አዲስ አበባ:- በመልከአ-ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት አብዛኞቹ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የወቅቱን የክረምት ዝናብ ተከትሎ ሊደርሱ ለሚችሉ የተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ በመሆናቸው እነዚህን የአደጋ ስጋቶች ለመከታተል፣ ለመቀነስ፣ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የከተማው ነዋሪ አደጋ የመቋቋምና የመከላከል ዝግጁነቱን፣ የመከታተልና መረጃ የመሰብሰብ አቅሙን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳት አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ኮሚሽኑ የነዋሪዎችን አደጋ ቀድሞ የመከላከል እና የመቋቋም አቅም ባህልን ለማሳደግና የነዋሪዎችንና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትን የተቀናጀ የአደጋ ስጋት ቅነሳን ለማዳበር፣ የተጋላጭነት ደረጃን ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የአደጋ ክስተት መንስኤዎች፣ ወቅት፣ የተጋላጭነት ሁኔታና ደረጃ፣ እንዲሁም አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የቅድመ ጥንቃቄ ዕርምጃዎች ተለይተው ህዝቡ እንዲያውቃቸው ተደርጓል።
የኮሚሽኑ ኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን መኮንን ከአደስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ከተማዋ በተለያዩ፣ ክረምቱን ተከትለው ሊከሰቱ በሚችሉ አደጋዎች የተጋለጠች ነች፤ ይህም በጥናት ተረጋግጧል፤ አካባቢዎቹም ተለይተዋል። ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ኮልፌ ክፍለ ከተማ በ13 ወንዞችና በ20 ማፋሰሻዎች በድምሩ በ23 ሊከሰቱ ለሚችሉ አደጋዎች የተጋለጠ ሲሆን ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ በ2ኛ፣ አዲስ ከተማ በ3ኛ ደረጃ የተጋለጡ ናቸው።
ደረጃው ይለያይ እንጂ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አደጋዎች ሊከሰቱ ስለመቻላቸው ጥናቱ አመልክቷል የሚሉት አቶ ሰለሞን ከምን ጊዜውም በላይ ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይናገራሉ።
እንደ የእሳት አደጋ ስጋት ሽራ አመራር ኮሚሽን ኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ማብራሪያ ህይወት ከመጥፋቱ፣ ጤና ላይ ተፅእኖ ከመድረሱ፣ በንብረትና በመሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ ጉዳት ከመድረሱ፣ የማህበራዊና ኮኖሚያዊ ልማት ከመስተጓጎሉ፤ ወይም አካባቢ ላይ የከፋ ጉዳትና ውድመት ከመድረሱ በፊት ነዋሪው ከወዲሁ አስፈላጊውን ክትትልና መከላከል ሊያደርግ ይገባል።
ከከተማው አቀማመጥ ባለፈ የቤቶች አሠራር ሁኔታ ከቆርቆሮና ጭቃ መሆን፣ በብሎኬት የተሠሩትም ቢሆን የጥራት ማነስ መኖሩና የመቋቋም አቅማቸው 22 በመቶ ወይም ዝቅተኛ መሆኑ፣ በከተማው አደጋ ቢከሰት ቶሎ ደርሶ ለመቆጣጠር ያለው የመንገድና ሌሎች ሁኔታዎች 55 በመቶ ላይ መገኘት፤ የቆሻሻ ማስወገጃ ዘዴ 28 በመቶ፣ የተቀናጀ የልማት ሁኔታ 34 በመቶ፣ እንዲሁም አደጋን የመቋቋም አቅም 27 በመቶ ከመሆኑ አኳያ አደጋ ቢደርስ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑና ሰብዓዊ ቀውስና ቁሳዊ ውድመቱም ቀላል ስለማይሆን ሁሉም የከተማው ነዋሪና ባለድርሻ አካላት ይህንን በመገንዘብ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄና መከላከል ሊያደርጉ እንደሚገባ የኮሚሽኑ ጥናት አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2011
ግርማ መንግስቴ