋ ህዝብ ባደረገው ጥረት ነው፡፡ይህም የከተማዋን ህዝብ ሰላም ወዳድነትና ስልጡንነት አመላካች ነው” ሲልም አስተያየቱን ሰጥቶናል ወጣት ዮሴፍ፡፡
የሆቴል ባለሙያው አቶ እስቲበል ደርሶ በበኩላቸው፤ ችግሩ ከተከሰተበት ዕለት አንስቶ ስለባህርዳር ከተማ ሲወራ የነበረው ከእውነታው የራቀ ነበር ይላሉ፡፡በጥቃቱ ማግስት በእግራቸው በመዟዟር ከተማዋን መቃኘታቸውንና ህዝቡ ኀዘንና ቁጭት ውስጥ መሆኑን ከሚያሳዩ አንዳንድ ስሜቶች በዘለለ ከተማዋ እጅግ ሰላማዊ እንደነበረች ተናግረዋል፡፡“ሁሉም ዓይነት እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡የግልና የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትም አገልግሎታቸውን ሲሰጡ ነበር” ብለዋል፡፡
“ህዝቡ በአሉባልታዎች ባለመነዳት፣ ራሱንና አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ በመቻሉ የከተማችን ሰላም አልደፈረሰም” የሚሉት አቶ እስቲበል፤ በጥቃቱ ዙሪያ ግልጽ ያልሆኑን እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎች በህዝብና በመንግሥት መካከል የነበረው መተማመን እንዲደፈርስ አድርጓል ብለዋል፡፡ይህም ህዝቡን ለውዥንብር መዳረጉንና አሁንም ቢሆን በጉዳዩ ዙሪያ ግልጽ የሆኑ መረጃዎች ለህዝቡ ሊደርሱ ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ፋርማሲስት ፈለገወርቅ አሰፋ በበኩላቸው፤ ግልጸኝነት የሌለበትና በሃሳብ የበላይነት ላይ ያልተመሰረተ ፖለቲካ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ትልቅ ሥራ ይሠራሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸውን የህዝብ መሪዎች እንዲቀጠፉ አድርጓል፡፡ሀገሪቷ ውድ መሪዎቿን እንድታጣም ምክንያት ሆኗል፡፡ዳግም መሰል ችግር እንዳይፈጠር ግልጽነትና በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ማራመድ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
እንደ ፈለገወርቅ ገለጻ፤ በተለይም ለህዝብ ጥቅም የሚሠሩ አመራሮች ግልጸኝነት የተሞላበት ፖለቲካ በማካሄድ ለህዝቡ አርዓያ ሊሆኑ ይገባል፡፡መንግሥት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ብቻውን ችግሮችን አይቀርፍም፡፡ህዝቡ ለራሱ ብቻ ከማሰብ ወጥቶ ለሀገር አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ማሰብ ይጠበቅበታል፡፡ለሀገር ያለውን ፍቅር በቃል ብቻ ከመግለጽ ወጥቶ በተግባር ማሳየት አለበት፡፡
በከተማዋ በሹፍርና ሙያ የሚተዳደሩት አቶ ፈቃደሥላሴ እሸቱ በበኩላቸው እንደገለጹት መንግሥት የህግ የበላይነት በማስከበር ረገድ ድክመቶች ይታዩበታል፡፡መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ምንም ሊያመነታ አይገባም፡፡ መብት ነው ተብሎ ሁሉም ነገር ልቅ መደረጉ ሀገሪቷን ዋጋ እያስከፈላት ነው፡ ፡የህዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ የሚሠሩ ሥራዎች ሳይሠሩ ሁሉንም ነገሮች ልቅ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ መንግሥት ህግን የማስከበር ተግባሩን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል፡፡መንግሥት ህግ ማስከበር ላይ ያለውን ውስንነቶች ማስተካከል ከቻለ ብዙ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ይላሉ፡፡
አቶ ፈቃደሥላሴ እንደሚሉት መንግሥት ሀሉንም ነገር የሚያይ ዓይንና የሚሰማ ጆሮ ሊኖረው አይችልም፡፡በመሆኑም መንግሥት ሰላምን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ህዝቡ ሊያግዝ ይገባል፡፡መንግሥት ማስተካከል ያለበትን ነገሮች ማስተካከል የሚችለው ከህብረተሰቡ በሚሰጥ ጥቆማና አስተያየት ነው፡ ፡ለሰላም ጸር የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ ለፖሊስና ለጸጥታ አካላት በመጠቆም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2011
መላኩ ኤሮሴ