በአሜሪካ የሚገኙ ስደተኞች ቤት ውስጥ ለመደበቅ ተገድደዋል

በአሜሪካ የሚገኙ ስደተኞች ዶናልድ ትራምፕ እየወሰዱ ያለውን ርምጃ በመፍራት ከቤት መውጣት አለመቻላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል:: የትራምፕ አስተዳደር ወደስልጣን በመጣ ማግስት ከወሰዳቸው ርምጃዎች አንዱ የሕገ ወጥ ስደተኞች ጉዳይ ሲሆን፤ በዚህ ውሳኔም በርካቶች ወደሀገራቸው እየተመለሱ ይገኛሉ:: የአይስ አባላት ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከትምህርት ቤት፣ ከሥራ ቦታ፣ ከእምነት ተቋማት፣ ከሆስፒታል እና ከመሰል ሊሸሸጉበት ይችላሉ ብሎ ካመነበት ስፍራ እያሳደደ ይገኛል:: በዚህ ስጋት የተነሳ ሥራ መሄድ እንዳቆሙና እና ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ እንዳልቻሉ ቃላቸውን ለቢቢሲ ከሰጡት ስደተኞች ማወቅ ተችሏል::

በዚህ አሰሳ የወንጀል ሪከርድ ያለባቸውም ሆነ የሌለባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ማጎሪያ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል:: በቀን ከአንድ ሺህ በላይ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር እንደሚያውል የተናገረው የአይስ ቡድን፤ ይሄን አሰሳ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የስልጣን ዘመን ከነበረው አሰሳ ጋር ሲያነጻጽረው በሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ አሜሪካ ወሳኝ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ገልጿል:: በጆባይደን ዘመን በቀን በአማካይ ሶስት መቶ አስራ አንድ ስደተኞችን በሕግ ጥላ ስር በማዋል እርምጃ ይወሰድ እንደነበር አያይዞ ገልጿል::

ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን በያዙ ማግስት የተጀመረው አሰሳ ውጤታማ መሆኑን በመግለጽ በቅርቡ በሰኔቱ የወንጀል ታሪክ ያላቸውን ስደተኞች በሚመለከት ሕግ ሆኖ የጸደቀው የምክር ቤቱ ትዕዛዝ ለሕግ አስከባሪዎች ሰፊ ስልጣን ሰጥቷል:: ከዚህ ስልጣን አንዱ ሰነድ አልባ ስደተኞች በተያዙበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከአሜሪካ እንዲባረሩ ማድረግ ሲሆን፤ ይህ አይነቱ ተግባር ቀደም ባለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ በጦርነት ወቅት ካልሆነ በቀር የማይደረግ ነበር::

ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የትራምፕን ውሳኔ የሚተቹ ሀገራትና ግለሰቦች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም:: ፒየስ አሊ የፖርት ላንድ ፖሊስ አማካሪ ናቸው:: የፕሬዚዳንት ትራምፕን አስጨናቂ ውሳኔ በመቃወም ‹‹ሕጉ ላልተፈለገ ዓላማ እየዋለ ነው›› ይላሉ:: እንደምሳሌ የሚያነሱትም በእምነት ተቋማት እና በሆስፒታል አካባቢ ያሉ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት በማንሳት ነው:: በዚህ ስፍራ ያሉ ሰዎች በምንም አይነት መልኩ የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይገባም በማለት ይናገራሉ::

ሁሉንም ስደተኞች እንደሕገ-ወጥ በመቁጠሩ ሕጉ ባልተፈለገ ሁኔታ እየተተረጎመ መሆኑን ያነሳሉ:: አማካሪው በማያያዝ ‹‹ስደተኞች ቤታችሁ ሲንኳኳ እና ደጅ የቆሙት ፖሊሶች ከሆኑ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወደቤቴ መግባት አትችሉም›› ስትሉ ተሟገቷቸው ሲሉ ለስደተኞቹ ምክር እስከመለገስ ደርሰዋል::

ከአስራ ሰባት ሀገራት የመጡ አንድ ሚሊዮን ስደተኞች በአሜሪካ ጊዜያዊ ከለላ ተደርጎላቸው እየኖሩ ይገኛል:: አሜሪካ ለካሜሮን፣ ለደቡብ ሱዳን እና ለኢትዮጵያ ዜጎች የሰጠችው ልዩ የከለላ መብት በዚህ ዓመት ማብቃቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ጊዜው እንዳበቃ እነዚህ ዜጎች ከአሜሪካ ልንባረረ እንችላለን በሚል ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል::

የአይስ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ባለፈው የፈረንጆቹ 2024 ብቻ በሜክሲኮ ድንበር የገቡ አንድ ሺህ ስምንት መቶ አስራ ስምንት አፍሪካውያን ከአሜሪካ ተባረዋል:: ከአስራ አንድ ዓመት በፊት ከኮንጎ የተሰደደው ሀኪም ካዱሊ ‹‹ትራምፕ ሰብአዊነትን ከፖለቲካ ሊያለካኩ አይገባም:: ሁሌም ቢሆን ሰብአዊነትን ሊያስቀድሙ ይገባል:: አሜሪካ ታላቅነቷን የምታገኘው ያኔ ነው›› ሲል ለወቅቱ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት መልዕክቱን አስተላልፏል::

አንዳንዶች አሜሪካ እየወሰደችው ያለው የስደተኞች እርምጃ የአፍሪካ መሪዎች ከተጠቀሙበት መልካም እድል እንደሆነ ይናገራሉ:: የስደት በሮችን በመዝጋት፣ ዜጎቻቸው የሚለወጡበትን እድል በመፍጠር በባዕድ ሀገር የሚፈሰውን እውቀት እና የሰው ኃይል ለሀገራቸው መጠቀም ይችላሉ› በማለት ተናግረዋል:: የመረጃው ምንጭ ቢቢሲ ነው::

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You