የአፍሪካ አንድነት አባቶች

እ.ኤ.አ. በ1963፣ ሰላሳ ሁለት ነፃ መንግሥታት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ያቋቋሙ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ 2002 የአፍሪካ ሕብረት ከተቋቋመ በኋላ የአባላቱ ቁጥር ወደ 45 ደርሶ ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ራዕይ የነበረው ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት አህጉሪቱ እየገጠሟት የነበሩትን ተግዳሮቶች እንዲሁም የቅኝ ግዛት እና የዘር መድልዎ መወገድን በተመለከተ ነበር።

አውሮፓውያን በ19ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን በመቀራመት ዜጎቿን ለባርነት፣ ሀብቷንም ለግል ጥቅማቸው በማዋል በርካታ በደሎችን ፈጽመዋል:: በዚህም ከኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ በስተቀር ሁሉም ለቅኝ ግዛት ተዳርገው ቆይተዋል::

ይህ የቅኝ ግዛት ታዲያ ለብዙዎቹ አፍሪካ ሀገራት እስከዛሬ የግጭት እና የድህነት መንስኤ ሆኖ ቆይቷል:: ቅኝ ገዢዎች አፍሪካውያንን በዘር እና በአካባቢ እንዲከፋፈሉ በማድረግ የግጭት እርሾ በማኖራቸው ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከፊሎቹ ለመለያየት፣ ከፊሎቹም ለእርስ በርስ ግጭት እንዲዳረጉ አድርገዋል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግን በተለይ ከቅኝ ግዛት የተላቀቁ የአፍሪካ ሀገራት ይህንን ታሪክ ለመቀየር ሕብረት መመስረት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት አድርገዋል:: በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በዚህ መሰረት ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ የወቅቱ መሪዎች መካከል ጥቂቶቹን ዛሬ እናስታውስ።

ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጋር ተያይዞ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሳ የወቅቱ መሪዎች መካከል ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አንዱ ናቸው:: ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከማድረጋቸውም ባለፈ ድርጅቱ ከተመሰረተ በኋላ በተፈጠረው ክፍፍል ድርጅቱን ከመፍረስ የታደጉ መሪ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩት ሀገራት ነጻነት የከፈለችው ዋጋ ውድ ነው:: ነጻነቷን ጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያ ብቻዋን የመንግሥታቱ ማኅበር አባል በነበረችበት ወቅት የአውሮፓውያንን የግፍ ወረራ አውግዛለች፤ ብቻዋንም በፍትህ አደባባይ ቆማለች::

ኢትዮጵያ የዓለም ሕብረቶችን መሥራች ሆና በአባልነት የምትቀላቀለው በዓለም ላይ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ጉልበተኞች አቅመ ቢሶችን እንዳይጨፈልቁ እና ሁሉም የዓለም ሕዝብ በእኩልነት የመኖር መብቱ እንዲከበርለት ነው::

ለዚህም ነው ራሷ ነጻነቷን ስላስከበረች በቃ ብላ ያልተቀመጠችው:: አፍሪካውያን ወንድሞቿ ነጻ ሳይወጡ ነጻነቷ ሙሉ ስለማይሆን አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲሆኑ የታገለችው:: የዓለምን ፍትህ የማይሻው የምዕራባውያኑ ጎራ ይህን የኢትዮጵያን ጥረት ለማሰናከል እና አፍሪካን ድምጽ አልባ ለማድረግ ዛሬም ኢ-ፍትሃዊ ጫናቸውን እንደቀጠሉ ነው::

ኢትዮጵያ አፍሪካ ነጻነቷን እንድታገኝ ካደረገቻቸው ትግሎች ጎን ለጎን አፍሪካውያን ሕብረት ፈጥረው የሚደርስባቸውን ጫና እንዲቋቋሙ እና ሕዝቦቻቸው ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲሸጋገሩ ስትሰራ ቆይታለች:: ጋና በ1949 ዓ.ም ነጻነቷን በማግኘት የጀመረችው ጉዞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከተመሠረተበት ግንቦት 1955 ዓ.ም ድረስ 32 ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ወጥተዋል:: እነዚህ ሰላሳ ሁለት ሀገራትም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሰረቱ::

ኢትዮጵያ እና ሌሎች የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞች ድርጅቱን ለመመሥረት ያነሳሳቸው ነጻነታቸውን ያላገኙ ሀገራት ነጻ እንዲሆኑ ነጻነታቸውን ያገኙት ደግሞ ነጻነታቸው ሙሉ እንዲሆን ነበር::

