
ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነበር:: ምሁሩ የአዕምሮ ምጡቅ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ያመሩት:: እኝህ ሰው በጊዜው በቀላሉ መታከም የሚችሉ አይነት ሕመምተኛ አልነበሩም:: ፍልስፍናቸው ከስነልቦና ሐኪሞቹ እሳቤ በላይ የረቀቀና የላቀ ነው:: ሀኪሞቹ በቀላሉ ያሉበትን የሕመም ደረጃ ለመለየት ከብዷቸዋል::
በተለይም ኃላፊነት ወስደው የሚሰሩት ባለሙያ የአዕምሯቸው ምጥቀት እጅጉን ያስደምማቸው ነበር:: ሰውዬውን በቀላሉ እንደማያክሟቸው ሲረዱ ሌሎች አማራጮችን ወደመጠቀም ገቡ:: በእርግጥ አንድ የሱስ ሕመምተኛ በአንድ ሰው ብቻ አይታከምም:: ብዙ ባለሙያዎች በተለያየ ምልከታቸው ሊደግፉትና ከነበረበት ችግር ቀና ሊያደርጉት ግድ ይላል::
ለእኝህ ሰው በቅርብ ክትትል የሚያደርግላቸው አንድ ባለሙያ ቢመደብ ሌሎች የእገዛው አካል ይሆናሉ:: ስለዚህም ተባብረው የተሻለውን አማራጭ ለማግኘት ወሰኑ:: ሰውዬው በሥራዎቻቸው ብዙዎች የሚደነቁባቸው፣ በአስተሳሰባቸውም ለበርካቶች ግርምት የሚፈጥሩ ናቸው:: ከቤተሰቡም አስተሳሰባቸው ይለያል:: ሌሎች ድርጅቶች ላይ ገና ሲቀጠሩ ጀምሮ የሚያመጧቸው ለውጦች አጀብ ያሰኛሉ:: ይህ ሁኔታቸው የጀመረው ደግሞ ገና ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ጀምሮ እንደነበር የኋላ ታሪካቸው ያስረዳል:: ከዩኒቨርሲቲ ሲመረቁ በከፍተኛ ማዕረግ ስለነበር ዩኒቨርሲቲው በግቢው ሊያቆያቸው የሚሻ ተፈላጊ ነበሩ:: ሱሰኝነታቸው ግን ዕንቅፋታቸው ሆነ:: ከአርዓያነታቸው ይልቅ ሌሎች ጤናማ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ በሚል ሳይወዱ በግድ ለሌሎች ድርጅቶች አሳልፈው እንዲሰጧቸው ግድ አለ::
ከዩኒቨርሲቲው ቢወጡም አቅማቸውን የሚያውቁ ድርጅቶች ‹‹ለእኔ ለእኔ›› ማለታቸውን አላቆሙም:: በወቅቱም መርጠውና ፈቅደው ወደ አንዱ ድርጅት ገብተዋል:: በዚህ ድርጅት በሥራው አንቱታን አትርፈው አርኣያ የሚሆኑ ሰራተኞች ፈጥረዋል:: ሆኖም በቆይታቸው በአንድ ነገር እጅጉን ተፈተኑ:: ከሱሰኝነቱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች የማይፈቱበት ደረጃ ላይ አደረሷቸው::
ይህ ደግሞ ለትልቁ ድርጅት ራስ ምታት ሆኖ ዘልቋል:: የሕይወታቸውን ምስቅልቅል ሲመለከቱም ስለእሳቸው የሚከፉ አልጠፉም:: ይህ ግን ለቀጣይ መንገድ የተሻለ አማራጭ በር ከፋች ሆኖ ተገኘ:: የሚመሩት ተቋም ከሙሉ ቤተሰቡ ጋር በመሆን ለችግሩ እልባት ለመስጠትና ለምክክር በአንድ መስመር ተገናኝቷል::
ከዚያም አልፎ እርሳቸውን በማሳመን ወደ ሆስፒታል እንዲሄዱ አድርጓል:: የባለሙያዎቹ፤ የድርጅቱ ባለቤትና ቤተሰቦቻቸው ያደረጉት ጥረት ዛሬ ላይ ብዙ ይሉት ተስፋን አሳይቷል:: መልከ መልካሙንና የዋሁን ምሁር በእጅ አስገብቷል:: በተለይ የሥነ ልቦና ሕክምናውን በተናጠልና በቡድን ማድረግ ሲጀመር ያለው ለውጥና አመለካከት እሳቸው ለብዙዎች እንዲተርፉ አስችሏል::
