ከታዳጊዎች ምዘና ውድድር ባሻገር

በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርት ውጤታማነትን ለማስቀጠል በበርካታ ሀገራት ተግባራዊ ከሚደረጉ አሠራሮች መካከል ዋነኛው የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ልማት ነው። በረጅም ጊዜ የተቀናጀ፣ የተጠናከረና ተከታታይነት ያለው የስልጠና ሂደትም ብሔራዊ ቡድንን ሊተኩ የሚችሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያስችላል ተብሎ ይታመናል። ይህ ለዓመታት የሚዘልቅ የታዳጊዎች ስልጠና ከምልመላ እስከ ስልጠና ልዩ ትኩረት የሚሻና በምዘና የሚለካም መሆን አለበት።

በኢትዮጵያም ስፖርቱን ለማሳደግ ከታዳጊ ወጣቶች ስልጠና መጀመር አስፈላጊ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል። በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የላቀ ችሎታ ያላቸውና ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆነ ታዳጊዎች በሳይንሳዊ ስልጠና ምርጥ ስፖርተኞች እንዲሆኑ መሥራት ከተጀመረ ሰነባብቷል። ይሁንና በተለያዩ ክልሎች በነበረው የጸጥታ ችግር፣ በዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ይደረግ የነበረው የምዘና ውድድር ተቋርጦ ቆይቷል። በዚህም በስልጠና ያለፉ ታዳጊዎች ወደ ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ አካዳሚዎችና ክለቦች የሚገቡበት ዕድል እየጠበበ መጥቷል።

ይህንን ፈር ለማስያዝ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የታዳጊ ወጣቶች ፕሮግራም ምዘና ውድድርን ከ6 ዓመታት በኋላ ዘንድሮ በወላይታ ሶዶ ከተሞች በማካሄድ ላይ ይገኛል። የታዳጊዎች ልማት ለስፖርቱ ዕድገት መሠረት በመሆኑም “የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለአሸናፊ ሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ እያካሄደ ይገኛል። በዚህም ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ታዳጊዎች በ11የስፖርት ዓይነቶች በምዘና ውድድሩ በመፎካከር ከስልጠና ያገኙትን አቅም በማሳየት ላይ ይገኛሉ።

ሀገር ተረካቢ የሆኑ ታዳጊ ወጣቶችን በአካልና በአዕምሮ ለማብቃት በሚደረገው እንቅስቃሴ የምዘና ውድድሩ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ተሳታፊ ክልሎች ጠቁመዋል። በቦክስ ስፖርት ከፍተኛ ፉክክር በማሳየት በውድድሩ ስፍራ የተገኙ ተመልካቾችን ካስደመሙት መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው። የቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑት ዘሪሁን ጥበቡ፣ የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶች በየትኛውም ስፖርት መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ስፖርቱ እንዲነቃቃና በቀጣይ ያለው ተስፋም የሚታይበት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል። ከውድድር መድረክነት ባለፈ በየክልሉ ያለው የስፖርት እንቅስቃሴ የሚታይበት በመሆኑም ክፍተቶችን በመለየት ከስፖርት ማህበራት ጋር የሚሠራበትን እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

መሠል ውድድሮች ላይ በስፋት የሚታዩና ቅሬታ ከሚቀርብባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እድሜ ነው። ይህ የእድሜና የአቅም አለመመጣጠን ችግር በምዘና ውድድሩ ላይ መስተዋሉ እንዳልቀረ አሰልጣኙ ይጠቁማሉ። ይሁንና የውድድሩ መጀመር ካለው ጠቀሜታ አንጻር የጎላ የሚባል አይደለም። የተጋነነ ችግር ያለባቸው ግን ተለይተው ከተወዳዳሪነት የተሰረዙ መሆኑን አስረድተዋል።

በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ታዳጊዎችን በማፎካከር ላይ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ቡድን መሪ ቶሎሳ ጨመዳም የምዘና ውድድሩ መካሄድ ያለውን ፋይዳ ያብራራሉ። በስልጠና ሂደት አልፈው በቀጣይ ሀገርን ሊወክሉ የሚችሉ ስፖርተኞች የሚገኙበት መድረክ በመሆኑ ከዓመታት መቋረጥ በኋላ መመለሱ ለስፖርቱ በርካታ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ይላሉ። እንደ ኦሊምፒክ ባሉ ውድድሮች ኢትዮጵያ ከውጤት እንድትርቅ ካደረጓት ምክንያቶች መካከል ታዳጊዎች ላይ አለመሠራቱ ነው የሚል አመለካከትም አላቸው።

ከውድድርም በላይ ታዳጊዎቹ የውድድር ልምድ የሚያገኙበት፣ እርስ በእርስ የሚቀራረቡበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበትና የውድድር ልምድ የሚያገኙበት መድረክ እንደሆነ ቡድን መሪው ተናግረዋል። የምዘና ውድድሩ በእድሜ ገደብ ከሚካሄዱ ውድድሮች የተሻለ የሚባል ቢሆንም ከተደረገው የእድሜ ማጣራት ሾልከው የወጡ ችግሮች መኖራቸውን ያስረዳሉ። በመሆኑም በሁሉም ባለሙያዎች በተገቢ ሁኔታ ሊሠራና ኃላፊነትንም መወጣት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ልዑክ አሰልጣኝ የሆኑት ኢንስትራክተር አበራ ጌታቸውም በዚህ ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ ያነሳሉ። ከዓመታት በኋላ ስፖርቱን በሚመራው አካል ታስቦበት ይህን መሰል ውድድር መዘጋጀቱ ለስፖርቱ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ግን አልሸሸጉም። የምዘና ውድድሩ በተቋረጠበት ወቅት በየክልሉ በሚሰጠው ስልጠና እየተሳተፉ ነገር ግን በውድድር የመመዘን ዕድል ያላገኙ በርካታ ታዳጊዎች ነበሩ። ስለዚህም የመድረኩ መመለስ ስፖርቱን በማነቃቃት በኩል ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ብርሀን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You