ድርጅቱ ገና የምሥረታ ሀሳቡ ሲጠነሰስ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ያላቸው ቡድኖች ተፈጠሩ:: እነሱም የሞኖሮቪያ እና የካዛብላንካ ቡድኖች ናቸው:: እራሱን “የዘመናዊ እና ተራማጅ አስተሳሰብ አቀንቃኝ” ብሎ የሚጠራው እና በጋናው ፕሬዚደንት ክዋሜ ንክሩማ የሚመራው የ“ካዛብላንካ ቡድን” ሲሆን፣ ቡድኑ አፍሪካ በሕብረት መዋሀድ አለባት የሚል ዓላማ የያዘ ነበር:: አባላቱም ጋና፣ አልጄሪያ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ማሊ እና ሊቢያ ነበሩ።

ሁለተኛው የ”ሞኖሮቪያ ቡድን” ሲሆን የተመራው በሴኔጋሉ ፕሬዚደንት ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንግሆር ነበር። አባላቱ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ላይቤሪያ እና ኢትዮጵያ ሲሆኑ የነሱ ሀሳብ ደግሞ በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ሕብረት መመሥረት አዳጋች ስለሆነ የአንድነት ድርጅት ተመስርቶ በሂደት ወደ ሕብረት ማደግ አለበት የሚል ነበረ።

በዚህ መሀል ገለልተኛ ሆነው ወደ የትኛውም ቡድን ያልተቀላቀሉ ሀገራትም ነበሩ:: እነዚም ቤኒን፣ ቱኒዚያ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ቶጎ፣ ሶማሊያ፣ ኮትዲቯር፣ ኬንያ፣ ኮንጎ፣ ጋቦን፣ ማዳጋስካር፣ ሞሪታኒያ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሴራሊዮን፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ኒጀር፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ማላዊ ነበሩ::

ኢትዮጵያም በወቅቱ የነበረውን የዓለም ሁኔታ፣ ሀገራቱ የነበሩበትን የሥነ-ልቦና ደረጃ እና ውጫዊ ተጽዕኖዎችን ከግምት በማስገባት ሁለቱን ቡድኖች በማግባባት እና ሁሉንም ያካተተ ድርጅት የመመሥረት ትልቅ የቤት ሥራ ወስዳ ሥራ ጀመረች:: የኢትዮጵያ እና የአጋሮቿ የወቅቱ አቋም የነበረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመስርቶ የማሰባሰቡን ሥራ ከሰራ በኋላ ወደ ኅብረት እና ውህደት እንዲሄድ ነበር::

ለዚህም ምክንያቶቹ በወቅቱ ሁሉም ሀገራት ሙሉ በሙሉ ከቅኝ አገዛዝ ስላልተላቀቁና በዚህ ሁኔታ የሚፈጠረው ኅብረትም የተሟላ ስለማይሆን፣ በሌላ በኩል ነጻነታቸውን ያገኙ ሀገራትም ቢሆኑ ከቅኝ ገዢዎቹ የሥነ-ልቦና ጫና ባለመላቀቃቸው ይህም እንኳን ወደ ውህደት የሚሄድ ኅብረት ቀርቶ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እንኳን ለመግባባት ከባድ ስለሚሆን ነበር::

በዚህም መሰረት በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ታላቅ ጥረት እና በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በሳል ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ሁለቱም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ እንዲገናኙ ተደርጎ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ በኢትዮጵያ ሀሳብ ተስማሙ::

በስምምነቱ መሠረትም ገለልተኛ የሆኑ ሀገራትንም ጨምሮ 32ቱ ሀገራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቻርተር እንዲፈርሙ ተደርጎ ድርጅቱ ተመሰረተ። ለዚህ ስኬት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ቀደማዊ ሀይለስላሴ ሚና እጅግ ጉልህ ነው።

ከወቅቱ መሪዎች መካከል ሌላው ዶክተር ክዋሜ ንኩሩማህ ናቸው። ዶ/ር ክዋሜ ንክሩማህ ነፃነቷን ያገኘች የመጀመሪያዋ ከሰሃራ በታች ያለች የአፍሪካ ሀገር የጋና መሪ ነበሩ። በመቀጠልም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት በተካሄደው ዘመቻ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኑ። ለፓን አፍሪካኒዝም ጥብቅና በመቆም እ.ኤ.አ. በ1963 በአዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል።

ለመጀመሪያ ግዜ የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ያካሄዱ መሪ ነበሩ:: የክዋሚን የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግልን ተከትሎ በርካታ ሀገራት የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል መጀመራቸው የሚታወስ ነው:: በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ጨለማዋ አህጉር ተብላ ትጠራ የነበረው አፍሪካ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን የሚያወሱ ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮቻቸው አፍሪካ ከቅኝ ገዢዎች የግፍ አገዛዝ እንድትወጣ ፋና ወጊም ነበሩ:: ንክሩህማ ::