ታላቁ የዕውቀት ሰው ወደተፈጥሯዊ ማንነታቸው በመመለሳቸውም ሁሉም በተለየ ደስታ ረክቷል:: ሀገር የምትፈልገው ድንቅ ሰው በዚህ ደረጃ ወደ ቀልቡ በመመለሱም በርካቶች የልባቸው ሞልቷል:: ከሁሉም በላይ ሰውዬው ዛሬ ላይ ትልቅ የሚባለውን ተቋም በአቅምም፣ በእውቀትም መምራት ብቻ ሳይሆን በሆስፒታሉ የቡድን ሕክምናውን በሙያቸው እየደገፉ ነውና ተሞክሮው ለብዙዎች የሚጋራ መሆኑን አቶ ስዩም ዘውዴ በአማኑኤል ሪፈራል ሆስፒታል የክሊኒካል ሳይኮሎጂ ባለሙያ ነግረውናል::
አቶ ስዩም እንደሚሉት፤ ሱሰኝነት አንዱ የሥነ አዕምሮ ጤና ችግር መሆኑን ይናገራሉ:: ሱስ አንድን ነገር በተደጋጋሚና ለረጅም ጊዜ በመጠቀም ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥገኝነትን በራስ ላይ ያሳድራል:: የሱሰኝነት መገለጫዎቹ በርካታ ናቸው:: ዋና ዋናዎቹን ሱስ የሆነብንን ነገር ካላገኘን ሥራ ለመስራት መቸገር፤ ሰውነታችንን በወጉ አለማዘዝ፣ መንዘፍዘፍና መንገድ ላይ መውደቅ ሊከሰት ይችላል::
ከዚህ ባለፈም አካላችን ላይ ጉዳት እንድናደርስ ማስገደድ፤ ጤናማ ሕይወትን ለመምራት መቸገር፤ ውስጣዊ ረብሻን ማስተናገድ፤ በነገሮች አለመርካት፤ ከሌሎች ጋር መግባባት አለመቻል ይስተዋልብናል:: ሱስ ለማቆም ስንሞክር ደግሞ በጊዜያዊነት ጭምር የሚረብሽ ስነልቦናዊ ክስተቶች ሊፈጠሩብን ይችላሉ::
እንደ ሀገር ይህንን መረጃ በአንድ ቋት አስቀምጦ በተከታታይነት የሚያሳይ ተቋም ባለመኖሩ ምን አይነት ለውጥ እንዳለው መረዳት ያስቸግራል:: የተለያዩ ጥናቶች በተለያየ መልኩ ካስቀመጡት በመነሳት ግን ሁኔታውን በአማካኝ ለይቶ መናገር ይቻላል::
ባለሙያው በሰጡን መረጃ መሰረት፤ በ2021 በተደረገው ጥናት ሱሰኛ የሆኑ ዜጎች ቁጥር በዓለም ላይ ከ40 እስከ 46 በመቶ ይሆናሉ:: በአፍሪካ ደረጃ ሲታይ ደግሞ 60 በመቶ ነው:: በሀገር አቀፍ ደረጃ የሱሰኝነት ተጠቂው መጠን ከ37 እስከ 40 በመቶ ይደርሳል:: ይህም ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 ዓመት ባሉት ላይ በስፋት የሚታይ መሆኑ ተመላክቷል::
በሀገር ውስጥ ከተሞችን መሰረት በማድረግ ካለው መረጃ ለአብነት አዲስ አበባ ከተማ ላይ የተጠኑትን ስንመለከት 41 በመቶ የሚሆኑት ከ18 እስከ 25 ዓመት የእድሜ ክልሎች ውስጥ ያሉ ወጣቶች ሲሆኑ እነሱም በአልኮል ሱሰኝነት ተጠቂ የሆኑ ናቸው:: በዚሁ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ 32 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጫት ተጠቃሚ እንደሆኑ መረጃዎቹ ያመላክታሉ:: አሁን ላይ ደግሞ በአዲስ መልክ እየመጡ ያሉት የሱስ ምንጮች ካናቢስና ማሪዋና የሚባሉት ናቸው:: እነዚህን በመድሃኒትና በመርፌ መልክ የሚወሰዱት ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች ብዙዎች እየተጠቀሙባቸው እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ::
የሱሰኝነት መንስኤ
የመጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰደው የእድሜ ሁኔታ ሲሆን፤ በተለይ ወጣትነት ብዙ ነገሮችን የሚሞከርበት፤ አዲስ ነገር የሚፈለግበትና ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመራመድ እንቅስቃሴ የሚጀመርበት በመሆኑ ለሱስ መጋለጥ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል:: መነሻ ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ፍርሃት፤ ሥራ ማጣት፤ አካባቢያዊ ሁኔታዎች፤ ኃይማኖታዊ አስተምሮዎች፤ ልምዶችና ባሕሎች፤ ነገሮችን ለመርሳት የሚደረጉ ጥረቶች፤ የአቻ ግፊቶች፤ ሌሎችን ለመመሳሰል መሞከር፤ የሌሎችን ጫናን መቋቋም አለመቻል ሲሆኑ፤ በተጨማሪም ለችግሮቻቸው መደበቂያነት ንጥረ ነገሮቹን መምረጥና በሕጻንነታቸው በተለያዩ ችግሮች ማለፍ፣ ከችግሩ ለመላቀቅ ሲባልም የተለያዩ ሱስ አምጪ ነገሮችን መጠቀም የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
እነዚህ ባሕሪያት በብዛት የሚስተዋሉት በዩኒቨርሲቲ አካባቢዎች፤ ከፍተኛ ብር ተከፍሎባቸው በሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ፤ ማሕበረሰቡ በሚኖርባቸው አካባቢዎችና ገንዘብ እንደ ልብ በሚያገኙ ሰዎች ዘንድ እንደሆነም ባለሙያው ያስረዳሉ:: እነዚህ ድርጊቶች ጤናማ ያልሆነ የችግር መቋቋሚያ ዘዴ እንደሚባሉም ይናገራሉ:: ምክንያቱም ተግባራቱ ከሰውነት ጎራ የሚያስወጡ፤ ቤተሰብን የሚበትኑ፤ ኢኮኖሚን የሚያደቁንና ማሕበረሰቡን በድህነት ውስጥ የሚዘፍቁ ናቸው:: ሀገርም ብቃት ያለው ትውልድ እንድታጣና የሚሰራው የሰው ኃይሏ እንዲመነምን ምክንያት ይሆናሉ::
ሱስን የመከላከያ ዘዴዎች
የመጀመሪያው ሱስን መከላከል የሚቻለው ወጣቱ ቁርጠኛና በራሱ የሚተማመን ዜጋ ሲሆን ነው:: ለዚህ ደግሞ የተለያዩ አካላት ድርሻ አላቸው:: ከነዚህ አንዱ በማሕበረሰቡ ዘንድ ትክክል ናቸው ተብለው የሚወሰዱ ሱስ አምጪ ተግባራትን በማስተማርና በመረዳዳት ማስቆም መቻል ነው:: ለምሳሌ፡- በቡድን ሆኖ በቋሚነትና በተደጋጋሚነት አልኮልን መጠቀም፤ አካላዊና ስነልቦናዊ ጫናን እስኪፈጠሩ ድረስ ጫትን ጥቅም ላይ ማዋልን መግታት የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ:: የኃይማኖት አስተምህሮቶችም በብዙ መልኩ ቆም ብሎ ማየትን የሚያትቱ ቢሆኑ ለወጣቱ የተሻሉ እድሎችን እንደሚያመጡ ይናገራሉ::
ሱስን ቀድሞ ለመከላከል ከምንም በላይ ወላጆች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ:: የልጆቻቸውን አዋዋል፤ ስነምግባር በሚገባ መከታተል ይጠበቅባቸዋል:: የተገራና በስነምግባር የተኮተኮተ ልጅ ካለ ትምህርት ቤትም ሆነ ሌሎች ሱስን ሊያመጡ በሚችሉ አካባቢዎች ላይ ቢገኝ ከነበረበት የሚነቀንቀው አይኖርም:: ራሱን የመግዛት ባሕልን ያዳበረ በመሆኑም በቀላሉ ወደ ሱስ አይገባም:: በራስ የመተማመኑም ሁኔታ ሁሉም የተሻለ ይሆናል:: ስለዚህም የቤተሰብ ድርሻ ጎልቶ መውጣት አንዱ ሱስን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ዘዴ ነው::
