የአዲስ አበባ ለውጥ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ተሳታፊዎችን ቆይታ ያራዝማል

አዲስ አበባ፡በ38ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመሳተፍ የሚመጡ መሪዎችና ዲፕሎማቶች አዲስ አበባ ከተማ በተላበሰችው ውበትና ምቹ ሁኔታ ቆይታቸውን የሚያራዝሙ ይሆናል ሲሉ ዲፕሎማት እና ፖለቲከኛ ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር) ገለጹ።

ተሻለ ሰብሮ ዶ/ር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ገጽታዋን በቀየረችው አዲስ አበባ ከተማ መካሄዱ ለእንግዶች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው። መሪዎችና ዲፕሎማቶች አዲስ አበባ ከተማ በተላበሰችው ውበትና ምቹ ሁኔታ ደስታ ስለሚሰማቸው ቆይታቸው ከዚህ ቀደም ከነበረውም በላይ ያማረና የሚረዝም ይሆናል።

በጉባዔው ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ የአፍሪካ እና የዓለም ሀገራት የሚመጡ በርካታ ጋዜጠኞች እንደሚገኙ የገለጹት ተሻለ (ዶ/ር)፤ እነዚህ ጋዜጠኞች የአዲስ አበባን አዲሱን ገጽታዋን ለዓለም ሕዝብ ሊያስተዋውቁ እንደሚችሉ አመላክተዋል።

ይህን ተከትሎም ከተማዋ ባሳየችው መነቃቃት ለሌሎች ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች (ኮንፈረንሶችም) የማዘጋጀትና የማስተናገድ የመመ ረጥ ዕድሏ እንደሚሰፋ ገልጸዋል።

የከተማዋ ለውጥ መንግሥት የሠራቸውን የልማት ሥራዎች በተጨባጭ የሚያሳይ እና የአፍሪካ መሪዎችም የሚማሩበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ተሻለ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተሠሩት የልማት ሥራዎች የሕዝቡን ፍላጎትና ዓለም የደረሰበትን የእድገት ደረጃ መነሻ አድርገው የተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሌላው ገጻቸው ከተማዋ ያሳየችውን ለውጥና ማራኪነት አጎልተው የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

የዓድዋ ድል የአፍሪካዊያን ኩራት እንደሆነ ሁሉ ለመታሰቢነት ተብሎ የተሠራው የዓድዋ ሙዚየምም የከተማዋ አንድ ድምቀት እንደሆነ ጠቅሰዋል። አፍሪካውያን ስለዓድዋ ድል አንብበው ወይም አድምጠው ያወቁትን ታሪክ በሙዚየሙ ተገኝተው የተደራጁ ታሪክ አዘል ቅርጻ ቅርጾችን በማየት ሙሉ ምስል የሚጨብጡበት እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት እንደሆነች ሁሉ አሁንም በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎችም የተሠራው ከተሞችን የማዘመን ሥራም ይሁን ሌሎች የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን ተምሳሌትነት ያስቀጠሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንግዶች የሀገሪቱን መልካም ስም ይዘው የሚሄዱት የከተማዋን ማማር ብቻ አይተው ሳይሆን የሰላሟና የጸጥታዋ ጉዳይም አስተማማኝ ሲሆን ነው ብለዋል።

የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ እንዲህ አይነት አህጉር አቀፍ መድረኮችን ጠብቀው የሀገር ገጽታን ለማበላሸት የሚሰሩ ኃይሎች አይጠፉም ያሉት ተሻለ (ዶ/ር)፤ ሕዝቡ ከምንጊዜውም በላይ የከተማዋን ሰላም ጠብቆ እንግዶች በሰላም ጉባዔውን ጨርሰው እንዲሄዱ መተባባር አለበት ብለዋል።

አዲስ አበባ ከተማ ምንም አይነት ኮሽታ ሳይሰማባት እንግዶቿን አስተናግዳ በሰላም እንድትሸኝ ነዋሪዎችም ሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You