ንክሩህማ የእኛ ነጻ መውጣት (መላው አፍሪካ ነጻ ሳትወጣ) ብቻ ትርጉም የለውም የሚል ዘመን አይሽሬ ንግግር ነበራቸው:: ንክሩህማ ሁሉም (አርባ አራቱም የአፍሪካ ሀገራት) ከቅኝ ገዢዎች ነጻ መውጣት አለባቸው ብቻ ማለታቸው አልነበረም:: ይሁንና አፍሪካ ከችጋር፣ እርሃብ፣ በሽታ እና ድንቁርና ነጻ መውጣት አለባቸው ማለታቸው ነበር::

ክዋሜ አፍሪካ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንድትወጣ፣ አንድነቷ እንዲጠበቅ፣ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መዳፍ ስር እንዳትወድቅ፣ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነጻ መውጣት እንዳለባት፣ ወዘተ ጠንካራ ርዕዮት ዓለም ነበራቸው:: ከመጽሐፋቸው የተወሰደው የሚከተለው አረፍተ ነገር ጠንካራ አመለካከትና ሕልም እንዳላቸው ማሳያ ነው::

አፍሪካን አንድ ለማድረግ ታላቁ የንክሩሁማ ታላቅ ሃሳብና ራዕይ በሌሎች የአፍሪካ ፓንአፍሪካኒስት ጽንሰ ሃሳብ አራማጆች አፍሪካውያን ተቀባይነት ነበረው:: ለአብነት ያህል የጊኒው ፕሬዚደንት ሴኩቱሬ ይጠቀሳሉ::

በድህነት ለመኖር የመረጥን ነን:: እኛ ወደ ባርነት እየሄድን ነው:: ጊኒ ትንሽ ሀገር ናት:: ይሁንና ፍርሃታችንን አስወግደን ነጻነታችንን ለመጎናጸፍ መነሳት አለብን:: ማንም ሰው የሌሎች አፍሪካውያን ብቸኛ የነጻነት ታጋይ እኔ ብቻ ነኝ ማለቱ ስህተት ነው:: አፍሪካውያን ሁላችንም በሕብረት ነጻነታችንን ማስጠበቅ አለብን:: እያንዳንዱ አፍሪካዊ ስለ አፍሪካ ብልጽግናና ሉአላዊነት በተመለከተ ሃሳቡን መሰንዘር መብት አለው:: (ፕሬዚደንት ሴኩቱሬ)

ሌላው በግዜው የታወቁት አፍሪካዊ መሪ የነበሩት የሴኔጋሉ ፕሬዚደንት ባለቅኔውና ጸሃፊው ሊኦፖልድ ሴንጎር (Leopold Senghor) ነበሩ:: እኚህ ታላቅ ሠው ጥልቀት በርካታ ጽሁፎቻቸው ለአፍሪካ አንድነት ጽኑ አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል:: ከዚህም ባሻገር ሊኦፖልድ ለአፍሪካ ባሕል መጠበቅና መጎምራት የኔግሮ (Negritude) ጽንሰ ሃሳብም እንዲበለጽግ በብዙ የደከሙ መሪ ነበሩ::

ከላይ በስም የተጠቀሱት የአፍሪካ መሪዎች ሁሉ የአፍሪካ ሰብዓዊና የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢንዱስትሪዎችን በማበልጸግ፣ ንግድ እና ገበያን በማስፋፋት የተባበረችው አፍሪካን ለመመስረት እቅድና ዝግጅት እንደነበራቸው የአሁኑ ትውልድ ሊገነዘበው ይገባል::

ሌላው የኬኒያው መሪ ጆሞ ኬንያታ ናቸው። ኬንያታ የማኦ ማኦ ንቅናቄ በመባል የሚታወቀው የኬንያ የነጻነት ንቅናቄ መሪ ነበሩ፣ በአፍሪካውያን ተወላጆች ቁጥጥር ስር ላለው የኬኒያ መንግሥት ጠንካራ ደጋፊ እና የሀገሪቱ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመጀመሪያ ፕሬዚደንት ነበሩ። እ.ኤ.አ. በ1963 ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራቾች አንዱ ናቸው። አምስተኛውን የፓን አፍሪካ ኮንግረስ በማዘጋጀትም ረድተዋል።

ሴዳር ሴንጎር ሴኔጋላዊ ገጣሚ፣ ፖለቲከኛ እና የባሕል አጥኚ ነበር፣ ከነጻነት በኋላ የሴኔጋል የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ሆነ። ሴንጎር የሴኔጋል ዲሞክራቲክ ብሎክ ፓርቲ መስራችም ነበር። ሴንጎር የአካዳሚ ፍራንሷ አባል ሆኖ የተመረጠ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ነው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩት የአፍሪካ ምሁራን እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች አንዱ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይገመታል።

ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ትልቅ አስተዋጽኦ ከነበራቸው የወቅቱ መሪዎች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው። ለድርጅቱ ምስረታ ከ30 በላይ መሪዎች ፊርማቸውን ማኖራቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You