ሌላው መምህራንን ጨምሮ ያለው የትምህርት ማሕበረሰብ ድርሻ ሲሆን፤ የግብረ ገብነት ትምህርትን በማስተማር ተማሪዎች በትምህርት ቤትም ሆነ ከትምህርት ቤት ውጪ ያላቸውን አዋዋል መከታተልና ካሉበት ችግር እንዲወጡ ማገዝ ነው:: አሁን ላይ አንዳንድ የተሻሉና ውድ የሚባል ክፍያ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ሱሰኛ ዜጎችን እያፈሩ መሆኑን መታዘብ ይቻላል:: እንደ ባለሙያው ዕምነት ይህን ችግር መፈተሽና አግባብነት ያለው ሥራ መከወን ለችግሩ እልባት መስጠት ይሆናል::
በጣም ከፍተኛ የስነ አዕምሮ ቀውስ ሊያመጡ የሚችሉትን እንደ ማሪዋና አይነት ንጥረ ነገሮችን በመርፌና በመድሃኒት መልክ የመውሰዱ ሁኔታ አሁን ላይ እየሰፋ ያለውም በእነዚህ አከባቢዎች ላይ በመሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ በተለየ መልኩ ክትትል በማድረግና የተለየ ሕግ በማውጣት መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ያስፈልጋል:: በተጨማሪም የስነ አዕምሮ ጤናን ይጎዳሉ ተብለው የሚጠቀሱ ሱስ አምጪ ንጥረነገሮችን እንደከዚህ ቀደሙ ከፍተኛ ታክስ በመጣል ወጣቱን መታደግ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ::
ችግሩን የመፍቻ ዘዴዎች
ሰዎች ሱስን ሙሉ ለሙሉ ማቆም ይችላሉ፡ ከምንም በላይ ግን በሱስ የተያዘው ሰው ቁርጠኝነት ያስፈልጋል:: የቤተሰብና የማሕበረሰቡም ድጋፍ እንዲሁ የግድ ይላል:: ምክንያቱም ሱስ ግለሰቡ ጋር ብቻ የሚቀር ተግባር አይደለም:: ከዚህም የተሻገረ የጤና ችግርን ያስከትላል:: ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን አካባቢን ብሎም ማሕበረሰቡንና ሀገርን ጭምር ይጎዳል:: ማሕበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና አካላዊ ቀውሶችን ይፈጥራል:: ከግለሰብ ቁርጠኝነት ጀምሮ በሚሰሩ ሥራዎች ሱስን ማቆም ይቻላል:: ለዚህም አብነት የሚሆኑ ዜጎች አሉን:: ድነው ራሳቸውን፤ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን የሚያገለግሉ::
ግለሰቦች ቁርጠኛ ከሆኑ በኋላ ቀጣዩ ሥራ የማገገሚያ ተቋማት ድርሻ ይሆናል:: ዜጎች ከሱስ ውስጥ ወጥተው ጤናማ ሕይወትን እንዲኖሩ ሱሱን የማከም ተግባርን ያከናውናሉ:: ይህ ግን የተሟላ ለመሆን የተቋማቱ ምቹነትን፤ የአገልግሎት አሰጣጣጡን፤ የግብዓትና ባለሙያ ፍላጎትን በቂ ማድረግን ይጠይቃል::
በዚህ ልክ የተሟላ ተቋምና ባለሙያ አለ ወይ ከተባለ ግን እንደ ሀገር ብዙ ይቀራል:: ከዚህ አንጻርም ሱሰኛ የሆኑ ዜጎቻችንን አክመን ወደነበሩበት የተረጋጋ ሕይወት ለመመለስ እንቸገራለን:: በርካታ ከችግሩ የወጡ ዜጎችን ማግኘት ያልተቻለውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ባለሙያው ያነሳሉ::
ብዙ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ በሱስ ውስጥ ያሉ ዜጎች የእድሜ ቆይታቸው ከሌሎች ከ15 እስከ 20 የሚያንስ ነው:: በተጨማሪም ለሌሎች ተጓዳኝ ሕመሞች የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው:: ሕክምናውን በተሟላ መጠን የማያገኙ ከሆነ ደግሞ አይደለም ሱሱን ማስቆም በሕይወትም ለማቆየት እጅጉን ይከብዳል::
ይህንን ለማድረግ በተለይም ከግለሰቦቹ ቁርጠኝነት በኋላ የተሟላ አገልግሎት አለማግኘት፤ የቤተሰብ ድጋፍና ክትትል ጠንካራ ያለመሆን፤ የማሕበረሰቡ ማግለል፤ አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት ጥቂት መሆን፤ ባለሙያውና ሕመምተኛው ያለመመጣጠን፤ ሕክምናው ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ መሆኑ ታውቆ ትኩረት የሚቸራቸው መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ::
ሱስ መታከም ያለበት እንደ ሌሎች ሕመሞች ሁሉ ቀድሞ ነው:: ነገር ግን የተማረው ማሕበረሰባችን ጭምር ሱስን ሕመም አድርጎ የመቀበል ሁኔታ አይታይበትም:: ይህ ደግሞ ሕክምናውን ውስብስብ ያደርገዋል:: በቀላሉ አክሞ ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ ለማዳንም አስቸጋሪ ያደርገዋል:: እናም ሰዎች አቅም ከማጣታቸው፤ ተስፋ ከመቁረጣቸው አስቀድሞ እንዲሁም ኢኮኖሚያቸው ሳይዳሽቅ መታገዝ ይኖርባቸዋል:: ይህን እውነትም ሁሉም ማሕበረሰብ ማወቅና መገንዘብ እንዳለበት ይመክራሉ::
የሕክምና አይነቶች
በሱስ ሕክምና ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የስነ ልቦና ሕክምና ነው:: ነገር ግን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው የሚመጡ ከሆነ ቅድሚያውን የሚሰጠው ለየመድሀኒት ሕክምና ነው:: ይህ ሕክምና በሰውነታቸው ውስጥ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረውን ንጥረ ነገር ማስወገድ የሚቻልበት ሲሆን፤ ከ12 እስከ 20 ቀናት በሚሆኑ ጊዜያት ተግባሩ ይከወናል:: ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ሁለተኛው ደረጃ ሕክምና ይሰጣል:: ይህም ራሳቸውን ካወቁና ዝግጁ ከሆኑ በኋላ የሚሰጠው ሲሆን፤ ሕክምናውም የስነልቦና ሕክምና ይባላል::
ተግባሩ የሚፈጸመው በሁለት አይነት መንገድ ሲሆን፤ በተናጠልና በቡድን ነው:: በተናጠል የሚደረገው ሕክምና ሱስ ውስጥ የከተታቸው ምክንያት የሚታይበት፤ ለምን ከችግሩ መውጣት እንዳልቻሉ መንስኤዎቹ የሚመረመሩበት፤ ተጓዳኝ ችግሮቻቸው የሚለዩበት ነው:: ከዚያ ለእያንዳንዱ ለገጠማቸው ስነልቦናዊ እና አካላዊ ስብራቶች መፍትሄ የማበጀት ሥራ ይከናወናል:: የቡድን ሕክምና የሚባለው ደግሞ በሱስ ውስጥ የነበሩ ሰዎች በጋራ ችግሮቻቸው ዙሪያ የሚመክሩበት ነው:: ይህም ከስምንት እስከ 12 በሚደርሱ ሰዎች መካከል የሚደረግ ሲሆን፤ በሳምንት አንዴ አለያም ሁለቴ የሚከናወን እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ:: በዚህ ሕክምና ባለሙያዎች እንደ ቤተሰብና ጓደኛ ሆነው የሚሳተፉበት ሲሆን፤ አንዱ ከአንዱ የሕይወት ልምድን እንዲማር፤ ችግሩን አቅልሎ እንዲመለከትና፤ ካለበት የሱሰ ጥገኝነት እንዲላቀቅ የሚሆንበት ነው:: ነገውን የተሻለ ለማድረግም ዕድሉ በስፋት ይመቻችለታል::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም